የአሰብ ጦርነት አይቀሬነት

የአሰብ ወደብ ጦርነት አይቀሬ ነው። ሁለቱም አገራት እየተዘጋጁበት እንዳሉ መረጃዎች እየወጡ ነው። በኤርትራውያን ዘንድ ኢትዮጵያ ጦሯን ድንበር ላይ እያሰማራች ነው፣ የአለም ትኩረት ጋዛ ላይ ባለበት በኣሁኑ ወቅት ድንገት ጥቃት ልትከፍት ትችላለች የሚል ከፍተኛ ስጋት አለ። ጦርነቱ ከተጀመረ፣ ህልማቸው መና እንደሚቀርና ታሪክ ሆነው እንደሚቀሩ ስለገባቸው፣ ኤርትራውያን አረቦቹንም እነ ቻይናንም አሸማግሉን የሚል ተማጽኖ እያሰሙ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ህልማቸው የቀጠናው ቁንጮ መሆን ነውና፣ ይህን ለማሳከት ኢትዮጵያን እንደፈለጉት መጠምዘዝ ባይችሉ፣ እንድትበጣበጥና እንድትበተን ሳይታክቱ ከመስራት አይቆጠቡም። ለዚህም ፋኖን በዋናነት እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።

የአብይ መንግስት አሁን ባለበት ሁኔት፣ ከጦርነት አዙሪት የመውጣት እድሉ ዝቅተኛ እንደሆነ ተገንዝቧል። በዚች አጭር የስልጣን ዘመኑ፣ ከማንምና ከምንም በላይ ለስልጣኑ ሲል በህዝቦች መካከል ያለውን ቅራኔ በማስፋቱ፣ ከጦርነት አዙሪት ሊወጣ አይችልም። ከኣንዱ ጋር በድርድርም ሆነ በሌላ መንገድ ሰላም ቢያወርድ፣ አውቶማቲካሊ ከሌላው ጋር ጦርነት ይጀምራል፤ ቅራኔያቸውን በመስፋቱ ስጋት እንጂ መተማመን የላቸውም። ከዚህ አዙሪት ለመውጣት ድሮ ያመለጠውን ዕድል፣ ማለትም ህዝቦችን የማወያየትና የማቀራረብ ስራ ልስራ ቢል እንኳን፣ የኤርትራ ጣልቃ ገብነትና ፍትፈታ እስካለ ድረስ አይሳካለትም። ስለሆነም ቀዳሚ ታርጌቱ ኤርትራ ትሆናለች። የወደብ ጦርነቱን አይቀሬ የሚያደርገው ደግሞ ይኸው ነው።

የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር፣ ኢትዮጵያ እንደአገር ከቀጠለች አሰብ ወደ ኢትዮጵያ መመለሷ አይቀሬ ነው። የማይቀርለት ጉዳይ ዛሬ በመድፈርና አሰብን በማስመለስ፣ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነትን ያጣው የአብይ መንግስት፣ በተወሰነ ደረጃ ተቀባይነትን እንዲያገኝ ይረዳዋል። ከምንም በላይ ደግሞ የህዝቡን ትኩረት ከአገር ውስጥ ወደ ውጭ በማስቀየስ፣ ድጋፍ የማግኘት እድሉን ይጨምርለታል። ጦርነቱ ከተጀመረ የማሸነፍ እድሉ ከፍተኛ እንደሆነ ያቃል። አሸንፎ በኢትዮጵያ ጉዳይ የሚፈተፍቱ የሻዕቢያ እጆችን ከቆረጠ፣ የአገር ውስጥ ተቀናቃኞቹ (በተለይ የአማራ ሸኔ የሚላቸው) ገመዳቸው አጠረ ኦክስጅናቸው ተበጠሰ ማለት ነው። እነሱንም የማንበርከክ አቅሙ ይጎለብታል።

ይህ ከሆነ፣ ስልጣኑን አራዘመ ማለት ነው። ከጦርነት አዙሪት የመውጣት እድሉም ይኖረዋል። ሻዕቢያን አጥፍቶ፣ አሰብን አስመልሶ፣ በሻዕቢያ የሚታገዙ የአገር ውስጥ ተቀናቃኞቹን ካኮላሸ፣ ወደ ልማትና ህዝብን የማቀራረብ ስራ በመመለስ፣ አገሪቱ ከጦርነት አዙሪት የምትወጣበትን መንገድ መፍጠር ይችላል ማለት ነው። ለዚህም ነው ሊያከትምለት አንድ ሓሙስ በቀረው በአሁን ወቅት የአሰብ ካርድ ደምቃ የታየችው።

ይችን ካርድ ባይስባትስ? አሸናፊ በሌለው የእርስ በእርስ ግጭት እንደሚዳክር ያውቃል። በመጨረሻም እጣፈንታው ከፍ ቢል እንደ ሶሪያ (የመንደር ንጉስ መሆን) አሊያም እንደነ ሊብያ ከስሞ የጎስት አገር መፍጠር እንደሚሆን ያውቃል።

እናም አጅሬ ተዘጋጅቷል፣ እናንተም ለባሰ የኑሮ ውድነት ተዘጋጁ። (እንደወረደ!)

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *