አትኦ ለሰላም! አቶ ለአብሮነት! ATO for Reconciliation!

የፈረንጆች አመት ከመገባደዱ ከሳምንት ወይም ሁለት ሳምንት በፊት፣ ከመተላለቅ አዙሪት ለመውጣት መነጋገር ያስፈልጋል የሚል ሀሳብ እዚህ ቀርቦ ነበር። ከሁለት ወር ባነሰ ግዜ ውስጥ፣ ከፋኖም ከሻዕቢያም ጋር መነጋገር ጀምራችኋል የሚል ክስ ማሰማት ጀምሯል፣ በሽብር እየተናጠ ያለ የብልጽግናው ባንዳ መንግስት። በመሆኑም የወልቃይትን ጉዳይ በማራገብ ረገድ አዲስ የተጧጧፈ ዘመቻ ከፍቷል። በርካቶች ወጥመዱ ውስጥ በቀላሉ ሲገቡም እየተመለከትን ነው። መንቃት አለብን። አርቆ በማሰብ ሴራውን ማክሸፍ ይጠበቅብናል። አለበለዚያ ድንጋዮቹ እኛው ነን።

የወልቃይትና የራያ ጉዳይ ዛሬ ደም ካቃባን ብኋላ ይቅርና፣ ያኔ ገና የፖለቲካ መነታረኪያ አጀንዳ ብቻ በነበረበት ዘመን፣ በህዝቦች መካከል እሳት ለመጫር ስስ ብልት ሆኖ አገልግሏል። ዛሬም ያንኑ እየኮረኮሩ አማራና ትግራዋይ እየተበጣበጠ እንዲኖር ቀላሉ ዘዴ ሆኗል። ምንም ሳይደብቁ ደግሞ በአደባባይ ሴራና ፍላጎታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።

አብይ አሕመድና ብልጽግና ስልጣን ላይ ሆነው፣ በህዝቦች መካከል ሰላምና እርቅ ይሰፍናል ማለት ዘበት ነው። ዝሆን በመርፌ ቀዳዳ ቢሾልክ ይቀላል። ያንን ልዩነት እያጋጋሉ፣ ህዝብን በማራራቅ፣ አልገብር ያላቸውን በአፈሙዝና በድሮን ማስገበር የሰርክ ስልታቸው ነው። ደርግ እንደሔደው፣ ኢህአዴግ ቁጥር 1 እንደሔደው፣ ብልጽግና (ኢህአዴግ ቁጥር 2) መሔዱ አይቀርም። ትላንትም ዛሬም ቁርሾ የያዘው ህዝብ ግን ወደፊትም ይኖራል። ወደፊት አብሮ ለመኖርም ሆነ ተጎራብቶ ለመኖር ደግሞ ሰላም ወሳኝ ነገር ነው። ለሰላም ደግሞ ንግግርና ውይይት ያስፈልጋል። ከብልጽግና ጋር ለመነጋገር ያልተቸገሩ ቡድኖች እርስ በእርስ ለመነጋገር ሊያዳግታቸው አይገባም።

ይኽን ስል በአማራና በትግራይ መካከል ብቻ ማለቴ አይደለም። የኦሮሞ ህዝብም ከሌላው ባላነሰ በዚህ ነፍሰ በላ የወያላ ስብስብ ስርዓት ቁም ስቅሉን እያየ ያለ ህዝብ ነው። የሶስቱም ህዝብ ተወካዮች በአገር ውስጥም ከአገር ውጭም ተቀራርበው መነጋገርና መወያየት አለባቸው። እርግጥ ነው ባለፉት አምስት አመታት ብዙ አዳዲስ ቁርሾዎች ተፈጥረዋል። የፍትህ ጥያቄ ይኖራል፣ ሌላም ሌላም ይኖራል። በመሆኑም ነገሮች ከዜሮ (ክስር መሰረታቸው) ሊጀምሩ ይችላሉ። ይገባልም። ደግሞም የተሻለ መንገድ የለም። እኛም የፈጸምነውን እኛም ላይ የተፈጸመውን ግምት ውስጥ በማስገባት ከተሻለ የመፍትሔ ሀሳብ ጋር ለንግግር መዘጋጀት ያስፈልጋል። ይህን በማድረግ ብቻ ነው የወያላዎችን ሴራ ማክሸፍና ህዝብ ዳግም በሰላም መኖር የሚችልበትን እድል መፍጠር የሚቻለው።

መነጋገር፣ አብሮ መስራትና የጋራ ጠላትን በጋራ መምታት ቀዳሚው ምርጫ ሊሆን ይገባል። የአማራ የትግራይና የኦሮሞ (የአትኦ) ህዝብ የጋራ ጠላት በዚህ ሰዓት የወያላው ስብስብ ነው። ከወያላው ስብስብ መመታት ብኋላ ስላለፉት ጥፋቶች ፍትህ ማግኘት ይቅርታና እርቅ መፍጠር ወዘተ ይከተላል። ከዛ ብኋላ ለሁሉም የሚሆን የጋራ ስርዓት በጋራ መፍጠር ይሻ(ቻ)ላል። አለበለዚያ እርስ በእርስ እየተፋጠጥክ፣ በወያላው እየተቀጠቀጥክ፣ አናትህ ላይ እየተሸናብህ ትኖርና፤ ወያላው በራሱ ጊዜ ድንገት የተፈረከሰ እለት ደግሞ ወደ ለየለት የእርስ በእርስ እልቂት ታቀናለህ።

ሴናሪዎችን ሁሉ ካመዛዝንን፣ አሁን ከመነጋገርና በጋራ ይህን ሽባ ስርዓት ከግብአተ መሬቱ ከቶ ስለነገ የህዝቦች አብሮነትና ሰላም በጋራ ለመስራት ከመዘጋጀት የተሻለ ሌላ አማራጭ ያለ አይመስለኝም።

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *