,

ትርጉም የለሽ ምጥ የለም!

አብይ አሕመድ (መሽሬ) ስልጣን እንደያዘ በጥቂት ሳምንታት የህወሓት ባለስልጣናትን ከ4ኪሎ ሲያጸዳ፣ የፓርቲ ፖለቲካ ነበር። ያኔ እኔን ጨምሮ ብዙ ትግራዋይ ግድ አልሰጠንም ነበር። እንዲያውም አብዛኛው ትግራዋይ እንደማንኛውም የተቀረው ህዝብ በደስታ የሰከረበት ግዜ ነበር።
መሽሬ ኢህአዴግን አፍርሶ ህወሓት የሌለበት ብልጽግናን ሲመሰርትም የፓርቲ ፖለቲካ ነበር። የፌደራል ስርዓቱ ሲምቦል ተደርጎ የሚወሰደው የድርቶች ስብስብ/ግንባር፣ ተጨፍልቆ ወጥ መሆኑ ፌደራላዊውን ስርዓት አፍርሶ አሃዳዊ ስርዓት ለመተካት የሚደረግ ርብርብ መስሎ የታየው (ትግራዋይን ጨምሮ ሌሎች የብሔር ፖለቲካ አራማጆች) ስጋቱን ከመግለጹ ውጪ፣ ከፓርቲዎች ሽኩቻ ነጥሎ የሚያይበት ምክንያት አልነበረውም።
ትግራይንና ህወሓትን ያገለለ የኢትዮ ኤርትራ ግኑኝነት ግን ከፓርቲ ፖለቲካ በላይ ነበር። የኢሳያስ የመጨረሻ ግብ በቀል እንደሆነ እያንዳንዱ ትግራዋይ ጠንቅቆ ያውቃል። ትግራይን ያገለለው ሽርጉድ ህልውናው ላይ እንደተጋረጠ አደጋ ቆጥሮታል፣ ከዴይ ዋን ጀምሮ።
ከአመት በላይ የዘለቀው የአማራ የመስፋፋት ፍላጎትና ጦር ጉሸማም ከፓርቲ ፖለቲካ በላይ ነበር። የትግራይ ህዝብ እንደ ኤግዚስቴንሻል ትሬት ያየበት፣ በላይ በኤርትራ በታች በአማራና በስልጣን ፈላጊ ምንደኞች ተቀርቅሮ በእሳት ሊለበለብ እንደሚችል አስቀድሞ ተገንዝቧል።
ለዚህም ህዝቡ ህልውናውን ቀስ በቀስ ከፓርቲው ህልውና ጋር አቆራኝቶ ማየት ጀመረ።
መሽሬ ስልጣኑን በህገወጥ መንገድ አራዝሞ ሌሎችም ምርጫ እንዳያካሂዱ ሲያግድ፣ የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አፈንግጦ ምርጫ አደርጋለሁ ሲል በእርግጥ የፓርቲ ፖለቲካና የስልጣን ሹክቻ ጉዳይ ነው። ነገር ግን ከዛም በላይ ነው፤ የህገመንግስታዊ መብት፣ የሉአላዊነትና የህልውና ጉዳይ ነው።
ፌደራል መንግስት እውቅና አልሰጥም እያለ፣ ህገወጥ ነው እያለ፣ የክልሉ መንግስት ምርጫ አካሂዷል። ህዝብም ተገዶ ሳይሆን ወዶና ፈቅዶ በአደባባይ እየጨፈረ በምርጫ ተሳትፏል። በነበረው የአገሪቱ ሁኔታና የህዝብ ስጋት፣ ህዝቡ ህልውናዬን፣ መብቴን፣ ጥቅሜን ከሌሎች በተሻለ ያስጠብቅልኛል ብሎ ላመነው ድርጅት ድምጹን ሰጥቷል።
እዚህ ላይ ህዝቡ ሁለት ሀላፊነቶችን willingly እንደወሰደ ልብ እንበል፤ አንደኛ የፌደራል መንግስቱን ትዕዛዝ አልቀበልም ብሏል። ሁለተኛ የሚበጀኝን የመምረጥ ህገመንግስታዊ መብቴን እጠቀማለሁ ብሎ የሚበጀውን መርጧል።
ከዚህ ብኋላ ያለው ጉዳይ በሙሉ የፖርቲ ፖለቲካ ሳይሆን የህዝብና የሉአላዊነት ጉዳይ ሆኗል።
ከ2ሚልዮን በላይ ድምጹን የሰጠበት ምርጫ ማንም በምንም መንገድ ሊሰርዝ ሊደልዘው አይችልም። ተገድጄ ነው የመረጥኩት ካላለ፣ ለመገደዱ ማስረጃ ከሌለ፣ በስተቀር ማንም ሰው/ሀይል በምንም መንገድ የህዝቡን ውሳኔና የወሰደውን ሃላፊነት መደለዝ አይችልም። አራት ነጥብ።
ከምርጫው ብኋላ ህጋዊ ክልላዊ መንግስት ነኝ፣ ሳይመረጥ የፌደራል መንግስት ነኝ ለሚለው ህገወጥ ቡድን እውቅና አልሰጥም ሲል፣ የፌደራል “መንግስት”ና የክልሉ መንግስት መውጫ የሌለው ቅርቃር ውስጥ እየገቡ ነበር። አብሮ መስራት አይቻልም። ሁሉንም ያሳተፈ አገር አቀፍ ድርድር አድርጎ ችግሮችን ለመፍታትም የፌደራሉ ማፊያ ቡድን ፍላጎት አልነበረውም። (የኦሮሚያና የአዲስ አበባ ተቀናቃኞቹን ማሰር ችሎ ስለነበር፣ ስልጣኑን ለመቆጣጠር ከግማሽ መንገድ በላይ የተጓዘ መስሎታል። Why’d he retreat?)
እንደመፍትሔ የወሰደው እኔም ለክልሉ መንግስት እውቅና ስለማልሰጥ ግኑኝነቴን በቀጥታ ከወረዳ ጋር አደርጋለሁ የሚል ነበር። ዳሩ ግን እስከ ቀበሌ ድረስ ያለው መንግስታዊ መዋቅር፣ የክልሉን መንግስት የተቆጣጠረው ፓርቲ ነው ያለው። ከወረዳዎች ጋር በቀጥታ ሊገናኝ የሚችልበት አጋጣሚ አለነበረም። ግኑኝነታችን ከክልሉ መንግስት ጋር ነው የሚል ምላሽ ነበር የሚያገኘው።
እዚህ ቅርቃር ውስጥ የገባው የፌደራሉ ማፊያ፣ ለክልሉ መንግስት እውቅና ስለማይሰጥና ወረዳዎችም በቀጥታ ለመገናኘት ሀላፊነት መውሰድ የማችሉ ስለሆኑበት፣ በጀቶችን መቁረጥ፣ የህክምና ቁሳቁስ አለመላክ፣ እርዳታ ማስቀረት፣ ወዘተ አይነት እርምጃ ገባ። ህዝቡም ህገወጥ ነው እየተባለ ምርጫ ተሳትፎ ድምጹን ስለሰጠ፣ አብሮ መቅጣት እንደ አምራጭ ታዬ።
ጉዳዩ የፖለቲካ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሉአላዊነት ጉዳይ እየሆነ መጣ። የህዝብ አጀንዳ ሆነ።
በዚህ መልኩ ሊቀጥል እንደማይችል ሲያውቅ ቀድሞ ሲዘጋጅበት የቆየውን በጉልበት የማንበርከኩን አማራጭ ገፋበት። አቅሙን ፈተሸ። የኤርትራን አቅም ፈተሸ። ኢሳያስን ጋብዞ አቅሙን አሳየ። በተቀናጀ መልኩ ጦርነት ለመክፈት ዝግጅቶች ተጠናቀቁ።
የሰሜን እዝ አዛዥ ለመቀየር ሞከረ፣ የክልሉ መንግስት ከለከለ።
ዘ ሬስት ኢዝ ሂስትሪ።
ጦርነት ክልሉ ላይና ህዝቡ ላይ ሲከፈት፣ ህግ የማስከበር ጉዳይ፣ በህግ የሚፈለጉ ግለሰቦች የመያዝ ጉዳይ ወይም የፖለቲካ ፓርቲ ጨዋታ አይደለም።
በተለይ ደግሞ የውጭ ሀይሎችን አሳትፎ፣ የተለያዩ በቀል የተጠሙ ቡድኖች አሰባስቦ፣ በሰማይና በምድር ደግሞም ሁሉም አቅጣጫ እሳት እየለቀቁ የገቡበት ጦርነት፣ የህወሓት ባለስልጣናትን ከ4 ኪሎ ሲያባርሯቸው እንደነበረው አይነት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጨዋታ አይደለም።
ወገኖቻችን ያለቁበት፣ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የተፈናቀሉበት፣ እናቶቻችንና እህቶቻችን የተደፈሩበት፣ ንብረቶቻችን የወደሙበትና የተዘረፉበት፣ ከተሞቻችን የበረሱበትና በጄኖሳይድ ንጹሀን የተጨፈጭፉበት፣ ትግራዋይነት ላይ የተከፈተ ጦርነት ነው።
በህግ የሚፈለጉ የግለሰቦች ጉዳይ አይደለም። የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉዳይ አይደለም። እንደኮንቬንሽናል ዋር የአንድ ትውልድ ጉዳይም አይደለም። የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው!
ይህን ሁሉ እያደረጉም፣ ሲቪልያን ከጦር ቀጠና እንዳይሸሹ መንገድ ዘግተው፣ መላወሻ አሳጥተው፣ ንብረታቸውን እየዘረፉ፣ ቀለባቸውን እየተናጠቁ፣ ከአለም ነጥለው፣ የደረሰባቸውን ግፍ እንዳይገልጹ፣ ሮሯቸውን እንዳያሰሙ፣ ቆልፎ መቀጥቀጥ፣ የፓርቲ፣ የግለሰብ፣ የአንድ ትውልድ ጉዳይ አይደለም።
ለዚህም ነው እያንዳንዱ ጤነኛ ትግራዋይ ይህን በማንነቱ ላይ የተቃጣ የዘር ማጥፋት ዘመቻ በጋራ ለመመከት በጋራ መቆም ያለበት።
ትግራይ ምጥ ላይ ነች።
አንዳንዶች ትርጉም የለሽ ጦርነት ነው ይላሉ። እናት ትርጉም የለሽ ምጥ አምጣ አታቅም። እናት የምታምጠው ለመውለድ ነው። ትግራይ ነጻ ሀገርን ለመውለድ እያማጠች ነው።
ማርያም ጽዮን ብሽልምትኺ ተውፅእኪ ንበላ። ንደግፋ! ኩልና ንረባረብ!
3 replies
  1. ጋሻው በዛ
    ጋሻው በዛ says:

    ትግራይ ግን ተገንጥላ ለምን ነፃ ሃገር አትመሰርትም? ያው ትምክህተኞች እንዳያስቸግሩ ወልቃያት ሆመራ እና ራያን እንመልስላቸው!

    Reply
  2. Kedir
    Kedir says:

    ህወሐት ላለፉት 27 ዓመታት ከትግራይ ህዝብ ተነጥላ ነበር።መሽረፈት ወደ ስልጣን የመጣ ግዜም ትግራይ ላይ የነበራት ተቀባይነት ዝቅተኛ ነበር።በመሽረፈት ተንኮል መክንያት ህወሐት ዳግም የትግራይ እና ትግራዋይነት ማንነት አዳኝ ሆና ተከሰተች።መሽረፈት ይህ ጦርነት ሰልጣን የያዘ ቀን ቢያደርገው ኖሩ አብዛኛው ትግራዋይ ባይደግፈውም አይቃወመውም ነበር።ያለፉት ሁለት ዓመታት የመሽረፈት ትክክለኛ ማንነት እና የስልጣን ጥማት የገባው ትግራዋይ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ ከህወሐት ጎን ሁኖ እንዲታገለው ሆኗል።በመጨረሻም ድል የትግራይ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም።

    Reply

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *