የሴራ ፖለቲካ ያዋለደው የአንጃዎች ህብረት

ብልጽግና ተቀናቃኞቹን ከጉልበት ይልቅ በሴራ ማሽመድመዱን እንደ አዋጭ ስልት ይዞታል። እስካሁን የተለፋበትንና የተሞከረውን ያህል ያልተሳካው በኦሮሚያ ነው። የጃልመሮን ቡድን ለሳምንት ወይም ሁለት ሳምንት ቢያወዛግበውም፣ ቡድን ህብረቱን እንደጠበቀ ቀጥሏል።

በሌላ በኩል ቀድሞዉኑ የተማከለ አደረጃጀት የሌለውን ፋኖን ለሁለት አንጃ ከፍሎ እያባላው ነው። እስክንድር ነጋ በውጪ ዲፕሎማቶች እውቅና ያለው በመሆኑ፣ በእነሱ ግፊት ብልጽግና ከፋኖ ጋር ውይይት እንዲጀምር ሲወተወት (ከሪፎርሙ በፊት ነው ይሔ)፣ እስክንድር ነጋን መርጦ ሌሎቹን ንቆ በመተው በመካከላቸው ቅራኔ እንዲፈጠር አድርጓል። ይህ ቅራኔ ከግዜ ወደ ግዜ እየሰፋ ሄዶ፣ የእስክንድርን ቡድን ከጨዋታ ውጪ የሚያደርግ እንቅስቃሴ ሌላኛው አንጃ ጀምሯል። አዳዲስ ዘመቻዎች እየተጀመሩ መሆናቸውንም እየሰማን ነው።

ከወደ ትግራይ ደግሞ ህወሓት ለሁለት ተከፍሏል። አንደኛው ቡድን ልክ እንደ እስክንድር ነጋ፣ ከብልጽግና ጋር ተሸማግሎ አብሮ መስራት ይፈልጋል። ሌላኛው ቡድንም ይህንኑ የሚፈልግ ቢሆንም፣ ልክ እንደ ሁለተኛው የፋኖ አንጃ በአብይ አሕመድ የማይፈለግና የተናቀ ቡድን ነው። ይህ ቡድን ከወዲሁ “የህግ ጥሰቶች” ሊባሉ የሚችሉ ጉዳዮችን እየፈጸመ በመሆኑ፣ ወደ ትጥቅ ትግል የመግባት እድሉ ከፍተኛ ሆኗል።

ሁለተኛው የህወሓት አንጃ (የደብረጽዮን ቡድን) ጫካ ከገባ፣ ከሁለተኛው የፋኖ አንጃና ሻዕቢያ ጋር አብሮ ሊሰራ ይችላል። ከዚህ ቀደም በብልጽግናው መሪ ከሻዕቢያና ከፋኖ ጋር እየተነጋገራችሁ መሆኑን አውቃለሁ የተባለው ያለምክንያት አልነበረም። የደብረጽዮን ቡድን ግማሽ ኤርትራዊያን በሆኑ አመራሮች የተሞላ ነው።

ዞሮ ዞሮ ቡድኖቹን የመከፋፈሉ ሴራ፣ ሌላ አዲስ ህብረት እንዲፈጥሩ ሰበብ እየሆነ ነው። ይህ ከሆነ ለብልጽግና ትልቅ ራስ ምታት መሆናቸው ነው።

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *