የዘውግ ፖለቲካ አጥፊነት

ሰ.ነ.

ከባዕዴን ያፈነገጡ ዘውጌዎች የብሔር ፖለቲካውን አጡዘውት ግራ ተጋብቶ እንጂ አማራ ከኢትዮጵያዊነት ከወረደ በቀዬው ነው ራሱን የሚገልጸው። አይደለም ተራው ዜጋ ቀርቶ፣ የዘውግ ፖለቲካውን የተቀላቀሉትም ኢትዮጵያዊነትና አማራነት ሲምታታባቸው፣ በሁለት እግር ሁለት ዛፍ ላይ ለመውጣት ሲራወጡ ነው የምታይዋቸው። ከዚህ ግራ መጋባት ጎን ለጎን የጠራ አጀንዳ ስሌላቸው የሚናገሩትና የሚሰሩት ነገር ለቀደምት ኦሮሞና ትግሬ ዘውጌዎች ትርክት እውቅና የሚሰጥ፣ ድጋፉን የሚገልጽ፣ ይበልጥ እንዲቀጣጠል ደግሞ ክብሪት የሚያቀብል እንቅስቃሴ ነው የሚያደርጉት። አማራነት የሰውነት ውሀ ልክ ነው፣ ሰው ፈጣሪውን ማመስገን እንዳለበት ኢትዮጵያ አማራን ማመስገን አለባት፣ ትምክህተኞች ነን አንሸማቀቅበትም ወዘተ የሚሉ አገላለጾች፣ ባህላችንና ቋንቋችን ተረግጦ አማርኝና የአማራ ባህል በላያችን ላይ በግድ ሲጭኑብን ነበር፣ አማራ የትምክህት ለሀጩን ማራገፍ አለበት ወዘተ ለሚሉ አወዛጋቢ ትርክቶች ይሁንታቸውን የሰጡና ማረጋገጫ ያቀረቡበት አገላለጽ ነበር።

ለአማራው የቱ ነው የሚሻለው? እነዚህ ዘውጌዎች ግራ ከመጋባታቸውም በላይ በክፍለሀገርና በአውራጃ ተከፋፍለውም የሚፋጁ ናቸው። ለምሳሌ የወሎና ሸዋ ህብረብሔራዊነት በይፋ የተነገረላቸው፣ በርካታ ጥናቶች የተደረጉባቸውና ዓለም ዓቀፍ እውቅና ያላቸው ቦታዎች ናቸው። በወሎዬንቱ ለማይደራደር ሰው ጎንደሬ ወይም ጎጃሜ ከወሎዬ በላይ ተቆርቋሪ ሆኖ በማጅራት መች ክቡር የሰው ልጅን ሲያስደበድቡ አይታችኋል። ይህ ገና በእንጭጭነት ያላ ነገር ነው። ነገ ጧት በለስ ቢቀናውና ዘውጌ ቢያሸንፍ፣ በከተሞች መሀል ያልተመጣጠነ የእድገት ልዩነት ይኖራል። የፖለቲካ ማእከላቸው የክልል ከተማ ላይ ስለሆነ፣ ባህርዳርን ሲያሳድጉ፣ ደሴንና ጎንደርን የመሳሰሉ ታላላቅ ከተሞች እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ወደ ኋላ የሚቀሩበት ሁኔታ አለ። ከርዕዮተ አለሙ ጋር (ርዕዮተ አለም ከተባለ ነው እንግዲህ) የተቆራኘ ስለሆነ። ባለፉት 27 ዓመታት ገዢው ፓርቲ፣ ከሌላው ብሔር የሚያምነው ትግሬውን፣ ከትግሬውም የማእከላይ ዞኑን፣ ከዞኑም ዓድዋ ወረዳን፣ ከወረዳውም የተመረጡ ጣብያዎች ይብለጥ የሚታመኑበት ሁኔታ የነበረው፣ ገዢዎቹ ትግሬ ስለሆኑ ሳይሆን፣ በዘውግ ተደራጁ ስለነበሩ ነው። የጋራ ርዕዮተ አለም፣ ፖሊሲና ስትራቴጂ የነበራቸው ሰዎች አንድ ላይ ተሰባስበው አገር የሚመሩበት ሳይሆን፣ በፍርሀት ፖለቲካ የሚነዳ ደም ላይ መሰረት ያደረገ የዘውጌ ስርዓት ይከተሉ ስለነበር ነው። ነገ በዘውግ የተደራጀ አማራም ኦሮሞም ሶማሌም ቢመጣ ትግሬዎቹ ከሔዱበት የተለየ መንገድ ሊሔድ አይችልም።

መርጠን የተወለድንበት ወይም መርጠን የምንቀይረው ማንነት ስለሌለ፣ በዘውግ መደራጀት ለለውጥ ዝግ ነው። ትላንት ማርክሲስት የነበረ ዛሬ ኒዮሊበራሊስት ሊሆን ይችላል። ወይም በተቃራኒው ካፒታሊዝምን ያቀነቅን የነበረ ሶሻል ዴሞክራሲን ሊያቀነቅን ይችላል። ይህ ከማወቅና ከባለፈው ስህተት በመማር የሚመጣ ለውጥ ነው። ሰው በሒደት ነው ከስህተቱ የሚማረው። እየተማረ አቋሙን ይቀይራል። እየበሰለ ሲሔድ የበሰለ ሀሳብ ያፈልቃል ወዘተ። በዘውግ የተደራጀ ግ ን የተወለደበትን ብሔር መቀየር ስለማይችል፣ ወይም የኔ ብሔር ስህተት ነው ብሎ ከሌላ ተቀናቃኝ ብሔር ጎን ቆሞ መታገል የክህደት ያህል ስለሚከብደው፣ አካሔዱ በአገርና በወገን ላይ ይቅር የማይባል ጥፋት እያስከተለ ያለ መሆኑን ቢያውቅ እንኳን አይኑን ሙልጭ አድርጎ በጨው ታጥቦ በክህደት የጀመራትን መንገድ እስኪሞት ድረስ ይጓዛታል እንጂ ሊቀየር አይችልም። ከነ አቦይ ስብሓትና ከነስዩም መስፍን የምንማረው ይህንን ነው። እድሜ፣ የስራ ልምድ፣ ሀብት ወዘተ ሊቀይረው ያልቻለ ጥፋትን የሚያሳድድ አቋም ይዘው ዛሬ ድረስ የሚንገታገቱበት ሚስጥሩ ይኸው ነው።

የተሻለውን መንገድ ምረጡ።

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *