«ታላቁ ዝላይ» ና የወረቀት ላይ ዕድገት

በ1958 እኤአ የቻይናው መሪ ማኦ ዜዱንግ (Mao Zedong) «ታላቁ ዝላይ» (The Great Leap Forward) የተባለ የልማት ዘመቻ ቀርጾ አገሪቱን በዕዝ ኢኮኖሚ (command economy) ከድህነት ለማላቀቅ ሞክሮ ነበር። ዘመቻው ለበርካታ ዓመታት ሲዘልቅ የታለመለትን የኢኮኖሚ ዕድገት ግብ ሊያሳካ ቀርቶ የተገላቢጦሽ አገሪቱን ለባሰ የድህነት የርሃብና የጭቆና አዙሪት ዳረጋት። በወቅቱ የቻይና ህዝብ ወደ ግማሽ ቢልዮን ይገመት የነበረ ሲሆን የአብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል መተዳደሪያው ደግሞ ግብርና ነበር። በዘመቻው መሰረት ገበሬዎች በግዳጅ ከቀያቸው ተፈናቅለው ሌላ ቦታ በህብረት እንዲያለሙና የሚያመርቱትን ምርት ለመንግስት እንዲያስረክቡ ይጠበቅባቸው ነበር። መንግስት በበኩሉ ከገበሬው ተቀብሎ ለእያንዳንዱ ዜጋ የለት ራሽን ይሸነሽናል – ለአረሰው ገበሬም ጭምር።

ይህ አሰራር በእስረኞች ላይ ከሚጣል የቅጣት ስራ የማይተናነስ በመሆኑ፡ ገበሬዎች ጠንክረው እንዳይሰሩ ይልቁንም እንዲለግሙ የሚያበራታታ ባህርይ ነበረው። በኮታ ያመረቱትን መንግስት የሚወስድባቸው ከሆነ፡ ተጨማሪ ጥረት ማድረግ ራስን በራስ እንደመቅጣት ይሆናል። ምክንያቱም አንድ ጊዜ ከተሰጣቸው ኮታ በላይ ማምረት ከቻሉ መንግስት ትርፉንም ጭምር ከመውሰዱ ባሻገር፡ ለቀጣዩ ዓመት የሚመደብላቸው ኮታ ከፍ ያደርገውና ለተጨማሪ ልፋት ይዳርጋቸዋል። በዚህ ምክንያት ገበሬዎች እየለገሙ የአገሪቱ ምርት ከዓመት ወደ ዓመት እያሽቆለቆለ፡ ድህነት እየተንሰራፋ፡ ርሃብ እየተስፋፋ ቢሔድም፡ የማኦ መንግስት አገሪቱ የ8% ዕድገት ለተከታታይ ዓመታት እያስመዘገበች መሆኗንና የእርሻ ምርቷ በዕጥፍ ማደጉን ከመግለጽ ወደ ኋላ አላለም ነበር። ለዚህ ፕሮፓጋንዳ ፍጆታ የሚውሉ የታይታ ልማቶችን አልፎ አልፎ ማስመረቁም አልቀረም። ከሁሉም የከፋው የታይታ ፖሊሲው ደግሞ በኤክስፖርት ዘርፍ ይታይ የነበረ ሲሆን ከአገሪቱ አቅም በላይ የእርሻ ምርቶችን ወደ ውጭ እየላከ በአገር ውስጥ የምግብ እጥረትን በማባባስ ርሃቡን አስከፊ አድርጎት ነበር።

      ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲህውም የፕሬስ ነጻነት በሌለበት አገር እውነታውን ለማወቅ ሁሌም አስቸጋሪ ነው። በተለይ ደግሞ አንድ ፓርቲ ሁሉንም የመንግስት መዋቅር ሙሉ በሙሉ በተቆጣጠረበት ሁኔታ፡ ፕሮፓጋንዳ በየቦታው ተደጋግሞ ሲስተጋባ ለጊዜው እውነት ሊመስል ይችላል። በአፈናና በፕሮፓጋንዳ ብዛት የሰውን ልጅ አእምሮ ምናልባት መቆጣጠር ይቻል ይሆናል። ተፈጥሮን ግን ፈጽሞ ማታለልም ሆነ ማንበርከክ አይቻልም። የማኦ መንግስት ከዘመቻው ብኋላ አመርቂ ዕድገት በማስመዝገብ ላይ ነኝ፡ ከተትረፈረፈው የእርሻ ምርቴ ለአለም ገበያም ማቅረብ ችያለሁ ቢልም፡ ዘመቻው ከተጀመረ ከአንድ ዓመት ብኋላ ጀምሮ ለ3 ተከታትይ ዓመታት በሰው ልጅ ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ የርሃብ እልቂት ቻይና ልታስተናግድ ተገዳለች። ከ1959 እኤአ ጀምሮ ለ3 ተከታታይ ዓመታት በርሃብ ምክንያት የሞተው ህዝብ በአስርት ሚልዮኖች የሚቆጠር ነበር። ትክክለኛ ቁጥሩን ለማወቅ አስቸጋሪ ቢሆንም ከ10 ሚልዮን እስከ 50 ሚልዮን ባለው ቁጥር መካከል እንደሚገመት ይነገራል። የዚህ ዕልቂት መነሻ ምክንያት በተፈጥሮ የተከሰተ ድርቅ ነው የሚሉ ቢኖሩም፡ የተሳሳተው የመንግስት ፖሊሲ ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ አያጠራጥርም።ግልጽነትና የመንግስት ተጠያቂነት ባለበት አገር ርሃብ ሊኖር እንደማይችል በጥናት የተረጋገጠ እውነታ ነው።

      የለውጥና ዕድገት ዘመን

      ቻይና ክርሃብ ተምሳሌትነትና መገለጫነት ተሸጋግራ፡ አመርቂ የሆነ የኢኮኖሚ ለውጥ በተጨባጭ ማሳየት የጀመረችው፡ ስልጣን ላይ የነበረው (እና እስከዛሬ ያለው) ኮሚኒስት ፓርቲ ገበያውን ሙሉ በሙሉ ከመቆጣጠር አባዜው ቀስ በቀስ መላቀቅ ሲጀምር ነው። ይህም ከማኦ ሞት ብኋላ የታየ ለውጥ ሲሆን የፓርቲው ሰዎች ከማኦ ሞት ብኋላ ትንሽ የነጻነት አየር መተንፈስ በመቻላቸው የተገኘ ለውጥ መሆኑ ይነገራል። ከማኦ ህልፈተ ህይወት ብኋላ የፓርቲው ሰዎች የመጡበትን መንገድ ለመገምገም ሲሞክሩ፡ አንድ ያነሱት መሰረታዊ ጥያቄ ነበር። ይኸውም “ከስርዓቱ እየሸሸ በሰው አገር ተሰድዶ ይኖር የነበረው ዳያስፖራ፡ በሄደበት ሁሉ የተሻለ ኑሮ መኖር ሲችልና በተሰማራበት ዘርፍ ስኬታማ መሆን ሲችል፡ አገር ውስጥ ያለው ህዝብ በኑሮው ላይ መሰረታዊ ለውጥ ማሳየት ያልቻለው ለምንድን ነው?” የሚል ነበር። ይህ ጥያቄ ፓርቲው ወደ ውስጡ እንዲመለከት፡ ችግሩ ከኛ እንዳይሆን ብሎ ራሱን እንዲፈትሽ ምክንያት ሆነው። ይህንን ተከትሎም አንዳንድ ሪፎርሞችን ማድረግ ጀመረ። ቀደም ሲል ፓርቲው ገበያውን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠሩ ምክንያት የሸቀጦች ዋጋ በመንግስት ይተመን የነበረ ሲሆን፡ ብኋላ በአምራቹና በሸማቹ ግኑኝነት በሸቀጦች አቅርቦትና ፍላጎት መሰረት ዋጋ በገበያ እንዲተመን በማድረግ፡ መንግስት ጣልቃ ገብነቱን ቀስ በቀስ መቀነስ ጀመረ። ቀጥሎም በቻይና ታሪክ መሰረታዊ (radical) የተባለለትን ከመሬት ፖሊሲ ጋር የተያያዘ ሪፎርም ማድረግ ጀመረ። ይኸውም ገበሬ በኮታ የተተመነለትን ምርት (ግብር) ለመንግስት ከከፈለ ቀሪው ምርት የራሱ ይሆናል የሚል ነበር። ቀደም ሲል ያመረተውን ሙሉ በሙሉ በመንግስት ይነጠቅ ለነበረ ገበሬ ይህ ትልቅ ማበረታቻ (incentive) በመሆኑ ገበሬው ሳይለግም ታትሮ በመስራት ምርቱን ማሳደግ ጀመረ። የቻይና መሰረታዊ የለውጥ አብዮት የሚጀምረውም ከዚህ ብኋላ ነው።
      የቁጠባና የለውጥ ዘመን – በግብርና ዘርፍ ምርታማነት ሲጨምር ገበሬዎች ቁጠባ (saving) ጀመሩ። የቁጠባ ሂሳባቸው ዳጎስ ማለት ሲጀምር አንዳንዶች ልጆቻቸውን ከእርሻ አሰናብተው ትምህርት እንዲከተታተሉ ማድረግ ጀመሩ። ሌሎች ደግሞ ቁጠባቸውን ይዘው ከተማ በመግባት በንግድ ስራ መሰማራት ጀመሩ። እንደገና ሌሎች ደግሞ ግብርናውን ትተው ወደ ከተሞች እየፈለሱ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ተቀጥረው መስራት ጀመሩ። የአገሪቱ ቁጠባ እየጨመረ ሲሄድ ኢንቨስትመንቱ እየጨመረ ኢንዱስትሪው እየተስፋፋ ለብዙዎች የስራ ዕድል እየፈጠረ የብዙዎችን ኑሮ እያሻሻለ መሄድ ጀመረ። በግብርናው ዘርፍ የተገኘው ውጤት ለሌሎቹ የኢኮኖሚ ዘርፎች መለወጥ ዋንኛ ምክንያት ነበር። ይኽም ሊሆን የቻለው ለኢንዱስትሪዎች የሚቀርቡ የምርት ግብዓቶችና ርካሽ የሰው ጉልበት በብዛት የሚገኘው ከግብርናው ዘርፍ ስለነበረ ነው።

      የዕድገት ሞተሮች

      በቻይና የለውጥ ሂደት የሚጠቀሱ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም ዋንኞቹ የዕድገት ሞተሮች (engines of growth) ግና የሚከተሉት ሶስት ነጥቦች ይመስሉኛል፡

      • የመጀመሪያው ተዓምራዊው የቁጠባ ባህላቸው ነው። ቻይና በ1980ዎቹ ከአገሪቱ ጠቅላላ ገቢ (GDP) 30 በመቶውን ያህል መቆጠብ (save ማድረግ) ችላለች። ይህ መጠን በ1990ዎቹ ወደ 40 በመቶ ከፍ ያለ ሲሆን፡ በ2008 ከፍተኛውን ሪኮርድ በዓለም በማስመዝገብ 53 በመቶ መቆጠብ ችላለች። የዚህን ቁጥር እንድምታ በትክክል ለመረዳት ትንሽ ጠለቅ ያለ የማክሮ ኢኮኖሚክስ እውቀት ይጠይቅ ይሆናል። አጠቃላይ ግንዛቤ ለመስጠት ያህል ግን በኢኮኖሚው ውስጥ ተዋናይ የሆኑት ግለሰቦች የንግድ ተቋሞችና መንግስት በአማካይ ከ30 እስከ 50 በመቶ ገቢያቸውን save ማድረግ የሚችሉበት የኢኮኖሚና የባህል አብዮት መፍጠር ችለዋል ማለት ነው። አንድ ቢልዮን ህዝብ በአማካይ 50 በመቶ (ግማሽ) ገቢውን በዓመት መቆጠብ ቻለ ማለት አስደናቂ ተአምር ነው።
      • ሁለተኛው ምክንያት ከርካሽና ታታሪ የሰው ጉልበት (labor) ጋር የተያያዘ ነው። የሰው ጉልበት በብዛት የታደላቸው ጸጋ በመሆኑ አሰሪዎች በርካሽ ዋጋ (wage) ሰራተኞችን መቅጠር ይችላሉ። ይህ ዝቅተኛ ክፍያ በተለይ ኤክስፖርት ለሚያደርጉ አምራቾች እጅግ በጣም የሚያበረታታ (incentive) ሲሆን በዓለም ገበያ ምርቶቻቸውን በዝቅተኛ ዋጋ በማቅረብ በገበያ ውድድር እንዲያሸንፉና ትርፋማ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። ቻይና ወደ ውጭ የምትልካቸው ምርቶች በሄዱበት ሁሉ ለሸማቹ ማህበረሰብ በዝቅተኛ ዋጋ የምታቀርብ በመሆኗ አብዛኛውን የዓለም ገበያ በቁጥጥሯ ስር አውላዋለች ማለት ይቻላል። በአገራቸው ገበያ በቻይና አምራቾች የተሸነፉት ምዕራባዊያን ነጋዴዎች፡ የሰው ጉልበት ርካሽ መሆኑ ስለማረካቸውና አትራፊ ሆኖ ስላገኙት፡ ያገር ውስጥ ሰራተኞቻቸውን እያሰናበቱና ድርጅቶቻቸውን እየቆለፉ፡ ሻንጣቸውን ሸክፈው ቻይና በመግባት በአዲስ ፉክክር እንዲጠመዱ ተገደዋል። (ይህን ርካሽ የሰው ጉልበት እላይ ካነሳነው የቁጠባ ባህል ጋር ስናያይዘው፦ ዝቅተኛ ደሞዝ እየተከፈላቸው በአማካይ ግማሹን ያህል ባንክ ማስቀመጥ መቻላቸው የበለጠ አስገራሚ ያደርገዋል። ታድያ ባገር ውስጥም የሸቀጦች ዋጋ (ኑሮ) ርካሽ መሆኑ ይሰመርበት።)
      • ሶስተኛው ምክንያት የቴክኖሎጂ ፈጠራ (technological innovation) ነው። ቻይና ከ30 እስከ 50 በመቶ ገቢዋን በየዓመቱ መቆጠብ ቻለች ማለት ያን ያክል ገቢዋን በሚቀጥለው ዓመት ኢንቨስት ማድረግ ችላለች ማለት ነው። የውጭ ብድርና እርዳታ ሳያስፈልጋት በራሷ ገንዘብ ፋይናንስ የምታደርጋቸው ሰፋፊና ትላልቅ ኢንቨስትመንቶች በየዓመቱ ማከናወን ችላለች ማለት ነው። መንግስት በትምህርት በጤና በመሰረተ ልማት አውታሮችና በመሳሰሉት ኢንቨስት እያደረገ ልማትን ሲያፋጥን ለትምህርት ጥራትና ተደራሽነት የሰጠው ልዩ ትኩረት ደግሞ ለዚህ የቴክኖሎጂ ስኬት ወሳኝ ሚና ነበረው። ቻይና በሌላው ዓለም የተፈጠሩ ቴክኖሎጂዎችን ከመኮረጅ (imitate ከማድረግ) ባለፈ በፈጠራው ዘርፍ አዳዲስ ግኝቶችን በመፍጠር ለዓለም ለማበርከት በቅታለች። የትምህርት ተቋማቷ ከቴክኖሎጂ ጋር አብረው መራመድ የሚችሉና መፍጠር የሚችሉ ብቁ ዜጎችን ገበያው የሚፈልገውን ያህል በብዛት በማፍራት። የኮምፕዩተር፡ የኤሌክትሮኒክስ፡ የቤት ቁሳቁሶች ወዘተ በገፍ እያመረቱ በርካሽ ዋጋ ለውጭ ገበያ ማድረስ ኢኮኖሚያቸው የቆመበት ሶስተኛው ምሰሶ ነው።

      በድህረ ማኦ ባለው ጊዜ በተለይም ከታይንማን አደባባይ አመጽ ብኋላ ቻይና ባደረገቻቸው መሰረታዊ የፖሊሲ ክለሳዎች በአገሪቱ ስር ነቀል ለውጥ መጥቷል። ይህ ለውጥ በአገሪቱ የኢኮኖሚ ጡንቻ፡ በህዝቡ ኑሮ፡ በመንግስቱ ጥንካሬ፡ በግለሰቦችና ድርጅቶች ብቃት፡ አገሪቱ በዓለም ገበያና በዓለም ፖለቲካ ባላት ተጽእኖ እንዲህውም በሌሎች ዘርፈ ብዙ መስኮች የሚታይና የሚንጸባርቅ ህልውና ያለው ለውጥ ነው። በማኦ ዘመን እንደነበረው መሬት ላይ በተጨባጭ የማይታይ የወረቀት ላይ ዕድገት አይደለም። ይልቁንም ነፍስ ያለው ተዓምራዊ ለውጥ ነው። ቻይና ካላት ህዝብ አንጻር በድህነት የሚኖሩ በርካታ ዜጎች ዛሬም በገጠሩ ክፍል ቢኖሯትም፡ ከ800 ሚልዮን በላይ ህዝብ ከድህነት አረንቋ ታድጋዋለች። ከ350 ሚልዮን በላይ የሚሆን ህዝብ (ማለትም ጠቅላላ የአሜሪካን ህዝብ የሚያክል ወይም የአፍሪካን ህዝብ አንድ ሶስተኛ የሚያክል ወይም የኢትዮጵያን ህዝብ ሶስት ዕጥፍ የሚያክል ህዝብ) በ3 አስርት ዓመታት ውስጥ ብቻ መካከለኛ ገቢ ያለው ህዝብ ማድረግ ችላለች። በሰብአዊ መብት አያያዝ፡ ገበያውን ሙሉ በሙሉ ነጻ ካለማድረግ እና የመንግስት ጣልቃ ገብነት ትልቅ ከመሆኑ ወዘተ ጋር በተያያዘ የቻይና ስርዓት የሚተች ቢሆንም በአንድ ትውልድ ግማሽ ዕድሜ አገሪቱን ከመጨረሻ የድህነት ተምሳሌትነት ወደ ሁለተኛ የአለማችን ጠንካራ ኢኮኖሚ ማሸጋገር መቻል የሚያስቀና ትልቅ ስኬት ነው።

      በሚቀጥለው ክፍል የኢትዮጵያን ዕድገት እንዳስሳለን። የኢኮኖሚ ዕድገቱ በባህሪው ከየትኛው ዘመን የቻይና ኢኮኖሚ ጋር እንደሚዛመድ ለማነጻጸር እንሞክራለን። መልካም ቆይታ!

      0 replies

      Leave a Reply

      Want to join the discussion?
      Feel free to contribute!

      Leave a Reply

      Your email address will not be published. Required fields are marked *