አዲሱ ጠ/ሚ/ር ዶ/ር አብይና ከፊታቸው የተጋረጡባቸው የለውጥ እንቅፋቶች ሲዳሰሱ!
******

አዲሱ ጠ/ሚ/ር ዶ/ር አብይ አሕመድ ብዙ ፈተናዎች ከፊታቸው ተደቅነውባቸዋል። ዋንኛውና ትልቁ ፈታና የህዝብ ጥያቄ ነው። ህዝብ መሰረታዊ የሆነ ለውጥ ይፈልጋል፤ የህግ የበላይነት እንዲሰፍን፥ ወንጀለኞች ለህግ እንዲቀርቡ፥ የስልጣን ሽግግር እንዲደረግ ወዘተ። በሌላ በኩል ደግሞ ጥቅማቸው የሚጎድልባቸውና በስጋት ውስጥ የሚኖሩ የስልጣን ማማ ላይ “የተሸሸጉ” ወንጀለኞች አሉ፤ ቅንጣትም ታክል ለውጥ እንዲደረግ የማይፈልጉ። በብዙሃኑ ህዝብ እና በጥቂቶች ነገር ግን የመከላከያና የደህንነት መዋቅሮችን በቁጥጥራቸው ስር ባደረጉ የህወሓት መሪዎችና ጀሌዎቻቸው መሀል ጠ/ሚ/ሩ ተቀርቅረው ይገኛሉ። ጨዋታው ፈታኝ ነው!

ጠ/ሚ/ሩም ሆነ ቲም ለማ ባጠቃላይ የህዝብ ጥያቄ የወለዳቸው የለውጥ አራማጆች ቢሆኑም ድርጅታቸውን አደጋ ላይ ይጥላሉ ተብሎ አይታሰብም። ይልቁንም ጠ/ሚ/ሩም አቶ ለማም በንግግራቸው እንዳንፀባረቁት ፍላግትና ዓላማቸው የህዝብን ጥያቄ በማስተናገድ ድርጅታቸውን መታደግ ነው። ይህንን ለማሳካት ደግሞ ተማፅኗቸው የህዝብ ድጋፍ ላይ ትኩረት አድርጓል። ከውስጥ ምን ዓይነት ፈተናዎች ተደቅነውባቸዋል? እስከዛሬ ድረስ የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነት ተቆናጥጠው እንደፈለጉ ሲፈነጩ የነበሩት የህወሓት መሪዎችና ጀሌዎቻቸው የለውጥ እንቅስቃሴን ለማደናቀፍና የከፍታ ቦታቸውን ለማስከበር ምን ዓይነት ስልቶችን ሊከተሉ ይችላሉ? ከቀላል ወደ ከባድ ስልት በቅደም ተከተል እንሆ እይታዬን፥

1. የለውጥ ቡድኑን ማዳከም።

  • ቲም ለማን ከቲም ገዱ መነጠል።
  • የቲም ለማ አባላትን ማሰር፣ ማፈን፥ ማስፈራራት፥ ወዘተ።
  • በለውጥ አራማጆች መካከል አለመተማመንና ግጭትን መፍጠር።

2. ዶ/ር አብይን በውድም በግድም ከቡድኑ መነጠል።

  • በውድ፥ የተለያዩ አማላይ መደለያዎችን ለድርድር በማቅረብ።
  • በግድ፥ በዶ/ሩና በቤተሰቡ ላይ እርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉ በማስፈራራት።
  • በሸር፥ ከነ አቶ ለማ ጋር በማጋጨት።

3. ቡድኑን ባጠቃላይ በተለይ ደግሞ ዶ/ር አብይን ከህዝቡ መነጠል።

  • ከፍተኛ የስም ማጥፋት ዘመቻ በመክፈት ህዝብ ላይ የስነልቦና ጦርነት ማወጅ። እንዲጠራጠር፥ አመኔታ እንዲያጣ ድጋፉን እንዳይሰጣቸው ማድረግ።
  • ከየአቅጣጫው ከፍተኛ ግፊት መፍጠር። እጅግ በጣም ብዙ እና አወዛጋቢ እንዲህውም እርስ በእርሳቸው የሚጋጩ ጥያቄዎችን ከሁሉም አቅጣጫ እንዲቀርብ በደህንነቶቻቸው አማካኝነት መስራት።
  • የጎሳ፥ የብሔርና የድንበር ግጭቶችን በየቦታው በማስነሳት በለውጥ ሀይሉና በጠ/ሚ/ሩ ከፍተኛ ራስ ምታት መፍጠር። በተለይ ደግሞ ኮማንድ ፖስቱ ከተነሳ፥ ይህንን አማራጭ በግንባር ቀደምትነት ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ አምናለሁ።

4. የማያሰሩ መዋቅሮችን መዘርጋት

  • አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አንዱ ነው። ይህ እንዳይነሳ እስከመጨረሻው ድረስ እንደሚሟሟቱ አምናለሁ። በጠ/ሚ/ሩ እና በለውጥ ሃይሉ እንቅስቃሴ ብቻ ይህ አዋጅ መነሳት ስለመቻሉ እጠራጠራሉ። ከህዝብ ግፊት መኖር አለበት። ዓለም ዓቀፍ ማህበረሰብ ጫና እንዲፈጥር መሰራት አለበት።
  • ሌሎች አፋኝ የሆኑ አዋጆችና አሰራሮች እንዳይሻሩ የቻሉትን ሁሉ ያደርጋሉ። የፀረ ሽብር አዋጅ፥ የፕሬስ አዋጅ፥ የመያድ አዋጅ፥ ወዘተ።
  • እንግዳ የሆኑ የማያሰሩ መንግስታዊ መዋቅሮችንና አሰራሮችን መዘርጋት። ለምሳሌ በሰፊው እያነጋገረ ያለ ታስክ ፎርስና የስልጣን ገደቡ።

5. ግልፅና ቀጥተኛ የሆኑ አፍራሽ እርምጃዎችን መውሰድ

  • ኩዴታ (ግልበጣ)
  • ኢህአዴግን ማፍረስ (የማፍረስ ትሬት)
  • የመገንጠል ጥያቄዎችን በየአቅጣጫው ማስነሳት።

እጅ መስጠት

  • እነዚህን ተራ በተራ በሙሉ ወይም በከፊል ሞክረው ከከሸፈባቸው፥ ወይም
  • የለውጥ ቡድኑ የህዝብ ድጋፍ አግኝቶ ካዳከማቸው፥ ወይም
  • እርስ በእርሳቸው ተከፋፍለው ከተዳከሙና እጅ መስጠት የተሻለ ሆኖ ካገኙት ሽንፈታቸውን ተቀብለው፥ በድርጅቱ ውስጥ የተጀመረውን ለውጥ ሳይወዱ በግድ ሊቀበሉ ይችላሉ። ከዚህም ያተርፋሉ እንጂ አይጎዱም።

መደምደሚያ!

ህዝብ ሰላምና መረጋጋትን ከፈለገ፥ አስከትሎም የሚፈልገውን ለውጥ ለማምጣት ከፈለገ፥ እነዚህን ሰዎች የማዳከም ስራ ላይ ቅድሚያ ትኩረት መስጠት አለበት። በእርግጠኝነት እጅ መስጠታቸው ሲታወቅ የለውጥ ሃይሉ ላይ የሚፈጠር ግፊት ይበልጥ አመርቂ ውጤት ያስገኛል የሚል እምነት አለኝ። ይህን ከማረጋገጣችን በፊት ሁኔታዎችን በጥንቃቄ ያላገናዘቡ ግፊቶችን በየአቅጣጫው መፍጠር የለውጥ ሂደቱ እንዲቀለበስ ራሱን የቻለ አሉታዊ ሚና ይኖረዋል። አገራችን ከገባችበት አጣብቂኝ አንፃር ሲታይ አሁን እየተፈጠረ ካለው፥ ተስፋ ሰጪና ሰላምና መረጋጋትን ማዕከሉ ያደረገ የለውጥ እንቅስቃሴ አንፃር ሲታይ፥ ሌላ የተሻለ አማራጭ መንገድ ስለመኖሩ እጠራጠራለሁ። አጋጣሚውን በጥንቃቄና በደንብ በተሰላ መንገድ እንደምንጠቀምበት ተስፋ በማድረግ ፅሁፌን እዚህ ላይ ልቋጭ።

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Recent
Comments