Tag Archive for: ኢኮኖሚ

የአገሪቱ አጠቃላይ የውስጥና የውጭ ዕዳ 2.01 ትሪሊየን ብር መድረሱን መንግሥት ይፋ አደረገ

ምንጭ | ሪፖርተር | ዮሐንስ አንበርብር

የዕዳ መጠኑ ከአገሪቱ አጠቃላይ ምርት (ጂዲፒ) 50.8 በመቶ እንደሆነ ተመላክቷል

የኢትዮጵያ አጠቃላይ የአገር ውስጥና የውጭ ብድሮች ዕዳ 2.01 ትሪሊየን ብር መድረሱን፣ ሰሞኑን የወጣው የመንግሥት የዕዳ መጠን መግለጫ ይፋ አደረገ።

የገንዘብ ሚኒስቴር ሰሞኑን ይፋ ያደረገው አጠቃላይ የዕዳ መጠን መግለጫ ሰነድ፣ እ.ኤ.አ. እስከ ሴፕቴምበር 2020 ድረስ ኢትዮጵያ ያለባትን አጠቃላይ የአገር ውስጥና የውጭ ብድሮች ዕዳ የሚገልጽ ነው።

በዚህም መሠረት ማዕከላዊ መንግሥት በቀጥታና መንግሥት በሰጠው የብድር ዋስትና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከአገር ውስጥና ከውጭ ምንጮች ተበድረው ያልከፈሉት አጠቃላይ ዕዳ 54.7 ቢሊዮን ዶላር እንደ ደረሰ ሰነዱ ያሳያል።

ከአጠቃላይ 54.7 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ 28.99 ቢሊዮን ዶላር የሚሆነው ከውጭ የብደር ምንጮች የተገኘ ሲሆን፣ ይህም ሰነዱ በተዘጋጀበት ወቅት በነበረ የብር የውጭ ምንዛሪ ተመን ተሰልቶ 1.06 ትሪሊየን ብር እንደሆነ ሰነዱ ያመለክታል።

ከተጠቀሰው 54.7 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ፣ ከውጭ አበዳሪዎች የተገኘው ተቀንሶ የሚቀረው 25.7 ቢሊዮን ዶላር ደግሞ ለአገር ውስጥ የብድር ምንጮች የሚከፈል የአገር ውስጥ ዕዳ እንደሆነ ሰነዱ ያስረዳል። ለአገር ውስጥ የብድር ምንጮች መከፈል፣ ያለበት ዕዳ ይህ የዕዳ መጠን ሰነዱ በተዘጋጀበት ወቅት በነበረ የብር የውጭ ምንዛሪ ተመን ተሠልቶ የቀረበ ሲሆን፣ በዚህ ሥሌት መሠረት የአገር ውስጥ የመንግሥት ዕዳ 945 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ተጠቅሷል።

አጠቃላይ ከሆነው 54.7 ቢሊዮን ዶላር የአገር ውስጥና የውጭ የዕዳ መጠን ውስጥ 30.6 ቢሊዮን ዶላር የሚሆነውን በቀጥታ ማዕከላዊ መንግሥትን የሚመለከት ሲሆን፣ ይህም የአጠቃላይ ዕዳው 56 በመቶ ነው።

ከአጠቃላይ የዕዳ መጠን ውስጥ ማዕከላዊ መንግሥትን የሚመለከተው ከተቀነሰ በኋላ የሚቀረው 24.1 ቢሊዮን ዶላር፣ ወይም የአጠቃላይ ዕዳው 44 በመቶ የሚሆነው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ዕዳ ነው።

ከአጠቃላይ የዕዳ መጠን ውስጥ 25.7 ቢሊዮን ዶላር ወይም 945 ቢሊዮን ብር የሚሆነው ከአገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት የተወሰደ ሲሆን፣ በአመዛኙም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተወሰደ መሆኑን ሰነዱ ያመለክታል።

ከተጠቀሰው የአገር ውስጥ ዕዳ 525 ቢሊዮን ብር የሚሆነውን ያበደረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደሆነ ማስረጃው መረዳት ተችሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከጥቂት ወራት በፊት ይህንኑ ሁኔታ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማስረዳታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በወቅቱ ባደረጉት ንግግርም መንግሥታቸው ተግባራዊ ማድረግ የጀመረው የኢኮኖሚና የፋይናንስ ዘርፍ ሪፎርም ፈጥኖ ባይደርስ ኖሮ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመውደቅ አደጋ ተጋርጦበት ነበር ማለታቸው አይዘነጋም።

መንግሥት እያደረጋቸው ከሚገኙ ሪፎርሞች መካከል የመንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተበድረው ያልከፈሉትን ዕዳ ቀስ በቀስ ወደ መንግሥት ማዘዋወር አንዱ ተግባራዊ መደረግ የጀመረ የመፍትሔ አማራጭ መሆኑን ሪፖርተር ያገኛቸው ሌሎች መረጃዎች ያመለክታሉ።

ከአጠቃላይ የአገሪቱ ዕዳ ውስጥ ለውጭ አበዳሪዎች የሚከፈለው 28.99 ቢሊዮን ዶላር ወይም 1.06 ትሪሊዮን ብር ግን አለመክፈል የሚቻልበት ሁኔታ ዝግ በመሆኑ፣ የኢትየጵያ ደግሞ በማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ውስጥ በመውደቁ፣ ለመንግሥት ከፍተኛ የራስ ምታት ሆኗል፡፡ መንግሥትም ይኼንኑ ሕመሙን ሳይሸሽግ በተደጋጋሚ ጊዜ ሲገልጸው መቆየቱ ይታወሳል።

ይኼንን የውጭ ዕዳ የመክፈያ ጊዜ እንዲራዘም ከመደራደር ውጪ የመክፈሉ ግዴታ የማይለወጥ እንደሆነ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ይህንን የውጭ ዕዳ ኢትዮጵያ መክፈል እንደማትችል ከተረጋገጠ ደግሞ አገሪቱን ጥቁር መዝገብ ውስጥ እንድትሰፍርና በቀጣይ የውጭ ብድር ፍላጎቷ በር የሚዘጋ ሁኔታን ሊፈጥር እንደሚችል ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

የውጭ ዕዳን ሙሉ በሙሉ ማሰረዝ አስቸጋሪ መሆኑን የሚገልጹት ባለሙያዎቹ፣ የቀደሙ የኢትዮጵያ መንግሥታት በአሁኑ ወቅት ከፈረሰችው ሶቪዬት ኅብረት ተበድረው ያልመለሱት ዕዳ፣ አሁንም ድረስ በዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) የኢትዮጵያ የውጭ ዕዳ ተብሎ እስካሁን ተመዝግቦ እንደሚገኝ ይገልጻሉ።

አገሪቱ ካለባት የውጭ ዕዳ ውስጥ ብቻ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ድርሻ 36 በመቶ መሆኑን ሰነዱ የሚያመለክት ሲሆን፣ 54.7 ቢሊዮን ዶላር ከሆነው አጠቃላይ የአገሪቱ የአገር ውስጥና የውጭ ዕዳ ውስጥ 44 በመቶው ወይም 24.1 ቢሊዮን ዶላር የሚሆነው የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ዕዳ እንደሆነ ይጠቁማል።

አጠቃላይ የመንግሥት ዕዳ የኢኮኖሚ ዕድገት መለኪያ ከሆነው አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) 50.8 በመቶ እንደሚሆን መረጃው ያመለክታል። ከዚህ ውስጥ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች የአገር ውስጥ ዕዳ ለብቻው ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት አንፃር 12.5 በመቶ ድርሻ ይዟል።

የአገሪቱ የውጭ ዕዳ አማካይ የመክፈያ ጊዜ 15 ዓመት መሆኑንም መረጃው ያመለክታል።

ሊበራላይዜሽን?መለስ ዜናዊ እና አብይ አሕመድ

መለስ ዜናዊን በብዙ ምክንያት እቃወመው ነበር። ይህን ከፋፋይ የዘር ፖለቲካ ማምጣቱ፣ ስልጣን ላይ ሙጭጭ ማለቱ፣ ስልጣን ላይ ለመቆየት የተጓዘበት ርቀት(የሚመራው ድርጅት በሀሳብ ድርቅ እስኪጠቃ ድረስ የተማረ ሰው የማያስጠጋ መሆኑ)፣ ወዘተ ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው። ማንም የማይክደውና የሚደነቅበት ብቃት ደግሞ ነበረው። የኢኮኖሚክስ እውቀቱ ከባድ ሚዛን (ወርልድ ክላስ) ነበር።

መለስእነ ጆሴፍ ስቲግልዝ (በኢኮኖሚክስ ኖቤል ተሸላሚዎች) ፣ እነ ፒተር ጊልስ (አዋርድ ዊኒንግ ጋዜጠኞች)፣ እነ አሌክስ ዴ ቫል እና ሌሎችም ብዙ ግዜ መስክረውለታል። መጽሀፋቸው ላይ አንድ ምእራፍ ሙሉ ሰጥተው ትንታኔውን ከትበውታል፣ አድናቆታቸውን ችረውታል። መለስ የተደነቀበት የኢኮኖሚክስ እይታ “በድሀ አገር ሙሉ በሙሉ ነጻ ገበያ መፍቀድ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል”፣ “ሉአላዊነታቸውን ያሳጣቸዋል”፣ “በውጭ ባለሀብቶችና ኢንቨስተሮች ቁጥጥር ስር ይወድቃሉ” በሚለው አቋሙ ነው። በኢትዮጵያ ይህን ከምፈቅድ፣ እንደኤሊ ቀስ እያልን ብናዘግም እመርጣለሁ። የሚል ጽኑ አቋም ነበረው። በተለይ ጆሴፍ ስትግልዝ ከባንክና ከመሬት ሊበራላይዜሽን ጋር በተያያዘ በአንዲት ሌሊት ብዙና ጠንካራ የመከራከሪያ ጭብጦችን ማንሳቱ በአግራሞት ያወሳል። በተለይ ከኢስት ኤሽያ ክራይስስ ብዙ ምሳሌዎችን በመጥቀስ፣ ካገሩ ሁኔታ ጋር በማያያዝ አስደማሚ ክርክሮችን ማንሳቱን በአድናቆት መጽሀፉ ላይ ከትቦታል።

ዛሬ ሴንሲብል የሆኑ የአሜሪካ ምሁራን ጆሴፍ ስቲግልዝን ጨምሮ የነጭ ካፒታሊዝም ተቃዋሚዎች ናቸው። ዘ ኢኮኖሚስት በተደጋጋሚ የሚጽፋቸውን አርቲክሎች ላነበበ፣ የስካንዲኔቭያን ዓይነት ኢኮኖሚክ ሞዴል ተግባራዊ ለማድረግ የከጀሉ ይመስላል። በተደጋጋሚ በሚያስተዋውቁት አንድ የሽፋን ገጻቸው “ሶሻሊዝም የነገ ርእዮተ ዓለም” የሚል ምጸት ይዘው ቀርበዋል። የአየር ለውጥ የሚያሳስባቸው ኢኮኖሚስቶችና ፖለቲካል ሳይንቲስቶች፣ እንደዚሁም የአካባቢ ጥበቃ አድቮኬሲ ቡድኖችና ፈላስፋዎች እንደነ Naomi Klein ፣ Noam Chomsky፣ Slavoj Žižek እና የመሳሰሉት አለምን ለማዳን ከነጭ ካፒታሊስት (ነጻ ገበያ) ስርዓት መውጣት አለብን፣ ሲሉ ላንቃቸው እስኪነቃ ድረስ ያቀነቅናሉ።

በአንጻሩ አብይ አሕመድ ወደ ስልጣን ከመጣ ጀምሮ ማንም ሳይመርጠውና ይሁንታውን ሳይሰጠው፣ የኢትዮጵያን ህዝብና አገር ወክሎ የሚወስናቸው ውሳኔዎችና የሚፈጽማቸው ውሎች፣ እስከዛሬ ድረስ መለስና ኢህአዴግ አስከብረዉት የነበረ የኢኮኖሚ ሉአላዊነት የሚያስደፍር ነው። ይህ ድርጊቱ የአገሪቱን ሉአላዊነት በረጋግዶ አሳልፎ ከመስጠት ተለይቶ ሊታይ አይችልም። የአለም ካፒታሊስት ስርዓት አራማጅ ወደ መሀል እየመጣ ባለበት፣ በቅይጥ ኢኮኖሚ ስርዓት(ቅድሚያ ላገር ውስጥ ባለሀብት ቦታና ትኩረት በመስጠት) ኢኮኖሚያቸውን እያሳደጉ ያሉ አገራት በተበራከቱበት፣ አብይ ብቻውን ወደዚህ መንደር የሚያደርገው ግስጋሴ ከእንጭጭ ጭንቅላት የመነጨ ከሰራቸውና እየሰራቸው ካሉ ክፋቶች ሁሉ የከፋ ተግባር ነው።

አዎ ኢህአዴግ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ያስመዘገበው እድገት አለ። ከሚያገኘው ከፍተኛ ድጋፍና ብድር ጋር የማይመጣጠን ዝቅተኛ እድገት ቢሆንም የኢኮኖሚ ዕድገት ነበረ። ኢህአዴግ የሚወገዘው እድገት ባለማስመዝገቡ ሳይሆን፣ ህዝብን የዛ እድገት ተጠቃሚ አለማድረጉና የተመዘገበው እድገት ለጥቂቶች ብቻ የተደፋ ዳቦ በማድረጉ ነበረ። በሌላ አነጋገር በግልጽም ይሁን በድብቅ እየዘረፉ ራሳቸውንና በዙሪያቸው ያሉትን ብቻ እየጠቀሙ ሌላውን አድኽይተው ለመግዛት መሞከራቸው ነበር ትልቁና ዋነኛ ስህተታቸው። ይህን ስህተት አብይ በቀላሉ ማረም ይችል ነበር። ገበያውን በረጋግዶ ለውጭ ኮርፖሬሽኖች ልስጥ ማለት አያስፈልገውም ነበር።

ህዝብን የእድገቱ ተጠቃሚ ለማድረግና የተሻለ እድገት እንዲኖር ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለበት አሰራር መዘርጋት ነበር የሚያስፈልገው። በሌላ አነጋገር በነጻ ገበያ ስም ያገር ሀብት ከመቸብቸብ በፊት የህግ የበላይነት ማስከበር መቅደም ነበረበት። ሙስኞችን ለህግ ማቅረብ፣ የህዝብ ንብረት ማስመለስ፣ ነጻ ሚድያ፣ ነጻ የፍትህና የኦዲት ስርዓት መዘርጋት ወዘተ በማስቀደም ህዝብን ተጠቃሚ ማድረግ መቅደም ነበረበት። በሒደት የአገር ውስጥ ባለሀብት አቅም ካካበተ ብኋላ እና ዛሬ ለውጭ ባለሀብት ሊበራላይዝ እየተደረጉ ያሉ የመንግስት ኩባንያዎችን በጨረታ ተወዳድሮ የማሸነፍና የመግዛት አቅም ሲፈጥር ነበር፣ ዛሬ እየተወሰደ ያለው የሪፎርም እርምጃ ሊወሰድ ይገባ የነበረው። በሌላ አነጋገር፣ ለአገር ውስጥ ባለሀብት ቅድሚያ በሚሰጥ ፕሮቴክሽኒስት ፖሊሲ ነው ነጻ ገበያ መለማመድ የሚኖርብን።

ከፈረሱ በፊት ጋሪው ቀድሟልና ወደ ተግባራዊነቱ ከመሸጋገሩ በፊት የሚመለከታቸው አካላት፣ ዩኒላተራሊ እየተወሰነ ባለው በዚህ ሰውዬ አካሔድ ላይ ልጓም ቢጤ ቢያኖሩለት ይመከራል።

ስደት – የስልጣን ማደላደያና የገንዘብ ምንጭ

ስደት – የስልጣን ማደላደያና የገንዘብ ምንጭ ስደት ትላንት – ከጦርነትና ከርሀብ በቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ወቅት፣ ከቀያቸው ተፈናቀለው በስደተኞች ካምፕ የተጠለሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በሚልዮኖች ይቆጠር ነበር። በዚህም ምክንያት በዓለማችን ከፍተኛ የስደተኞች…

ዕድገት: በቻይናና ኢትዮጵያ (ክፍል 1)

«ታላቁ ዝላይ» ና የወረቀት ላይ ዕድገት በ1958 እኤአ የቻይናው መሪ ማኦ ዜዱንግ (Mao Zedong) «ታላቁ ዝላይ» (The Great Leap Forward) የተባለ የልማት ዘመቻ ቀርጾ አገሪቱን በዕዝ ኢኮኖሚ (command economy) ከድህነት…