አራቱ የኢትዮጵያ ህገ-መንግስታት

በአብዛኛዉ የታሪክ ክፍል የኢትዮጵያ አስተዳደር በሁለት ቁልፍ ሰነዶች ይመራ ነበር፡ በክብረ ነገስት እና በፍትሀ ነገስት። በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተጻፈው ክብረ ነገስት፣ የስልጣን ምንጭ ከሰለሞናዊው ስርወመንግስት የሚመነጭ መሆኑን ያስቀምጣል። በ13ኛው ክፍለ ዘመን በአረብኛ የተጻፈው እና ኋላም ወደ ግእዝ የተተረጎመው ፍትሀ ነገስት በበኩሉ፣ የቤተ ክርስቲያን መተዳደሪያ ደንቦችንና የፍትሐ ብሔር ሕጎችን ይዘረዝራል። እነዚህ ሁለቱ ሰነዶች በአተገባበር ላይ ልዩነቶች ቢኖራቸውም፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ተፅዕኖ በመፍጠር ረገድ አቻ የሌላቸው ቁልፍ ሰነዶች ነው።

ህገ-መንግስታት

ዘመናዊቷ ኢትዮጵያ በአራት ሕገ መንግሥታት ተስተዳድራለች። በ1930ዎቹ በአጼ ሀይለስላሴ ለመጀመሪያ ግዜ የተዋወቀውና በስራ ላይ የዋለው ህገመንግስት፣ ልክ እንደ ክብረነገስት ሁሉ፣ የስልጣን ምንጭ ከሰለሞናዊው ስርወ መንግስት እንደሚቀዳ ይጠቅሳል። ይህ ህገመንግስት ተስፋ ሰጪ የሪፎርም አንቀጾችን አካትቶ የነበረ ቢሆንም፣ አብዛኛውን ስልጣን ለንጉሰ ነገስቱ በመስጠት፣ በዋናነት ህጋዊነትን የማላበስ ሚና ተጫውቷል።

በ1950ዎቹ ተሻሽሎ የቀረበው የዚሁ ህገመንግስት ቅጥያም፣ አንዳንድ ተጨማሪ መብቶችን አካትቶ የነበረ ቢሆንም፣ ቀዳሚ ሚናው አሁንም ለንጉሰነገስቱ ስልጣን ህጋዊ ሽፋን መስጠት ነበር። በ1970ዎቹ ይህንኑ ህገመንግስት ለሶስተኛ ግዜ ለማሻሻል፣ ረቂቅ ተዘጋጅቶ የነበረ ሲሆን፣ በአብዮቱ ምክንያት ወደ ተግባር ሳይቀየር ተጨናግፎ ቀርቷል።

ዘውዳዊው ስርዓትን በመፈንቅለ መንግስት ገርስሶ ስልጣን ላይ የተቀመጠው የደርግ ስርዓት በበኩሉ የራሱን ህገመንግስት ስልጣን ከያዘ ከ10 ዓመት ብኋላ ያጸደቀ ሲሆን፣ ከራሺያው ኮሚኒስት ስርዓት እንደወረደ የተቀዳ እንደነበር የሚናገሩት ብዙዎች ናቸው። ይህ ህገመንግስት የኢትዮጵያ ሰራተኞች ፓርቲን (ኢሰፓ) ወሳኝ ስልጣን በማላበስ፣ በአገሪቱ ጉዳይ ፈላጭ ቆራጭ ሀይል አድርጎ ያስቀምጣል። በሰብአዊ መብቶች ረገድ፣ አሁን በስራ ላይ ካለው ህገመንግስት ያልተናነሰ ድንጋጌዎች የነበሩት ቢሆንም፣ በተግባር ወታደራዊው ስርዓት ለነዛ መብቶች ቁብ የማይሰጥ እንደነበረ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚያውቀው ጉዳይ ነው።

አራተኛውና ከ1987 ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ በስራ ላይ ያለው ህገመንግስት፣ በዋናነት የሚታወቀው፣ ለብሔር ብሔረሰቦች ልዩ መብት (እስከመገንጠል ድረስ) የሚያጎናጽፍ መሆኑ ነው። በኢህአዴግ መሪነትና አብላጫ ድምጸ ውሳኔ የጸደቀው ይህ ህገመንግስት፣ ዛሬ ኢትዮጵያ ለምትገኝበት የእርስ በእርስ ግጭትና ቁርቁዝ፣ መነሻ ምክንያት እንደሆነ የሚናገሩት ብዙዎች ናቸው። እንደነዚህ ተከራካሪዎች አባባል፣ ብሔሮችን እክስመገንጠል ድረስ የሚያጎናጽፍ ያልተገደበ መብት፣ በፖለቲከኞች መካከል አለመግባባት ሲፈጠር፣ መገንጠልን እንደፖለቲካ ካርድ የመጠቀም አዝማሚያ እንዲኖር አስተዋጽኦ አድርጓል ይላሉ። በሌላ በኩል ለብሔሮች እውቅና የማይሰጡት የመጀመሪያዎቹ ሶስት ህገመንግስታት፣ በአንድ ብሔር የበላይነት ተቀርጸው፣ አሃዳዊ ስርዓት በህዝቦች ላይ በግድ እንዲጫን አድርገው የነበረ በመሆኑ፣ የመገንጠል ጥያቄ አነግበው የተነሱ በርካታ ቡድኖች እንደነበሩ የሚያወሱ ተከራካሪዎችም አሉ። በመሆኑም ይላሉ እነዚህ ተከራካሪዎች፣ የመገንጠልና የእርስ በእርስ ግጭት አደጋው ያኔም በተጨባጭ ታይቶ ነበረ። እነዚህ ክርክሮች በጋራ የሚጠቁሙት ነገር ቢኖር የተሻለው አማራጭ ያለው በሁለቱ መካከል መሆኑን ነው። ምናልባትም ለዘላቂ ሰላምና አብሮነት ሲባል ሁሉንም ግምት ውስጥ ያካተተ ህገመንግስታዊ ማሻሻያ ማድርገ ተገቢ ይሆናል።

አራቱን የኢትዮጵያ ህገመንግስታት፣ ከአጭር መግቢያና ሌሎች ጠቃሚ መረጃዎች ጋር፣ በኢንግሊዝኛ ቋንቋ በመጽሃፍ መልክ በልዩ ሁኔታ ተሰንዶ እዚህ ላይ ቀርቧል። ለወዳጅ ለዘመድ፣ ለጓደኛ ያካፍሉ።

የገና ስጦታዬ ነው ወዳጆች!

ጤና ይስጥልኝ!

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *