, , , , ,

የኢትዮጵያ ጉዞ ወዴት? የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ! (ክፍል 1)

  • የኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት (institutions) በአንድ ወቅት ከአውሮፓ አገራት ጋር ተመሳሳይ ነበሩ። ኢትዮጵያ ከአውሮፓ አገራት ጋር ተነፃፃሪ ቦታ ላይ ነበረች።
  • በመቶዎች የሚቆጠሩ ማንነቶች ከስመው ጥቂት ወጥ የሆኑ ማህበረሰቦች ብቻ ዘመናዊቷን አውሮፓ መስረተዋል። አሁንም ግስጋሴው ወደ አንድነት ነው።
  • አውሮፓ የተከተለችው መንገድ ሌሎች በርካታ አገራት ተከትለውታል። ወይም ቀድመው ሄደውበታል (ለምሳሌ ቻይና)።  ኢትዬጵያ ይህን መንገድ አልተከተለችም። ለምን?
  • የኢትዮጵያ የተለየ መንገድ እንድምታው ምንድን ነው? እነዚህንና ሌሎች ነጥቦችን የሚዳስስ ጽሁፍ በሁለት ክፍል ተዘጋጅቷል። ክፍል አንድ እንሆ። መልካም ንባብ!

የአውሮፓ መንገድ

በመካከለኛው ዘመን አውሮፓ ከ500 በላይ በጎሳ በብሔርና በሌሎች ማንነቶች የተደራጁ ተቀናቃኝ “አገራት” (“መንግስታት”) እንደነበሯት ይነገራል። ከዛን ጊዜ ወዲህ ማዕከላዊ መንግስት ለመመስረትና አገራቱ አሁን የያዙትን ቅርፅ ለማስያዝ ስፍር ቁጥር የሌለው የውስጥና የውጭ ጦርነት ተካሂዷል። በነዚህ ጦርነቶች አንዱ አሸናፊ ጎሳ/ብሔር/አገር ሌላውን እየደፈጠጠና እያከሰመ፤ እሱም በተራው ሲሸነፍ በሌላው እየተደፈጠጠና እየከሰመ ዛሬ አውሮፓ የቆመችው 30 በማይሞሉ አገራት ብቻ ነው። ዝነኛው የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ Francis Fukuyama በ2014 ባሳተመው Political Order and Political Decay በተሰኘው መፅሃፉ በተለይ በአውሮፓ የነበረውን የአገር ምስረታ ሂደት አስከፊ ገፅታውን እንዲህ ሲል አስቀምጦታል፥

”Any idea of a nation ineivitably implies the conversion or exlusion of individuals deemed to be outside its boundaries, and if they don´t want to do this peacefully, they have to be coerced [by states or by communal violence]. The twenty five or so nations that made up Europe at the middle of the twentieth century were the survivors of the five hundred or more political units that had existed there at the end of the middle ages.”

(እዚህ ላይ ፀሃፊው ”Any idea of a nation” ሲል የጀመረበት ምክንያት በቻይና በጃፓንና በሌሎች አገራትም የነበረው የአገር አመሰራረት ታሪክ ተመሳሳይ ስለነበረ ነው። ለበለጠ ግንዛቤ መፅሃፉን ማንበብ ይመከራል።)

የአውሮፓ አገራት በጊዜ ሂደት በባህል በቋንቋና በእምነት ከሞላ ጎደል ወጥ የሆነ ማህበረሰብ እየፈጠሩ፡ የማያሻማ ድንበርና ማዕከላዊ መንግስት በጉልበት እየመሰረቱ በመምጣት የአገር ግንባታቸውን ቀድመው አጠናቀው ዛሬ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት አስፍነው በስልጣኔ ጎዳና እየገሰገሱ ይገኛሉ።

ከዚህም አልፈው፡ አህጉሪቱን ወደ አንድ ታላቅ አገር (United States of Europe) የማሸጋገር ራዕይ ሰንቀው የጋራ ህበረት (European Union) በመፍጠር ላለፉት 7 አስርት ዓመታት ልዩነታቸውን በሚያጠብና አንድነታቸውን በሚገምድ ስራ ተጠምደው ቆይተዋል። በማንነት ፖለቲካ ግፊት ምክንያት በቅርቡ የተከሰተው የBREXIT ህዝበ ውሳኔ፡ ይህን ግብ ማሳካት ስለመቻላቸው ጥያቄ የሚያጭር ቢሆንም ራዕያቸውና ታሪካዊ አመጣጣቸው በጥቅሉ ሲታይ ወደ አንድነት ጎዳና የሚደረግ ያልተቋረጠ ጉዞ እንጂ የኃሊት የሚገሰግስ የመነጣጠል ጉዞ አለመሆኑን ያሳያል።

አገር በደምና ባጥንት የተገነባ የትውልዶች ርስት ነውና በእያንዳንዱ የአውሮፓ አገራት የሚኖሩ ዜጎች ከፋም ለማም የመጡበትን የታሪክ ጎዳና በፀጋ ተቀብለው፤ ካለፈው ስህተታቸው እየተማሩ ድንበር ተሻጋሪ የነገ መድረሻቸውን በጋራ ለማገንባት ተግተው ሲሰሩ ይታያሉ እንጂ ስለመጡበት መንገድ ሲነታረኩና አገራቱን እንዳዲስ አፍርሰው ለመገንባት ሲውተረተሩ አይታዩም። ምክንያቱም የኋላው ከሌለ የፊቱ እንደማይኖር ጠንቅቀው ያውቃሉ። የትላንቱን ጠባሳ መካስና መሻር የሚቻለው አገርን በጋራ ተረባርቦ በማበልፀግ እያንዳንዱን ዜጋ የብልፅግናው እኩል ተቋዳሽ በማድረግ ብቻ እንደሆነ ያውቃሉ። ዘላቂ ብልፅግና የሚኖረው ደግሞ የፖለቲካና የአስተሳሰብ ድንበሮችን አፍርሶ ልዩነትን በማጥበብ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ጠንካራ እንድነት/ህብረት በመፍጠር መሆኑን ያምናሉ።

የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ንፅፅር

Why Nations Fail በተሰኘው መፅሃፋቸው የMIT ና የHarvard ፕሮፌሰሮች የሆኑት Daron Acemoglu ና James A. Robinson (ከዚህ ብኋላ A&R) ኢትዮጵያን ከአክሱም ዘመነ መንግስት አንስቶ እስከ 16ኛው ክፍለዘመን ድረስ ከአውሮፓ አገራት ጋር ተነፃፃሪ የስልጣኔ እርከን ላይ ትገኝ እንደነበር ይገልፃሉ። ለምሳሌ አክሱም ከሮም ስልጣኔ ጋር ተነፃፃሪ (comparable) እንደነበረች ሲያትቱ በኢኮኖሚያዊ ተቋማቶቿ ብቻ ሳይሆን በፖለቲካ ርዕዮተ ዓለሟም ጭምር እንደሆነ ይገልፃሉ። ባህር ተሻጋሮ የንግድ ልውውጥ ማካሄድ፡ ገንዘብ መጠቀም፡ ትላልቅ ሃወልቶችንና መንገዶችን መገንባት እንዲህውም እርሻ ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ማራመድ የሚጋሯቸው እንቅስቃሴዎች ነበሩ። የሁለቱም አገራት ነገስታት በተቀራራቢ ጊዜ ክርስትና የተቀበሉ መሆናቸውና በተመሳሳይ ጊዜም ስልጣኔያቸው መዳከሙ ከሚያመሳስሏቸው በርካታ ነገሮች መካከል እንደሆኑ ይጠቅሳሉ።

አክሱም ስልጣኔ ከተዳከመ ብኋላ የአገሪቱ ዕጣ ፈንታ ከሌላው ዓለም ተነጥሎ ተራራ ላይ በመስፈር በዝባዥ የሆነ ፍፁማዊ ስርዓት (absolutist empire) መፍጠር ሆነ። በተመሳሳይ ሁኔታ ከሮም ስልጣኔ መፍረስ ብኋላ በአውሮፓም (ለምሳሌ በኢንግሊዝ) ተመሳሳይ ስርዓት ነገሰ። በኢትዮጵያ በ13ኛው ክ/ዘመን ገደማ (ምናልባትም ቀደም ብሎ) የጉልት ስርዓት ሲፈጠር፡ በአውሮፓም (በተለይ በኢንግሊዝ) ተመሳሳይ ስርዓት (Fuedal Land Tenure) ተፈጥሮ ነበር።  ይህ ስርዓት በሁሉም አገራት ባላባቶቹን እያጎለበተ ተራውን ገበሬ አቅም ቢያሳጣውም በተለይ በኢትዮጵያ በጣም አስከፊና ለረዥም ጊዜ ተገዳዳሪ ሳይገኝለት የዘለቀ ስርዓት እንደነበር ከበርካታ ጎብኚዎች ድርሳናት ማስረጃ ማግኘት ይቻላል። ለምሳሌ ፖርቹጋላዊ ሚስዮናዊ Alvares በ1520ዎቹ የጻፈው ምስክርነት እስከ መሬት ላራሹ ዘመን ድረስ የነበረውን የአገሪቱን እውነታ የሚያንፀባርቅ ነበር፡

“There would be much more fruit and tillage if the great men did not ill-treat the people. … Often one man plows the soil, another sows it and another reaps…. There is no one who takes care of the land he enjoys; not even any one to plant a tree because he knows that he who plants it very rarely gathers the fruit. For the king, however, it is useful that they should be so dependent upon him.”

ለረዥም ጊዜ በአገሪቱ ፖለቲካ የበላይነት ይዛ የቆየችው የቤተ ክርስቲያን ሚና ደግሞ በመንግስቱ ላይ የማያምፅ “ተመስገን ባይ ህዝብ” መፍጠር ሆነ። በፖለቲካው ረገድ ነገስታቱ መንበረ ስልጣናቸውን ከሰለሞናዊው ስርወ መንግስት ጋር በማቆራኘት በእግዜር የተመረጡና በካህን የተቀቡ መሆናቸውን በህዝቡ አእምሮ ውስጥ ማስረፃቸው ህዝብ በአመፅ እንዳይነሳባቸው እድርጓል። በሌላው አለም ላይ (ለምሳሌ በ16ኛው ክፍለዘመን በኢንግሊዝ) እንደታየው ህዝብ በፍፁማዊው አገዛዝ ላይ በማመፅ ነፃነትን ለማስከበር ንቃተ ህሊናው እልዳበረም ነበር። የነዚህ ጥምር ውጤት ደግሞ የ18ኛው ክፈለዘመን የታሪክ አጥኚ Edward Gibbon እንዳለው ከሌላው ዓለም በመነጠል ለዘመናት ጥልቅ እንቅልፍ ውስጥ ገብቶ መርረሳት ሆነ፡

“Encompassed on all sides by the enemies of their religion, the Ethiopians slept near a thousand years, forgetful of the world by whom they were forgotten.”

በየጊዜው የውጭ ወራሪ ኃይል ወይም አልፎ አልፎ የውስጥ ተስፋፊ ሃይል ሲያጋጥም ያንን ለመመከት በሚጎሸም የክተት ነጋሪት ከዕንቅልፉ ካልነቃ በስተቀር ተራራ ላይ የሰፈረው ህዝብ የራሱ የፖለቲካ አጀንዳ ወይም የስልጣኔ ራዕይ ኖሮት ራሱን ከበዝባዥ ስርዓት ነፃ ለማውጣት ወይም ለመስፋፋት አሊያም ወጥ ማህበረሰብ ለመፍጠር ሲሞክር አልተስተዋለም። ባጭሩ በመካከለኛው ዘመን እኩዮቹ የነበሩት የአውሮፓ አገራት የተከተሉትን መንገድ ሳይከተል ቀረ።

የኢትዮጵያ መንገድ

በ17ኛው ክ/ዘመን ኢትዮጵያ የተከተለችው የተለየ መንገድ፡ ከአውሮፓ አገራት (ከኢንግሊዝ) የተለየ ዕጣፈንታ እንዲኖራት ኣድርጓል። በ1660ዎቹ ኢንግሊዝ የፊውዳል ስርዓት ገርስሳ የዘውዱን ስርዓት በመጠኑም ቢሆን የሚገድብ ፓርላመንታዊ ስርዓት ስትከተል፡ ኢትዮጵያ ለረዥም ዓመታት በእርስበርስ ጦርነት ስትታመስ ቆይታ በመጨረሻ ማዕከላዊው መንግስት የተዳከመበትና መሳፍንት የገነኑበት ዘመን ውስጥ ገባች። ለሁለት ክፍለዘመናት (16ኛውና 17ኛው ክፍለዘመን) በጦርነት በምትታመስበት ጊዜ እንኳን የተስፋ ጭላንጭሎች ነበሯት። ከማርቲን ሉተር ኪንግ የተሃድሶ ዘመን 30 ዓመት በፊት በኢትዮጵያ የተሃድሶ እንቅስቃሴ በነ ደቂቀ እስጢፋኖስ ተጀምሮ እንደነበር ከፕሮፌሰር ጌታቸው ሃይሌ መጽሃፍ አንብበናል። እነ ፈላስፋው ዘርዓ-ያቆብ ያቆጠቆጡበት የጎንደር የ«cultural rennaisance» ዘመንም ቀላል የሚባል የለውጥ ጅማሬ አልነበረም። እነዚህ ጅምር እንቅስቃሴዎች ህዝቡ ውስጥ የዘለቁ አልነበሩምና ዘውዱን ሳይፈታተኑት ባጭሩ ተኮላሽተው ቀሩ። ነገር ግን የኢትዮጵያን ዕጣፈንታ እስከወዲያኛው የወሰነውን የፊውዳሎች ሹክቻን ማኮላሸት የቻለ ሃይል አልነበረም።

በ17ኛው ክ/ዘመን በኢንግሊዝ የፊውዳል ስርዓት ቀደም ብሎ ሊገረሰስ የቻለው ዘውዱን የሚፈታተን በግብር የተማረረ middle class ተፈጥሮ ስለነበር መሆኑን A&R ይገልጻሉ። በአንጻሩ ደግሞ በ18ኛው ክ/ዘመን በኢትዮጵያ ዘውዱን የተፈታተነው ሃይል ከፊውዳሊዝም ስርዓት ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን ያለመ (በዘመኑ አጠራር ኪራይ ሰብሳቢ) የመሳፍንት መደብ ነበር። በመሆኑም ከድሮው የከፋ የጌታና የሎሌ (የባላባትና የጭሰኛ) ስርዓት በየመንደሩ ገነነ። ይህን ሁኔታ ቁጭት በሚያጭር መልኩ A&R በመጽሃፋቸው አሳጥረው አጠቃልለውታል፦

“The reason Ethiopia is where it is today is that, unlike in England, in Ethiopia absolutism persisted until the recent past. … Because of this Ethiopian society failed to take advantage of industrialization opportunities during the 19th and early 20th centuries.”

ቢሆንም ለበጎ ሆነ 

በ19ኛውና 20ኛው ክ/ዘመን አውሮፓ (ኢንግሊዝ) በኢንዱስትሪ የዕድገት ጎዳና ስትገሰግስ፡ ኢትዮጵያ በመሳፍንት የተዳከመውን ማዕከላዊ መንግስት በመመለስና “የተበታተነችውን” አገር በመሰብሰብ (reunification ) ስራ ላይ ተጠመደች። በአጼ ቴዎድሮስ የተጀመረው ኢትዮጵያን ወደ አንድ የማሰባሰቡና ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት የመመስረቱ ሂደት፡ በአጼ ዮሃንስ አራተኛ ቀጥሎ በዳግማዊ (አጼ) ምኒሊክ ተቋጨ። የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ አባቶች አገሪቱን አንድ በማድረግ ሂደት በተጠመዱበት ዘመን፡ አውሮፓ ለኢንዲስቱሪዎቿ ፍጆታ የሚውል ጥሬ ዕቃ ፍለጋ አፍሪካን ለመቀራመት የሚያስችል እቅድ ነድፋ ተግባራዊ በማድረግ ዘመቻ ላይ ተጠምዳ ነበር።

ዳግማዊ ምኒሊክ አስቀድሞ ወደ ምስራቅና ደቡብ የአገሪቱ ክፍል ዘምቶ በጉልበት እያስገበረ ኢትዮጵያን ማቃናቱ፡ አገሪቱ ከዘመነ መሳፍንት በፊት እኩዮቿ በነበሩ አውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች ስር እንዳትወድቅ ረድቷታል። አጼ ምኒሊክ ከሁሉም የአገሪቱ አቅጣጫ ህዝቡን አሰባስቦ ወራሪውን የጣልያን ሃይል አድዋ ላይ ድባቅ በመምታት፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ለቅኝ ገዢዎች ያልተበገረ ነጻነቱን በጉልበቱ የተጎናጸፈ ህዝብ አድርጎታል። ይኽም የዓለምን ፖለቲካ እስከወዲያኛው የቀየረ የጀግንነት ታሪክ ሆኖ ተመዝግቧል።

አድዋ ላይ አስደማሚ ታሪክ ባይሰራ ኖሮ ምናልባትም ቅኝ ግዛት ህጋዊነትን ተላብሶ (legitimate ሆኖ) በአፍሪካ ምድር ሊቆይ ይችል እንደነበር የታሪክ አጥኚው ረይሞንድ ዮናስ “The Battle of Adwa: African Victory in the Age of Empire” በተሰኘው መጽሃፉ አስነብቦናል። ይህ ቢሆን ኖሮ ደግሞ ዛሬ የአፍሪካ ዕጣፈንታ እንደ ሰሜን አሜሪካና አውስትራሊያ በወራሪ ሰፋሪዎች ብቻ የቆመች አህጉር ልትሆን ትችል ነበር ማለት ነው። ወደ አሜሪካና አውስትራሊያ የሄዱ የቀድሞ የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ኗሪዎቹን (native Idians and Aborginal Australians) አክስመው እዛው በመስፈር አገራቱን መመስረታቸው ልብ ይሏል። ይህ ግን በአፍሪካ አልሆነም። ምክንያቱም ኢትዮጵያ እንደዘመነ መሳፍንቱ ጊዜ ተበታትና አልጠበቀቻቸውም። አንድ አገርና በአንድ ንጉስ ስር የሚተዳደር ህዝብ የነበራት “ጠንካራ” አገር ሆና ስለቆየቻቸው ቅኝ ገዢዎችን መመከት የቻለች የዓለማችን ብቸኛ አገር ልትሆን ችላለች። በሌላው ዓለም የሚገኝ ጭቁን የሰው ዘር በሙሉ ይኽንን ድል አይቶ ለገዢዎች የሚመች ቄጤማ መሆን አልቻለም። ተገዢው ብቻ ሳይሆን ገዢውም፤ የሰው ዘር በሙሉ እኩል መሆኑን አምኖ ለመቀበል ተገደደ። የዓለም ታሪክ፡ የዓለም ፖለቲካ እስከወዲያኛው ተቀየረ። የሆነው ቢሆንም ለበጎ ሆነ!

(ይቀጥላል)

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *