,

በትግራይ ጦርነቱ አሁንም እንደ ቀጠለ ነው ሲል ተመድ ገለጸ

የተመድ ልኡካን አዲስ በለቀቁት ሪፖርት እንደገለጹት ከሆነ በትግራይ አሁንም አለመረጋጋቱ ቀጥሏል።

ሪፖርቱ እስከተጠናቀረበት ድረስ በመቀለ፣ ሽረና ሸራሮ ዙሪያ በበርካታ ቦታዎች ጦርነቱ እንደቀጠለ ነው።  ልዑካኑ ወደ ሽረና ሽራሮ መጓዝ እንዳልቻለ ገልጿል።

የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት  (UN OCHA) በታህሳስ ወር በሁለት ቡድን ወደ ትግራይ ተጉዞ ጥናት ካደረገ ብኋላ በለቀቀው ሪፖርት መሰረት፣ በጦርነት በተጎዳው ክልል ውስጥ ከ4.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የገለጸ ሲሆን፣ ከጦርነቱ ወዲህ የምግብ እርዳታ ያገኙ ሰዎች 100 ሺ እንደማይሞሉ ለማወቅ ተችሏል።

በተጨማሪም ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ 2.2 ሚሊዮን የክልሉ ኗሪዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ጠቁሟል።

በፀጥታና በቢሮክራሲያዊ መሰናክሎች ምክንያት የከተማ አካባቢዎችን ብቻ ለመገምገም እንደተገደደ የገለጸው የልኡካን ቡድኑ፣ በክልሉ ውሱን የምግብ አቅርቦት እንዳለና ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እየታየ መሆኑን በሪፖርቱ አመላክቷል። የባንክ አገልግሎት ስለመጀመሩ የተገለጸ ነገር የለም።

የልዑካን ቡድኑ በጉብኝቱ “ደካማ የመንግስት አገልግሎቶች፣ አስከፊ የኑሮ ሁኔታ እና የሰብአዊ ጉዳዮች እንዳሉ” መታዘቡን በሪፖርቱ አመላክቷል ፡፡

በርካታ ንብረቶች እንደወደሙና እንደተዘረፉ ያመላከተው ሪፖርቱ፣ በክልሉ ከሚገኙ 40 ሆስፒታሎች ውስጥ በሽተኞችን በአካል ተቀብለው በማስተናገድ አገልግሎት መስጠት የሚችሉት 5 ብቻ መሆናቸውን ገልጿል። ከነዚህ በተጨማሪ አራት ሆስፒታሎች የስልክ አገልግሎት ብቻ ይሰጣሉ ብሏል።

የኤርትራ ወታደሮችም በውጊያው መሳተፋቸውን የኢትዮጵያ መንግስት ሲክድ የቆየ ቢሆንም፣ የንግድ ተቋማትን በመዝረፍ እና ስደተኞችን አፍኖ በመውሰድ የኤርትራ ወታደሮች ተሰማርተው ማየታቸውን ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጠየቁ የእርዳታ ሰራተኞች እና ዲፕሎማቶች ገልጸዋል፡፡

የሰሜን እዝ አዛዥ ሜጀር ጄነራል በላይ ስዩም እና በፌደራል መንግስት የተሾመው ጊዜያዊው የመቀለ ከንቲባ አቶ አታክልቲ ወልደስላሴ በተናጠል ከመቀለ ኗሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ እንደሚገኙ ማመናቸው ይታወሳል።

ሰ.ነ. 

 

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *