,

ስራ አጥነት፣ አለመረጋጋትና የስደተኞች ከካምፕ መውጣት እንደምታው

የኢትዮጵያ መንግስት ወደ አንድ ሚልዮን የሚጠጉ ስደተኞች ከካምፕ ወጥተው ወደ ስራ እንዲሰማሩ መፍቀዱ በመገናኛ ብዙሀን ተነግሯል። ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ዓለማችን ብዙ አስገራሚ ነገሮችን ስታስተናግድ አይተናል። የትራምፕ ፕሬዚደንት ሆኖ መመረጥ፣ የBrexit ህዝበ ውሳኔ፣ እንዲህውም በአውሮፓና በአሜሪካ የኒዮናዚ አቀንቃኞችና ጽንፈኛ ብሔርተኞች ማንሰራራት፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ስደተኞችን ከሚመለከት ፖሊሲና ፖለቲካ ጋር ተያይዞ የመጣ ቀውስ እንደሆነ ይነገራል። የኢትዮጵያ መንግስት የወሰነው ውሳኔ ቀላል የማይባል የፖለቲካ ውሳኔ እንደመሆኑ መጠን ጥቅምና ጉዳቱ ምንድን ነው የሚለውን እንመለከታለን።

1. ጥቅሙ

1.1 ከዲፕሎማሲ አንጻር –

ሀ. ድሀዋ ኢትዮጵያ በግዛቷ ስር ላሉ ስደተኞች የምታደርገው መልካም አያያዝ ለዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብና መንግስታት አርአያ የሚሆን በጎ መልእክት ያስተላልፋል።
ለ. ለሌሎች አፍሪካውያን ወንድሞቻችን በራችን ክፍት መሆኑን ያበስራል። ጥሩ ተምሳሌት በመሆን፣ በአፍሪካ በተለያዩ አገራት በስደት ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን መልካም አያያዝ እንዲደረግላቸው ጥሩ መልእክት ያስተላልፋል።

1.2 አገር ውስጥ –

ሀ. ጎሰኝነትን ቶሎ ለማርከስ ከኢትዮጵያዊነት በላይ ልቆ ማቀንቀን ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ፓን አፍሪካኒዝም ቀዳሚው አማራጭ ነው። ፓን አፍሪካኒዝም በተግባር እውን ሊሆን የሚችለው ደግሞ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ከአህጉራችን ለሚመጡ ሰዎች በራችንንና ልባችንን ክፍት ማድረግ ስንችል ነው። አብረውን ሲሰሩ፣ አብረናቸው ስንኖር፣ በጓደኝነትና በትዳር አጋርነት መተሳሰር ስንጀምር በሂደት ወደ ታች (ወደ ጎሳ) ማየቱን እየተውን ወደ ከፍታው እንድንመለከት ይረዳን ይሆናል።
ለ. ስደተኞቹ ስራ ፈትተው ካምፕ ውስጥ ተጎልተው የመጽዋቾችን እጅ ከሚጠባበቁ፣ ወደ ስራ ተሰማርተው፣ ኢኮኖሚያችን ላይ የራሳቸውን አስተዋጽኦ በማበርከት፣ ለመንግስት ግብር በመክፈል፣ ሸማቹን ማህበረሰባችንን ተቀላቅለው ምርታችንን በመግዛት እንዲህውም ለአገራቸው በማስተዋወቅ (የኤክስፖርት አቅማችንን የማጎልበት ፋይዳ አለው!) ዘርፈ ብዙ ጥቅም ሊያስገኙልን ይችላሉ። በተጨማሪም ከካምፕ የወጣ ሰው ስራ አያማርጥምና ካገኘም ስራ ላይ አይለግምምና፣ ልንማርበት የምንችል የስራ ባህል በማካፈል ረገድ ሊጠቅሙን ይችላሉ።

2. ጉዳቱ (ስራው ከየት ይመጣል?)

ኢትዮጵያ ያልተረጋጋች፣ በሁሉም አቅጣጫ ግጭት የበዛባት፣ መጨረሻው ሊተነበይ በማይችል የለውጥ ማእበል እየተናጠች ያለች አገር ናት።
የለውጥ ማእበሉን የቀሰቀሰው፣ ስራ አጥነትና የኑሮ ውድነት ያሰቃየው ወጣት ነው። ይኽ ወጣት የስርዓት ለውጥ አመጣ እንጂ፣ ኑሮው ላይ ገና ለውጥ አላየም። መንግስት የተጠመደው መሰረታዊ የሚባሉ መዋቅራዊ ሪፎርሞችን በማካሔድ ነው። ስራ የሚፈጥሩ ፕሮግራሞችንና ፕሮጀክቶችን ቀርጾ ስራ አጡን ወጣት የማረጋጋት ስራ ገና አልጀመረም። ባልተረጋጋ አገር ውስጥ የኢኮኖሚ ድቀት ሲታከልበት፣ ወጣቱ ወደ ወንጀል የመሰማራቱ እድል ይጨምራል።
መንግስት ሙሉ ትኩረቱን ሌላ ቦታ ላይ ባደረገበት በአሁኑ ወቅት፣ በመዋቅራዊ ለውጡ ምክንያት ጥቅሙ የተነካበት ኪራይ ሰብሳቢ ኤሊት ለውጡን ለማደናቀፍ ተግቶ እየሰራ እንዳለ ባደባባይ የሚታወቅ ሀቅ ነው። ይህ ሴራም እየተከናወነ ያለው፣ ገንዘባቸውን በመርጨት ስራ አጡን ወጣት ለጥፋትና ለነውጥ ማሰማራት በመቻላቸው ነው። ስለ ሰላም በሚዘመርበት ወቅት ታጣቂና ተደራጅቶ የሚዘርፍ ማፊያ እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አልመጣም። ቀድሞውኑ መንግስት ወጣቱን ወደ ስራ ለማሰማራት ቅድሚያ ሰጥቶ መንቀሳቀስ ሲገባው ቸልተኛ መሆኑ ሳያንስ አሁን ደግሞ አንድ ሚልዮን የሚጠጋ ስራ የሚቀራመት “ተፎካካሪ” ስደተኛ የlabor marketኡን እንዲቀላቀል መወሰኑ አደጋ ያለው አካሔድ ይመስለኛል። ይኽ ያለውን ያለመረጋጋት ሁኔታ ከማባባስ አልፎ በስደተኞቹ ላይ ጥላቻ ለማሳደርና ለግጭት እንዳይጋብዝ ያሰፈራል። ከዚህ በተጨማሪ ከጸጥታና ደህንነት ጋር የተያያዙ ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ። እንዴት ለሚለው ጥያቄ በአጭሩ እንመልከት።
የኢትዮጵያ ህዝብ በየዓመቱ በ2.5% ያድጋል። በዓመት ከሁለት ሚልዮን በላይ ማለት ነው። ከአመት በፊት በነበርንበት ሁኔታ ለመቀጠል፣ መንግስት በዚህ ዓመት ቢያንስ ለ2 ሚልዮን ዜጎች ስራ መፍጠር አለበት። 1 ሚልዮን ስደተኛ ከጨመርንበት ደግሞ፣ ቢያንስ ለ3 ሚልዮን ሰው ስራ መፍጠር አለበት። ይህን ማድረግ ካልቻለ ዘርፈ ብዙ ቀውስ ይፈጠራል። ስደተኛው ራሱ ከካምፕ ወጥቶ ስራ ካጣ ወንጀል ውስጥ ሊዘፈቅ ይችላል። ኢህአዴግን ለውድቀት ከዳረጉት ምክንያቶች አንዱ ምናልባትም ግንባር ቀደሙ፣ ከህዝብ ቁጥራችን ጋር መመጣጠን የሚችል ስራ በየዓመቱ መፍጠር ባለመቻሉ ነው። የዘንድሮ ከአምናውና ካካቻምናው እየባሰ ሲሔድ፣ ሲጠራቀም፣ ሞልቶ የፈሰሰ ዕለት ነው፣ ጎርፍ ሆኖ ጠራርጎ የወሰደው። ዛሬም የስራ አጡንና የህዝብ እድገቱን የሚመጥን ስራ መፍጠርና አገሪቱን ማረጋጋት ባልቻለበት ሁኔታ፣ ይህን ውሳኔ መወሰኑ፣ ለ22 ተጫዋችና ለ3 ዳኛ ብቻ በሚፈቀደ ሜዳ ላይ ተመልካቹንም ፈትቶ እንደመልቀቅ ይቆጠራል።
0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *