የፍልስፍና እና የሳይንስ ወጎች – ካነበብኩት

በሰለሞን ነጋሽ

******

ሶቅራጠስ እስከ ሽምግልና እድሜው ድረስ ወጣቶችን ሰብስቦ ሲያስተምር ኖረና በመጨረሻ ሀሳብን እንደጦር በሚፈሩ የዘመኑ ልሂቃን ክስ ቀረበበት። ወንጀሉ? የወጣቶችን አእምሮ መበከልና መናፍቃዊነት። በዘመኑ የዚህ ዓይነት ክስ ለሚቀርብባቸው ዜጎቿ አቴንስ ሁለት ምርጫ ትሰጣለች – አገር ለቆ መውጣት (ኤግዛይል) ወይም ፍርድ። ሶቅራጠስ ያጠፋሁት አንድም ነገር የለም፣ የምወዳትንና እድሜ ልኬን ያገለገልኳት አገሬን ጥዬ የትም አልሄድም የፈለጋችሁትን ፍረዱ ብሎ ፍርዳቸውን ለመጋፈጥ ወሰነ። ዳኛ ፊት ቀርቦ መሰረተ ቢስ ክሶቹን አንድ በአንድ ከጥልቅ ፍስልፍና ጋር አስረዳ። የአቅም ጉዳይ ሆኖ አጥጋቢ ሆኖ አላገኙትም። በዘመኑ የአቴንስ ባህል መሰረት ጥፋተኛ ነው አይደለም የሚለው የሚወሰነው በዴሞክራሲያዊ ድምፅ አሰጣጥ ነበርና ጥፋተኛ ነው የሚለው በዝቶ ሃምሎክ የሚባል መርዝ ጠጥቶ እንዲሞት ተደረገ። (በዚህ ምክንያት የሶቅራጠስ ተማሪ የነበረው ፕላቶ ዴሞክራሲን አይወድም። ለፕላቶ ከዘውጋዊ፣ ከአምባገነናዊና ከወታደራዊ ስርዓትም የከፋ የመጨረሻው መጥፎ ስርዓት ዴሞክራሲ ነው። ሞብ ሩል (የመንጋ ስርዓት) ይለዋል። የዴሞክራሲ ትርጉምና ባህሪ ያኔና ዛሬ የተለያየ መሆኑን አንባቢ ልብ ሊል ይገባል!) ፍርዱ ከተወሰነ ብኋላ መርዙን ጠጥቶ እስኪሞት ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ሶቅራጠስ ያወራቸው ፍልስፍናዎች ዓለምን እስከዛሬ ድረስ ይንጧታል። ለብዙ ፈላስፋዎችና ሳይንቲስቶች (ሴኔካ፣ ሲሰሮ፣ ጋሊልዮ፣ ወዘተ) ደግሞ ተምሳሌት ሆኖ ሞትን ሳይፈሩ ላመኑበት እስከ መጨረሻ ድረስ መቆም እንደሚቻል  የሚያስታውስ ፅናት ነበር። ዛሬ ከማንም በላይ ገዝፎ የሚታየው ሶቅራጠስ ነው። ከሳሾቹ፣ ፈራጆቹና ገዳዮቹ ደግሞ እንደ ጧት ጤዛ ያኔ ረግፈው ወዲያው ተረስተዋል።   

*****

ሳይንስ ዛሬ ዓለምን በመዳፉ ስር ከማስገባቱ በፊት፣ ኋላቀርና ልማዳዊ አስተሳሰብ ከሚያራምዱ የጭለማ ሃይሎች ጋር እልፍ አእላፍ ጦርነቶችን አካሔዷል። ህዝብን በሀሰት እያወናበዱ የሀብትና የዝና ምንጫቸው ካደረጉ ከተደራጁ ሀይሎች ጀምሮ፣ አዲስ ሀሳብ እንደጦር እስከሚፈሩ ተራ ግለሰቦች ድረስ ሳይንስ ብዙ ጦርነቶችን አሳልፏል። ለምሳሌ በ7ኛው ክ/ዘመን አጋማሽ ላይ ሙስሊሞች ግብፅን በቁጥጥራቸው ስር ሲያስገቡ፣ በአሌክሳንድርያ ቤተመፃህፍት ይገኙ የነበሩ የጥንት የፍልስና፣ የሳይንስ፣ ወዘተ መፃህፍቶች በመሪያቸው ካሊፍ ኡማር ትዕዛዝ አማካኝነት እንዲቃጠሉ ተደርጓል።  ካሊፍ ኡመር ያስተላለፈው ትዕዛዝ እንደ ፈላስፋው ሩሶ አገላለፅ የሚከተለው ነበር ፡ “If the books of this library contain matters opposed to the Koran, they are bad and must be burned. If they contain only the doctrine of the Koran, burn them anyway, for they are superfluous. 

(እነዚህ መፃህፍት በውስጣቸው የያዙት ነገር ከቁርዓን ጋር የሚጋጭ ከሆነ መጥፎ ናቸውና መቃጠል አለባቸው። በውስጣቸው የያዙት የቁርዓን ዶክትሪን ብቻ ከሆነም አላስፈላጊ (ተገዳዳሪ) ናቸውና መቃጠል አለባቸው።) 

በዚህ ድርጊት ምክንያት እውቀት ተጨናግፎ ለ1ሺ ዓመታት የሰው ልጅ በጭለማ ውስጥ ኖረ። በሙስሊም ፈላስፋዎችና ሳይንቲስቶች አማካኝነት ከቃጠሎው የተረፉ ጥቂት ስራዎች ተገኝተው ሳይንስም ፍልስፍናም ከወደቁበት ዳግም ተነስተው ማንሰራራት  የቻሉት የአብርሆት ዘመን ተብሎ በሚታወቀው በ17ኛውና 18ኛው ክ/ዘመን ነው። ለዚህ መዘግየት ዋንኛ ምክንያቱ ደግሞ ከእስልምና ብኋላ የበላይነትን ተቆናጥጦ ዓለምን ሲንጥ የነበረው የካቶሊክ ቤተክርስትያን ነው።  ፈላስፋው ሩሶ የካቶሊክ ጳጳሳት ከካሊፍ ኡመር የተሻሉ ሳይሆኑ የባሱ እንደሆኑ ሲገልፅ እንዲህ ይላል፡ “… suppose Gregory the Great was there instead of Omar and the Gospel instead of the Koran. The library would still have been burned, and that might well have been the finest moment in the life of this illustrious pontiff.” (ትርጉሙ ይለፈኝ!)

በቅደመ ሶቅራጥስ ዘመን የፓይታጎረስ ተከታይ የነበሩ ፈላስፋዎች የሰው ልጅ (ወይም መሬት) የዓለማት ማዕከል አይደለም የሚሉ (eg. Philolaus) ፣ የሁሉም ነገር መሰረቱ ፊዝካሊ ኢንዲቪዝብል የሆኑ ነገር ግን ጂኦሜትሪካሊ ዲቪዝብል የሆኑ አተም-ኦች ናቸው የሚሉ (eg. Democritus, Leucippus) እና ሰው ከእንስሳት ኢቮልቭ ያደረገ ፍጡር ነው የሚሉ (eg. Anaximander) የተለያዩ ፈላስፋዎች ነበሩ። ከ2ሺ ዓመታት ብኋላ ግን እነዚህ ተመሳሳይ ሀሳቦች ዳግም በሳይንቲስቶች (በነጋሊልዮ፣ ዳርዊንና ሌሎችም) ሲነሱ ለእስራትና ለጥቃት ያጋልጡ ነበር፣ የካቶሊክ ቤ/ያን በዘረጋው ሲስተም ምክንያት! ዛሬ እዚህ ለመድረስ በርካታ ሊቃውንት መስዋዕት ሆነዋል። 

*****

ከላይ የተጠቀሰው የአብርሆት ዘመን ዘግይቶም ቢሆን ጮራውን መፈንጠቅ የጀመረው ከበርካታ የነፃነት ተጋድሎና የፖለቲካ ስርዓት መሻሻሎች ብኋላ ነው። ለምሳሌ በኢንግሊዝ የነበረው ዘውዳዊ ስርዓት በፓርላመንታሪያን ሀይሎች ተንኮታኩቶ አዲስ ስርዓት የተዘረጋው እኤአ ከ1688 ዓም ጀምሮ ነበር። ይህ በተወሰነ ደረጃ ለFree Thinkers (አሰላሳዮች) የተወሰነ ነፃነትን አጎናፅፎ የምርምርና የዕውቀት ስራዎች ከአንዱ ወደ ሌላው በነፃነት እንዲዛመቱ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሯል። የስርዓት ለውጥ ለማምጣት ለፓርላመንታሪያን ሀይሎች ጉልበት የሰጣቸው ነገር ቢኖር ደግሞ ምናልባት የማርቲን ሉተር የፕሮቴስታኒዝም ሪፎርም (Reformation) ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ሳይሆን አይቀርም።  የዚህ ሪፎርም እንቅስቃሴ የተጀመረው ማርቲን ሉተር “The Ninety-five Thesesን” በፃፈበት እኤአ በ1517 ዓም ነው ተብሎ ይታመናል። ከዛ በፊት (ከበርካታ ዓስርት ዓመታት በፊት) በአገራችን በአፄ ዘርዓ-ያቆብ ዘመነ መንግስት (1426-1460 ዓም) ተመሳሳይ የተሃድሶ እንቅስቃሴ በእነ ደቂቀ-እስጢፋኖስ አማካኝነት ተካሂዶ እንደነበር ከፕ/ር ጌታቸው ድንቅ ስራ አንብበናል። በዛን ወቅት ተራ መኖክሴዎች ለተሀድሶ ተነስተው፣ በዝባዥ ተቋማትንና ስርዓቶችን ባደባባይ እያወገዙ  ብዙ ተከታዮችን ማፍራት ችለው የነበረ ቢሆንም፣  ሆድ አምላካቸው የነበሩ የቤ/ክ/ያን መሪዎች ከንጉሱ ጋር በመመሳጠር የእንቅስቃሴውን መሪዎችና ታማኝ ተከታዮቻቸው በተለያዩ አረመኔያዊ እርምጃዎች ድራሻቸውን አጥፍተዋቸዋል። አገሪቱን ከተኛችበት የሚቀሰቅስና በባዕድ አገራት ከተሸረበባት ተንኮል ስር ሳይሰድ አርነት የሚያወጣ አንድ እንቅስቃሴ በእንጭጩ ተጨናግፎ ቀረ። (በነገራችን ላይ ስለ ኢትዮጵያ ሳስብ ሁሌም የሚቆጨኝ ይህ የታሪክ ምዕራፍ ነው! አዳዲስ ባዕድ ሀይማኖት ሲመጡ ለመቀበል የማይቸግረው ህዝብና አገር ከውስጡ የወጡ የለውጥ አራማጆችን መቻልና ማድመጥ ተስኖት የራሱን ወገን ያውም (የእግዚአብሔር ሰው ነኝ የሚል) እንዲህ ሲሰለቅጥ በታሪካችን የመጀመሪያ ሳይሆን አይቀርም። ንጉሱ ደግሞ የለውጥ ሀይሉን ከበላ ብኋላ፣ ጭራሽ ከለውጥ ሀይሉ በተቃራኒ የሆነ ነገር በአዋጅ እንዲፀድቅ አደረገ! ) 

*****

በዚህ ባለንበት ዘመን ሳይንስና ምክንያታዊነት ጣራ በነካበት ዘመንና ተፅእኖዎቹ በተጨባጭ ጎልተው በሚታዩበት ዘመንም፣ እንቅፋትና ለውጥ አጨናጋፊ አድሀርያን በየቦታው አሉ። የአየር ለውጥ መዛባት ውሸት ነው የሚሉ፣ ግሎባል ዋርሚንግ ቢኖርም ሰው ሰራሽ አይደለም የሚሉ፣ የበርሃማነት መስፋፋት ተረት ነው የሚሉ (ከአንድ አስተማሪዬ ጋር የተጋጨሁበት ወቅት ነበር በዚህ ጉዳይ!) በዚህ በሰለጠነው የዓለማችን ክፍልም አሉ። ክትባት የሚፈሩ ብቻ ሳይሆን ህዝብን በተቃራኒ የሚቀሰቅሱ፣ የተዳቀሉ የሰብልና የእንስሳት ምርቶች ሰው እንዳይበላ የሚቀሰቅሱ፣ የተሳሳተ ትምህርት የሚያስተምሩ፣ ወዘተ በየቦታው አሉ። ከዚህ ዓይነት እንቅስቃሴ ጀርባ ያሉ ሰዎች ቢጠኑ መነሻ ምክንያታቸው ከሁለት ነገሮች አይዘሉም፥ አንድም በሳይንስ ምክንያት የሚጎድልባቸው ጥቅም ይኖራል አሊያም አለማወቃቸውን የማያውቁ አዋቂ ነን ባይ ግብዞች (በጨዋ ቋንቋ – ደንቆሮዎች!) ይሆናሉ። በተለያየ ዘርፍ የህዝብን ኑሮ በማሻሻል ረገድ፣ የሰው ልጅ በህይወት የሚኖርበት አማካኝ ዕድሜን ከፍ በማድረግ ረገድ፣ እወቀትና መረጃ ሁሉም ዘንድ የሚደርስበት መንገድ በመጥረግ ረገድ፣ . . . በአጭሩ ከመቶና ከሁለት መቶ ዓመት በፊት ከነበረው የሰው ልጅ ኑሮ በማንኛውም መመዘኛ በብዙ እጥፍ የተሻለ ህይወት እንድንኖር ያስቻለን (ለዘላለም ይንገስና!) ሳይንስ ነው።  ይህ ሲባል ግን ሳይንስ ህዝብ ላይ ያስከተለው ምንም ዓይነት ችግር የለም ማለት አይደለም። ሁሌም የሳይንስ ዓላማ በጎ ቢሆንም አልፎ አልፎ ይሳሳታል። የስህተቱ ገፈት ቀማሾች ይኖራሉ። ከዛ የከፋው ግን ሳይንስ ልክ እንደጠላቶቹ ሁሉ ለክፋት የሚጠቀሙበት “ወዳጆችም” አሉት።  

ለምሳሌ አንዳንድ ሳይንሳዊ ግኝቶች ለጦርነት ሲውሉ ይታያል። እንደዚህውም ዘረኛ ፖሊሲ ለሚያራምዱ ሳይኮፓዝ መሪዎች ጥሩ ዘረኝነትን የማስፋፊያ መሳሪያ ሆነው ያገለግላሉ። ዛሬ በአገራችን እየተከናወኑ ካሉ አስፀያፊ ምግባሮች መካከል ሌላ ምሳሌ እንመልከት ቢባል የዘመኑ አወናባጅ ነብያትና ደብተራዎችን ማየት ይቻላል። እነ ነብይ እስራኤል ዳንሳና መምህር ግርማ ሲታመሙ ሌላ ነብይ ወይም መምህር ዘንድ አይሄዱም። የሚሄዱት ውጭ ድረስ ዘመናዊ ህክምና ለመታከም ነው (መፅሀፍ ቅዱስ ጨብጦ ድራማ በመስራት እድናለሁ ብለው ሲሞክሩ አታዩም!) ። የሀብትና የዝና ምንጫቸው የሆነውን ድሃው በቀጥታ እነሱ ዘንድ እንዲሔድ የሚያጠምዱት የሳይንስ ውጤቶችን በመጠቀም ነው።  የውሸት ትርክታቸውን ለበርካታ የዋህ ምእመኖቻቸው የሚያደርስላቸው የዘመኑ ቴክኖሎጂ (ካሜራው፣ መብራቱ፣ ድምፅ መቅረጫው፣ ማህበራዊ ሚድያው ምኑ) የሳይንስ ውጤት ነው። ዝናና ገቢያቸው እንደዚህውም ተፅእኗቸው እየገነነ የሚሔደውም በነዚህ የሳይንስ ውጤቶች አማካኝነት ነው። ሁሉንም ለመጥቀም የተፈጠረው ቴክኖሎጂ ለአጭበርባሪዎች ሲሳይ ለሌሎች የባርነትና የብዝበዛ ቁስ ሲሆን እንደማየት የሚያም ነገር ፈፅሞ የለም።

ቢሆንም ጥቅምና ጉዳቱ ለንጽጽር የሚቀርብ አይደለምና፣ ከጠላቶቹ ይልቅ ወዳጆቹ እንደ አሸን የፈሉ ናቸውና ሳይንስን እናፈቅረዋለን። እንገለገልበታለን። ቀርበን እናጠናዋለን። እንከታተለዋለን።

***

1 reply

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Recent
Comments