የአገሪቱ አጠቃላይ የውስጥና የውጭ ዕዳ 2.01 ትሪሊየን ብር መድረሱን መንግሥት ይፋ አደረገ
ምንጭ | ሪፖርተር | ዮሐንስ አንበርብር
የዕዳ መጠኑ ከአገሪቱ አጠቃላይ ምርት (ጂዲፒ) 50.8 በመቶ እንደሆነ ተመላክቷል
የኢትዮጵያ አጠቃላይ የአገር ውስጥና የውጭ ብድሮች ዕዳ 2.01 ትሪሊየን ብር መድረሱን፣ ሰሞኑን የወጣው የመንግሥት የዕዳ መጠን መግለጫ ይፋ አደረገ።
የገንዘብ ሚኒስቴር ሰሞኑን ይፋ ያደረገው አጠቃላይ የዕዳ መጠን መግለጫ ሰነድ፣ እ.ኤ.አ. እስከ ሴፕቴምበር 2020 ድረስ ኢትዮጵያ ያለባትን አጠቃላይ የአገር ውስጥና የውጭ ብድሮች ዕዳ የሚገልጽ ነው።
በዚህም መሠረት ማዕከላዊ መንግሥት በቀጥታና መንግሥት በሰጠው የብድር ዋስትና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከአገር ውስጥና ከውጭ ምንጮች ተበድረው ያልከፈሉት አጠቃላይ ዕዳ 54.7 ቢሊዮን ዶላር እንደ ደረሰ ሰነዱ ያሳያል።
ከአጠቃላይ 54.7 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ 28.99 ቢሊዮን ዶላር የሚሆነው ከውጭ የብደር ምንጮች የተገኘ ሲሆን፣ ይህም ሰነዱ በተዘጋጀበት ወቅት በነበረ የብር የውጭ ምንዛሪ ተመን ተሰልቶ 1.06 ትሪሊየን ብር እንደሆነ ሰነዱ ያመለክታል።
ከተጠቀሰው 54.7 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ፣ ከውጭ አበዳሪዎች የተገኘው ተቀንሶ የሚቀረው 25.7 ቢሊዮን ዶላር ደግሞ ለአገር ውስጥ የብድር ምንጮች የሚከፈል የአገር ውስጥ ዕዳ እንደሆነ ሰነዱ ያስረዳል። ለአገር ውስጥ የብድር ምንጮች መከፈል፣ ያለበት ዕዳ ይህ የዕዳ መጠን ሰነዱ በተዘጋጀበት ወቅት በነበረ የብር የውጭ ምንዛሪ ተመን ተሠልቶ የቀረበ ሲሆን፣ በዚህ ሥሌት መሠረት የአገር ውስጥ የመንግሥት ዕዳ 945 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ተጠቅሷል።
አጠቃላይ ከሆነው 54.7 ቢሊዮን ዶላር የአገር ውስጥና የውጭ የዕዳ መጠን ውስጥ 30.6 ቢሊዮን ዶላር የሚሆነውን በቀጥታ ማዕከላዊ መንግሥትን የሚመለከት ሲሆን፣ ይህም የአጠቃላይ ዕዳው 56 በመቶ ነው።
ከአጠቃላይ የዕዳ መጠን ውስጥ ማዕከላዊ መንግሥትን የሚመለከተው ከተቀነሰ በኋላ የሚቀረው 24.1 ቢሊዮን ዶላር፣ ወይም የአጠቃላይ ዕዳው 44 በመቶ የሚሆነው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ዕዳ ነው።
ከአጠቃላይ የዕዳ መጠን ውስጥ 25.7 ቢሊዮን ዶላር ወይም 945 ቢሊዮን ብር የሚሆነው ከአገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት የተወሰደ ሲሆን፣ በአመዛኙም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተወሰደ መሆኑን ሰነዱ ያመለክታል።
ከተጠቀሰው የአገር ውስጥ ዕዳ 525 ቢሊዮን ብር የሚሆነውን ያበደረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደሆነ ማስረጃው መረዳት ተችሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከጥቂት ወራት በፊት ይህንኑ ሁኔታ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማስረዳታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በወቅቱ ባደረጉት ንግግርም መንግሥታቸው ተግባራዊ ማድረግ የጀመረው የኢኮኖሚና የፋይናንስ ዘርፍ ሪፎርም ፈጥኖ ባይደርስ ኖሮ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመውደቅ አደጋ ተጋርጦበት ነበር ማለታቸው አይዘነጋም።
መንግሥት እያደረጋቸው ከሚገኙ ሪፎርሞች መካከል የመንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተበድረው ያልከፈሉትን ዕዳ ቀስ በቀስ ወደ መንግሥት ማዘዋወር አንዱ ተግባራዊ መደረግ የጀመረ የመፍትሔ አማራጭ መሆኑን ሪፖርተር ያገኛቸው ሌሎች መረጃዎች ያመለክታሉ።
ከአጠቃላይ የአገሪቱ ዕዳ ውስጥ ለውጭ አበዳሪዎች የሚከፈለው 28.99 ቢሊዮን ዶላር ወይም 1.06 ትሪሊዮን ብር ግን አለመክፈል የሚቻልበት ሁኔታ ዝግ በመሆኑ፣ የኢትየጵያ ደግሞ በማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ውስጥ በመውደቁ፣ ለመንግሥት ከፍተኛ የራስ ምታት ሆኗል፡፡ መንግሥትም ይኼንኑ ሕመሙን ሳይሸሽግ በተደጋጋሚ ጊዜ ሲገልጸው መቆየቱ ይታወሳል።
ይኼንን የውጭ ዕዳ የመክፈያ ጊዜ እንዲራዘም ከመደራደር ውጪ የመክፈሉ ግዴታ የማይለወጥ እንደሆነ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ይህንን የውጭ ዕዳ ኢትዮጵያ መክፈል እንደማትችል ከተረጋገጠ ደግሞ አገሪቱን ጥቁር መዝገብ ውስጥ እንድትሰፍርና በቀጣይ የውጭ ብድር ፍላጎቷ በር የሚዘጋ ሁኔታን ሊፈጥር እንደሚችል ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
የውጭ ዕዳን ሙሉ በሙሉ ማሰረዝ አስቸጋሪ መሆኑን የሚገልጹት ባለሙያዎቹ፣ የቀደሙ የኢትዮጵያ መንግሥታት በአሁኑ ወቅት ከፈረሰችው ሶቪዬት ኅብረት ተበድረው ያልመለሱት ዕዳ፣ አሁንም ድረስ በዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) የኢትዮጵያ የውጭ ዕዳ ተብሎ እስካሁን ተመዝግቦ እንደሚገኝ ይገልጻሉ።
አገሪቱ ካለባት የውጭ ዕዳ ውስጥ ብቻ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ድርሻ 36 በመቶ መሆኑን ሰነዱ የሚያመለክት ሲሆን፣ 54.7 ቢሊዮን ዶላር ከሆነው አጠቃላይ የአገሪቱ የአገር ውስጥና የውጭ ዕዳ ውስጥ 44 በመቶው ወይም 24.1 ቢሊዮን ዶላር የሚሆነው የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ዕዳ እንደሆነ ይጠቁማል።
አጠቃላይ የመንግሥት ዕዳ የኢኮኖሚ ዕድገት መለኪያ ከሆነው አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) 50.8 በመቶ እንደሚሆን መረጃው ያመለክታል። ከዚህ ውስጥ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች የአገር ውስጥ ዕዳ ለብቻው ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት አንፃር 12.5 በመቶ ድርሻ ይዟል።
የአገሪቱ የውጭ ዕዳ አማካይ የመክፈያ ጊዜ 15 ዓመት መሆኑንም መረጃው ያመለክታል።
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!