ወልቃይት፡ የማንነት ጥያቄና የመፍትሔ አቅጣጫ
*****

ወልቃይትኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም ቦታ ከክልል እስከ ክፍለሀገር እስከ ዞን እስከ አውራጃ እስከ ወረዳ እስከ ቀጠና እስከ ቀበሌና ጎጥ ድረሳ ከዛም በታች ካለ፥ የኢትዮጵያ ሉአላዊ ግዛት፥ ንብረትነቱም የኢትዮጵያ ህዝብ ነው። ንብረትነቱ የአንድ ክልል ወይም የአንድ ብሄር የሆነ መሬት በህግ የለም። ያንን ህግ ወደፊት ማውጣት ከተቻለ እሰየው፥ የሚቻል ግን አይደለም። ህዝብን ያፋጃል።

ከማንነት ጥያቄ ጋር ተያያዞ የሚቀርብ የባለንብረትነት ጥያቄ በየትም ቦታ ቢሆን ህጋዊ መሰረት የለውም። የማንነት ጥያቄ ሌላ፥ የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ ሌላ።

በወልቃይት የማንነት ጥያቄ አለ። ከማንነታችን ጋር የሚስማማ አስተዳደር ይኑረን ነው መሰረታዊ ጥያቄው። ወልቃይት የአማራ ነው፥ የትግሬ ነው የሚል ጥያቄ የህዝብ ጥያቄ አይደለም፥ ተገንጣይ አጀንዳ ያላቸው የብሔር ፖለቲከኞች መሰረተ ቢስ ጥያቄ ነው። እስከዛሬ ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረ ህግ አንዲት ስንዝር መሬት የክልል ወይም የብሔር ንብረት መሆኑን አያረጋግጥልንምና የአማራ ነው የትግሬ ነው የሚለው ክርክር መሰረት የሌለው፥ ህገመንግስታዊ ሊሆን የማይችል ጥያቄ ነው።

ወልቃይት ለሚኖረው ቀርቶ ከየትም ቢሆን መጥቶ ጎጆ ቀልሶ መኖር ለሚፈልግ ዜጋ በማንኛውም የአገሪቱ ክፍል መሆን አንዳለበት ህገመንግስታዊ መብቱ ነው። ምክንያቱም መሬቱ የኢትዮጵያ ህዝብ መሬት ነውና።

  • “The right to ownership of rural and urban land, as well as of all natural resources, is exclusively vested in the State and in the peoples of Ethiopia.” Article 40.3

ዋናው ጉዳይ የማንነትና የአስተዳደር ጥያቄውን እንዴት እንፍታው ነው። ይህ ጥያቄ ደግሞ በሁለቱም በኩል ያሉ የብሔር ፖለቲከኞች ለግል የፖለቲካ ፍጆታቸው ቢያራግቡትም፥ ያን ያክል ከባድ ጥያቄ አይደለም። መፍትሔው ያለው በኗሪው ህዝብ ድምፅ ነው። ህዝቡ ከአማራ ክልል ስር መተዳደርን ከመረጠ ውሳኔው ይከበርለታል። በትግራይ ክልል ስር መተዳደርን ከመረጠ ውሳኔው ይከበርለታል። ህዝቡ የሚሰጠው ድምፅ በጣም አሻሚ ከሆነ ልዩ ዞን ሆኖ ኗሪው ራሱን በሁለት ቋንቋ እንዲያስተዳድር ማድረግ ይቻላል። በጣም ቀላልና ህገመንግስትን መሰረት ያደረገ ፍትሓዊ ምላሽ ይኸው ነው።

ዞሮ ዞሮ ኢትዮጵያውያን በተለይ የአንድነት አራማጆች ማስመር ያለብን ዋናው ጉዳይ የትም ያለ መሬት የኢትዮጵያ ህዝብ መሬት መሆኑን ነው! ለክልል ወይም ለብሔር ለመስጠት የሚከጅሉት ተገንጣይ አጀንዳ ያላቸው ሰዎች ናቸው። ወልቃይትን ደግሞ በተለየ የሚጠቀሙባትና እንደተቆርቋሪ የሚያራግቧት፥ የመሬት ባለቤትነትን ከኢትዮጵያ ህዝብና አገረ መንግስት ወደ ክልልና ብሔር implicitly ለማስተላለፍ አመቺ ክፍተትን እየፈጠረች ስላለች ነው። ይህንን በደንብ ልናጤነው ይገባል!!

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *