ከወለድ ነጻ የሆነ የባንክ አሰራር አለ?(ክፍል 1)

ሰለሞን ነጋሽ

ባንክከወለድ ነጻ የሆነ ኢስላሚክ ባንክ እንዲቋቋም መንግስት ድጋፉን ይሰጣል የሚል ዜና በሰማሁ ማግስት የተቀናጀ የዘረፋ ቢዝነስ ነው ተጠንቀቁ ብዬ በፌስቡክ ገጼ ላይ የጻፍኩት አስተያየት መስመሩን ስቶ ብዙ አላስፈላጊ ክርክር እያስነሳ ነው። ሃይማኖታዊ ይዘት ለመስጠትም ሞክረዋል። አጭበርባሪዎች ላይ ጣትህን ስትቀስር ሮጠው በብሔራቸው ወይም በሃይማኖታቸው ስም መሸሸግ የተለመደ ዘዴ አድርገውታል። የኢንተግሪቲ ሰው ስትሆን የዚህ አይነት ማጭበርበር እንዳላየ ማለፍ አይቻልህም። አጭበርባሪ ብሔርና ሃይማኖት የለውም። የቤተ ክርስትያን መሪዎች ሆነ የመጅሊስ መሪዎች ከአንድም ሁለት ሶስት ጊዜ የተከታዮቻቸውን ሀብት አባክነዋል። ወይም በብሔር ፖለቲከኞች ቋንቋ መጠኑ ያልታወቀ የምእመናቱ ገንዘብ ላይ ጉዳት ሲያደርሱ ኖረዋል። ማለትም ብጹአን አይደሉም። በሀይማኖት ሽፋን የሚመጡ ሌቦች እንዳሉ ይህ ህያው ማስረጃ ነው።

ነጥቤ ዘራፊዎች ዛሬም በመካከላችሁ አሉ፣ እናንተም ይህን ታውቃላችሁ ነው። መልክና ስማቸውን ቀይረው የሚመጡ፣ የባንክ ስም ተላብሰው የሚመጡም አሉ። እኔ ባልፋቸው እንኳን በዘርፉ የተሰማሩ የባንክ ባለሀብቶችና ባለድርሻ አካላት አያልፏቸውም። ያጋልጣሉ። የተጭብረበረ አስራራቸውን ለአደባባይ ያበቃሉ። ከወዲሁ ማጋለጥ የጀመሩም አሉ።

ወደ ወለዱ ክርክሩ ልመለስ።

ክርስትናና እስልምና ከነመፈጠራቸው ሳይታወቅ በፊት፣ አራጣ ጽያፍ ነበር። የግሪክ ፈላስፋዎች እነ ፕላቶና አሪስቶትል ጽፈውበታል። አራጣ ሞራሊ ትክክል አይደለም የሚል ውግዘት ከዛን ግዜ ጀምሮ ነበር።

ኢንግሊዛዊው ፈላስፋ በርትራንድ ራስል፣ History of Western Philosophy በሚለው ገናና ስራው እነዚህን ፈላስፋዎች በጥልቀት ይተቻል። ሎጂካል አይደለም ይላል። ኢንተግሪቲያቸውንም ጥያቄ ውስጥ ይከታል። እንደ ራስል አገላለጽ አበዳሪና ተበዳሪ ከጥንት ጀምሮ ነበሩ። አበዳሪዎች አራጣ ይፈልጋሉ፣ ተበዳሪዎች አራጣ አይፈልጉም። በዛን ዘመን ተበደሪ የመሬት ከበርቴው ሲሆን አበዳሪው ነጋዴ ነበር። የፖለቲካ ስልጣን የነበራቸው ደግሞ የመሬት ከበርቴዎቹ ነበሩ። የያኔ ፈላስፋዎች አንዳንዶቹ መደባቸው/ክላሳቸው ከከበርቴዎቹ ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ የከበርቴዎቹ ቅጥረኞች ነበሩ። እናም አራጣን ሲኮንኑ ለተበዳሪ ከበርቴ የሚያደላ ህግ ማስቀመጣቸው ነበር።

ከግሪክ ፈላስፋዎች ብኋላ የመጡት የቤተክርስትያን ፈላስፋዎች (እነ St. Augustine እና St. Thomas Aquinas) ነበሩ። ያኔም ቤተክርስትያን የመሬት ከበርቴ ነበረች። እናም ቄሶቹ ፈላስፋዎች አራጣ ውጉዝ ነው የሚለውን የቆየ የግሪክ ፍልስፍና መቀየር አላስፈለጋቸውም። ተቀብለው ቀጠሉበት። በተለይ ደግሞ ያኔ አበዳሪዎች የነበሩት ጅዊሽ ነጋዴዎች ስልሆኑ፣የአራጣን ውጉዝነቱን በደንብ አጸኑት። … ይላል ፈላስፋው ራስል።

ከክርስትና ብኋላ እስልምና ተከለተለ። መቼስ መጽሀፍቱ ብዙም ልዩነት የላቸውም። እስልምናም ላይ አራጣ ሃራም ሆኖ ቀጠለ። አስር እጥፍም ቢሆን ነግዶ ማትረፍን ይፈቅዳል፣ ሰባራ ሳንቲም በአራጣ መክፈል ወይም መቀበል ይኮንናል። ብኋላ በዝርዝር እንደምናየው በዘመናዊ የኢኮኖሚ ስርዓት፣ ትርፍም ሆነ ወለድ ለከት አለው። አንድም በገበያው አሊያም በህግ የተገደበ ተመጣጣኝ ትርፍና ወለድ ብቻ ነው የሚፈቀደው።

አንድ ምሳሌ እንመልከት። ዛሬ በአንድ ብር ዳቦ ገዝተህ ነገ በ5 ብር መሸጥ ትችላለህ፣ እስልምናም ክርስትናም እዚህ ላይ ችግር የለባቸውም። ነገር ግን ዛሬ ለአንድ የተቸገር 1 ብር አበድረህ ነገ 5 ብር መቀበል ውጉዝ ነው። ምናልባት ለልጁ የሚላስ የሚቀመስ ስለሌለውና ልጁን በህይወት ለማቆየት ፈልጎ ሊሆን ይችላል ዛሬ 1 ብር ካንተ ተበድሮ ዳቦ በመግዛት ነገ ደሞዙን ሲቀበል 5 ብር ለመክፈል ፈቃደኛ የሆነው። በሌላ በኩል ደግሞ ምናልባት የዳቦ እጥረት ስላለና ልጁን በህይወት ለማቆየት ፈልጎ ሊሆን ይችላል ትላንት በብር የገዛኸውን ዳቦ ዛሬ በ5 ብር እንድትሸጥለት የሚጠይቅህ። ግድየለም ትላንት 1 ብር ነው የገዛሁት፣ በብር ከአምሳ ውሰደው፣ ተገቢ ያልሆነ ትርፍ መሰብሰብ የለብኝም ሀራም ነው ወይም ሀጥያት ነው የሚል አማኝ በባትሪ ፈልጋችሁም ላታገኙ ትችላላችሁ። ነገር ግን ሁለቱ ሴናሪዮዎች ፋንዳሜንታሊ ተመሳሳይ ናቸው፣ ልዩነታቸው ቴክኒካል ነው።

በኢኮኖሚክስ ገንዘቡን ራሱ እንደ አንድ ኮሞዲቲ (ልክ እንደ ዳቦው) እናየዋለን። ዛሬ አንድ ብር ዋጋው አንድ ብር ነው። ከአመት ብኋላ ዋጋው ብር ከስሙኒ ሊሆን ይችላል። የምትገዛው ወረቀቱን ሳይሆን የገንዘቡን ቫልዩ ነው። ዳቦው ዛሬ አንድ ብር የነበረው ነገ 5 ብር የሚሆነው ቫልዩው ነው። እንጂ ዳቦነቱ አልተቀየረም። ያውም ሲቆይ ይሻግታል ወይም ኳሊቲው ይቀንሳል። ነገር ግን በምንገዛበት ሰዓት በጣም ስለፈለግነው የሆነ ቫልዩ ዳቦው ላይ አታች አድርገናል፣ ለዛ ቫልዩ ነው ተጨማሪ ዋጋ ለመክፈል ፈቃደኛ የምንሆነው። ሰውዬው ልጁን ካላበላ የከፋ ኪሳራ ሊገጥመው ስለሚችል 5 እጥፍ ከፍሎ መግዛት የተሻለ አማራጭ ሆኖ ታይቶቷል። አንተም የ4 ብር ትርፍ ካገኘህ፣ ቀን እንደወጣልህ ቆጥረክሀው እየቦረቅክ ወደ ቤትህ ትሔዳለህ። ያ ሰው በ5 ብር የገዛህ ተቸግሮም ቢሆን ስለሚችልና የባሰ ኪሳራን ማስቀረት ስለሚፈልግ ነው። 1ን ብር በ5 ብር ነገ ለመቀየር የሚስማማህም ስለሚችልና ስለነገ የተሻለ ኤክስፔክቴሽን ሳለለው  ነው። ካልቻለና ተስፋው ከተሟጠጠ ግን ስርቆትና ዘረፋ ውስጥ ነው የሚገባው። (እንኳን ወለድ ሌብነትም ጀስቲፋያብል የሚሆንበት ግዜና ሁኔታ አለ!)

ወደ ታሪኩ እንመለስ። ከእስልምና ብኋላ የፕሮቴስታንት ሪፎርሜሽን መጣ። አብዛኛዎቹ ፕሮቴስንታንቶች ነጋዴዎችና የተማሩ ደሞዝተኞች ነበሩ። ነጋዴ ወለድ ይፈልጋል። ደሞዝተኛም ወለድ ይፈልጋል። ወለድ መሰብሰብና መክፈል ምንም ክፋት አላዩበትም። የነዚህ መደብ የተሻለ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስታተስ ላይ ነበር። ህጉ እንዲቀየር ጫና ፈጠሩ፣ ሪፎርም ተደረገ። ሪዝናብል የሆነ መጠን እስከሆነ ድረስ interesse (or late payment) መክፈል ችግር የለበትም ተባለ። የካቶሊክ ቤተክርስትያን ለውጡን ተቀብላ ተራመደች። የተጋነነ ወለድ እንዳይጠየቅ ወዘተ ማሻሻያ ህጎች እየወጡ ዛሬ የደረስንበት ደረጃ ላይ ደረሰ። ቃሉም interest ወደሚለው ቃል ኢቮልቭ አደረገ። ክርስትያኖች ዛሬ የባንክ ወለድ ሲባል ምንም የማይመስላቸው አንድም ምክንያቱ ይኸው ነው። በአራጣና በወለድ መካከል ያለውን ልዩነት ይገነዘባሉ።

ዘመናዊ ባንክ እውን ከሆነበት ዘመን አንስቶ ያለወለድ የሚሰራ ባንክ የለም! ልዩነቱ አንዳንዶች በግልጽ የሚቀበሉትና የሚከፍሉት የወለድ መጠን ሲያሳውቁ፣ ሌሎች እንኳን ሊያሳውቁ ወለድ የሚለውን ቃል ከነአካቴው አይጠቅሱም። አሜሪካ ውስጥ ሞርጌጅ የሚያበድሩ አንዳንድ ባንኮ interest free እና with interest rate የሚሉ ቅጾች አሏቸው። የቤቱ ዋጋና ወርሃዊ ክፍያው ሁለቱም ላይ እኩል ነው። አንደኛው ለሙስሊሞች ሌላኛው ደግሞ ለሌሎች የተዘጋጀ ቅጽ ነው። ሌሎች ባንኮች ደግሞ አሉ ጭራሽ ከወለድ ነጻ ነን የሚል ነጭ ውሸት ይጨምሩበታል። እርግጥ ነው የቁጠባ ገንዘብ ሲቀበሉ ከወለድ ነጻ ነው፣ የሚከፍሉት ነገር የለም። ሲያበደሩ ግን ወለድን ታሳቢ አድርገው ነው ወርሓዊም ይሁን አመታዊ ክፍያ የሚሰበስቡት።

አራጣ (usury) እኛም አገር እስከ ቅርብ ግዜ ነበረ። ምናልባት አሁንም ድረስ ገጠር አካባቢ ሊኖር ይችላል። ነገር ግን ህገወጥ ነው። በእምነት ተቋማት ብቻ ሳይሆን በመንግስት ህግም የተወገዘ ነው። መንግስት አራጣ አበዳሪን እያሳደደ ያስራል፣ ሀብቱን ወደ መንግስት ካዝና ገቢ ያደርጋል። ልክ እንደ አራጣው ሁሉ፣ በህግ የተደነገጉ ተገቢ ያልሆኑ የንግድ ዘርፎችና እንቅስቃሴዎች አሉ። ለምሳሌ ትርፍን ለማጋበስ በመሻት አርቴፊሻል እጥረት ፈጥረው (ሆርዲንግ ይባላል) ዋጋ እንዲወደድ የሚያሴሩ ነጋዴዎች የትም አገር በህግ ይጠየቃሉ። በሞኖፖል የሚያመርቱት ምርት ወይም የሚሰጡት አገልግሎት ላይ የፈለጉትን ዋጋ መተመንና ትርፍ ማጋበስ አይችሉም። አንቲ ትረስት የሚባል ህግና ተቋማዊ አሰራር አለ። እኛም ጋ አንድ ሰሞን ሲያስመርሩት መለስ ዜናዊ ነጋዴዎችን ማሳደድ ጀምሮ ነበር። የዋጋ ተመን ሁሉ ማስቀመጥ ጀምሮ ነበር። እዛ ንግድ ውስጥ ሙስሊሞች ነበሩ፣ ወለድ ሓራም ነው የሚሉ። ነገር ግን ወለድ ከሚጠይቀው በላይ ድሆችን ተገቢ ያልሆነ ዋጋ በመጨመር ሲበዘብዙ የነበሩ ሱቃቸው የተዘጋባቸው ሙስሊም ነጋዴዎች ነበሩ። ክርስቲያኖችም ነበሩ ፎር ዛት ማተር። መልካቸውን ቀይረው በባንክ ድሪቶ ተጀቡነው መምጣታቸውን እረዳለሁ አሁን።

ይህን ሁሉ የማወራው፣ ከመነሻው፣ ከታሪካዊ አመጣጡ ጀምራችሁ ሁኔታውን በደንብ እንድትረዱና እንድትጠይቁ ነው። ወለድ በግልጽ መሰብሰብ ችግር የለበትም። የግድም ነው። ከሌላ የቁስ ዋጋ ጋር ለማመጣጠንና የመግዛት አቅሙን ለማካካስ የግድ ወለድ መኖር አለበት። ሰዉ ያለው አማራጭ መረጃውን አገናዝቦ የሚያዋጣውን መወሰን ነው። አበዳሪ (ሴቭ አድራጊ) ከሆነ ከፍተኛ ወለድ የሚሰጡትን፣ ተበዳሪ ከሆነ ደግሞ ዝቅተኛ ወለድ የሚጠይቁትን መርጦ ቢዝነሱን ማፋጠን። ወለድ ከመክፈልና ከመሰብሰብ የከፋ ብዙ ቆሻሻ ስራዎች ይሰራሉ። ከነዚህ መካከል ይህ ከወለድ ነጻ ነኝ የሚል የቀፍለህ ብላ ቢዝነስ ይገኝበታል። እርግጥ ነው በየቀኑ ባንክ የሚዘረፍበት አገር ውስጥ ነው ያለነው። ቢያንስ ግን እነዚህ ዘራፊዎች ወንጀለኞች መሆናቸውን የሚጠራጠር የለም። መረጃን በመደብቅና የሚያወሩትና የሚሰሩት በማወናበድ፣ የሰው ሀብት የሚዘርፉ፣ ሰው የሚገባውን እንዳያገኝ የሚያሴሩ ከባንክ ሰባሪዎቹ የከፉ ወንጀለኞች መሆናቸው ሊሰመርበት።

በሚቀጥለው ውስብስብ የሚያስመስል አሰራር የዘረጉበትን ሁኔታ በዝርዝር አስነብባችኋለሁ። እንደ አንድ ተራ የንግድ ባንክ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ኢንሹራንስ ኩባንያም፣ እንደ ኢንቨስትመንት ባንክም፣ እንደሌላም የሚያደርጋቸው ምክንያት ለምን እንደሆነ አስረዳለሁ። እስከዛው አንዳንድ ጥያቄ እንድትጠይቁና እንድታሰላስሉ ልጋብዛችኋለሁ።

1. ጥሬ ገንዘብ ተቀብለው ያለ ወለድ እንደሚያስቀምጡ ይታወቃል። በጥሬ ገንዘብ አበድረው ከአመታት ብኋላ በጥሬ ገንዘብ ያለወለድ የሚቀበል አሰራርስ አላቸው ወይ? ለምን?

2. የሚሰጡት ብድር ለምንድን ነው በአይነት ብቻ የሆነው?

3. ትርፍ መጋራት አራጣ ከመብላት በምን ይለያል? በመሰረቱ ይህ የኢንሹራንስ ኩባንያ አሰራር ነው። ኪሳራ ስለሚጋሩ ሪስክ አለው። ይህን ሪስክ ለመቀነስ ትርፍ ይጋራሉ። ነገር ግን ከትርፉ እንዲጋሩ የሚጠይቁት መጠን መደበኛ ባንኮች ከሚጠይቁት ወለድ ይበልጣል ወይስ ያንሳል?የሚበልጥ ከሆነ ከአራጣ የማይተናነስ ገንዘብ እየሰበሰቡ ነው ማለት አይቻልም?

4. ከወለድ ነጻ ነኝ የሚለው ባንክ የዚህ አይነት ዘዴ የሚጠቀመው ለምንድን ነው? ኢንሹራንስ ኩባንያ ፕሪሚዬም ሲያስቀምጥ ወለድ ታሳቢ አድርጎ አይደለም ወይ? ከዚህ የተለየ አሰራር እነዚህ አጭቤ ባንኮች አላቸው ወይ? ወዘተ

ይቀጥላል!

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *