ከእርስ በእርስ ጦርነትና የዕልቂት አዙሪት ለመውጣት
Read the English version here. በኢንግሊዝኛ ለማንበብ ይህን ማስፈንጠሪያ ይጫኑ።
1. አልፋና ኦሜጋ የሆነውን በአገር ሉኣላዊነት ብጽኑ የማመን መርህ ይኑረን። የሁሉም መነሻ የአገርንና የህዝብን ሉኣላዊነትን ማክበርና መጠበቅ ነው። በውጭ ሃይል እየተጠመዘዝክና እየታገዝክ፣ የአገርህን ሉኣላዊነት ሸጠህ፣ ከማንም ከምንም በምንም ነጻ ልትወጣ አይቻልህም። በተለይ ደግሞ ለሶስት አስርት አመታት አገሪቱን ለማፈራረስ በግልጽ ተግቶ ሲሰራ ከኖረው ሻዕቢያ ጋር መሞዳሞድ፣ ውሎ አድሮ የሚቋጨው በሌላ ግጭት መሆኑን ከትላንትም ከዛሬም ታሪክ መማር ያስፈልጋል።
2. ሉኣላዊነት የማክበርና የመጠበቅ መገለጫው፣ በስራ ላይ ያለውን ህገመንግስት ማክበርና ማስከበር ነው። ህገመንግስቱ መቀየር ወይም መሻሻል ካለበትም፣ ህጋዊ አሰራሩን ተከትሎ እስኪሻሻል ወይም እስኪቀየር ድረስ፣ በዛ ህግ መገዛትና ለዛ ህግ መቆም ግድ ይላል። የአንድ አገርና የፖለቲካል ማህበረሰብ ምሰሶ ህገመንግስቱ ነውና።
3. ይኽም ማለት ህገመንግስታዊ ጥያቄዎች ሁሉ፣ ህገመንግስታዊ ምላሽ እስኪያገኙ ድረስ፣ እያንዳንዱ ግለሰብና ቡድን ኢህገመንግስታዊ የሆኑ የአጭር ግዜ የመፍትሔ እርምጃዎችን ከመውሰድ ሊቆጠብ ይገባል ማለትነው ። ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት ከቀያቸው መፈናቀል መቆም አለበት። በጉልበት የተያዙ ቦታዎች ወደ ህገመንግስታዊ ስፍራቸው መመለስ አለባቸው። ወዘተ።
4. ሁሉም በየፊናው አሁን እየሔደበት ያለው መንገድ፣ ከመተላለቅና በመተላለቅ አዙሪት ከመጠመድ ውጪ የትም እንደማያደርሰው መገንዘብ አለበት። ይህን ለመገንዘብ ደግሞ ከባድ አይደለም። መፍትሔውም ሁሉም ኢጎዉን፣ ግብዝነቱን፣ ጥራዝነጠቅነቱን፣ ምናምኑን ትቶ፤ ትላንት አሻፈረኝ ወዳለውና ወዳጣጣለው ሁሉን አቀፍ አገራዊ የውይይትና የድርድር መድረክ መመለስ ነው። አገሪቱ እንደአገር ቀጠለችም አልቀጠለች፣ ነገ በሰላም ለመኖር፣ ከውይይትና መነጋገር ውጪ ሌላ ምንም (ይደገም፣ ሌላ ምንም) አማራጭ የለም። ደም ተፋስሰህ፣ ንጹሃንን አስጨርሰህ፣ ጉልበትህ ከዛለ ብኋላ በጉልቤዎች እየተጠመዘዝክ ለድርድር መቀመጥህ ላይቀር፤ ዛሬ ሰልጠን ቆፍጠን በልና በራስህ ተነሳሽነት ሞክረው። ታተርፍበታለህ። በታሪክ ስህተት ያልሰራ መንግስት፣ ህዝብን ያላፋጀ ቡድን፣ ያልተጋጨ ህዝብ የለም። ነገር ግን ብዙዎች በመነጋገር ብቻ የትላንት ጠባሳቸውን ሽረው፣ በጋራ ወደፊት መራመድ ችለዋል።
5. እርግጥ ነው፣ አብይ አሕመድ ዛሬም ለድርድር፣ ወይይትና መነጋገር አለርጂክ ነው። ተገዶ በጆሮው እየተጎተተ ካልሆነ በስተቀር፣ ውይይትን እንደተሻለ አማራጭ የሚያስበው ነገር አይሆንም። እንዲህ ያለውን ሃሳብ ቢፈልገው ኖሮ፣ ያኔ ያላንዳች ስራ በዜጎች ልብ በነገሰበት በዛ የስካር ዘመን፣ ይህን ማድረግ ይችል ነበር። የተጣሉትን አስታርቆ፣ የማይነጋገሩትን አነጋግሮ፣ ሁሉንም አደራድሮ፣ የጋራ መፍትሔ በጋራ አፍልቀው፣ አገሪቱ ወደኋላ የምትሸመጥጥበትን ሳይሆን ወደፊት የምትድህበትን መንገድ መፍጠር ይቻል ነበር። ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ጠንካራ ሌጋሲ ትቶ የማለፍ እድሉ ያኔ አመለጠ። ፍላጎቱ ንጉስ መሆን ነበርና የሆነው ሁሉ በተቃራኒ ነበር። ዛሬም ከዚህ የተለየ ያደርጋል ተብሎ አይጠበቅም። ስሌቱ ሁሌም ዙፋኑ ናት። ዛሬ ሰውዬው ስራው ሁሉ ባልበላው ልበትነው እንደሆነ የሚመስክሩት፣ የራሱ ግልገሎች ጭምር ሆነዋል። እርሱ እስካለ ድረስ ደግሞ ሰላም አይኖርምና (ስልጣን ላይ የማቆያ ቀዳሚ ስትራቴጂው ጦርነትና ስርዓት አልበኝነትን ማንገስ ሆኗልና) ቀዳሚው ትኩረት፣ እርሱን በግዜያዊ የባላደራ ወይም የሽግግር መንግስት መተካት ነው መሆን ያለበት። ይህን ለማድረግ ደግሞ ደም በተቃቡት፣ በማይግባቡት፣ በሚናቆሩት፣ እና እርስ በእርስ በጎሪጥ በሚተያዩት መካከል መነጋገርና መወያየት መጀመር ያስፈልጋል።
6. ወደ ሽግግሩ ለማቅናትም ሆነ ከሽግግሩ ብኋላ መደበኛ መንግስት ለማቋቋም፣ ሁሉም በህገ-ልቦና መገዛት ይኖርብታል። ብልጣብልጥነት አራዳነት ለሚመስለው ማህበረሰ ይህ ከባድ ቢመስልም፤ ሰላም ከተፈለገ ታዳጊ ህጻናት ሳይቀሩ የሚያውቁትን ይህን መሰረታዊ መርህ ለመተግበር ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው፥ “በራስ ላይ እንዲደርስ እማትሻውን ነገር በሌሎች ላይ ከማድረግ ከተቆጠብክ” በሰላም የማትኖርበት ምንም ምክንያት አይኖርም። የኮንሰንሰስ ቤዝድ ዴሞክራሲ መሰረቱም ይኸው ነው። የብልጣብልጥ መንገድ መጨረሻው ምን እንደሆነ ባለፉት አምስት አመታት ሁሉም አይቶታል። ማንም አልተጠቀመም። ተያይዞ እንጦሮጦስ ወረደ እንጂ። ከቅርብ ታሪካችን መማር ከቻለ የመትረፍ ተስፋ ይኖራል።
7. አልወያየም፣ አልነጋገርም፣ አልደራደርም፤ ፍላጎቴን በጉልበትና በዘዴ አሳካለሁ፣ ወዘተ… ብትል ያው ተሽመድምደህ ትቀራለህ። ሰውዬውና ዙፋኑ እንደሙጫ ተጣብቅውልህ ይቆያሉ።
አመቱ ከመገባደዱ በፊት፣ ልተንፍሳትና እናስብበት ብዬ ነው።
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!