ከምጽዓተ ኢትዮጵያ እንተርፍ ይሆን? አያዎ

ከምጽዓተ ኢትዮጵያ እንተርፍ ይሆን? በሚል ርዕስ አቶ ልደቱ አያሌው በጻፈው ጦማር በርካታ “አስፈሪ” ትንበያዎችን አስነብቦናል። አንዳንዱ እርስ በእርሱ የሚጋጭ ነው። ለምሳሌ አብይ አሕመድ እርስ በእርስ እያጫረሰ ለ5 ዓመታት እንደገዛው ሁሉ፣ ለሌላ አስር አመት የማይገዛበት ምክንያት አይታየኝም ይላል። በሌላ በኩል ደግሞ አሁን ያለው የኢኮኖሚ መንኮታኮት እንዴት አገርና ስርዓቱን በቀላሉ ሊንድ እንደሚችል በዝርዝር ይተነትናል። በኔ እምነት ሁለተኛው ግምት ነው ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው። ከወዲሁ እየጀማመሩ ያሉ ክስተቶች፣ ማለትም የአጋሮቹ ማፈንገጥና መኮበለል፣ ይህ ሊሆን እንደሚችል አመላካቾች ነው። በዚህ ሳምንት፣ የአብይ መንግስት የአንድ ቢልዮን ዶላር እዳውን መክፈል እንዳቃተው የአለም የሚድያ አውታሮች ይፋ አድርገዋል። ክሬዲት ሬቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየወረደ፣ አበዳሪ እየጠፋ፣ ኢንቨስተር ኮንፊደንሱ እየተሸረሸረ፣ እየሔደ ነው። በውጭ ምንዛሪ እጥረት ስርዓቱ መላወሻ አጥቶ፣ ምንዛሪውም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየወረደ፣ ያንን እጥረት ለመቅረፍ ሌላ አማራጭ ስለጠፋ፣ ብሩን የባሰ ዲቫልዩ ሊያደርገው እንዳሰበ ወሬዎች ሲናፈሱ እየሰማን ነው። ከሁለት ሳምንት በፊት አቶ ክቡር ገና እንዳስነበቡን ከፈረንጆች አዲስ አመት ብኋላ መንግስት ብሩን ዲቫልዩ ሊያደርግ እየተዘጋጀ መሆኑ ነው። ይህ ከሆነ፣ የብር ዋጋ የባሰ ወድቆ፣ የኑሮ ውድነት አሁን ካለበት በባሰ ሁኔት አሻቅቦ፣ በየቦታው የባሰ ትርምስ የምናይበት ግዜ ይሆናል። አጋጣሚውን ሲያገኙ የስልጣን ሹመኞችና ከፍተኛ ካድሬዎቹ የያዙትን እየያዙ ሻንጣቸውን ሸክፈው የሚኮበልሉበት ወቅት ነው።

የአገሪቱን ኢኮኖሚ በጦርነት ማንኮታኮቱ ሳያንስ፣ በቅንጡ ፕሮጀክቶች የሚያባክነው ገንዘብ፣ ዞሮ ዞሮ የራሱን የስልጣን እድሜ እያሳጠረ ለመሆኑ አብይ አሕመድ እስከዛሬ ድረስ አልተረዳም። ስራ መፍጠርና ምርት ማሳደግ ሳይችል፣ ቀድሞ የለማውን በማውደምና በእዳ ላይ እዳ በመቆለል የሄደበት የ5 አመት ጉዞ፣ የራሱን ገመድ ያሳጠረበት ሁኔታ ብቻ ነው የፈጠረው። አቶ ልደቱ እንደሚገምተው፣ እየሰራው ባለው ቤተመንግስት ለአስርት አመታት ሊኖርበት የሚችል እድል የለም። ለአንድ ሁለት አመት እድሜውን የሚያራዝምበት የቀረችው አንዲት መንገድ፣ ውስጣዊ ችግሩን ውጫው በማድረግ፣ ህዝቡን በድጋሚ በደመነፍስ በዙሪያው ማሰለፍ ነው። አዎ በትክክል ገምታችኋል፣ የአሰብ ጦርነት ያን የመሰለ ግዜያዊ ድጋፍ ያስገኝለታል። ነገር ግን አገሪቱ ሌላ ጦርነት የምትቋቋምበት ኢኮኖሚ ስለሌላት፣ ከጦርነቱ ብኋላ ሌላ ትርምስ ውስጥ ለመግባት ግዜ አይወስድባትም።

ዞሮ ዞሮ መውደቂያው የተቃረበ ስርዓት ነው ያለው። አቶ ልደቱ በትክክል ያስቀመጠው ነጥብ ቢኖር ከአብይ ብኋላ ምን ይፈጠር ይሆን የሚለው ስጋት ምን አይነት ቅርጽ እንደያዘ ነው፥ “በኢህአዴግ ዘመን፣ ድህረ ወያነ ከወያነ የባሰ ስርዓት ይመጣ ይሆን ዎይ ብለን ነበር የምንሰጋው፣ ዛሬ ግን ስጋቱ ከብልጽግና ብኋላ ኢትዮጵያ እንደአገር ትቀጥላለች ወይ ወደሚለው ተቀይሯል” ብሏል ልደቱ። “ይህን ደግሞ አብይ አሕመድ ሆን ብሎ የፈጠረው ነው” ሲል ይከራከራል። ይህ በጣም ትክክል ነው። እኛ ይህ እንደሚሆን ያወቅነው፣ ትግራይ ህዝብ ላይ በጅምላ ጦርነት የከፈተ እለት ነው። አንድ አገር የራሱን ህዝብ ሊያጠፋ ሲነሳ፣ ከሲዩሳይዳል ሚሽን የሚተናነስ አልነበረም። ለኢትዮጵያ መፍረስ ደግሞ ከአብይ ያላነሰ ድርሻ የተጫወቱት፣ ዛሬ አንጻሩ የተነሱትና በአብይ እየተገረፉ ያሉት የቀድሞ አጋሮቹና “የእልቂት ፍኖተ ካርታ” አርቃቂዎች ናቸው። ታድያ ዛሬም በተናጠል የብልጽናን ስርዓት ሲታገሉ፣ ድህረ አብይ ምን አይነት ሁኔታ ይፈጠር ይሆን፣ ብለው አያስቡ አይደለም።ጦርነታችሁ ፖይንትለስ ጦርነት የምንለው ደግሞ ለዚህ ነው። በተደጋጋሚ እንደምንለው፣ ቢሸነፉ ተሰብረው ይቀራሉ፣ ቢያሸንፉ ለሌላ የባሰ የእርስ በእርስ እልቂትና አገር የመበታተን አደጋ ያቀናሉ።

ይህን አይነቱ የጥፋት መንገድ ግምት ውስጥ በማስገባት ነው፣ እንደ አገር አብረን ኖርንም አልኖርንም፣ የሚያዋጣን በሰላም መኖር ነው የምንለው። በሰላም ለመኖር ደግሞ፣ ንግግርና ውይይት መጀመር ያስፈልጋል። ድህረ አብይ፣ ኢትዮጵያ የሚኖራት እድል መፍረስ እንዳይሆን ማድረግ የሚቻለው (ብቸኛው መንገድ) ይህንን የድርድርና ውይይት መንገድ በመከተል ነው። ከትላንቱ ጥፋት ተምሮ፣ ስለ ነገ የተሻለ እድል፣ ዛሬ ቁጭ ብሎ መነጋገር! ለተሻለ ውጤት ሌላ ሶስተኛ ወገን (የውጭ ታዛቢና አደራዳሪ) በተገኘበት መደራደር አስፈላጊ ሊሆን ይችላል።

ትንሽ መተባበር ቢኖር፣ ይህ ስርዓት በቀላሉ ሊወገድ የሚችል ሽባ ስርዓት ነው። ከዚህ በፊት ከነበሩት ስርዓቶች በሙሉ ደካማና በውድቀት ላይ ያለ፣ በሁሉም የማይፈለግ፣ መለወጥ ያለበት ስርዓት ነው። ነገር ግን ከዚህ ስርዓት ብኋላ የአገሪቱ እጣ ፈንታ ምን ይሆን የሚለው ጥያቄ በብዙዎች ዘንድ አስጨናቂ ጥያቄ ሆኗል። ይህን ጥያቄ ግምት ውስጥ ያስገባ እንቅስቃሴና ትግል ብቻ ሁሉንም ነጻ ያወጣል። ሁላችንም መገንዘብ ያለብንና እንደ እናት ጡት እርም ማለት ያለብን ነገር ቢኖር፣ ከዚህ ብኋላ ኢትዮጵያ በአንድ ብሔር ወይም ቡድን የመተዳደር እድሏ ማብቃቱን ነው። ዴድ ኢንድ! ሁሉንም የሚያሳትፍ ስርዓት በጋራ ለመፍጠር መረባረብ ወይም ለመበታተን መዘጋጀት ነው የቀረን አማራጭ።

5 replies
 1. z
  z says:

  ውይይት ንግግር ድርድር ትላለህ ማን ከማን ጋር ነው የሚደራደረው? እንዴት ነው የሚደራደረው? የማይመስል ነገር ነው። የሚሆነውን በቅርብ ቀን ጠብቅ።

  Reply
  • ሓምሓም
   ሓምሓም says:

   አታ ወዲ እታይ ገዲሹካ እዩባ ላሕ ትብል ዘለካ። ክተጥፈና ዝተለዓለት ሀገር ፋሕ ብትን ትብል ግዲ። ከም ተጋሩ ገዛ ዕዮና አፅፊፍና ንስራሕሞ ናይ ባዕልና ሀገር ነቅንዕ።

   Reply
   • Solomon
    Solomon says:

    ካብ ስምዒት ውጽእ ኢልና ነገራት ነመዛዝን። ናይ ሓደ ሀገር ምብታን ሒዝዎ ዝመጽእ ብዙሕ ጣጣ አሎ። ተጋሩ ድማ ይትረፍ ዶ ንዕኡ ክንዳሎስ፣ አብ ውሽጥና ንፋስ አትዩና፣ አካይዳና ሰንኪሉ እዩ ዘሎ። እቲ ሓቂ ንሱ እዩ።

    Reply

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *