ለመከራ ያለው መነኩሴ ዳዊቱን ሸጦ አህያ ይገዛል
አዲሱ የኢትዮጵያና የሶማሌላንድ የባህር በር ስምምነት፣ ኢትዮጵያን የባሰ ውጥረት ውስጥ ከቷቷል። ስምምነቱ ጠላት የሚያበዛና በራስ ላይ ገመድ የማጥለቅ ያህል ሆኗል።
ግብጽ ከሶማሊያ ጎን እንደምትቆም ግልጽ አድርጋለች። ሌሎች የአረብ አገራትም መከተላቸው አይቀርም። የአውሮፓ ህብረት አቋሙን ግልጽ በማድረግ ኢትዮጵያ አለም አቀፍ ህግጋትንና የሶማሊያን ሉኣላዊነት እንድታከብር ጠይቋል።
ከነዚህና መሰለ ክስተቶች ተነስተን እንገምት ካልን፣ ስምምነቱ ተግባራዊ ሊሆን እንደማይችል ነው። ለዘብ ያለው ከኢትዮጵያ የተሰጠው መግለጫ የሚያመላክተው ደግሞ ይህ ሊሆን እንደሚችል ነው። የኢትዮጵያ መግለጫ ሶማሌላንድ የምትፈልገውን እውቅና በግልጽ የሚያስቀምጥ ሳይሆን ለዘብ ያለ አቋማን ያንጸባረቀችበት መግለጫ ነው።
አብይ አሕመድ እንደጀማመረው አሰብ ላይ ቢያተኩር ያዋጠው ነበር፣ በብዙ ምክንያት። የአሰብ ጉዳይ ያን ያክል አለም አቀፍ ጫና የሚፈጥር ጉዳይ አልነበረም። ቢያንስ የሶማሊያ ጉዳይ እየፈጠረ ያለውን አለም አቀፍ ጫና ያህል አይሆንም ነበር። ምክንያቱም፥
አንደኛ የ120 ሚልዮን ህዝብ ጎጆ የሆነው ትልቅ አገር ያለ ባህር በር ተቆልፋ ለዘልአላለም መኖር እንደማትችል ሁሉም ያውቃል። በባሌም በቦሌም ብላ የባህር በሯን በእጇ እንደምታስገባ የሚጠበቅ ነው። የጊዜ ጉዳይ ብቻ ነው።
ሁለተኛ ኤርትራ ከኢትዮጵያ የተገነጠለች የኢትዮጵያ አካል ናት። እርግጥ ነው አወዛጋቢ ጉዳይ ነው፣ ነገር ግን ከፊል አለም አቀፋዊ ከፊል ውስጣዊ ቅርጽ ያለው ጉዳይ ነው፣ ልክ እንደ ሆንግኮንግ፣ እንደ ታይዋን፣ እንደ ጋዛ ምናምን፣ ያላለቁ አወዛጋቢ ጉዳዮች ያሏቸው አገራት።
ሶስተኛ ኤርትራ ሁለት የባህር በር ያለ አግባብ ይዛ የተገነጠለች ክፍለ ሀገር ናት። አሰብ ህጋዊ የኢትዮጵያ ወደብ ነው። በመሆኑም በኤርትራ ስር ለ30 ዓመታት ጥቅም አልባ ወደብ ሆኖ ቆይቷል። ከታሪካዊ ዳራው አንጻርም መንግስት ሰፊ ህዝባዊ ድጋፍ ሊያስገኝለት ይችል የነበረው አሰብን እውን የማድረግ ፕሮጀክት ነው። የሶማሊላንዱ ስምምነት ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ትርጉም የሚሰጥ ስምምነት አይደለም። በዛ ምክንያት ጦርነትና ትርምስ ውስጥ ግባ ብትለው፣ ማንም አይሰማህም። ለአሰብ ግን አቋሙ የተለየ ነው።
አራተኛ ኤርትራ የኢትዮጵያን ሰላምና አንድነት በማደፍረስ የተጠመደች፣ ምንም አይነት የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ድጋፍ በሌላቸው ማፊያዎች የምትመራ ቀጠናውን በነውጥ በማተራመስ የምትታወቅ አገር ናት። ቀኝህን በጥፊ ስትባል በጫማ ጥፊ መንጋጭላውን ማውለቅ የዘመኑ ምላሽ መሆኑን ሁሉም ይገነዘባል። በዛ ላይ በአለም አቀፍ ማህበረሰቡ ዘንድ በሻዕቢያ ላይ የሚወሰድ እርምጃ ለቀጠናው መረጋጋት እንደ አዲስ ምዕራፍ ከፋች ተደርጎ ሊታይ የሚችል እርምጃ ነው።
አምስተኛ በማንኛውም ሰዓት በሁለቱ አገራት መካከል ጦርነት ሊነሳ እንደሚችል የአለም አቀፍ ማህበረሰቡ ይገነዘባል።
ቋፍ ላይ የደረሰን ነገር ትተህ፣ ሌላ አዲስ ትርምስ የሚፈጥር፣ ያውም ጠላትህን የምታበዛበትና በጋራ እንዲሰባሰቡ የሚያደርግ አወዛጋቢ ስምምነት መፍጠር፣ በራስ ላይ ገመድ ከማጥለቅ አይተናነስም። ስለሆነም አሰላለፉ ከሻዕቢያና ፋኖ ጥምረት ወደ ሻዕቢያ፣ ፋኖ፣ አልሸባብ፣ ሶማሊያ፣ ግብጽና ሌሎች ጥምረት ተሸጋግሯል። ይህም ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ፈታኝ ያደርገዋል።
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!