, ,

ጎራችሁን ለዩ፥ ከህዝብ ወገን ወይስ ከወንጀለኞች ጎን

ሰለሞን ነጋሽ

ጦርነቱ ትክክል ነው፣ ከህወሓት ጋር ነው። ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብ የሚደረግ ህግ የማስከበር ስራ ነው። ብላችሁ ለምታምኑ ህሊናችሁን እንድትፈትኑት የሚጋብዝ ጽሁፍ ነው። 95 ሚልዮን ለ5 ሚልዮን፣ ይጥፉ ወይስ እንጥፋ፣ ወዘተ በሚል የታወረ እይታ የምታራምዱ ከሆነ፣ ይህን ማንበብ አይመከረም እዚሁ አቁሙ። አላማው ምን ያህሉ በተሳሳተ መረጃ፣ የተሳሳተ አቋም እንደያዘ ለማወቅ ነው። ሁላችንም አቋማችንን እያጠራን እንድንሔድ ይረዳናል።

  1. ህወሓት አታልሎም ይሁን አሳምኖ የትግራይን ህዝብ ከጎኑ አሰልፏል። የትግራይ ህዝብ በፌደራል የተላለፈውን ህግ እያወቀ የክልሉ መንግስት ባዘጋጀው ምርጫ ተሳትፏል። ህወሓትንም መርጧል። የህዝብ ውሳኔ ምን ማድረግ ይቻላል?
  2. አብይ አሕመድ በሁሉም ቦታ ተቀባይነቱን የሚሸረሽር ስራ ሲሰራ ላለፉት ሁለት አመታት ቆይቷል። ኦሮሞው አልተቀበለውም። አማራው እንደ ፔንዱለም ቢወዛወዝም የተቃወመውና ያማረረበት ጊዜ ይበጣል፣ አዲስ አበቤው አልተቀበለውም፣ ወላይታ ሲዳማ ጉራጌ ወዘተ ሁሉም ከአብይ መንግስት ጋር አልተስማሙም። የትግራይ ለብቻው አይደለም። ይህ እውነታ ሰፊ ቅስቀሳና ፕሮፓጋንዳ ሳያስፈልገው የትግራይ ህዝብ በራሱ ጊዜ ከህወሓት ጎን እንዲሰለፍ ዋነኛ ምክንያት ሆኗል። ወዶና ፈቅዶ ከጎኑ ከተሰለፈ ደግሞ እኔ አውቅልሀለሁ አይባልም። ፋሽሽታዊ ባህሪ ነው።
  3. በህገወጥ መንገድ ያለበቂ ምክንያት አብይ አሕመድ ስልጣኑን በራሱ መንገድ አራዝሟል። በዚህ ምክንያት ከህወሓት ጋር ብቻ ሳይሆን፣ ከሌሎች የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ጋር መግባባት አልቻለም። በሀሰት ክስ ሁሉንም አስሯቸውም ይገኛል። በተለይ ልደቱ አያሌውን ፍርድ ቤቱ በተደጋጋሚ ነጻ ቢለውም፣ ፈጽሞ ሊፈታው አልፈለገም። ከመስከረም 30 ብኋላ ሰላም እንደማይኖር በመናገሩ ብቻ ቂም ቋጥሮበታል። ልደቱ እንዳለው ታድያ የመጨረሻው ደረጃ ላይ ደረሰን አየን እንጂ፣ ግምቱ የተሳሳተ አልነበረም። (“አደባባይ ውጡ አልል፣ ተኩሱ አልል፣ ምንም አልልም። ዝም ብዬ ነው የማየው” እንዳለው፣ ይኸው እርሱ ምንም ሳይል እኛ ጥቅምት ሳይገባደድ እዚህ ደረጃ ላይ ደርሰናል ።)
  4. በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ግጭቶች ተስፋፍተዋል። ህወሓት ላይ ማሳበብ እንደማይቻል ባለፉት ጥቂት ቀናት ብቻ ያየናቸው ተደጋጋሚ ግጭቶች በቂ ማስረጃዎች ናቸው። ትግራይ ከተከበበች፣ ኔትዎርክ ከተዘጋና ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ በሌላ የአገሪቱ ክፍል የሲቪልያን ህይወትን የቀጠፉ ቢያንስ አምስት ግጭቶችን አይተናል። በህወሓት ማሳበብ አይቻልም።
  5. ኢሳያስን እየጋበዘ የጦር መሳሪያ ሲያስጎበኝ፣ አየር ሀይሉን ሲያሳይ፣ ለራሱም ኤርትራ ሄዶ አንዳንድ ሁኔታዎችን ሲያጠና፣ ወሎና ጎንደር ሄዶ ቅድመ ዝግጅት ሲያደርግ እንደከረመ ሁላችንም እናውቃለን። ከህዝብ የተደበቀ እውነታ አይደለም። በራሱ ሚድያ የዜና እወጃ ሆኖ ሰምተነዋል/አይተነዋል። የገንዘብ ቅየራው፣ ወታደሩን ማጓጓዝ፣ ወታደራዊ አመራሩን መቀየር ወዘተ የጦርነት ቅድመ ዝግጅቱ አንድ አካል ነበሩ።
  6. ጦሩን አጓጉዞ፣ ከነ ኢሳያስ ጋር መክሮ፣ ተዘጋጅቶበት ሲያበቃ፣ ኋላ እንደተረጋገጠው በኦሮሞ ነጻ አውጪ ታጣቂዎች የተወሰደውን እርምጃ ህወሓት ላይ ለድፎና ያንን ሰበብ አድርጎ “ምክር ቤቱ”ን በማላቀስ ሲያስወስን የዋለ እለት፣ ጦርነቱን የሚጀምርበት ሁኔታን እያመቻቸው እንደነበር እንገነዘባለን። (ህወሓት የሰሜን እዝ ላይ እርምጃ ወሰደ ስልሚባለው ወሬ ሰለማያግባባን እንተወው። ኦፕሬሽኑን ቀድሞ የጀመረው አማራና ሶማሌ ክልል ላይ እንዳደረገው በአውሮፕላን ኮማንዶ ጭኖ በመላክ የሞከረ ሲሆን ያ ሀይል ላይ ነው እርምጃ የተወሰደው፣ የሰሜን እዙ ከጎናችን ተሰልፏል ባይ ነው ህወሓት። እርሱ ደግሞ እዛ ሲጠብቁ የነበሩትን በተኙበት ወጓቸው ነው የሚለው። ተጣርቶ ማስረጃው እስኪወጣ ድረስ ማንም ሰው እርግጠኛ ሊሆን አይችልም። ለፎቶ ካለው ፍቅር አንጻር ማስረጃ ቢኖረው ኖሮ ይፋ ያደርገው እንደነበር ግን ማስታወስ ያስፈልጋል። )
  7. ጦርነቱ በይፋ ከመጀመሩ በፊት ህዝቡ ላይ የተፈጸሙ ግፎችን በቅድሚያ እንመልከት፥ በጀት መከልከል። የዓለም ባንክና የመሳሰሉ አለም አቀፋ ተቋማት የሚሰጡትን እርዳታ መከልከል። ከስፖርት ውድድር ተጋሩን ማግለል። የኮቪድ ቁሳቁስ ወደ ትግራይ አለመላክ። ከውጪ የተገዙ የተለያዩ ቁሳቁሶች ወደ ክልሉ እንዳይገቡ ማገድ። መንገድ መዝጋት። ነዳጅ እንዳይገባ ማድረግ። በሁሉም ዙሪያ ክልሉን መክበብ። ጦርነት ከከፈተ ብኋላ ደግሞ ተደጋጋሚ የአየር ድብደባ በከተሞች ጭምር ማካሔድ። ከቤታችሁ እንዳትወጡ እደበድባለሁ ብሎ በአደባባይ ማወጅና ህዝብን ማሸበር። ከትግራይ ውጭ ያሉ ተጋሩን ማዋከብ፣ ኢትኒክ ፕሮፋይሊንግና ድንገተኛ ፍተሻ ተጋሩ ላይ ማካሔድ። በጸጥታ መዋቅር ውስጥ የነበሩ የትግራይ ተወላጆች በሙሉ ከስራ ማገድ፣ ትጥቃቸውን ማራገፍ፣ ብሎም ማሰር። ተማሪና የውጭ ዜግነት ያላቸው ተጋሩ ጭምር ወደ ውጭ እንዳይወጡ ማገድ። ከትምህርት፣ ከስራ፣ ከቢዝነሳቸው ማስተጓጎል። ወዘተ
  8. በብሔር የተደራጀ ልዩ ሀይልና ምልሻ እዚህ ጦርነት ውስጥ እንዲገባ አድርጓል። ወደ ብሔር ግጭት ሊያመራ ይችላል የሚል ስጋት በስፋት አለ።
  9. የውጭ ሀይል ማለትም የኤርትራና (ዛሬ ደግሞ የሱዳንም ተጨምሮበታል እየተባለ ነው) ጦርነቱ ውስጥ ጎትቶ ማስገባት።
  10. ለአለም አቀፍ የተኩስ አቁሙ ጥሪ ጆሮ አለመስጠት።

ይህ ሁሉ የተደረገውና እየተደረገ ያለው ጥቂት በህግ የሚፈለጉ ሰዎችን ለመያዝ ወይስ ትግራዋይን ለመስበር? የፈለገውን ያህል ኪሳራ ያስከትል (ትግራዋይ ተሰብሮም ይሁን) ደንታ የለንም ከሆነ መልሳችሁ አንድ ነገር ነው። ጥቂቶችን ለህግ ለማቅረብ ይህን ያህል ርቀት መጓዝ ትክክልና ተገቢ ነው ብላችሁ ከሆነ የምታምኑትና እርምጃውን የምትደግፉት ዝምታችሁ መልስ ይሆናል። እንደነ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው “የለም ይህ ትክክል አይደለም፣ እብደት ነው” የምትሉ ከሆነ ደግሞ አቋማችሁን አጥርታችሁ ይህን ጦርነት ለማስቆም ጫና መፍጠር ይጠበቅባችኋል።

በበኩሌ አብይ ህግ አስከባሪ ሆኖ በህግ ሊፈልጋቸው የሚችሉ ወንጀለኞች ይኖራሉ ብዬ አላምንም። ምናልባት የኢትዮጵያ ህዝብ እርሱንና ጋሻ ጃግሬዎቹን ወደ ህግ ማቅረብ የሚፈልገውን ያህል ከህወሓት ባለስልጣና ሌሎችም በህግ ሊጠይቃቸው የሚፈልጋቸው ሊኖሩ ይችላሉ። አሉም። ነገር ግን አብይ ከነሱ ተሽሎ ህግ አስከባሪ ነኝ የሚልበት ምንም የሞራል መሰረት የለውም ብዬ አምናለሁ። በደም የተጨማለቀ በብዙ ወንጀል የሚፈለግ፣ በገለልተኛ አካል ብዙ መጣራት ያለባቸው የህዝብ ጥያቄዎች አሉ። የአማራ መሪዎች ሞት፣ የኢንጅነር ስመኘው ግድያ፣ የነጄነራል ሰዓረ ሞት፣ የአርቲስት ሀጫሉ ግድያ፣ የዜጎች በየቦታው መፈናቀል በየተለይ አዲስ አበባ ዙሪያና ኦሮሚያ፣ የንጹሀን ዜጎች በየቦታው መሞትና ሌሎችም ሁሉም በገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽን ተጣርተው ወንጀል ፈጻሚዎች ለፍርድ መቅረብ አለባቸው። አገሪቱ አሁን የገባችበትን ጦርነት ጀስቲፋይ የሚያደርግ በቂ ምክንያት ስለሌለ፣ ወደ ጦርነት የከተቱን  ተጠያቂ ሰዎች ተጣርቶ ለፍርድ ሊቀርቡ ይገባል። እስከዛው ያለ በቂ ምክንያት የተገባው ጦርነት አንድን ሉአላዊ ህዝብ ለማንበርከክ የተቃጣ ወረራና ጥቃት ነው ብዬ ነው የማምነው። ለዚህም ነው ከትግራዋይ ወገኔ ጎን የቆምኩት። ተሳሳትኩ?

1 reply

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *