የለውጥ መሰረቱ ህዝብን ከህዝብ ድርጅትን ከድርጅት ጋር ማቀራረብ ሲቻል ነው

ህዝብየኢትዮጳጵያ ህዝብ በጠቅላላ በተለይ ደግሞ የኦሮሞ ህዝብ ለዘመናት ታፍኖ ነበር። እንደብዛታችን መጠን በሚገባን ቋንቋ ሚድያ አላገኘንም ነበር። ESAT በከፈተው በር OMN ተከትሎ ለኦሮሞ ህዝብ ድምፅ መሆኑ በኦሮሚያ ለመብቱ የሚሞት ትውልድ ከጫፍ እስከ ጫፍ እንዲፈጠር የጎላ አስተዋፆ አበርክቷል። ይህ ብቻ አይደለም፥ ሲነሳ አብሮ የሚነሳ፥ ሲረጋ አብሮ የሚረጋ የመደማመጥ ባህልን ያዳበረህ ትውልድ ተፈጥሯል። በተጨማሪም ጥያቄውን በሰለጠነና በሰላማዊ መንገድ እያቀረበ ስርዓቱን ማሽመድመድ የሚችል አቅም ፈጥሯል። በግፍ እየሞቱ እንኳን ወደ በቀል ውስጥ አልገቡም። በጅምላ ተገድለው በጅምላ እየተቀበሩ እንኳን ወደ አመፅ አልገቡም። ይህ ሰላማዊ ትግላቸው ነው ኦህዴድ ውስጥ ከህዝብ ጎን የሚቆሙ ታጋዮችን (የለውጥ አራማጆችን) ሊያፈራ የቻለው። የተቃውሞ እንቅስቃሴ ነጥብ ያስቆጠረበት ቁልፍ ቦታ ቢኖር ይኸው ነው። የኢህአዴግ ካድሬዎችን ገልብጦ የህዝብ ትግል ውስጥ የከተተ እንቅስቃሴ ዋንኛው የህዝቡ ድል ነው።

ለማ መገርሳ፥ ዶ/ር አብይ፥ገዱ አንዳርጋቸው እና ሌሎችም በዚህ መንገድ የተወለዱ የለውጥ አራማጆች ስለሆኑ ብቻ ነው ዛሬ የደረስንበት ደረጃ ላይ ልንደርስ የቻልነው። እነዚህ ሰዎች የኢህአዴግ ከፍተኛ ካድሬዎችና መሪዎች መሆናቸው፥ እንዲህውም ለህይወታቸውና ስልጣናቸው ሳይሰስቱ፥ ደፍረው መውጣታቸው፥ ኢህአዴግ ውስጥ የለውጥ እንቅስቃሴ እንዲቀጣጠ ምክንያት ሆነዋል። ህወሓት ለወትሮ ለስልጣኔ ጠንቅ ናቸው በምትላቸው ዜጎች ላይ የምትወስደው የጉልበት እርምጃ  በእነዚህ ሰዎች ላይ መተግበትርና መመንጠር ያልቻለችው፥ ያን ብታደርግ ኢህአዴግን ራሱን ማፍረስ ስለሆነባት ነው። እንጂማ እነዚህ ሰዎች በተቃዋሚ ቦታ ቢሆኑ ኖሮ ይሄኔ ከሌሎች አኩዮቻቸው ጋር በየወህኒ ቤቱ ታጉረው ነበር፥ ህይወትም በተለመደው ዑደት በቀጠለች ነበር። የኛም ጥያቄ እሰረኞች ይፈቱ ከማለት ስንዝር ባልተራመደ ነበር። ይህንን ነው ብዙዎቻችን በቅጡ መረዳት ያቃተን።

እነ ለማ ተሟሙተው እዚህ የደረሱት ኢህአዴግ ውስጥ ስለሆኑ ብቻና ብቻ ነው። በአቅምም ቢባል በእውቀት ወይም በተነሳሽነት እስከዛሬ በተናጠል እየታገለ ሲታጎር የኖረው ተቃዋሚ ከነሱ የሚያንስና የተለየ ሆኖ አይደለም። ኢህአዴግ ልትደፍራቸው ባለመቻሏ ብቻ ነው። ከሁሉም በላይ በተለይ ለማና አብይ በድህንነት መስሪያ ቤት ውስጥ ሲሰሩ የነበሩ መሆናቸው፥ በኦሮሚያ የተዘረጋውን የደህንነት መዋቅር ሙሉ በሙሉ እንደኔትዎርክ ለመጠቀም ችለዋል። ይህንን ህወሓት መስበር አትችልም። ልሞክር ብትልም ኢህአዴግ ይናጋል። እነ አባይ ፀሃዬ ትግራይ ሄደው “ዋላ ኢህአዴግ ይበተን” ያሉት ከዚህ ተነስተው ነው። የራሳቸውን እግር ገዝግዞ መጣል ሆነባቸው። አሁንም ከፊታቸው ይነበባል፥ ሽንፈታቸውን አምነው መቀበል እና የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ በበጎ መልኩ ማየት አልፈለጉም።

በሌላ በኩል ደግሞ ተቃዋሚ ነኝ የሚል የዞረበት ክፍል አለ። ለማና አብይ እንዲህውም ገዱ ከነቡድናቸው የወጡት በብሔር ፖለቲካ ከተዋቀረ ድርጅት ነው። ዕድሜ ልካቸውን ሲያቀነቅኑት የነበረ ብሔርተኝነት ፈፅሞ ሊጥሉት አይቻላቸውም። ቢጥሉት የራሳቸው ህዝብ እንደሚናሳባቸውም ጠንቅቀው ያውቃሉ። እንደዚህውም ደግሞ የብሔር ፖለቲካ አደገኛነቱን በክልሎች መካከልና ውስጥ በተከሰቱ “ብሔርን” መሰረት ያደረጉ ግጭቶች አይተዋል። በተለይ በሶማሊያና በኦሮሚያ መካከል የተከሰተው ማንንም ቢሆን ያስደነብራል። ወዴት እያመራን እንደነበር በደንብ አድርጎ አሳይቷቸዋል። ከዛ ጎዳና መውጣት እንደሚያስፈልግ ያውቃሉ። ትኩረታቸውም የሆነው ያ ነው። ያን ለማድረግ በዘዴ፥ ቀስ በቀስ በተቃራኒ ቦታ የቆሙትን ኃይሎች ግምት ውስጥ እያስገቡ እንጂ ድንገት በአንድ ጀንበር በስርነቀል ለውጥ ወይም  አብዮት ሊቀለብሱት የሚችሉት ነገር አይደለም።

ዶ/ር አብይ እስከዛሬ ድረስ በየሄደበት እያደረገ ያለው ንግግር፥ ብሄሩን ለሚያስቀድም እውቅና እየሰጠና አኩሪ ማንነቱን እየገለፀ፥ ትኩረቱን ያደረገው የብሄርና የቋንቋ ድንበር ሳይገድብ የህዝባችንን አንድነት ፕሮሞት ማድረግ ላይ ነው። በዚህ አካሄዱ ሁለቱንም የተቃዋሚ ካምፕ በኩርኩም እየነረተው ያለ ይመስለኛል። ለዚህም ነው በሁለቱም ካምፕ አቃቂር ከማውጣት የዘለለ መሰረታዊ የሆኑ ጥያቄዎችንና ተግዳሮቶችን ማስቀመጥ ያልቻሉት። ፕላጂያራዝድ ነው ከተባለው ንግግሩ አንስቶ እስከ ሞተር ድረስ ማብጠልጠል እንደ ትልቅ ቁም ነገር ቆጥረዉታል። ዶ/ሩና ቡድኑ ግን ከህወሓት፥ ከጎሳ ፖለቲካ አራማጅ ተቃዋሚው፥ አንድነት ነኝ ከሚለው ካምፕ እንዲህውም በማብጠልጠል ከተጠመደው አክቲቭስትና ጋዜጠኛ የሚሰነዘርበትን ሁሉ ወደጎን ብሎ ህዝብን ከህዝብ፥ ድርጅትን ከድርጅት (በኢህአዴግ ውስጥ ያሉትንም ከኢህአዴግ ውጭ ያሉትንም) የሚያቀራርብ ስራ እይሰራ ነው።

በውስጡ እየታመሰ የነበረን ኢህአዴግ እየገራ፥ ከተቀናቃኝ ፓርቲዎች ጋር እያቀራረብ፥ ህዝብን ከህዝብ ጋር እያሰተሳሰረ፥ አገሪቱ ከገባችበት ቀውስ መታደግ የሚችሉ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ እያየን ነው። ሌሎቻችንን የኢትዮጵያ ህዝብ የሚለካን ይህን በታሪክ አጋጣሚ እየተፈጠረ ያለውን አገሪቱን ከተጋረጠባት የመፈረካከስና የመተላለቅ አደጋ የሚታደግ ብቸኛ ዕድል በአግባቡ እንጠቀምበታለን ወይስ እንደ ምርጫ 97ቱ ጊዜ የኋሊት ሸምጥጠን የታሪክ ተጠያቂዎች እንሆናለን? ጊዜ ለኩሉ አብረን የምናየው ይሆናል!

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *