, ,

ወደ አምባገነናዊ ስርዓት መመለስ አገር ያሳጣል

ለዚህ  ጽሁፌ መነሻ ምክንያት ወደ ሆነኝ ነጥብ ልምጣና የኢህአዴግ አልጋ ወራሽ የሆነው ብልጽግና ልክ እንደትላንቱ ዛሬም በተመሳሳይ ጎዳና እየገሰገሰ ይገኛል። ኩንትራቱን ሊጨርስ እየተቃረበ ያለው ጠ/ሚ/ር አብይ አሕመድ፣ በኢህአዴግ ውስጥ የተፈጠረውን ክፍፍል በአሸናፊነት ተወጥቶ ስልጣኑን ለማደላደል ሲል ብልጽግናን የመሰረተበት ሒደት፣ ድርጅቱን ለማጠናከርና አባላትን ለማፍራት እየተጓዘበትና ያለው መንገድ ከቀድሞ የኢህአዴግ ባህል ምንም የተለየ አይደለም። ኢህአዴግ የቀድሞ ስሙን ብቻ ቀይሮ በህይወት አለ። ልዩነቱ የቀድሞ ታጋዮች ኮትኩተው ባሳደጓቸው ካድሬዎች በፖለቲካ ጌም መሸነፋቸው ብቻ ነው። ሰዎቹ ተሸነፉ እንጂ የዘረጉት ባህል አልተሸነፈም። ካድሬዎቹ ከህወሓት ካድሬዎች ውጪ ቀሪዎቹ የነበሩት ናቸው። የሚተዳደሩት በለመዱትና በኖሩበት የድርጅት ባህል ብቻ ነው። ለዚህም ነው ብልጽግና ከኢህአዴግ የተለየ ባህል ሊኖረው የማይችለው።

ጠ/ሚ/ሩ በህዝብ ይሁንታ፣ በተሰጠው የሁለት አመት የስልጣን ገደብ ቀድሞ የገባውን ቃል አጥፎ፣ የዴሞክራሲ ተቋማትን ሳይገነባ፣ ነጻና ገለልተኛ ምርጫ ሳያካሒድ፣ ስልጣን በሰላማዊ መንገድ በህዝብ ለተመረጠ አሸናፊ ፓርቲ ማስተላለፍ የሚችልበትን እድል ሳይፈጥር፣ በማንኛውም መንገድ ስልጣን ላይ ለመቆየት የሚያስችሉትን አማራጮች እየዘረጋ ቆይቷል። አንዱ መንገድ የቀድሞ አጋሮቹን ገፍትሮ በአዲስና ታማኝ ካድሬዎች መተካት ነው። እኔ አሻግራችኋለው ከማለት ስልጣን ላይ ካልቆየሁ መታሰራችን ነው ወደ ማለት ተሸጋግሯል። ይህ አፍሪካ ነው፣ ምርጫ ማጭበርበር ብርቅ አይደለም ማለቱም ተሰምቷል። አንድ ሰሞን መተካከት የሚባል የፖለቲካ ዲስኩር ተፈጥሮ ነበረ። አቶ መለስ የቀድሞ ጓዶቹን በመተካካት አሰናብቶ፣ በአዲስ ሀይል ተካቸው። እኔም በቅቶኛል ስልጣን ለአዲሱ ትውልድ አስተላልፋለሁ ሲል ቆይቶ፣ ባለቀ ሰዓት ድርጅቴ መርጦ አዲስ አደራ ስለጣለብኝ፣ ግዴታዬን መወጣት አለብኝ አለ። በ99.96% አሸነፍኩ ብሎ የለየለት አምባገነን ሆኖ ብቅ አለ።

ዛሬም ዶ/ር አብይ እየተጓዘበት ያለው መንገድም ተመሳሳይ ነው። አሻግራለሁ ሲል ቆይቶ፣ ሌላ መሪ ማን አለ እስከማስባልና ዛሬ ስልጣን ላይ ካልቆየን መታሰራችን ነው የሚል አቋም እስከማራመድ ድረስ ዘልቋል።

ምርጫውን መራዘም አለበት የሚል ዘመቻ የተከፈተው አምና ነበር። ከተራዘመ የቅቡልነት ጥያቄ ሊነሳ እንደሚችል ሲገለጽ፣ ነሓሴ እንደሚካሔድ ተገለጸ። ውሳኔው ምርጫው በግፊት የሚራዘምበትን ሰበብ ለመፍጠር ያለመ ይመስል ነበር። የኮቪድ ወረርሽኝ ሲከሰት፣ ጥሩ አጋጣሚ ሆነለትና ምርጫው እንዲራዘም ተደረገ። ምርጫው መራዘሙ ብቻ ሳይሆን፣ ያልተገደበ ስልጣን የሚሰጠው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አሳወጀ። አዲስ የአፈና መርበብ ተዘረጋ። ስልጣን ላይ በጉልበት ለመቆየት ርብርቡ ቀጥሏል።

ይህ በዙርያው ላሰባሰባቸው ኪራይ ሰብሳቢዎች ትልቅ ሲሳይ ነው። ከህዝብ ተነጥሎ በካድሬና በድርጅቱ ሰዎት መተማመን ከጀመረ፣ መዝረፍ የፈለገ አሁን እንደልቡ ይዘርፋል። እንደድሮ በግፍ ራሱን ማዝናናት የሚያስፈልግ ካለም አሁን ያን ማድረግ ይችላል። ምክንያቱም ሰውዬው ከህዝብ ተነጥሏል። የሚፈራው ነገር እንዳይደርስበት ካድሬዎቹን ሸክፎ መያዝ አለበት። ሲሰርቁና ግፍ ሲፈጽሙ እየቀጣ ካድሬን ሸክፎ ማቆየት ደግሞ አይቻለውም። ስለሆነም ነጻ ይለቃቸው፣ ከቁጥጥሩ ውጭ ናቸው።

ትላንት በኮረና ስም፣ ትንሽ ሰብሰብ ያሉ ሰዎችን ለመበተን ሲባል፣ ወጣቶችን ገደሉ። እንደገና ቤት አፍርሰው ደግሞ በርካቶችን ለበሽታው ማጋለጣቸው አልቀረም። ከእንግዲህ እንዲህ አይነት ዝብርቅርቁ የወጣን ነገር ማስታረቅም፣ ማረምም አይቻለውም ጋሽ አጃግሬ። ያለው አማራጭ በስልጣኑ እስካልመጡበት ድረስ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ማለፍ ነው።

አብይ ብዙ ጊዜ ስቷል። አንኳር ስ ህተቶቹ ግ ን ሁለት ናቸው። አንደኛ ተቋማትን መገንባትና ራሳቸውን ችለው እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ ሲገባው፣ እርሱን የሚያወድሱና በስልጣን ላይ ሊያቆዩት የሚሹ አጨብጫቢዎችን አፈራ። ሁለተኛ ስልጣን እየጣፈጠችው ስትሔድ ከህዝብ እየራቀ ሔደ፣ አምባገነናዊ ባህሪ እየተላበሰ ሔደ። አሁን መፍራት ጀመረ። ፍራቻው አገርን እንዳያሳጣን እፈራለሁ።

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *