, ,

ከአርቲስት ሀጫሉ ግድያ በስተጀርባ ….

… በሆነው ነገር ከማዘን በላይ ተበሳጭቼ፣ ምንም ላለማለት ወስኜ ነበር። ነገር ግን ዝምታዬም ያስወቅሰኝ ጀምሯል። ታድያ … የሚሰማኝን ልጻፍና …

በቅድሚያ አንድ ነገር ልበል። በዚህ እድሜው በሰው እጅ ቀርቶ በበሽታም መሞት የማይገባው ወጣት ነበር አርቲስት ሀጫሉ። በፖለቲካ አመለካከቱ ባንግባባም፣ የሚያወራው ባይጥመኝም፣ ምናምን የሚል ቅራቅንቦ አልደርትም። ምንም ይሁን ምን ግድያውን ፍጹም አወግዛለሁ!! ገዳዮቹና አስገዳዮቹ (ህግ አስከባሪ የለም እንጂ) ለህግ ቀርበው የእጃቸውን ማግኘት እንዳለባቸውም አምናለሁ። በዚህ አጋጣሚ በአርቲስት ሀጫሉ ሞት፣ በሀዘን ልባቸው ለተሰበረ በሙሉ (አስመሳዮች የአዞ እንባ የሚያነቡትን ሳይጨምር) መጽናናትን ከልብ እመኛለሁ። እንዲህውም ከግድያው ብኋላ በተፈጠረ ቀውስ ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች ሀዘኔ ጥልቅ ነው። ለቤተሰቦቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን እመኛለሁ።

እንግዲህ ከሀጫሉ ግድያ በስተጀርባ ማን ሊሆን እንደሚችል ብዙ መላምቶችን ከተለያዩ አቅጣጫዎች እየሰማን ነው። ሞቱን ተከትሎም ሁሉም በየአቅጣጫው ለፖለቲካ ፍጆታው እየተጠቀመበት ነው። ለፖለቲካ ፍጆታ እንደሚውልና አመጽ እንደሚያቀጣጥል የሚጠበቅ ነበር። ለጊዜው መንግስት ነኝ የሚለው የአብይ ቡድን፣ ገዳዮቹ እነማን እንሆኑ እያጣራን ነው ባለበት ቅጽበት፣ ህወሓት ነው፣ ግብጽ ነው፣ የግብጽ ተላላኪዎች ናቸው፣ የሚሉ የተለያዩ ግራ የገባቸው ውንጀላዎችን ሰንዝሯል። ህግ ይዞታል ከተባለ፣ ተጣርቶ ሳያልቅ እንዲህ አይነት ውንጀላ፣ መነሻውና ጥቅሙ ምንድን ነው? የዛሬ ሁለት አመት፣ የምርመራ ውጤቱ ከመታወቁ በፊት ህወሓት ነው ከዚህ በስተጀርባ ያለው ብሎ የከሰሰው መሪ፣ ውጤቱ ሲታወቅ እስከዚች ደቂቃ ድረስ ይፋ እንዳላደረገ ይታወቃል። የዛሬ አመት ለተፈጠረው ግድያ በተመሳሳይ መልኩ ከምርመራው በፊት ጣቱን ሌሎች ላይ ቢቀስርም፣ የሆነው ግን ሌላ ሆኖ የተገኘው። ውጤቱም እስከአሁኗ ደቂቃ ድረስ ለህዝብ አልተነገረም። በመካከላቸው ለተፈጠረው አለመግባባት ተጨማሪ ቤንዚን ሆነ አገለገለ ይበልጥ መካረር ውስጥ ከተታቸው እንጂ የፈየደው ነገር አልነበረም። ዛሬም ምርመራ ከመካሔዱ በፊት ውንጀላው አንድ ቡድን ላይ (ህወሓት ላይ) አድርጎ እያደነ የሚያስረው ደግሞ ሌላ ቡድንን (የእነ ጀዋር) ነው። ህወሓት/ግብጽ ከሆነ ሀጫሉን የገደለው ኦሮሚያ ላይ የብልጽግና ውጋት የሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶችን የሚመሩ የፖለቲካ መሪዎችና ጋዜጠኞች ለምን እየታድኑ ታሰሩ?

ተጣርቶ እስኪታወቅ ድረስ መላምት መደረት የሚቻል ከሆነ፣ ከአጫሉ ግድያ በስተጀርባ ህወሓት፣ የኦሮሞ ብሔርተኞቹ፣ የግብጽ ተላላኪዎች ሊኖሩ ከቻሉ፣ አብይ ራሱ ሊኖር የማይችልበት ምክንያት ምንድን ነው? እስኪ በዝርዝር እንመልከተው። በአባይ ግድብ ዙሪያ በተደጋጋሚ እንዳየነው እርሱ የተካፈለበት ድርድር፣ የአገርን ሉአላዊነት አሳልፎ የሚሰጥ ነበር። በመጀመሪያ አሜሪካና የዓለም ባንክ አደራዳሪ እንዲሆኑ የተስማማው አብይ ነው። ሲቀጥል በሁለት ሳምንት ውስጥ ስምምነት ላይ መደረስ አለበት፣ ስምምነት ላይ ከመድረሳችን በፊት ግድቡን መሙላት አንጀምር ብሎ ግብጽን ያስፈነጠዘ ስምምነት የፈጸመው አብይ ነው። አጫሉ በተገደለበት እለት ደግሞ፣ ግድቡን የመሙላት ሂደት የመብት ጉዳይ ሳይሆን፣ የጦርነት ጉዳይ ይመስል፣ የጸጥታው ምክር ቤት አጀንዳ እንዲሆን ያደረገው አብይ ነው። እዛ ደግሞ ምን አይነት ስምምነት አድርጎ እንደመጣ አናውቅም። ምናልባትም ከዛ አጀንዳ ለማስቅየስ የተደረገ፣ ብሎም አገርን በማበጣበጥ፣ ግድቡን የመሙላት ሂደት ለማዘግየት የተቀነባበረ ሴራም ሊሆን ይችላል። በነገራችን ላይ በነዚህ ጉዳዮች ጀዋር ሲያራምድ የነበረው አቋም፣ እንደ አንድ ፖለቲከኛ ሳይሆን እንደ አንድ አገር መሪ ነበር። እንዲያውም መጨረሻ ላይ፣ በዲፕሎማሲው ረገድ ደህና ድል እያገኘን የነበረውን ሁኔታ የቀለበሰው፣ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ስራውን እንዳይሰራ ስለተደረገ ነው፣ የሚል ስሞታ አሰምቷል። አብይን በአገር ጉዳይ የማያምነው መሆኑ፣ ልክ ብዙዎቻችን የታዘብነውን አይነት ክህደቶችን የታዘበ መሆኑን የሚያሳይ ፍንጭ ጽፎ ነበር። በእርግጥ ግብጽን አልጎዳም ብሎ በማያውቀው ቋንቋ ደጋግሞ የማለውና የተገዘተው ማን እንደሆነ ሁሉም ያውቃል።

ይህን ግድያ አብይ ከግብጽ ጋር ያለውን ጉዳይ ለማለዘብ ብቻ ሳይሆን፣ ተቀናቃኞቹን ለመስበርም እየተጠቀመበት ያለ ይመስለኛል። ከላይ እንዳልኩት ኦሮሚያ ላይ፣ ሰማይ ምድሩ ቢገለበጥ፣ በነጻ ምርጫ ሊያሸንፋቸው የማይችሉ ተቀናቃኞቹ ለማሰር ተጠቀሞበታል። የኦሮሞ ተቀናቃኞቹን ከሰበረ ብኋላ በሙሉ ጉልበት ፊቱን ወደ ህወሓት ማዞር ነው ስሌቱ። ያው የጅል ስሌት ነው። ፊቱን ወደ ሰሜን ከማዞሩ በፊት፣ ኦሮሚያ ላይ በማሰው ጉድጓድ ራሱን ያገኘዋል። የት ድረስ እንደሚያዛልቀው እንኳን በደንብ ያሰላው አይመስልም። ለእርሱ ታማኝ የሆኑ አንድ ሁለት ቀበሌ ማተራመስ የሚችሉ ልዩ ሃይሎች ቢኖሩትም፣ የሚያስመካና ልትተማመንበት የምትችል ጉልበት ያላቸው አይደሉም። ሁሉም የተነሳባቸው እለት ድራሻቸው አይገኝም።
ከዚህ ሁሉ ግን፣ ከተቀናቃኞቹ ጋር ያለውን ችግር በድርድርና በውይይት ቀድሞ ፈትቶ ወይም ለመፍታት ሞክሮ ቢሆን ኖሮ ይህ ሁኔታ ሊፈጠር ይችል ነበር? አይመስለኝም። ምክንያቱም እርሱም ሆኑ ሌሎቹ ችግራቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ፣ በሰለጠነ መንገድ ከፈቱ የዚህ አይነት ሴራ ውስጥ መግባት አያስፈልጋቸውም ነበር። ለዚህ እነ ጀዋርም፣ ህወሓትም ሌሎችም ዝግጁ መሆናቸውን በተደጋጋሚ በግልጽ ሲናገሩ ሰምተናል። ለጥሪው ጆሯቸውን የቆለፉበት አብይና የአብይ ድርጅት ብቻ ናቸው። ይህን ባለማድረጉ ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል በሴራ ፖለቲካ ያለ እድሜው መሞት የማይገባው ወጣት እንዲሞት ሆነ። በዛ የተነሳም ሌሎች በርካታ ንጹሃን ዜጎች እንዲሞቱ፣ እንዲቆስሉ፣ አገሪቱ ሌላ ቀውስ እንድታስተናግድ (እግዜር ይሁናትና!) ምክንያት ሆነ። ታድያ ማነው ለዚህ ተጠያቂው? ማን ነበር ይህን ማስቀረት ይችል የነበረው? በማን ውሳኔና እጅ ነበር?

አብይ፣ ሰልፊሽና የስልጣን ጥመኛ በመሆኑ ብቻ፣ አገሪቱን ከማቀራረብ ይልቅ፣ የባሰ ጽንፍ ነው ያስያዛት። ህወሓትን ሲታገሉ መቀራረብ ጀመረው የነበሩትን፣ ያራራቃቸውና ጽንፍ ያስያዛቸው የአብይ መንግስት ነው። ይህንን ቀዳዳ ተጠቅመው የውጭ ሃይሎች አገራችን ውስጥ ሴራ ቢሞክሩ እንኳን አይፈረድባቸውም። የሚያራርቅ እንጂ የሚያቀራርብ መሪና አሰራር እንደሌለን ይታወቃል። በድጋሚ ላንሳውና በድርድር ልዩነቱን ቀርፎ ቢሆን ኖሮ፣ የውጭ ሃይል አገራችንን የማተራመስ እድል ይኖረዋል? ግብጽ ብትሞክር እንኳን፣ መግባባት ካለ፣ በጋራ ያከሽፉት ነበር። ታዋቂ ሰው/ፖለቲከኛ ገድለው አመጽ ለመቀስቀስ ቢሞክሩ፣ ታዋቂ ሰዎች (ተፎካካሪዎች) በጋራ ቆመው፣ ተሰሚነታቸውን ተጠቅመው፣ ህዝባቸውን ያረጋጉ ነበር። አሁን ባለበት ሁኔታ ግን ይህ የሚቻል አልሆነም። ምክንያቱም ሁሉንም ነገር በራሱ መንገድ ብቻ ከማስተናገድ ውጭ ሌላ ነገር ስለማያውቅ።

ሲጠቃለል ከሀጫሉ ግድያ በስተጀርባ ያለው ሀይል ማንም ይሁን ማን፣ የመንግስት ተጠያቂነት ጎልቶ ይታየኛል። ገዳዮ ምንም ፖለቲካል ሞቲቭ የሌለው አንድ ተራ ሰው (ለምሳሌ የምኒሊክ አምላኪ) ሆኖ ቢገኝ እንኳን፣ አገሪቱን እዚህ ቀውስ ውስጥ የከተተው (ምናልባትም የከፋ ቀውስ ውስጥም ሊከታት የሚችለው) ማን በፈጠረው ችግር ምክንያት እንደሆነ ለሁላችንም ግልጽ ነው። ደጋግመን ድርድር፣ ውይይት፣ ድርድር፣ ስንል የነበረው ለዚህ ነው። አሁንም አገሪቱ ከዚህ ውጭ ሌላ መውጫ ቀዳዳ የላትም።

በመጨረሻ አንድ አቋሜን ግልጽ ላድርግ፣ ከሀጫሉ ግድያ በስተጀርባ የነጀዋር እጅ አለበት ብዬ የማላምነውን ያህል፣ የተደራጀ የአማራ ፖለቲከኞች ቡድንም ይኖራል ብዬ አላምንም። እነ ጀዋር አመጽ መቀስቀስ ከፈለጉ፣ ሀጫሉን መግደል አያስፈልጋቸውም። የአመንስቲ ሪፖርት የፈጠረውን አጋጣሚ ተጠቅመው ማቀጣጠል ይችሉ ነበር። ሀጫሉ ካስፈለጋቸውም አብሯቸው እንዲያቀጣጥል ማድረግ ይችሉ ነበር። እንዲህውም ነፍጠኛ የምትሏቸው የተደራጁ የአማራ ብሔርተኞችም ከዚህ ጀርባ አይኖሩም፣ ምክንያቱም የምኒሊክ ስም ከመጥፋት በላይ (ያውም ያልተለመደ አይደለም) የሚያሳስብ ዘርፈ ብዙ ችግር አለ። ለማይረባ ነገር ያን የመሰለ አርቲስት ገድሎ፣ የባሰ ጥፋትና ኪሳራ እንጂ ጥቅም እንደማይገኝ አያውቁም ለማለት አልደፍርም።

 

ሰ.ነ.

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *