ሶስቱ የጥፋት ፈረሶችና የኢትዮጵያ ፍጻሜ!

ከዚህ ጦርነት ብኋላ፣ መደምደሚያው ምንም ይሁን፣ ኢትዮጵያ እንደ አገር የመቀጠል እድሏ ዜሮ ሆኗል። አክትሞላታል። ህወሓት ጦርነቱን ቢያሽንፍ እንኳን ተመልሶ አገር በማስተዳደር ረገድ ከእንግዲህ ድርሻ ይኖረዋል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። ህዝቡም ህወሓትም ያንን እድል/ሁኔታ ዳግም የሚፈልጉት አይመስለኝም። ባንዳዎቹና ግልገሎቹ ከቀናቸውም ኢትዮጵያን ማስቀጠል አይችሉም። ዝርዝሩን አቀርባለሁ።

የኦሮሚያ ብልጽግና፣ የአማራ ብልጽግናና የሻዕቢያ አላቻ ጋብቻ በልጅነቴ እየሰማሁት ያደግሁት የዘንዶ ታሪክ ያስታውሰኛል። እነዚህ ሶስቱ ሀይሎች በተናጠል ከህወሓት አንጻር ሲታዩ ቁጫጭ ናቸው። በጋራ ካልሆነ በተናጠል ህወሓትን መሞከር ቀርቶ ማሰብ የማይታሰብ ነው። ጋብቻቸው ስትራቴጂካል ነው፤ በቅድሚያ በጋራ ተረባርበው ይጥሉታል፣ አንደኛው ለስልጣኑ፣ ሁለተኛው ለመሬቱ ሶስተኛው ለበቀል። ሶስቱም ግን ሌላ የሚያመሳስላቸው አንድ ወሳኝ ባህሪ አለ። ሶስቱም ኤክስፓንሺንስት/ተስፋፊ ና ኦፖርቹኒስቲክ ናቸው። በለስ ቀንቷቸው ህወሓትን ካስወገዱ ወይም ያስወገዱ ከመሰላቸው፣ በማግስቱ ሌላ የመስፋፋትና እርስ በእርስ የመዋዋጥ ጌም ይጀምራሉ፥

1 የኦሮሚያው ብልጽግና ሁለቱን የሚፈልጋቸው ለሚቀጥሉት አስርት አመታት ስልጣን ላይ ለመቆየት መጠቀሚያ ለማድረግ ነው። ካልጠቀለላቸው ይህን ማሳካት አልችልም ብሎ ነው የሚያስበው። ከእርሱ ፈቃድ ውጪ መግባትና መውጣት የማይችሉ፣ ወዶና ፈቅዶ ብቻ ስልጣን የሚሸነሽናቸው አሻንጉሊቶች መሆን የግድ አለባቸው። አለበለዚያ የቀድሞ ጓዶቻቸውን ጉድጓድ ይጋራሉ። በሀሳብ ደረጃ፣ ሶማሊያን፣ ጅቡቲ፣ ኤርትራን፣ ሱዳንን ጠቅልለን በምስራቅ አፍሪካ ታላቅ “አገር” በገዳ አምሳል እንመሰርታለን የሚል ጽንፍ የረገጠ ተስፋፊ አጀንዳ ይዞ የተነሳ ቡድን መሆኑ አይዘነጋም።

2 የአማራ ብልጽግና የመሬት ይገባኛል ጥያቄ በወልቃይትና በራያ አይመለስም። በሰሜን በኩል አሰብን ይጠይቃል። ዳር ድንበሬ ቀይ ባህር ድረስ ነው ይላል። ከኦሮሚያም ሰፋፊ የሚጠይቃቸው ግዛቶችና ከተሞች አሉት። በድሮዋ የኢትዮጵያ ካርታ የሚታየው የአገሪቱ ክፍል በጠቅላላ የአማራ ግዛት ነው፤ የአማራ መሬት ነው ብሎ ያምናል። ጠንካራ ኢኮኖሚና ጠንካራ ሰራዊት በመገንባት ማእከሉን ዳግም መቆጣጠር ይፈልጋል። ወይም መቆጣጠር አለብኝ ብሎ ያስባል። ካለበለዚያ ህልውናው ሁሌም አደጋ ላይ እንደወደቀ ይሰማዋል። እየተሽሎከልለከና በሁለት ሶስት ፓርቲዎች እየተደራጀ ጡንቻውን ማፈርጠም ከህዝብ ያልተሰወረ ስልቱ ነው።

3 ኢሳያስ ህወሓት በተወገደ ማግስት ከኋላ ሆኜ እዘውራለሁ፣ ኢትዮጵያን በእጃዙር እገዛለሁ ብሎ ነው የሚያምነው። እየኮረኮመ የሚያሰራውን ከመጋረጃው ጀርባ በቡችላው አብይ አማካኝነት መሾም መቻል ይሆናል ነው ምኞቱ። ካልሆነ ከወዲ ዜናዊ ጋር የተጀመረው ጸብ በሲዝን ሁለት ይቀጥላል።

አስተዋላችሁ? በመካከላቸው እርስ በእርሳቸውም ሆነ፣ ከነሱ ውጪ ካለው ቡድን ጋር በእኩልነት መኖር የሚያስችል አጀንዳና የስነልቦና ቅድመዝግጁነት የላቸውም። ባህሪያቸው አንዱ ሌላኛውን ውጦ መዘንደድ ነው። ህወሓት በክልል ቆራርጦ ኢትዮጵያን ቢያሳንሳትም፣ በህግ አውቶኖሚውን ለክልሎች ሰጥቷል። ተጠቅመውበታል አልተጠቀሙበትም ሌላ ጉዳይ ሆኖ፣ ካልተመቻቸው እስከመገንጠል ድረስ ልዩ መብት የሚያጎናጽፍ ህገመንግስት ሰጥቷቸዋል። ትናንሽ ግን አውቶኖመስ የሆኑ የፖለቲካ ዩኒቶች (ክልሎችና ልዩ ዞኖች) በእኩልነትና በመፈቃቀድ የተመሰረተ አብሮነት ሲኖራቸው ብቻ አገር በጋራ ያስቀጥላሉ፤ ተብሎ ለ30 አመታት (ግማሹ የኢትዮጵያ ህዝብ የተመረተበት አመታት) ተሰርቶበታል። ኖረውበታልም።

ገሚሱ የኢትዮጵያ ህዝብ ከዚህ የአስተዳደር ሲስተም ውጪ ሌላ የሚያውቀው ነገር የለም። እንደ አይንአር በአንዴ ጠርገህ ልታጸዳውና ሊረሳ የሚችል ጉዳይ አይደለም። እናም በማዕከላዊ መንግስት ይሁንታና ፈቃድ የሚሾሙ የሙስጠፌ፣ የተመስገን ምናምን አይነት ታማኝነታቸው ለአንድ ግለሰብ የሆኑ መሪዎችና ለይስሙላ ብቻ የሚሰየሙ ምክር ቤት ይኖራችኋል፣ ቢባሉ ማናቸውም አሜን ብለው አይቀበሉትም። የቀመሷት ነገር አለች የምትጥም፣ የምትጣፍጥ። ማንነቴን፣ ባህሌን፣ ቋንቋዬን፣ እምነቴን፣ የሚሏት ነገር።

አንዱ ሌላኛውን ሰልቅጦ ለመዘንደድ ሲቧጨቁ፣ ሌላው ለማንነቱ ሲንተጋተግ፣ ሰላም፣ መረጋጋት፣ ልማት፣ አገር፣ ብሎ ነገር ፈጽሞ ያከትምለታል።
ድሕረ ህወሓት የምትኖረው ኢትዮጵያ የፈራረሰች ኢትዮጵያ ብቻ ናት። የታሪክ መጻህፍት ላይ ብቻ የምታገኟት። ፍጻሜዋ ያላማረ። በ21ኛው ክፍለዘመን በእርስ በእርስ ጦርነት እስከዘላለሙ ያሸለበች ኢትዮጵያ።

ይህ እንዳይመጣ ነበር፣ በድርድርና በውይይት አብሮ የሚያኗኑር መላ ፈልጉ፤ ካቃታችሁ ያለው የፌደራሊዝም ስርዓት ይቀጥል ወይስ በሌሎች አማራጮች (ጂኦግራፊ መሰረት ያደረገ ፌደራሊዝም፣ ፍጹም አሃዳዊ ወዘተ) እንተካው ብላችሁ ህዝቡን ጠይቃችሁ በሪፈረንደም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ያግኝ፤ ብለን ስንመክራችሁ የኖርነው። በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተና የብዙሃን ይሁንታ ያገኘ ስርዓት ከመመምስረት ውጪ ሌላ አምራጭ የላችሁም ስንላችሁ የኖርነው በምክንያት ነው። ኢትኒክ ፌደራሊዝም በጉልበት ተጭኖ ሙሉ ተቀባይነትን እንዳላገኘ ሁሉ፣ አሃዳዊ ስርዓት በጉልበት ተጭኖ ሙሉ ተቀባይነትን አያገኝም። ግማሹን የህበረተሰብ ክፍል ያገለለ ስርዓት ደግሞ መቼም ቢሆን አይጸናም። እናም ከወዲሁ እላለሁ …

ነፍስ ይማር!

ሰ.ነ

 

3 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *