ስደት – የስልጣን ማደላደያና የገንዘብ ምንጭ

ስደት ትላንት – ከጦርነትና ከርሀብ

በቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ወቅት፣ ከቀያቸው ተፈናቀለው በስደተኞች ካምፕ የተጠለሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በሚልዮኖች ይቆጠር ነበር። በዚህም ምክንያት በዓለማችን ከፍተኛ የስደተኞች ቁጥር ከነበራቸው አገራት መካከል ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነበረች። ያ ወቅት በሰሜን ያገሪቱ ክፍል በመሸጉ ሽምቅ ተዋጊዎችና በወታደራዊው የኢትዮጵያ መንግስት መካከል የማያቋርጥ ጦርነት ይካሄድ ስለነበረ፣ ከዚሁ የአገራችን ክፍል የጦርነቱ ሰለባ ላለመሆን ወደ አጎራባች አገሮች ይሰደድ የነበረው ዜጋ በሚልዮኖች የሚቆጠር ነበር። በጦርነቱ ላይ በተፈጥሮ የሚከሰት የድርቅና ተያይዞ የሚመጣው የርሀብ አደጋ ሲታከልበት፣ የስደተኛው ቁጥር በታሪክ ጣራ የነካበት ዘመን ነበር።

ስደት ዛሬ – ከአምባገነናዊ ስርዓት

በ1991 ዓም ወታደራዊው አገዛዝ በኢህአዴግ ስርዓት ሲተካ፣ ቀድሞ የተሰደደው ኢትዮጵያዊ ወደ አገሩ እየተመለሰ፣ የስደተኛው ቁጥር እየቀነሰ የነበረ ቢሆንም፣ የኢህአዴግ አምባገነንነት እየበረታ ሲሔድ የስደተኛው ቁጥር በአስገራሚ ሁኔታ እያሻቀበ መጥቷል። ቁጥሩ በጦርነቱ ጊዜ የነበረውን ያህል ባይደርስም፣ ሰላምና መረጋጋት አለ በሚባልበት ዘመን እየተከሰተ ያለ “ትሬንድ” መሆኑ በበርካቶች ዘንድ አነጋጋሪ ሆኗል። ዛሬ የሚሰደደው ህዝብ ከጦርነት ለማምለጥ ወይም በተፈጥሮ አደጋ ከቀዬው በመፈናቀሉ ምክንያት አይደለም። ዛሬ የሚሰደደው ህዝብ ከኢህአዴግ ዱላና እስራት ለማምለጥ ይመስላል።

ምስል 1 – ከኢትዮጵያ የተሰደደና በUN የስደተኞች ወኪል የተመዘገበ ኢትዮጵያዊ ብዛት


ስደተኛ ዛሬ – በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ወኪል እይታ

UN Refugees Agency የተሰበሰበ መረጃ እንደሚያሳየው [ምስል 1] ዛሬ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በየዓመቱ አገራቸውን ለቀው እየተሰደዱ የፖለቲካ ጥገኝነትን ጠይቀው በተለያዩ መጠለያ ካምፖች ስር ይገኛሉ። ይህ መረጃ በUN ተመዝግበው የRefugeee status ያላቸውን ብቻ የሚመለከት ሲሆን፣ በUN ያልተመዘገቡና በኤርትራዊ ስም የተመዘገቡ እንዲህውም በት/ት፣ በስራ፣ በጋብቻ ወይም በሌሎች መንገዶች አማካኝነት ወደ ውጭ የሚሰደደውን ዜጋ አይጨምርም። ከምስሉ መረዳት እንደሚቻለው በመቀነስ ላይ የነበረው የስደተኛ ብዛት በተለይ ከምርጫ 97 ዋዜማ ጀምሮ ቁጥሩ እያሻቀበ መሔዱን ያሳያል። አፈናውን የሚያንጸባርቅ ቁጥር ነው ማለት እንችላለን።

ስደተኛው የት ይገኛል?

በ1883 ኢትዮጵያዊ የተሰደደባቸው አገራት ቁጥር 13 ብቻ የነበረ ቢሆንም ዛሬ ከ90 አገራት በላይ በሚገኙ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ ኢትዮጵያውያን ይገኛሉ [ምስል 2] ። በርግጥ በዘመነ-ግሎባላይዜሽን የተከሰቱ ፈጣን የትራንስፖርት አቅርቦትና የመረጃ ልውውጥ ለዚህ ቁጥር መጨመር የራሳቸው የሆነ አስተዋጽኦ ቢኖራቸውም፣ ከሌሎች አገራት አንጻር ሲታይ ይህ ቁጥር የተጋነነ መሆኑ በኢትዮጵያ ያለውን አስከፊ ጭቆና በተወሰነ ደረጃ የሚንጸባርቅ ነው ማለት ይቻላል። እዚህ ላይ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ በስደተኛ ስም የሚወጣ ቢኖርም ቁጥሩ በትክክል የማይታወቅ መሆኑ መጥቀስ ያስፈልጋል።  ከላይ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰውም በኤርትራዊ ስም እጁን የሚሰጥ ኢትዮጵያዊ ቁጥሩ በትክክል ባይታወቅም ከፍተኛ እንደሆነ ይገመታልና ስሌቱን ያጣፋዋል ማለት እንችላለን።

ምስል 2 – ኢትዮጵያዊ የሚሰደድባቸውና እጁን የሚሰጥባቸው አገራት በየጊዜው እየጨመረ መሆኑን የሚያሳይ ምስል። በዓለማችን ከሚገኙ 200+ አገራት ውስጥ እስከ 2014 ድረስ በ94 አገራት የፖለቲካ ጥገኝነትን ጠይቆ ይኖራል።

ስደት – የውጭ ምንዛሪ ምንጭ?

በተለያየ መንገድ አገሩን ለቅቆ የወጣ ኢትዮጵያዊ በየዓመቱ ቀላል የማይባል ገንዘብ ወደ አገር ቤት ይልካል። ይህ ገንዘብ በውጭ ምንዛሪ እጥረት በተደጋጋሚ እጅና እግሩ ለሚጠፈረው የኢትዮጵያ መንግስት እጥረቱን የሚያስታግስበት ጥሩ አማራጭ ምንጭ ሆኖ ያገለግለዋል። የመንግስት አፈና ሲበረታ፣ የዜጎች አማራጭ ስደት ከሆነና ተሰዶ ገንዘብ ወደ አገርቤት ሲልክ የመንግስትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት የሚደጉም ከሆነ፣ መንግስት ስደትን አያበረታታም ማለት ይቻላል?  ምስል 3 እንደሚያሳየው ከ2005 እኤአ (ምርጫ 97) ወዲህ ከዳያስፖራ የሚላከው ገንዘብ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መጥቷል።

ምስል 3 – ከተባበሩት መንግስታት የመረጃ ክፍል እንደተገኘው ማስረጃ ከሆነ ከምርጫ 97 ወዲህ ከዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን ወደ አገር ቤት የተላከ ገንዘብ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ይገኛል። ይህ ጭማሪ አገዛዙን አልጠቀመም ማለት አይቻልም።

ስደት – የዳያስፖራ የልማት ድርሻ?

ከላይ የተመለከተው ምስል በህጋዊ መንገድ ከዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን የተላከ አጠቃላይ ገንዘብ ሲሆን ይህ መጠን በአገሪቱ አጠቃላይ የGDP መጠን ያለውን ድርሻ በመቶኛ ሲታይ ዳያስፖራው የማይናቅ የልማት አበርክቶ እያደረገ መሆኑን ያሳያል። በተለይ ከምርጫ 97 ወዲህ በጥቁር ገበያ የሚላከውን ሳይጨምር በአማካኝ የGDP 1.3% ድርሻን ይዟል።

ምስል 4 – ከምርጫ 97 ወዲህ ከዳያስፖራ የሚላከው ገንዘብ በአማካይ የGDP 1.3% ይገመታል።

ስደት – ገንዘብም ይሰደዳል

በኢህአዴግ የሚመራው አምባገነኑ የኢትዮጵያ መንግስት በሰብአዊ መብት አያያዝ ጉድለት በስፋት መተቸቱ የአደባባይ ሚስጥር ነው። ምናልባት ከዚህም በላይ የሚታወቅበት ችግር ቢኖር ስር የሰደደ የሙስና ባህሉ ነው። በኢህአዴግ መንግስት ዜጎችም የአገሪቱ ሀብትም እኩል ወደ ውጭ ይሰደዳሉ። ከአስከፊ ጭቆና የሸሸው ኢትዮጵያዊ በአገሩ ልማት የሚያደርገውን አስተዋጽኦ ካየን፣ በአሳዳጆቹ የሚደረገው ጸረ-ልማት የገንዘብ ኩብለላ ማየቱ ተገቢ ነው። ከስር የተመለከተው ምስል በ2015 Global Financial Integrity በተባለ ዓለም ዓቀፍ ተቋም ከተለቀቀ ሪፖርት በተገኘ መረጃ ላይ ተመስርቶ የተሰራ ነው። በዚህ መረጃ መሰረት ከ2004 እስከ 2013 25.8 ቢልዮን ዶላር ወደ ውጪ ኮብልሏል።ከጥቂት ቀና በፊት በዋሺንግተን ፖስት ቀርቦ የነበረ ጦማር ሌላ ምንጭ በመጥቀስ ከ2013 ወዲህ ያለውን ጨምሮ 30 ቢልዮን የሚገመት ሀብት ከኢትዮጵያ መኮብለሉን ተመልክቷል።

ምስል 5 – እኤአ ከ2004 እስከ 2013 ድረስ 25.8 ቢልዮን የአሜሪካን ዶላር በህገ ወጥ መንገድ ከኢትዮጵያ ወጥቷል።

መደምደሚያ

አምባገነን መንግስታት የስልጣን ጊዜያቸውን ለማራዘም ከሚጠቀሙባቸው በርካታ ስልቶች መካከል የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸውን ማሳደድ ነው። ከኢትዮጵያ ጦርነትን ወይም የተፈጥሮ አደጋን ሳይሆን የኢህአዴግ ስርዓትን በመሸሸ የፖለቲካ ጥገኝነት የሚጠይቀው ኢትዮጵያዊ ቁጥር እያሻቀበ መምጣቱን በዚህ ጦማር ተመልክተናል። ጥገኝነትን የሚጠይቅባቸው አገራት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱንም ተመልክተናል። በግማሽ የዓለማችን አገራት ኢትዮጵያዊያን የፖለቲካ ጥገኝነትን ጠይቀው እየኖሩ ይገኛሉ። ከፖለቲካ ጥገኝነት በተጨማሪ በተለያዩ መንገዶች በየዓመቱ ወደ ውጪ የሚወጣው ህዝብ ቁጥሩ በ200ና 500 ሺ መካከል ይገመታል። ይህ ስደተኛ ከተሰደደበት ሆኖ በአገሩ ልማት ላይ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ቢሆንም፣ አምባገነኑ መንግስት የአገሪቱን ሀብት ማስኮብለሉን ተያይዞታል። ከዚህ አዙሪት መውጣት የሚቻለው እንዴት ነው የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ይመስለኛል።

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *