የአክሱም ሙስሊሞች ጉዳይ

*****

በ1983 ሻዕቢያ አስመራን፥ ወያኔ አዲስ አበባን ከተቆጣጠሩ ከጥቂት ወራት ብኋላ፥ የተወለድንባትን የአስመራ ከተማን ተሰናብተን እናቴ ወደ ተወለደችባት ጥንታዊት ከተማ አክሱም ገባን። እንደገባን ያረፍነው አክስቶቼ ቤት ነበር። አክስቶቼ ተከራይተው ነበር የሚኖሩት። ሁሉም የተከራዩት አንድ ግቢ ውስጥ ነው። የግቢው ባለቤት በዕድሜ ጠና ያሉ ሙስሊም እናት ነበሩ። ሲበዛ ደግ ሰው ነበሩ። ለራሳቸው አንዲት ክፍል አስቀርተው፥ የቀረውን በሙሉ ለድሃ ነው ያከራዩት። ቤታቸው ለገበያው ቅርብ ከመሆኑ የተነሳ በብዙ ሰው ይፈለጋል። ሶስትና አራት እጥፍ ጨምረን እንክፈል ያስወጡልን ብለው ደላላ የሚልኩ ነጋዴዎች ነበሩ። መልሳቸው ሁሌም አላደርገውም ነበር። ቤት ሲወደድና ሌሎች አከራዮች ሲጨምሩ እሳቸው አይጨምሩም። ያ ብቻ አይደለም፥ ተከራዮቻቸው የቤት ኪራይ የሚከፍሉት ሲችሉ ነው። የዚህን ወር አምጡ ብለው ጭቅጭቅ ውስጥ አይገቡም። ባይኖራቸው ነው ብለው ዝም ነበር የሚሉት። እስከ ስድስት ወርና ከዛ በላይም ሊከማች ይችላል። በጣም ሲቸገሩ ብቻ ነበር አልፎ አልፎ የሚጠይቁት። እንዳይበዛባችሁ፥ ብኋላ እንዳትቸገሩ እያሉ በትህትና ነበር የሚጠይቁት። ታድያ ግቢው ውስጥ የሚኖር ተከራይ በሙሉ ከልጅ እስከ አዋቂ እንደ አያቱ በስስት ነበር የሚያያቸው። አክስቶቼና ልጆቻቸው ያለ እኚህ ደግ እናት ህይወት ከባድ ፈተና ነበር የምትሆንባቸው። ሁሉም በፍላጎታቸው ነበር መጨረሻ ላይ ግቢውን የለቀቁት። የራሳቸውን ቤት ሰርተው።

ይህ ምናልባት የተጋነነ ደግነት ሊመስል ይችላል። ግን አይደለም። በርግጥ በከተማዋ የሚኖሩ አብዛኛዎቹ ሙስሊሞች የሚታወቁት በእንደዚህ ዓይነት ደግነታቸው ነው። የተራበን ማብላት፥ የታረዘን ማልበስ፥ የተቸገረን መርዳት፥ ዋንኛ መገለጫቸው ነው። የረባ የብድር አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም ባልነበረበት ወቅትና አራጣ አበዳሪዎች በገነኑባት ከተማ፥ የአክሱም ሙስሊሞች ከተማዋን ከወለድ ነፃ በሆነ የብድር አገልግሎት ቀጥ አድርገው የያዙበት ጊዜ ነበር። ስራ ላይ ታታሪዎች ናቸው። ሰርተው ያሰራሉ። እርስ በእርስ መረዳዳትና መደጋገፍ  ዋና መገለጫቸው ነው። “የራስህን ቢዝነስ የምትከፍትበት መነሻ ገንዘብ ልስጥህ፥ ራስህን ስትችል ትመልስልኛለህ” ብሎ ያበረታታኝ የቅርብ ዘመዴ ሳይሆን፥ ትምህርት ቤት የማውቀው የአንድ ሙስሊም ጓደኛዬ ታላቅ ውንድም ነበር። ብዙዎች መነሻ ገንዘብ ከሙስሊም ወዳጆቻቸው ወስደው የራሳቸውን ቢዝነስ በመክፈት ህይወታቸውን እስከወዲያኛው ቀይረዋል። ህይወት በአክሱማውያን ይህን ትመስላለች።

ወደ ግቢው እንመለስና ሌላ ምሳሌ ልጨምር። እኝያ እናት ህዳር ፅዮን ሲደርስ ለበዓል ተከራዮቻቸውን ይረዳሉ። የሙስሊም በዓል ሲከበርም፥ ለብቻቸው አያከብሩም። ሁሉንም ሰብስበው ነበር የሚያከብሩት። ሙስሊሙም ክርስቲያኑም ለሚያከብረው በዓል የተለየ ቦታ ይሰጡ ነበር። ጎረቤቶቻቸውም ቢሆኑ እንዲሁ። እስላምና ክርስቲያን በአክሱም ከተማ በፍቅር ተቆላልፈው ለሺ ዓመታት በዚህ መልክ አብረው ኖረዋል። ያ መተሳሰብ ነበር። አሁንም አለ። ወደፊትም ይኖራል። የአክሱም ህዝብ እርስ በእርስ በመደጋገፍ እንጂ በመጠላለፍ አይደለም እዚህ የደረሰው። ወደፊትም ቢሆን ተሰናስሎ በአብሮነት መኖሩ የሚያጠያይቅ አይሆንም።

ታድያ በዚህ አብሮነታቸው ውስጥ የማይታለፉ የሚመስሉ ጥቃቅን ቀያይ መስመሮች ነበሩ። አንዳንዶቹ አሁንም ድረስ አሉ። ለምሳሌ አንዱ ሌላኛው ባርኮ ያረደውን እንስሳ (ስጋውን) አይበላም። አንዱ ከሌላኛው ጋር የፍቅር ግኑኝነት አይፈፅምም፥ ትዳርም አይመሰርትም (ከፈፀሙም በሁለቱ በኩል ከባድ ፈተና ይገጥማቸዋል)። ሙስሊሞች መስጊድ መገንባት አይችሉም። ሲሞቱ የሚቀበሩት ከከተማዋ ወጣ ብሎ የሚገኝ የመቃብር ስፍራ ነው። ወዘተ።

እነዚህ እንግዲህ አንዳቸውም የመፅሀፍ ቅዱስ ወይም የቁርዓን መሰረት የላቸውም። አንዱ ከሌላው ጣልቃ ገብነትና ቅየጣ፥ እምነቱን ጠብቆ ያቆየበት ባህላዊ ዘዴ ነው። (አይሁዶችም እንዲሁ፥ ከኦርቶዶክስና ከሙስሊም ራሳቸውን ለይተው ያቆዩበት ዘዴ አለ፥ ምናልባት ሌላ ጊዜ እንመለስበት ይሆናል። ማወቅ ለሚፈልግ ግን በሶስቱም የእምነት ተከታዮች የነበረውን ታሪካዊ ግኑኝነት የሚዳስስና የልዩነታቸውን ድንበር ያሰመሩበት ዘዴ በባለሙያ መነፅር የሚያስቃኝ መፅሀፍ እንዲያነብ ልጠቁም፥ The Hyena People ይሰኛል። መነበብ ያለበት መፅሀፍ ነው።)

እነዚህ ባህላዊ ዘዴዎችና ልማዳዊ አስተሳሰቦች የሰው ልጅ በትምህርት፥ በመረጃ ልውውጥ፥ ከቦታ ወደ ቦታ በመዘዋወር በሚያገኘው ተሞክሮ ንቃተ ህሊውና እየዳበረ ሲሔድ ሊስተካከሉ የሚችሉ ነገሮች ናቸው። ዘልዓለማዊ አይደሉም።  በዳበረ ንቃተ ህሊና በተጠየቅ እየተፈተኑ፥ አንድም እየተሞረዱ አሊያም እየተጣሉና በሌላ እየተተኩ መሄዳቸው የተፈጥሮ ግዴታ ነው። ምሳሌ ብንጠቅስ፥ በርካታ የአክሱም ክርስትያኖች፥ እዛ ሲኖሩ ሙስሊሞች  ባርከው የቆረሱትን ነገር በፍፁም አይቀምሱም። ወደ አውሮፓ ወይም አሜሪካ ሲመጡ ግን የሚያሳድዱት የሓላል ስጋን ነው። አዲሱ የኑሮ ዘይቤ ልማዳዊ አስተሳሰባቸውን እንዲጠይቁ አድርጎ የተሻለ ግንዛቤ እንዲፈጥሩ አስገድዷቸዋል፥ “ካልተባረከ ይልቅ የተባረከ ይሻላል” የሚለው ኃልዮት የተሻለና አሳማኝ ሆኖ አግኝተውታል። ይህ በጊዜ ሒደት በከተማዋ ውስጥም ሊዛመት የሚችል ነገር ነው። ለፍቅር ግኑኝነትም ሆነ ትዳር ለመመስረት፥ የእምነት ልዩነት እንቅፋት ሊሆን እንደማይችል በሒደት እየተገለጠልን የሚመጣ ጉዳይ ነው።

በብዙዎች ዘንድ እንደ ቁልፍ ችግር ተደርጎ የሚወሰደው መስጊድ የመገንባት ጉዳይም ቢሆን እንደዚሁ ወደፊት መፍትሔ የሚያገኝ ጉዳይ ነው። በከተማዋ ሙስሊሞች መኖራቸው አልቀረም፤ ያውም ቁጥራቸው ከመቼውም ጊዜ በላይ እያደገ መጥቷል። እዛ ሲኖሩ መስገዳቸው አልቀረም፤ ያውም ግላጭ ሜዳ ላይ። በዛ ላይ ከብዛታቸው አንፃር መተላለፊያ መንገዶች በስፋት እየተዘጉ ለአደጋ አጋላጭ የሆነ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው። ሰው ቢታመም፥ አምቡላንስ ፈጥኖ ለመድረስ የሚቸገርበት ሁኔታ፥ እሳት ቢነሳ እሳት አደጋ ቶሎ ለመድረስ የሚቸገርበት ሁኔታ፥ ወንጀል ቢፈፀም ፖሊስ በፍጥነት ለመድረስ የሚቸገርበት ሁኔታ፥ የሚፈጥር ልማዳዊ አካሄድ ፈፅሞ ሊቀጥል አይችልም። የሁለትም እምነት ተከታይ የሆኑ አባቶች እና ያገር ሽማግሌዎች መፍትሔ እንደሚያፈላልጉለት በፍፁም አልጠራጠርም። ነገር ግን ለዘመናት የኖረ ልማድ እንደመሆኑ መጠን በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሔ ላይገኝለት ይችላል። ወራትም ይፍጅ ዓመታት፥ ይህ ችግር አይሆንም።

ችግር የሚሆነው፥ በሃይማኖት ሽፋን የራሳቸውን የፖለቲካ አጀንዳ የሚያራመዱ የተለያዩ የውስጥና የውጪ ኃይሎች ጉዳዩን ከመጠን በላይ እያራገቡ ለዘመናት በፍቅር ተዋህዶ የኖረውን ህዝብ በዚህ ሰበብ ማፋጀት ከቻሉ ነው። በአገር ውስጥ የሚኖሩ ያገባናል ባይ የእስልምና እምነት ተከታዮች፥ በሰብአዊ መብት ተቆርቋሪነት ስም ጣልቃ እየገቡ ጉዳዩን ፖለቲሳይዝ ሲያደርጉት ብዙ ጊዜ እናያለን። በእንደዚህ ዓይነት ድርጊት ምክንያት መንግስት በእምነት ተቋማት ጣልቃ ቢገባ ይፈረድበታል? እምነት ሌላ ፖለቲካ ሌላ ከሆነ፥ እኛም የእምነትን ጉዳይን ፖለቲሳይዝ ከማድረግ መቆጠብ ይኖርብናል። በመሰረቱ የአክሱም ሙስሊሞች ጉዳይ፥ የከተማዋ ኗሪ ህዝብ ጉዳይ ነው። መፍትሔ የሚያገኘውም የሚያጣውም በሌላ በማንም ኃይል ሳይሆን፥ እዛው በሚኖር የሁለቱም እምነት ተከታይ ህዝብ ነው። ልዩነታቸውን አቻችለው ችግራቸውን የሚፈቱት እነርሱ እነርሱ ብቻ ናቸው። የሌላው አጫፋሪ ጣልቃ መግባት አያስፈልጋቸውም። እርስ በእርሱ ሲደጋገፍ የኖረ ህዝብ ደግሞ ችግሩን በሰከነ መንፈስ መፍታት አያቅተውም።

ለአንድ የአክሱም ሙስሊም አብሮት ከሚኖረው ክርስትያን ጎረቤቱና አብሮ አደጉ ይልቅ በአዲስ አበባ፥ ደሴ፥ ሀረር ወይም ባሌ የሚኖር ሙስሊም ቅርበት ሊኖረው ፈፅሞ አይችልም። አንድ የደሴ ወይም የባሌ ሙስሊም፥ መግቢያው ላይ ለጠቀስኳቸው እኝያ እናትና ልጆቻቸው ከኔና ከአክስቶቼ ልጆች በላይ ሊቆረቆርላቸው አይችልም። ከተማዋ በሙሉ የተገመደችው ደግሞ በዝህ ዓይነት ትስስር ነው።

በሰብአዊ መብት ተቆርቋሪነት ስም ሃይማኖታዊ ሽፋን የተላበሰ ጣልቃ ገብነትን የምናራምድሰዎች  ፖለቲካ እያራመድን መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል። ይህ ማለት ደግሞ ጉዳዩ በአክሱም ብቻ ተገድቦ የሚቀር ሳይሆን ወደ መላው አገራችን የሚዛመድ የሰደድ እሳት ሊቀሰቅስ እንደሚችል መረዳት አለብን ማለት ነው። የውጭ ኃይሎች በጉዳዩ ላይ ጣልቃ የሚገቡበት ዋንኛ ምክንያትም ይህንን ፖቴንሽያሉን ስለተረዱ ነው። እናም ልብ ያለው ልብ ይበል!!

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *