የመለስ ሌጋሲ በዘመነ ብልጽግና
የቀድሞ የኢፌድሪ ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ ጀምሮ ያልጨረሰው አንድ ጥናታዊ ጽሁፍ ነበረ። ወዳጁ አሌክስ ዴቫል ለመታሰቢያነት፣ ብሎም የመለስ መከራከሪያ ሀሳብ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብሎ በማሰብ፣ መለስ በሞተበት አመት በአንድ የኦክስፎርድ ጆርናል አሳተመለት። ጽሁፉ States and Markets: Neoliberal Limitations and the Case for a Developmental State ይሰኛል። በዚህ ጽሁፍ መለስ እንደመሪ የነበሩትን አቋሞች የሚያንጸባርቁና ለፒኤችዲ መመረቂያ ጀምሮት ከነበረው ድራፍት ጋር የሚመሳሰል ሀሳቦችን አቅርቧል። የጽሁፍ ዋነኛ ጭብጥ ነጻ ገበያ የታዳጊ አገራትን ችግር ስለማይፈታ መንግስት ያልተገደበ ጣልቃ ገብነት ሊኖረው ይገባል የሚል ነው። እግረመንገዱን ለልማታዊ መንግስት በቂ ነው ያለውን ኬዝ ለመፍጠር ሞክሯል።
ነጻ ገበያ በታዳጊ አገር ቀርቶ በበለጸጉት አገራትም ፍጹም እንዳልሆነና የተወሰነ ጣልቃ ገብነት አስፈላጊ ሊሆን እንደሚችል አብዛኞቹ አገራትም የሚቀበሉት እውነታ ነው። “የነጭ ካፒታሊዝም” ሻምፕዮን ናት የምትባለው አሜሪካን ጨምሮ። ነገር ግን የልዩነት ምንጭ የሆነው ዋነኛ ጥያቄ ጣልቃ ገብነቱ እስከየት ድረስ ይሁን የሚለው ነው። መለስ እንደሁኔታው የሚወሰን፣ ገደብ የለሽ መሆን አለበት ነበር የሚለው። ሌሎቹ ደግሞ በተቻለ መጠን ስቴቱ ሚኒማሊስት መሆን አለበት ይላሉ። መንግስት ገደብ የለሽ ጣልቃ ገብነት የማድረግ ስልጣን ከተሰጠው ለሙስናና ለአፈና ይዳርጋል። ተጠያቂነትም አይኖረውም ብለው ይከራከራሉ። ይህም በታሪክ በበርካታ አገራት በኢትዮጵያ ጨምሮ ታይቷል። መለስ ከዚህ ጋር ተያይዘው ለሚነሱ ጥያቄዎች በቂ መልስ መስጠት ነበረበት። ጥሩ ምላሽ ነው ብሎ ያሰበው የራሱንና የሌሎችን ጥቅም የሚያስጠብቅ አውራ ልማታዊ የፖለቲካ ፓርቲ ሊኖር ይገባል የሚል ነው። ይህ በግርድፉ ሲፈታ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት አስፈላጊ አይደለም እንደማለት ነው። (አገር ቤት የፈጠረውን ስርዓት በአካዳሚው አለም እውቅና እንዲያገኝ ጀስትፊኬሽን እያቀረበ ነበር የሚመስለው።)
ልማታዊ ፓርቲው የመላዕክት ስብስብ እንዳልሆነ መለስም ያምናል። በጽሁፉ ገልጾታልና። ይሁን እንጂ መንግስት ሙሰኛና ተጠያቂነት የጎደለው ሊሆን እንደሚችል ካመነ፣ ሙሰኛ የሆኑት ግዑዛን ተቋማቱ ሳይሆኑ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉት ሰዎች ናቸውና፣ የሰዎች ስብስብ የሆነው ልማታዊ ፓርቲስ የዚህ ችግር ሰለባ ላይሆን የሚችልበት ምክንያት ምንድን ነው? መለስ ማስረዳት ነበረበት። ለዚህ ክፍተት ምላሽ ይሆናል ብሎ የመረጠው ሀሳብ፣ የልማታዊ ድርጅት አባላት የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ የአገርና የህዝብን ጥቅም ማስጠበቅ እንዳለባቸው የሚያምኑ ናቸው፤ ይህም ከምልመላ ጀምሮ በየደረጃው እስከሚሰጣቸው ስልጠና ድረስ ብቁ በማድረግ ሀርቨስት የሚደረግ እሴት ነው ይላል። ከመስመር ሲወጡም በድርጅቱ ህግና ደንብ መሰረት የእርምት እርምጃ ከምቅጣት ጀምሮ እስከማሰርና ማባረር ድረስ የሚበለጽግ ባህል ነው ይላል። መለስንና የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለሚያውቅ ሰው፣ ይህ የመከራከሪያ ነጥቡ በፓርላማና በሚድያ ያደርጋቸው ከነበሩ ንግግሮቹ ጋር ስምም ሆኖ ያገኘዋል። ለነ አሌክስ ዴቫል ምኑ ብርቅ እንደሆነባቸው ግን ግራ ይገባል።
በተግባር በዚህ እሳቤ የተገነባው ድርጅት ማለትም ኢህአዴግ የሌቦች ጥርቅም ብቻ እንደነበረ አይተናል። መለስና ጓዶቹ በዘረጉት ስርዓት ውስጥ፣ አገሪቱ በብድርና በእርዳታ ካገኘችው 50 ቢልዮን ዶላር፣ ከ30 ቢልዮኑ በላይ አገሩን ጥሎ መኮብለሉን ሰምተናል። ኮንዶሚንዬሞች ሲተኑ፣ በ10ሺ ቶኖች የሚቆጠር ቡና (የድሃ ገበሬዎች ንብረት) ተነኑ ሲባሉ፣ ባሌስትራ በወርቅ ሲቀይር፣ ፍራሻቸው ስር ብር ቀብረው ሲያዙና ስኳር እንዳባለጋቸው ሲናዘዙ እየሰማንና እያየን ኖረናል። ሰሞኑን አንድ የድርጅቱ ሰው እንደገለጸው፣ ዱባይ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ኢንቨስት ከሚያደርጉ የውጭ አገራት መካከል ኢትዮጵያውያን 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ሰዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት የላቸውም። ያ ብቻ ሳይሆን ውጭ አገር ካለ ኢንቨስትመንታቸው የሚያገኙት ትርፍ ወደ አገር ቤት አይልኩም ገልጿል። ይህ የመለስ “የልማታዊ መንግስት” ስነሀሳብ ትሩፋት ነው።
ላልተገደበ ጣልቃ ገብነት መለስ ሌላም የመከራከሪያ ነጥብ ነበረው። ይኸውም የግል ሴክተሩ በገበያ ህግ ሊሰራ ከሚችለው በላይ መንግስት መስራት ይችላል የሚል ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን መንግስት የሚሰራው ለህብረተሰቡ የሚያስፈልገውን ነው ይላል። በሌላ አነጋገር የግል ባለሀብቱ ትርፍ ያለበት ዘርፍ ላይ ብቻ ስለሚያተኩር፣ በጣም ወሳኝ የሆኑ መሰረተ ልማቶች (እምብዛም ትርፍ የማያስገኙ) ወደጎን ይተዋቸዋል፣ መንግስት ግን ግዴታውም ስለሆነ ለልማት የሚያስፈልጉትን በቅደም ተከትል መስራት ይችላል ማለቱ ነው። ይሁን በጀ ባልነ። ሆኖም ሜቴክን አየነው። ሰባሰባት ቢልዮን ብር ድራሹን ሲያጠፋው። አውራጎዳናንም አየነው፣ አንድ ፕሮጀክት ላይ ለአስርት አመታት ላይ ሲተኛበትና በቻይና ሲራቆት። መብራት ሀይልንም አየነው። ቴሌንም አየነው። ከሙሰኝነት ባለፈ የፓርቲና የግለሰብ መሳሪያ ሆነው፣ ወሬ መጥለፍ በሚያስችላቸው አቅም ልክ መብራትና ኔትዎርክ ሲለቁ የኖሩ።
በኔ መረዳት ከዚህ ሁሉ ክሽፈት በስተጀርባ ያለው እንከን ስልጣን ወዳድነት ይመስለኛል። መለስ በዛ ጽሁፉ ውስጥ ለስሙ እንኳን አንዲትም ጊዜ checks and balances ስለሚባለው ኮንሴፕት አልተናገረም። ቃሉን ጭምር አልጠቀሰውም። ስንቱን ትዮሪና “ፓራዳይም” በአንድ አንቀጽ ድምጥማጡን ለማጥፋት እየሞከረ፣ ዴሞክራሲና የመንግስት ተጠያቂነት የቆሙበት ዋና ምሰሶ ለደቂቃም ትዝ አላለውም። ሙስና እንዳይኖር፣ ተጠያቂነት እንዲኖር፣ መልካም አስተዳደር እንዲኖር ሶስቱ መሰረታዊ የመንግስት መዋቅሮች መኖር አለባቸው፣ ቼክና ባላንሳቸውን እየጠበቁ የሚሔዱበትን ነጻነት (ኢንዲፐንደንስ) መጎናጸፍ አለባቸው። እነዛ መዋቅሮች እያንዳንዳቸው ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ግልጽነትና ተጠያቂነት በተሞላበት መንገድ ስራቸውን ይሰራሉ፣ ካልሰሩም ኢንዲፐንደንት በሆነው ተቀናቃኝ መዋቅርና የሲቪክ ማህበራት ይጠየቃሉ፣ ይወቀሳሉ፣ በህግም ይቀጣሉ።
ልብ ብለን ካስተዋልነው፣ በነጻገበያ የሚሰራው የአዳም ስሚዝ የInvisible hand ኮንሰፕት በነዚሁ በሶስቱ የመንግስት መዋቅሮች ላይም ይሰራል። ያ ነው መንግስት በሙስና እንዳይጠቃ፣ ተጠያቂነት እንዲኖረውና ኢፌክቲቭ እንዲሆን የሚረዳው። የፓርቲ ዲሲፕሊን፣ የፓርቲ ህገደንብ፣ ወይም ከራስ በላይ የሌሎችን ጥቅም የሚያስጠብቅ ጻዲቅ ካድሬ በመመልመል በምናምን አይደለም። ፓርቲውን የተቆጣጠረ ሀይል ሁሉንም ነገር መቆጣጠር የሚያስችል ቀዳዳ እንዳለው በተግባር መለስ ከዘረጋው ስርዓት አይተናል።
መለስ ከስልጣን ላለመውረድ ብቻ ሳይሆን፣ ስልጣን ላይ እስካለ ድረስ፣ ያልተገደበ ስልጣን ኤክሰርሳይስ ለማድረግ ጽኑ ፍላጎት ነበረው። ያ ተቀባይነት እንዲያገኝ በተለያዩ መንገዶች ሞክሯል። ጥናታዊ ጽሁፍ አሳትሞ ተቀባይነት ለማግኘት እስከመሞከር ድረስ ዘልቋል። በባለራዕይ ልማታዊ መሪዎች ካልሆነ በስተቀር ልማትና ብልጽግና በነጻ ገበያ እውን አይሆንም ሲል ሞገቷል። ሰዎች የሚበጃቸውን አያውቁም ኢራሽናል ናቸው ብሎ ተከራከሯል። ተቋማትን ከመገንባት፣ ግለሰቦችንና የግለሰቦችን ስብዕና መገንባት የተሻለ መሆኑን በቀጥታም በተዘዋዋሪም ሰብኳል። ለዚህም ነበረ በተጨባጭ ለእርሱ ታማኝ የሆኑ ሰዎችን ሰብስቦ ልማታዊ ድርጅትን የፈጠረው። ልማታዊ ካድሬዎችን ያፈራው። ልማታዊ ካድሬዎቹ ግን በእርሱ የስልጣን ዘመንም፣ ከእርሱ ብኋላም ሲዘርፉ ኖሩ። በገበያ ህግጋት ኪራይ ሰብሳቢ ይሆናሉ ብሎ የገፈተራቸው ባለሀብቶች፣ ማልያቸውን ቀይረው፣ ኢህአዴግነትን ከተጠመቁ ብኋላ ልማታዊ ባለሀብት ሆነው ኪራይ ለመሰብሰብ አልተቸገሩም። ሰርቶ ከመብላት ይልቅ ዘርፎ መብላት አስከብሯቸዋል። ኪራይ መሰብሰብ በልማታዊ መንግስት ስር እስከሆነ ድረስ የልማት ውጤት እንጂ vice አይደለም የሚል አዲስ ባህል ተፈጥሯል። ስር የሰደደ የድርጅቱ ዋና መገለጫ ባህል ሆኖ አሁንም በዘመነ ብልጽግና ተጠናክሮ ቀጥሏል።
…
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!