ሙስና ፣ ነጻ ገበያና ቼክ ኤንድ ባላንስ

መግቢያ

አገሪቱን ጥሎ የኮበለለ ገንዘብ ማስመለስ አንድ ነገር ነው፣ ሙስናን ግን በዚህ መልኩ መከላከል አይቻልም። የአገሪቱ ሀብት ከኮበለለ ብኋላ ሰዶ ማሳደድ፣ በብዙ መልኩ ውጤታማ ላይሆን ይችላል። አንደኛ የት እንደገባ የማይታወቅ ይኖራል። ሁለተኛ የት እንዳለ ቢታወቅ እንኳን ማስመለስ አይቻል ይሆናል። ይህ ደግሞ ገንዘቡን ከማጣት በላይ የዲፕሎማሲ ግኑኝነትን ሊያሻክር ይችላል። ሶስተኛ ማስመለስ ቢቻል እንኳን ወጪው ከፍተኛ ሊሆን ይችላል። የገንዘብ ብቻ ሳይሆን፣ የጊዜና ሌሎችም። ስለሆነም ሙስናን መዋጋት ውጤታማ የሚሆነው ምንጩን ማድረቅ ሲቻል ነው። እንዴት የሚለውን ከማየታችን በፊት፣ ሙስና ምንድን ነው፣ ጥቅምና ጉዳቱስ ምንድን ነው የሚለውን በአጭሩ እንቃኛለን።

ትርጉም

የኢህአዴግ መዝገበ ቃላት ሙስናን አሽሞንሙና ሲተረጉማት “የመንግስትን ስልጣንና ኔትዎርክን ተጠቅሞ አለአግባብ መበልጸግ ይለዋል”። ማሽሞንሞን የማያስፈልገው እንቅጭ ትርጉሙ ደግሞ ሌብነት ነው። አንድ ሙሰኛ፣ የመንግስት ስልጣን ሊኖርውም ላይኖርውም ይችላል፣ ኔትዎርክ ሊኖርውም ላይኖርውም ይችላል፣ ሊበለጽግም ላይበለጽግም ይችላል። ምንም ዓይነት ስልጣን ሳይኖረው፣ ኔትዎርክም ሳይኖረው፣ ለራሱ ሳይበለጽግ ሌሎች አለአግባብ እንዲበለጽጉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ሙሰኛ ሊኖር ይችላል። ምሳሌ የኮንትሮባንድ ዘብ ጠባቂ።

ጥቅምና ጉዳቱ

የቢሮክራሲ ማነቆዎችን ተሻግር ያሰቡትን ከማሳካት አንጻር ያለው ጥቅም

ሙስና ጉዳቱ እንደሚያመዝን ቢታመንም ጥቅምም አለው። ለምሳሌ የቢሮክራሲ ተዋርድ እጅግ ሲበዛ ባለጉዳዮችን ያጉላላል፣ ኢንቨስተሮችን ያሸሻል፣ ወዘተ። በዚህ ሰዓት የሚችሉና አዋጭ ሆኖ የሚያገኙት ለሚመለከተው ባለስልጣን ጉቦ ሰጥተው፣ የተወሰኑ የቢሮክራሲ ተዋረዶችን መዝለል ይችሉ ይሆናል። ወይም የመንግስት ሰራተኛው በትጋት ሰርቶ ቶሎ ጉዳያቸውን እንዲያስፈጽምላቸው ቦነስ ሊሰጡት ይችላሉ። እነዚህ ጉዳዮች ቢሮክራሲው የፈጠራቸውን ማነቆዎች ቶሎ ተሻግረው ጉዳያቸውን ለማስፈጸም የተጠቀሙበት እንደመሆኑ መጠን፣ ኢንቨስተር ከሚሸሽ በዚህ መልኩ ማነቆውን ተሻግሮ ኢንቨስት ቢያደርግ ከጉዳቱ ይልቅ ጥቅሙ ያመዝናል። ከዚህ በመነሳት አንዳንድ ጊዜ ሙስና ቢሮክራሲ የሚፈጠርውን ማነቆ ለመሻገር የሚሰጥ ምክንያታዊ ምላሽ ነው ብለን መደምደም እንችላለን። አላስፈላጊ የቢሮክራሲ ውጣ ውረዶች በመቀነስ ሙስናን መቀነስ ይቻላል። ፈጣን አገልግሎት ለሚፈልጉ ደንበኞች፣ ተጨማሪ ክፍያ ከፍለው አገልግሎታቸውን የሚያገኙበት አሰራር መፍጠር። ከዚህ ተጨማሪ ገቢ የመንግስት ሰራተኛውን መደጎም ወይም የተለያዩ ማበረታቻዎችን መስጠት፣ ሙስናን ለመዋጋት ብቻ ሳይሆን ተገልጋዩ የሚረካበትን አስተማማኝ አገልግሎት ለመስጠት ይረዳል።

ከልማት አንጻር ያለው ጥቅም

ሌላኛው ጥቅም ከልማት ጋር የተያያዘ ነው። በተለያየ መንገድ በሙስና የተገኘ ገንዘብ አገሪቱ ውስጥ ኢንቨስት ከተደረገ፣ ምርት ከመፍጠር አንጻርም ሆነ የስራ እድል ከመፍጠር አንጻር አስተዋጽኦ ይኖረዋል። ለምሳሌ ከእያንዳንዱ ተረጂ አንድ አንድ ኪሎ ወይም ብር ቀንሶ፣ ወደ ቁጠባ አካውንቱ የሚያስገባ የገጠር ሊቀመንበር፣ አጠራቅሞ የግል ወፍጮ ላይ ኢንቨስት ቢያደርግ፣ ከስነምግባር አኳያ ሌብነት ቢሆንም ከልማት አንጻር ጥቅም ይኖረዋል። አንዳንድ ብር አዋጡና የማህበር ወፍጮ እናስገባ ቢባል ምናልባት ላይሳካ የሚችል ፕሮጀክት ሊሆን ይችላል። በተመሳሳይ መንገድ ከህዝብ ሃብት መንትፈው፣ ፋብሪካ የሚያቋቁሙ፣ ከስነምግባር አንጻር ሌቦች ቢሆኑም፣ ከልማት አንጻር አስተዋጽኦቸው የላቀ ነው። የዚህ ዓይነት ሌብነት፣ በተለይ በድሃና በማደግ ላይ ባሉ አገራት ብዙ ጊዜ የሚስተዋል ሌብነት ነው። ነባራዊ ሁኔታዎችን አገናዝቦ የሚሰጥ ምክንያታዊ ምላሽ አድርገን ልንመለከተው እንችላለን። በአንድ በኩል በቂ መነሻ ካፒታል የላቸውም፣ የብድር አገልግሎት ደካማ ነው፣ ስራ የመፍጠርና ትርፍ የማጋበስ ተሰጥኦ አላቸው፣ ሪስክ የመውሰድ ድፍረታቸው ከፍተኛ ነው። በሌላ በኩል ሲሰርቁ የሚይያዙበት መንገድ ጠባብ ነው፣ ቢያዙ በጉቦ ሊገላገሉት የሚችሉበት እድል ከፍተኛ ነው፣ በጉቦ ባይገላገሉት የገንዘብና የእስራት ቅጣቱ ባይያዙ ሊያገኙ ከሚችሉት ትርፍ አንጻር ሲታይ ትንሽ ሊሆን ይችላል ወዘተ። በአጭሩ ትርፍና ኪሳራቸውን አስልተው ነው የሚሰርቁት። ሰርቀውም ኢንቨስት የሚያደርጉት። ኢንቨስት ከተደረገ ብኋላ ሊያወድሙብን ይችላሉ ብሎ የሚሰጋና ሪስክ መጋፈጥ የማይችል ፈሪ ሲሆን ደግሞ ገንዘቡን ወደ ውጭ ያሸሻል።

ሌሎች ምሳሌዎችንም መዘርዘር ይቻላል። ለጊዜው ይብቃንና የተወሰኑ ጉዳቶቹን እንመልከት።

ጉዳቱ

የሙስና ዋናው ችግር፣ ሶሻል ካፒታልህን የሚንድ፣ አመኔታ የሚባል ነገር የሚያሳጣ መሆኑ ነው። መተማመን ከሌለ ስንዝር መራመድ አይቻልም። ሙስናን ስንጀምረው የቢሮክራሲ ማነቆዎችን ለመሻገር፣ የእለት ችግሮችን(የገንዘብ እጥረት)ለመቅረፍ እያልን እንደቀልድ ቢሆንም የማታ ማታ የስነምግባር ለከት የሚያሳጣ፣ ክህደት ላይ የመነከርና ውሎችን የማፍረስ አባዜ የሚከተን መጥፎ በሽታ ነው ። በአንድ አገር አመኔታ/Trust የሚባል ሶሻል ካፒታል ከሌለ፣ ውሎችን መፈጸም፣ አብሮ መስራት፣ ኢንቨስት ማድረግ ወዘተ አስቸጋሪ ይሆናል። በዚህ ምክንያት ልማት የሚባል ነገር ፈጽሞ የማይታሰብ ይሆናል። ከታሰበም ለሙስና የሚመች ብቻ ይሆናል።

ሙስና ሰርቶ የሚበለጽገውን ሳይሆን ኪራይ የሚሰበስበውን ያበረታታልና ዜጎች አምራች ከሚሆኑ ይልቅ ኪራይ ሰብሳቢዎች እንዲሆኑ ያበረታታል። ዜጎች የፈጠራ ችሎታቸውን እንዳይጠቀሙ፣ ይልቁንም በኪራይ ሰብሳቢ ዘርፎች እንዲሰማሩ ይገፋፋል።

ሙስና ጤናማ ያልሆነ የሀብት ልዩነትን ይፈጥራል። በተለይ በብሔር በቋንቋና በእምነት የተሰባጠረ እንደኛ ዓይነት ማህበረሰብ ላይ ሲሆን አደጋው ልማት ማደናቀፍ ወይም የሀብት ልዩነትን ማስፋት ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ማህበረሰባዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ሊያስከትል የሚችል፣ ለግጭትም የሚዳርግ ነው።

የኢኮኖሚ ኪሳራው ከፍተኛ ነው። ለምሳሌ ለሌብነት ከሚመቹ ዘርፎች አንዱ የግንባታ ዘርፍ ነው። የኮንዶሚንዮም ህንጻዎች ተነው የሚጠፉበት፤ የስኳር ፋብሪካዎች ድራሻቸው የሚጠፉበት፤ ምድረወገብን ሁለቴ የሚዞር መንገድ ተሰራ የሚባልበት፤ ግድቦች፣ መንገዶችና ህንጻዎች በተሰሩ ማግስት የሚፈርሱበት አገር ላይ ስላለን ከማንም በላይ ይህን እናውቀዋለንና ተጨማሪ ማብራሪያ መስጠት የሚያስፈልግ አይመስለኝም።

መፍትሔው ምንድን ነው?

ራሱን የቻለ ረዥም ጽሁፍ የሚያስፈልገው ቢሆንም፣ ይህ ጽሁፍ እንዳይንዛዛ በኔ እይታ ሙስናን ከምንጩ ለማድረቅ መፍትሔ ነው የምላቸውን ሁለት ነጥቦች አሳጥሬ በማቅረብ ጽሁፌን ልቋጭ።
ሙስናን ከምንጩ ለማድረቅ መፍትሔው፦

1. የነጻ ገበያ ስርዓት በማራመድ ፉክክር ላይ የተመሰረተ አሰራር መዘርጋት

2. በመንግስት አወቃቀር ጠንካራ የቼክ ኤንድ ባላንስ አሰራር መዘርጋት ናቸው።

የነጻ ገበያ ስርዓት መዘርጋት ሲባል የመንግስት ሚና ለነጻ ገበያ አመቺ ሁኔታዎችን በመፍጠር የተገደብ ሆኖ ባብዛኛው ስርዓት በማስከባር፣ ውሎችን በማስፈጻም፣ ጸጥታ በማስጠባቅ፣ የምርቶች ስታንዳርዶችን በማውጣት ጥራት መቆጣጣር ወዘተ ላይ ያተኮረ ሆኖ የተቀረውን የልማት ዘርፍ ለግሉ ባለሀብት የሚተውበት አሰራር መፍጠር ማለት ነው። ለምሳሌ ኮንዶሚንዮም እየሰራ አደላለሁ ብሎ ሙስናን ከሚያስፋፋ፣ ብሎም አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ዜጋ ከሚፈጥር፣ ለግል ባለሀብቶች ቢተወው በተሻለ ጥራትና ፍጥነት የተጠናቀቁ ህንጻዎችን በቅናሽ ዋጋ ለደንበኛ ሊያቀርቡ ይችላሉ። የመንግስት ሚና ጥራቱን ከመቆጣጠር በተጨማሪ ከሚሰበስበው ግብር ለመነሻ የሚሆኑ የብድር አገልግሎቶችን መስጠት ሊሆን ይችላል። በተመሳሳይ ሁኔታ የአገር ውስጥ ባለሀብት ሊሳተፍባቸው በሚችሉ የኢኮኖሚ ዘርፎች፣ ለባለሀብቱ ቅድሚያ ትኩረት መስጠትና ድጋፍ ማድረግ ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ነው።

የቼክ ኤንድ ባላንስ አሰራር መዘርጋት፣ ታሳቢ የሚያደርገው የህግ የበላይነት ይኖራል፣ የመንግስት መዋቅሮች በህግ የተሰጣቸው የስራ ድርሻና ሃላፊነት አላቸው የሚል ነው። በአጭሩ በወረቀት ላይ የሰፈረው ህግ፣ ተግባራዊ ማድረግ ነው። ተግባራዊ በማድረግ፣ የመንግስት መዋቅሮች፣ ማንም ጣልቃ ሳይገባባቸው፣ ህገመንግስታዊ አሰራሩን ተከትለው ሀላፊነታቸው እንዲወጡ ማድረግ፣ ካልተወጡም በእርስ በእርስ ቁጥጥር አስፈላጊውን እርምጃ የሚወሰድባቸው አሰራር እውን ማድረግ ነው። ለሶስቱም የመንግስት አካላት እኩል ስልጣን ከተሰጠና ገለልተኛ ከሆኑ፣ ስልጣናቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ ይፎካከራሉ። ፉክክራቸው ሌላውን የመቆጣጠርና ራሳቸውን ህግ በሚፈቅደው አሰራር መግራት ይሆናል። ወዘተ። የተጭበረበረ ኮንትራት፣ ህገወጥ አገልግሎት መስጠት ወዘተ እርስ በእርስ የሚቆጣጠሩት ችግር ይሆናል። የተሻለ አገልግሎት በመስጠት ፉክክር ሊጠመዱ ይችላሉ፣ ይህም ማለት አላስፈላጊ የቢሮክራሲ ማነቆዎችን ማስወገድ፣ የተሻለ አሰራር በየዘርፋቸው መዘርጋት ወዘተ ይችላሉ ማለት ነው።

መደምደሚያ

ሙስናን ከስሩ ለመዋጋት እነዚህ ሁለቱ የመፍትሔ ሀሳቦች ወሳኝ ናቸው ብዬ አምናለሁ። እርግጥ ነው ሙስናን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት አይቻልም። ነገር ግን አሳሳቢ የሆነውን፣ የተጋነነውንና በተለይ ደግሞ በጋራ ህልውናችን ላይ አደጋ የሚደቅነውን የሙስና ዓይነት በዚህ አሰራር መቅረፍ እንደሚቻል አምናለሁ። መለስ ዜናዊ እጅግ በተሳሳተ እሳቤ ተነስቶ ነበር ሜቴክን ያቋቋመው። የግሉ ዘርፍ ኪራይ በመሰብሰብ እንጂ ምርታማነትን በሚያሳድግ (ቫልዩ አድ በሚያደርግ) ዘርፍ ስለማይሳተፍ መንግስት በከፍተኛ ሁኔታ ጣልቃ በመግባት ባለሀብቱን ተክቶ መስራት አለበት ከሚል ፍስፍናው ተነስቶ ነበር ሜቴክን ያቋቋመው። ይሁን እንጂ በአገሪቱ ታሪክ ፈጽሞ አቻ የማይገኝለት የአገር ሀብት ብክነትና ዘረፋ የተፈጸመውም በዚህ ተቋም ነበር። ተቋሙ ራሱ የፍልስፍናው አንቲ ቴሲስ መሆኑን በተግባር አሳይቷል። ጊዜው ከዚህ በፊት ያልሞከርነውን የምንሞክርበት መሆን አለበት።

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *