ክሪቶ፥ ፕላቶ እንደጻፈው

አንዳንዱ መጽሓፍ አመት ሔደህበትም አያልቅም። ካልታደልክ አንብበህ ስትጨርስ የጨበጥከው ፍሬነገር ስለመኖሩ ትጠራጠራለህ። አንዳንዱ ከትንሽነቱ የተነሳ ቡና እየጠጣህ ገና በረካ ሳይደርስ ላፍ ታደርገዋለህ። ማነሱ ሲገርምህ ቁምነገሩ ዘመን ተሻጋሪ ሆኖ ታገኘዋለህ። ይቺኛዋ ጥራዝ እንደዛ ናት። ሃያ ምናምን ገጽ ናት፣ ፕላቶ ሶቅራጠስ ከእስር ቤት ስለ መጥፋት ምን እንደሚያስብ ይተርካል። ጓደኛው ክሪቶ፣ ወዳጆቹን አማክሮ፣ ገንዘብ አሰባስቦ፣ እቅድ አውጥቶ፣ ሶቅራጠስን ና ወደ ፈለግከው አገር/ከተማ እናስመልጥሃለን ይለዋል። ሶቅራጠስ መሸሽ ለምን እንደሌለበት፣ ጓደኛውን ተገልብጦ ያሳምነዋል። በዛ ቃለ ምልልስ፣ ስለ አገር፣ ስርዓት እና ግብረገብነት፣ ስለ ሎጂክ እና የአቋም ጽናት ብዙ ነገር እንማራለን። አገር ብትበድልህ፣ መሪዎች ቢበድሉህ፣ ህዝብ ቢበድልህ፣ ምን ማድረግ እንዳለብህ ያስተምርሃል። ይቺን ጥራዝ የአንድ ትልቅ መጽሓፍ (The Last Days of Socrates) አካል ሆና በኢንግሊዝኛ ካነበብኳት ከ10 ዓመት በላይ ይሆናል። ወደ አማርኛ ስመልሳት የሰጠኝን ያክል እርካታ ግን አልሰጠችኝም ነበር። በብዙ ነገር ከተፈተንክ ብኋላ ተመልሰህ እንዲህ ዓይነት መጽሓፍ ስታነብ፣ መልካም ነው። ራስህን የማድመጥ እድል ይሰጥሃል። እልም ብዬ ጠፍቼ አይደል እንዴ የነበረው።
ለማንኛውም የመጽሓፍ ማንበቢያ መተግበሪያችን (ቤተመጽሓፍታችን) በትክክል እየሰራ እንደሆነ ለመሞከር ያህል፣ ይችኑ ድንቅዬ ጥራዝ በገበታችን እንድታነቡ ጋበዝኳችሁ። እንሆ ሊንኳን
ሰናይ ቅዳሜ!