ማስጠንቀቂያ! ‘የሶሻል ሚድያ’ አጠቃቀምዎን ቢያስቡበት ይሻላል ይላሉ የዘርፉ ባለሙያዎች

ቢቢሲ አማርኛ

ከዓለማችን ሕዝብ 40 በመቶ ያህሉ ማኅበራዊ ድር-አምባዎች ላይ ተተክሎ ይውላል። 3 ቢሊዮን ሕዝብ ማለት ነው።

አንድ ሰው በቀን ቢያንስ 2 ሰዓት ያህል ማኅበራዊ ድር-አምባዎችን እንደሚጠቀም ይነገራል፤ ‘ላይክ’ በማድረግ፣ በማጋራት እንዲሁም ‘ትዊት’ በማድረግ።

አንድ ጥናት እንደሚጠቁመው ‘ስናፕቻት’ የተሰኘው ድር-አምባ ላይ ብቻ ግማሽ ሚሊዮን ፎቶዎች በአንድ ደቂቃ ውስጥ ይሸከረከራሉ።

አጀብ! አይደል ታድያ? ነገሩ ይገደናል የሚሉ ሰዎች ግን አንድ ጥያቄ ያነሳሉ። ሕይወታችን ውስጥ እንዲህ ሰርፆ የገባው ‘ሶሻል ሚድያ’ በአዕምሮ እና አካላዊ ጤናችን ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ምን ያህል ነው? የሚል።

ዘመኑ የሶሻል ሚድያ ነው። ምንም ጥያቄ የለውም። ክፉ ደጉን መመዘን ደግሞ የእኛ ሥራ ነው። ጥናቶችም ብቅ ብቅ ማለታቸውን ቀጥለዋል። እንዲያውም በዚህ ዘመን የማይነጥፍ ሥራ ቢኖር የ’ሶሻል ሚድያ’ ትሩፋቶች ላይ ያተኮረ ጥናት መሆን አለበት።

እርግጥ ነው ‘ሶሻል ሚድያ’ ገና ወጣት ነው። ፌስቡክ እንኳ ወደመንደራችን ከገባ አስራዎቹ ቢሆነው ነው። ጥናቶቹ በብርቱ ያተኮሩትም ከፌስቡክ በሚገኝ መረጃ ነው።

ውጥረት

የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኝ አንድ መሥሪያ ቤት የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየው ‘ሶሻል ሚድያ’ ውጥረት ከማቃለል ይልቅ ጭራሽ ያባብሳል።

1800 ሰዎች የተሳተፉበት ይህ ጥናት ሴቶች ከወንዶች በላቀ ለውጥረት ተጋላጭ እንደሆኑ ይጠቁማል። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ፤ ጥናቱ ላይ የተሳተፉ ወንዶች ከሴቶች አነስ ባለ መልኩ ወደ ማኅበራዊ ድር-አምባዎች ብቅ ማለታቸው ነው።

አንድ የማንካካደው ነገር አለ፤ የበይነ መረብ ግንኙነት ያላቸው ስልኮች ሰዎች እርስ በርስ የሚያደርጉትን ጭውውት እየገደቡ መሆኑ።

‘ሙድ’

ይህ ጥናት የተወሰደው በአውሮጳውያኑ 2014 ነው። ”እስኪ ስልካችሁን ምዘዙ” ተባለ፤ “ግማሾቻችሁ ፌስቡካችሁን ከፍታችሁ ለ20 ደቂቃ ያህል አስሱ” የሚል ትዕዛዝ ተከተለ።

የተቀሩቱ ደግሞ ወደ ፌስቡክ ድርሽ እንዳይሉ፤ ነገር ግን ሌላ ነገር ማሰስ እንደሚችሉ ተነገራቸው።

ውጤቱ ይህንን ጠቆመ። ፌስቡክ የተጠቀሙት ሰዎች ፀባያቸው (ሙድ) ልውጥውጥ ይል ጀመር፤ ጊዜያቸውን እንዲሁ እንዳባከኑ እንደተሰማቸው አሳወቁ።

የጥናቱ አንኳር ነጥብ ፌስቡክ እና መሰል ማኅበራዊ ድር-አምባዎች ላይ የምናያቸው ዜናዎች ይጋቡብናል የሚል ነው። ፌስቡካችንን ከዘጋን በኋላ እንኳ፤ ያየነውን ዜና እያሰብን ላልተገባ ጭንቀት እንጋለጣለን ይላሉ የዘርፉ ሰዎች።

ሰዎች ደስታቸውን ሲያጋሩን ደስተኛ እንሆናለን፤ ሃዘንን የሚፈጥሩ ‘ፖስቶች’ ስናይ ደግሞ ሃዘን ይጋባብናል ነው ቀመሩ እንግዲህ።

ጭንቀት

ትኩረት ማጣት፣ መጨናነቅ፣ ድብርት. . . ከማኅበራዊ ድር-አምባ አጠቃቀማችን ጋር የሚያያዙ መሆናቸውን ደርሰንበታለን ይላሉ አጥኚዎች።

ፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ኢንስታግራም፣ ዋትስአፕ፣ ቴሌግራም. . . ብቻ ምኑ ቅጡ. . . እኒህን ማኅበራዊ ድር-አምባዎች አብዝተው የሚጠቀሙ ሰዎች ‘ወዮላቸው!’ ነው የሚለው የተገኘው የጥናት ውጤት።

ምክንያቱም እኒህ ሰዎች ጭራሹኑ ‘ሶሻል ሚድያ’ ከማይጠቀሙት ወይም በመጠኑ ከሚጠቀሙ ሰዎች በላቀ ከላይ ለተጠቀሱት የአዕምሮ ጤንነት ጠንቆች ተጋላጭ ናቸው።

እንቅልፍ

ድሮ ድሮ ‘በደጉ ዘመን’. . . (መቼም ድሮ ተብሎ ‘ደጉ ዘመን’ ካልታከለበት ለጆሮ አይጥምም በማለት እንጂ). . . ብቻ በቀደመው ጊዜ የሰው ልጅ በጊዜ ወደ መኝታው ያመራ ነበር። ለዚህ ደግሞ ትልቁ ምክንያት የመብራት ነገር ነው።

መብራት እንደልብ ባልነበረበት ዘመን የሰው ልጅ በጊዜ ወደ መኝታው ይሄድ ነበር፤ አሁን ግን ሰው ሰራሽ መብራቶች ከመብዛታቸው የተነሳ ቀንና ሌሊቱ ይዛባ ይዟል።

እስቲ ስንቶቻችን ነን ወደ መኝታችን ካቀናን በኋላ ትራሳችንን ተደግፈን ከፌስቡክ መንደር የተገኘ ወሬ የምንለቃቅም?

ሳይንቲስቶች ባደረጉት ጥናት መሠረት ‘ሶሻል ሚድያ’ እና እንቅልፍ ትልቅ ቁርኝት አላቸው። ይህ ግንኙነታቸው ታድያ ጤናማ አይመስልም፤ ማኅበራዊ ድር-አምባው እንቅልፍ አዛቢ ነውና።

የአጥኚዎቹ ምክር “እነ ፌስቡክና ኢንስታግራምን ተጠቀሙ ችግር የለም፤ ነገር ግን እባካችሁ በእንቅልፍ ሰዓት አይሁን” ነው።

ሱስ

የምን ሱስ አለብዎ? የመጠጥ? የዕፅ? ወይስ. . .? ምንም እንኳ ‘ሶሻል ሚድያ’ በይፋ ከሱስ ተራ ባይመደብም ሱስ አስያዥ እንደሆነ ይነገራል።

በእንግሊዝ አፍ ‘ዲስኦርደር’ ይባላል፤ መዛባት የሚለው የአማርኛ ፍቺ ሊገልፀው ይችላል። ሁለት አጥኚዎች በዚህ ዙሪያ የተሠሩ በርካቶች ጥናቶችን አዋህደው ከመረመሩ በኋላ የ’ሶሻል ሚድያ’ ሱስ የሀኪም ክትትል የሚሻ የአስተሳሰብ መዛባት ያመጣል ሲሉ ይደመድማሉ።

ከልክ ያለፈ የ’ሶሻል ሚዲያ’ አጠቃቀም ከሰዎች ጋር ያለንን ግንኙነት ያውካል፤ የትምህርት አቀባበላችንን ይበክላል፤ የእውነተኛውን ዓለም ፈተና በፅኑ እንዳንጋፈጥ ይጋርደናል ሲሉ ሳይንቲስቶቹ ይከራከራሉ።

በራስ መተማመን

ፌስቡክና ኢንስታግራም ላይ ከወገባቸው ቀጠን፤ ከመቀመጫቸው ደልደል ብለው የሚታዩ ሴቶች በወጣት ሴቶች ራስ መተማመን ላይ አሉታዊ አስተዋፅዖ እንሚያመጡ ተደጋግሞ ይነገራል።

ከ18-34 ዕድሜ ላይ የሚገኙ 1500 ወጣቶች የተሳተፉበት ጥናት ላይ እንደተመለከተው ታዳጊዎች ማኅበራዊ ድር-አምባ ላይ ከሚያይዋቸው ሰዎች ጋር ራሳቸውን አነፃፅረው የበታችነት ስሜት ይሰማቸዋል።

የፍቅር ግኑኝነት

“የፍቅር ጓደኛዎ ፌስቡክ ላይ ተቃራኒ ፆታ ጓደኛ ሲያደርጉ ምን ዓይነት ስሜት ይሰዋዎታል?” ከ17-24 ዕድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ወጣቶች የቀረበ ጥያቄ ነበር።

አብዛኛዎቹ ምላሻቸው ተመሳሳይ ነበር፤ ‘ምቾት አይሰጠንም’ የሚል። ቅናት ቢጤ ይወረናል፣ ወደ ጭቅጭቅ እናመራለን እና መሰል መልሶች የመመለሻ ቅፁ ላይ ሰፍረው ታይተዋል።

ስለ ቅናት ከተነሳ ደግሞ የፍቅር ግንኙነት ውስጥ ያሉ ብቻ ሳይሆኑ ላጤዎችም ራሳቸውን ‘ሶሻል ሚድያ’ ላይ ካሉ ‘ስኬታማ’ ሰዎች ጋር አነፃፅረው የሚሰማቸውን ስሜትም ይጠቀሳል።

ብቸኝነትም የሶሻል ሚድያ ሌላኛው አሉታዊ ጎን እንደሆነ መነገር ከጀመረም ሰንበትበት ብሏል።

ማኅበራዊ ሚድያን አብዝተው የሚበዘብዙ ሰዎች ከማኅበረሰቡ እንደተገለሉ ይሰማቸዋል ይላል 7 ሺህ ሰዎች የተሳተፉበት ሌላ ጥናት።

እናጠቃለው. . .

እርግጥ አብዛኛዎቹ ጥናቶች የተሠሩት አደጉ በሚባሉ ሀገራት ነው። ነገር ግን ሳይንቲስቶች መከራከሪያ ያስቀምጣሉ።

እኒህ የ’ሶሻል ሚድያ’ ትሩፋቶች ዓለም አቀፋዊ ናቸው። እያደጉ ባሉ ሀገራት አሁን ባይስተዋሉ እንኳ ትንሽ ቆይቶ መምጣታቸው አይቀርምና።

“ዋናው ቁም ነገር”. . . እንደ ሳይንቲስቶቹ ምክር. . . “ዋናው ቁም ነገር ማኅበራዊ ድር-አምባዎችን በአግባቡና በተመጠነ መልኩ መጠቀም ነው” አዎንታዊ ውጤታቸው የሚካድ አይደለምና።