ጄነራል አሳምነው ጽጌ በፌደራል መንግስት ላይ የተቃጣ መፈንቅለ መንግስት ለምን ማድረግ አይችልም?

ይሔ ለውጥ መጣ ከተባለ እለት አንስቶ ኦሮሚያ ክልል አንድም ቀን ሰላምና መረጋጋት ኖሮት አያውቅም። የተለያየ ኢንተረስት ግሩፖችን የሚወክሉ የክልሉ ፖለቲከኞች፣ እርስ በእርስ ሲሞሻለቁ ኖረዋል። በተለያዩ ብሔሮች ላይ ያነጣጠረ ጥቃትም በየጊዜው ፈጽመዋል።  ከሶማሌ፣ ከጌድዮ፣ ከቤንሻንጉል፣ ከሀረር፣ ከድሬዳዋ ኖሪዎች፣ ከጋሞ፣ ከጉራጌ፣ ከአማራ፣ ከትግሬ ወዘተ ጋር በተለያዩ ቦታዎች (በክልላቸውና ከክልላቸው ውጪ) ጦርነት ከፍተዋል። ከባሌ እስከ ቡራዩ፣ ከለገጣፎ እስከ አጣዬና ከሚሴ፣ ከቤተመንግስት እስከ መስቀል አደባባይ ድረስ አምሰዉታል። ኦነግ ግማሽ የኦሮሚያ ክልል በቁጥጥሩ ስር አስገብቶ ግብር እየሰበሰበ የሚንቀሳቀስ ዲፋክቶ መንግስት ሆኗል። በጠቅላይ ሚንስትሩ ላይ በተደጋጋሚ የግድያ ሙከራ አድርጓል። ከኦነግ ውጪ ያሉ ጽንፈኞች ወይም ሁለተኛ መንግስት ነን የሚሉ ውርጋጦች፣ በአዲስ አበባ የሚፈልጉትን ነገር ማስፈጸም፣ የማይፈልጉትን በተደጋጋሚ ማስቀረት ችለዋል። መከላከያውን፣ ደህንነቱን፣ ሚድያውን፣ ምኑን አዝዛለሁ የሚለው መንግስት፣ እነዚህን ሀይሎች ስርዓት ማስያዝ አልቻለም። ለመሞከርም አልደፈረም። በየቀኑ ባንክ ቢዘርፉ፣ ቢገድሉ፣ ቢደነፉ፣ የፌደራል መንግስት ምንም አይነት እርምጃ ወስዶ አያውቅም። አቅም አሳጥተዉታል። አቅም ከማሳጠትም በላይ አንዳንዶቹ እጁን ጠምዝዘው ጉዳያቸውን የሚያስፈጽሙ ሆነዋል። (ግባቸው አንድ ነው፣ አምነውበት ነው የሚፈጽሙት አለማለትም አይቻልም።) ይህን እውነታ ከእኔና ከእናንተ ባልተናነሰ ጄነራል አሳምነው ጽጌ አሳምሮ ይረዳል።

መከላከያንና ፖሊሲን አዛለሁ፣ የደህንነት ቢሮውን እመራለሁ የሚል “መንግስት” ፍጹም ስርዓት አልበኝነት የነገሰበትን ክልል ማረጋጋት ተስኖት አንድም ቀን ህግ የማስከበር እርምጃ ወስዶ በማያውቅበት ሁኔታ፣ ጥቂት የገበሬ ምልሻዎችን ብቻ የያዘ አንድ የሌላ ክልል የጸጥታ ሀላፊ እንዴት የፌደራል መንግስትን ለመፈንቀል ያስባል? በምን ጉልበቱ ህግና ስርዓት አስከብራለሁ ብሎ አስቦ? በራሳቸው ምልሻ የሚተዳደሩና ከፌደራል መንግስት ያፈነገጡ ጠርዝ ላይ ያሉ ክልሎችን (እንደ ኦሮሚያ፣ ትግራይና ሶማሌ የመሳሰሉትን) እንዴት እገዛለሁ ብሎ አስቦ ነው መፈንቅለ ፌደራል መንግስት የሚከጅለው? መፈንቅለ መንግስቱ ቢሳካልት እንኳን መንግስት በሆነ ማግስት፣ አገሪቱ በጠቅላላ ልትበታተን እንደምትችል አጥቶት ነው?  ኦሮሚያን በምን ጉልበቱ ማን ሊይዝለት? ይህን እብደት የሚጋራ ኦሮሞስ ከመነሻው ከየት/እንዴት አግኝቶ ነው? ትግራይንስ እንዴት ሊያደርገው ነው? ለመበታተን አንድ ሀሙስ የቀረውን አገር ጥቂት ምልሻ ብቻ ይዞ በህገወጥ መንገድ መጥቶ ምን እፈይዳለሁ ብሎ ይሆን ይህን እብደት ለማሰብ የሚዳዳው? እንደው ቢታሰብስ እነ ጄነራል ሰዓረን አሳምኖ ተባባሪ ማድረግ ይቀላል ወይስ ከኦሮሞ ጄነራሎችና መሪዎች በፊት እነሱን የግድያ ኢላማ ማድረግ? እነ ደብረጽዮን፣ ለማ፣ አብይና ዳውድን ሳይመታ አማራ ወንድሞቹን ቀድሞ መምታትስ መፈንቅለ መንግስት ከሚያስብ ጄነራል የሚጠበቅ ስልት ነው? ብዙ ተመሳሳይ ጥያቄዎችን ማንሳት እንችላለን። አንዳቸውም መንግስት እንደአዲስ የፈበረከውን ትርክት ደግፈው መቆም የሚችል መልስ አይኖራቸውም።

እነ ኦነግና ህወሓት ከ50 አመታት በላይ በውጭ የኢትዮጵያ ጠላቶች ተደግፈው በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አእምሮ የዘሩት የአማራ ጨቋኝነትና የበላይነት ትርክት፣ አማራ ባልሆነ በእያንዳንዱ ብሔር ተቀባይነት አኝይቶና እንደ እውነት ታይቶ ለአማራ የሚያሳዩት ጥላቻና ንቀት ባየለበት በዚህ ወቅት፣ ጄነራል አሳምነው የተሳካ መፈንቅለ መንግስት ቢያደርግስ የትኛው ህዝብ አሜን ብሎ መንግስትነቱን ይቀበልልኛል ብሎ አስቦ ነው፣ የመንግስት ግልበጣ ለማድረግ የሚከጅለው? ይህ ሰው እኮ ጠንካራ የአማራ ብሔርተኝነትን የሚያቀነቅን፣ ወያኔ ባጠረው የጂኦግራፊ ካርታ ተወስንነን አንኖርም፣ የሚል የጸና አቋም የነበረው ሰው ነው። እንደዚህ አይነት አቋሞቹ በሌላ ወገን ጠላትንና መደናበርን እንደሚፈጥሩ አያጣውም። ይህን አቋም መያዙን እያወቀ፣ የሌላ ብሔር ተወላጅ ከጎኑ ተሰልፎ መፈንቅለ መንግስት ለመሞከር አያዳዳውም። ጄነራሉ መፈንቅለ መንግስት ያስባል ቢባል እንኳን፣ ጠላቶቹ ብዙ መሆናቸውንና ጠንካራ ሀይል እንደሚያስፈልገው አያጣውም። ስንቁን የማይሸፍን እፍኝ የገበሬ ምልሻ ይዞ እንደዚህ አይነት ዘመቻ ሊያስበውም አይችልም። አንድ ተራ ሰው ይህን ማገናዘብና መጠየቅ ከቻልኩ፣ የካበተ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ልምድ ያለው ጄነራል ይህን አለማገናዘብና አለመጠየቅ ይችላል ብሎ ማሰብ ይከብዳል።

በፌደራል ደረጃ መፈንቅለ መንግስት ለመሞከር ቀርቶ ለመወጠን የሚያበቃ ሁኔታ አልነበረም። አገር ለማፍረስ ቆርጦ የሚነሳ ካልሆነ በስተቀር አሁንም የተመቸ ሁኔታ የለም።። ጄነራሉ ደግሞ የሚታወቀው “ኢትዮጵያን ለማፍረስ አማራ የመጀመሪያም የመጨረሻም መሆን የለበትም” በሚል ዘመን ተሻጋሪ ምክሩ ነው።

ለማጠቃለል

ጄነራል አሳምነው ጽጌ መፈንቅለ መንግስት ለማሰብ የሚያስደፍር ሁኔታ ላይ አልነበረም። ለመሞከርም  አይደፍርም። በቂና ጠንካራ ሀይል አልነበረውም። በጠንካራ የአማራ ብሔርተኝነት አቋሙ ምክንያት ከብሔሩ ውጭ ኔትዎርክ አልነበረውም። ከነበረውም በጣም የላላ ነው ሊሆን የሚችለው። ቋፍ ላይ ያለች አገር፣ ሁሉም ቦታ ላይ ውጥረት በሰፈነበት ሁኔታ፣ እንደነ አሜሪካ (የኸርማን ኮኽንን ብልግና ያስታውሷል) የመሳሰሉ በጸረ አማራ ትርክታቸው የሚታወቁ ሃያላን አገራት አገሪቱን እንደፈለጋቸው በሚያደርጉበት በዚህ ዘመን፣ ጄነራሉ ሊሞክረው ቀርቶ የተሳካ መፈንቅለ መንግስት ማድረግ ይቻላል ብሎ ሊያስብም አይችልም። ከወያኔና ኦነግ ጀምሮ እስከ ጎረቤት አገር ሻዕቢያና ሃያላን አገራት እነ አሜሪካ መፈናፈኛ አሳጥተው በአጭር ሊቀጩት እንደሚችሉ አያጣውም። ጄነራል አሳምነው ይህን ፈጽሞ አያደርገውም። አያስበውምም። እብድ አይደለም። እብድ ነው ቢባል እንኳ እብድን ተከትሎ መፈንቅለ መንግስት ለመሞከር የሚሰለፍ የአማራ ሀይል አይኖረም።

ቀደም ሲል በጄነራሉ ላይ ያቀረቡትን (የክልል መንግስት ላይ የተቃጣ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ) ክስ በወጉ ማስተባበል ሲያቅታቸው የፈበረኩት ያልተደረገ ብቻ ሳይሆን ሊሞከር የማይችል ክስ መሆኑ ግልጽ ነው። ክሱ/ትርክቱ ውሃ የማይቋጥር ሲሆን፣ ማንም የማይክደው አንድ የፖለቲካ ትርፍ ግን ለግዜው አስገኝቶላቸዋል። ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ተሞከሯል ባሉት ክስ፣ በገፍ ያሰሩት ሲቪሉን የአማራ ተወላጅ ነው። በአማራ ክልልና ከአማራ ክልል ውጭ በከፍተኛ ሁኔታ እየተጠናከረና ህዝባዊ ተቀባይነትን እያገኘ የመጣው፣ ለኦሮሞ የብሔር ፖለቲከኞች ትልቅ ስጋት የሆነውን አብንን ለማዳከም አባላቱን በገፍ አፍሰው አስረዋል። አማራን ያነሳሳሉ ብለው የሚያስቧቸውን ጋዜጠኞችና አክቲቪስቶች እየለቀሙ አስረዋል። ከ250 በላይ ሰዎች ማሰራቸውን ቢያውጁም፣ ምን ያህል ወታደር እንዳሰሩ ሊነግሩን አልደፈሩም። በአለማችን ታሪክ ሲቪል ብቻ ያሳተፈ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ተሞክሮብኛል የሚል መንግስት ቢኖር ይህ የኦሮሞ መንግስት ብቻ ነው። እንቁ መሪዎችን መግደላቸው ሳያንስ፣ ከሞት የተረፉት ላይ የሚፈጽሙት ግፍ አብሮ የሚያኗኑር አይደለም። ኢትዮጵያ ለሁሉም ካልሆነች ለማንም አትሆንም!

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *