ሃቅ ሃቁን ብቻ እናውራ ከተባለማ …
የፖለቲካ ወይም የኢኮኖሚ ፍልስፍና እይታቸውን ፈጽሞ የማልስማማበት፣ ነገር ግን በጣም የማደንቃቸው ባለ ከባድ ሚዛን አስተማሪዎቼ (ተጽእኖ ፈጣሪዎች) በምድር ላይ ሁለት ሰዎች አሉ/ነበሩ። መለስ ዜናዊ እና አያን ራንድ። የአትላስ ሽራግድ እና ዘ ፋውንቴን ሄድ ደራሲዋና ፈላስፋዋ ራንድ፣ በጆን ጋልት እና በሃዋርድ ሮርክ አማካኝነት የምታስተላልፋቸው፣ ፍጹም የማታወላዳበት የኦብጀክቲቪዝም ፍልስፍና ብላ የምትጠራው ግለሰባዊነትን እስከጥግ ድረስ ለጥጣ የምታወድስባቸው ስራዎቿ በብዙ የማልስማማባቸው (አንዳንዴ የምጸየፋቸው ጭምር) ቢሆንም፣ ብዙ የተማርኩባት እና የማደንቃት ጸሃፊ ናት። ስለ ራንድ በሌላ ጊዜ እንመለስበታለን። አሁን ስለ መለስ እናውራ።
ራሳችንን ካልዋሸን በስተቀር፣ መለስ በተለይ በኢኮኖሚክስ ትንተናው አንድን ትውልድ አነሳስቷል፣ ቀርጿል፣ ቢባል ማጋነን አይሆንም። በመለስ ዘመን ስለ ዴቨሎፕመንታል ኢኮኖሚክስ የማይደሰኩር ፖለቲከኛ፣ ምሁር፣ ተማሪ፣ ካድሬ ወዘተ አልነበረም ቢባል ማጋነን አይሆንም። ስለ ኢኮኖሚክ ፓራዳይም፣ ስለ ግሪን ኢኮኖሚ፣ ስለ ኒዮሊበራሊዝም፣ ስለ ኪራይ ሰብሳቢነት (ሬንት ሲከርስ) ወዘተ የማይወራበት፣ የማይተነተንበት እና የማይተችበት ቀን አልነበረም። በፖለቲካው ልንቃወመውና ልንጠላው እንችላለን (በዛም ረገድ ሻምፕዮን እንደነበር አሁን እየበራልን ቢሆንም)፣ በኢኮኖሚክስ እውቀቱ፣ የትንታኔ ብቃቱ፣ ከኢንግሊዝኛ ወደ አማርኛና ትግርኛ የመመለስ ብቃቱ ግን ማንም ሰው አይክደውም።
እስኪ እውነት እንናገር እና፣ ስለ ርዕዮተ አለም፣ ስለ ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ፣ ስለ ኢኮኖሚክ ፍልስፍና ከመለስ ዘመን ወዲህ በማህበራዊም በሉት በመንግስት ሚድያ ተወርቶ ያውቃል? ያ አጀንዳ፣ ያ ሙግት፣ ያ ትችት አልናፈቃችሁም? በነ ኮንፍዩዝድ እና ኮንቪንስ ዘመን፣ መደመር ከምትለው የ3ኛ ክፍል አርቲሜቲካ የዘለለ አንዲት ቃል ሳንሰማ አስር አመት ሊሞላን ደረሰ። በመለስ ዘመን ፎር ግራንትድ ወስደነው የነበረ ጸጥታ፣ የማዕከላዊ መንግስት ጥንካሬ፣ ወዘተ ከመለስ ወዲህ አፈርድሜ ግጦ፣ ወሬያችን እና ኑሯችን ሁሉ ስለ ጦርነት ብቻ አልሆነም? እንደ ዘመነ ደርግ፣ ብልጽግና እድሜዋን በጦርነት ፈጀችው። ቅቤው ኢንስፓየር ያደረገው ትውልድ ቢኖር እነ ምናምን ድሪምስ እንደሚባሉት አነቃቂ እና ሰባኪ ነን ባዮችን ብቻ ነው። (የበርትራንድ ራስል ፍልስፍና መጽሃፍ ካነበባችሁ፣ እንዲህ አይነት ሰዎች የሚበራከተቱ ከአንድ ማህበረሰብ ውድቀት እና ስብራት ብኋላ መሆኑን ትገነዘባላችሁ። ትኩረት ሁሉ ራስን ለማጽናናት፣ ቀኑን እንደምንም ለማሳለፍ ይሆናል። የስቶይሲዝም ፍልስፍናን በዚህ መልኩ ነው ሩስል የሚገልጸው። ግሪኮች በጦርነት ተሸንፈው አገራቸው እንክትክት ስትል እና በሌሎች ቁጥጥር ስር ስትወድቅ፣ ያ ሰማይ ምድሩን የቧጠጠው፣ ከአተም እስከ አጽናፈ አለም የቃኘው ፍልስፍናቸው ከስሞ በነ ኢፒኲሬስና ኢፒክቲቱስ የሃፒነስ ፍልስፍና ተተካ። አይንህን ጨፍነህ የልብ ትርታህን ካዳመጥክ፣ ጭንቀትህ ሁሉ ውልቅ ብሎ ሲሔድ ታያለህ። የደስታ ምንጭ ወደ ውስጥ መመልከት ነው። ወዘተ)
መለስ በአደባባይ ጭምር ደረቱን ነፍቶ እየተከራከረ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከኒዮሊበራላይዝም ታደገው። በየጊዜው የሚቀርብበትን ጫና ተቋቁሞ፣ ተከራክሮ፣ እነ ጆ ስቲግልቲዝ አስደምሞ፣ የኢኮኖሚ ሉኣላዊነቱን አስከብሮ አለፈ። (አገሪቱ በየጊዜው የምትቀበለውን ምጽዋት ወደጎን ብለን)። ዛሬ አንድም ሳይቀር ገበያው በሙሉ ተበርግዶ ላለው ሲሰጥ፣ አንዲትም ክርክር አልተደረገም፣ ወይ አመክንዮ አልቀረብም። እንደሾካካ የተባለቱን ፈጽመው ጭጭ አሉ። ሃሳብ የደረቀበት ስርዓት እና ዘመን ላይ ሆነህ እንደ ወ/ሮ ጊዜሽወርቅ ተሰማ በድፍረት ምስክርነትህን ስትሰጥ … ያምርብሃልና የኔን እንሆ አልኳችሁ።

Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!