ጀግና ለሚያምንበት ግንባሩን ይሰጣል እንጂ አይሸሽም ወይም ሲሸሽ ከጀርባ ተወግቶ አይሞትም
እነ አምባሳደር ስዩም መስፍን ለብዙዎች ታላቅ አርአያ ሆነው፣ ትልቅ ሌጋሲ ተተው፣ በጀግንነት አልፈዋል!
አርአያነት
ተጋዳላይ ስዩም መስፍን ለትግራይ ከሰራው፣ ለኢዮጵያ የሰራው ይገዝፍ ነበር። አንድ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ለአንዲት ክልል ምን ሊሰራ ይችላል? ነገር ግን አዝማሪና ተመጽዋች በሚከበርበት አገር፣ እነ ቴዲ አፍሮና ታማኝ በየነ በገነኑበት አገር ግን፣ የተግባር ሰው እንደጠላት ተቆጥሮ ተገደለ።
እኔ በግሌ ለዓመታት እነ ስዩም የዘረጉትን ስርዓት ስቃወምና ስተች ኖሬያለሁ። ዛሬ ግን በሞታቸው ዘረረውኛል። ላመኑበት ነገር፣ እስከመጨረሻ ድረስ በጽናት እንደሚታገሉ ቃል ገብተው፣ ለቃላቸው ታምነው፣ በቃላቸውም ተገኝተው፣ በክብር አለፈዋል።
ከዚህ በላይ አርአያነት፣ ከዚህ በላይ የህይወት ትርጉም የለም። ሶቅራጥስ ከሌሎች ፈላስፋዎች ለምን ገዝፎ እንደሚታይ ታውቃላችሁ? የሚያስተምረውን በተግባር ሆኖ በመገኘቱ ነው። ብዙዎች ያስተምራሉ፣ በተግባር ሲፈተኑ ይወድቃሉ። እርሱ ግን በብዙ ተፈትኖ የሚያስተምረውን በተግባር ኖሮበት አለፈ።
የአቴና ወጣቶችን በክለሃል፣ ምንፍቅናን አስተምረሃል፣ ተብሎ ተከሰሰ። ቅጣቱ ሞት ወይም ስደት ነው ተብሎ ምርጫው ቀረበለት። ከተሰደድኩማ የማምንበትን፣ ያስተማርኩትን፣ ገደልኩት ማለት ነው። አለ። ያን ከማድረግ ሞቴን በጸጋ እቀበላለሁ ብሎ ያዘጋጁለትን መርዝ ጠጥቶ ሞተ። ከሞት ብኋላ ህይወት እንዳለ ያምን ነበርና እንሆ ዛሬ ድረስ “The greatest man who ever lived” ይባልለታል፤ ህያው ሆነ።
የነ ስዩም ሌጋሲም እንዲያ ነው። ህያው ናቸው! ኮሽ ሲል አገር ጥለው ከሚፈረጥጡ ሽንታምና ሙታን ገዳዮቻቸው መካከል አታገኟቸውም።
ሌጋሲ
የነስዩም መስፍን ሌጋሲ ተዘርዝሮ አያልቅም። አንድ ሆምለስ የጎዳና ተዳዳሪ መንገድ ላይ ሲንከራተት ኖሮ፣ ቆሻሻውን አራግፈህ፣ ጺምና ጸጉሩን ቆርጠህ፣ ገላውን አጥበህ፣ ንጹህ ልብስ አስለብሰህ፣ ብዙዎች በሚያዘወትሩበት አዳራሽ፣ መዝናኛ፣ ወዘተ ስትወስደው የሚሰማው አይነት ስሜት፤ እንዲያ ነበር ከጓዶቹ ጋር ኢዮጵያን ከትቢያ አንስተው፣ ከጎዳና ተዳዳሪነት አውጥተው፣ ሌሎች አገራት በሚያዘወትሩበት አዳራሽ አብራ መቀመጥና መምከር እንድትችል ያደረጉት።
በG8ና G20 ሲሰበሰቡ የምትታደም፣ ስለ አየር ለውጥ አፍሪካንና ድሃ አገራትን ወክላ የምትደራደርና በየኢኮኖሚ ፎረሙ ልምዷን የምታካፍል አገር አደረጓት። እነኔፓድንና ኢጋድን በምስላቸው ቀርጸው አፍሪካና የአፍሪካ ቀንድ ላይ ትልቅ አሻራቸውን ማሳረፍ የቻሉ፣ ባመኑበት ርዕዮተ አለም ለማንም ሳይበገሩ ሰርተው ውጤት ያሳዩ (ከነ ድክመቱም ቢሆን!)፣ ከነሱ በፊት የነበሩ መንግስታት ኢትዮጵያ በአለም ወይም በአፍሪካ የነበራትን ቦታና ያስረከቧቸውን አሳልፈው ሳይሰጡ ማስቀጠል የቻሉ፣ ለምሳሌ የኤዩ መቀመጫ ከኢዮጵያ እንዳይወጣ ያንን ሄድ ኳርተር አሰርተው መቀመጫዉን የቸነከሩ፣ ወዘተ ሰዎች ነበሩ። በአፍሪካ ቀንድ ብቻ አይደለም፣ በድፍን አፍሪካ ኢትዮጵያ ቁጥር አንድ የጸረ ሽብር ትግል አጋር ተደርጋ በምዕራቡ አለም የተወሰደችው፣ በነዚህ ሰዎች ስራና በስልጣን ዘመናቸው ነበር። ዛሬ አብይ አሕመድ ኢሳያስን ጎትቶ አምጥቶ አገሪቱን እሳት ለቀቀባት። የአረብ ጦረኛ አማካሪ አድርጎ ቀጠናውን አተራመሰው።
ሌጋሲያቸው ለሚቀጥሉት በርካታ ዓመታት ደምቆ ይታያል። ለበርካታ ምዕተ አመታት ይነገርለታል።
እየፈረሰ ባለ አገር የሚታይ ነገር ሰርተህ ይቅርና እንዲሁ ምንም ባትለውጥም፣ አገሪቱን አንድ ላይ ይዘህ ማቆየት ከቻልክ አንደ ትልቅ ድል ይቆጠርልሀል። መንግስቱ ሀይለማሪያም ምን ቢሰራ ነው እንዴ ዛሬ የሚወደሰው? አብይ እያፈረሳት ባለው አገር፣ አገሪቱን በዱላም ቢሆን ይዞ ማቆየቱም አይደል ገዝፎ እንዲታይ ያደረገው? ጭራሽ የፈረሰች ዕለት ደግሞ የመጫረሻዎቹና አንጸባራቂዎች የአገሪቱ መሪ ሆነው የሚታወሱት እነ ስዩም ይሆናሉ። መቼስ ከእንግዲህ፣ ኢትዮጵያ ከዚህ ጉድ ተርፋ፣ ከነሱ የተሻሉ ሰርተው የሚለውጡ መሪዎችን አግኝታ፣ ከተረት ባለፈ በተግባር ትበለጽጋለች ብሎ ተስፋ ከማድረግ፣ በሬ ይወልዳል ብሎ ተስፋ ማድረግ ይቀላል። ብዙ ተመኘንና፣ ብዙ የተሻለ ነገር አሻንና ለጉድ ተቸናቸው። ወቀስናቸው። ዘለፍናቸው። የግፋችን ግፍ፣ እነሱ የሰሩትን አንድ መቶኛ መስራት አይደልም መረዳትና ማስረዳት የማይችሉ ድውያን ላይ ጣለን።
በስዩም መስፍን ቦታ ወርቅነህ ገበየሁ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ሆኖ ነበር።
ጀግንነት
ተፈሪ መኮነን፣ በጣልያን ወረራ ጊዜ ህዝቡን ጥሎ ፈረጠጣና ንግስት ኤልሳቤጥ ቀሚስ ስር ለአምስት አመታት ተወሸቀ። ህዝቡ ታግሎ ራሱን ነጻ ሲያወጣ፣ ሊገዛ ተመልሶ መጣ።
መንግስቱ ሀይለማሪያም፣ አንድ ጥይትና አንድ ሰው እስኪቀር ድረስ ብሎ እንዳልፈከረ፣ ወታደሩንም ህዝቡንም ጥሎ ወደ ዝምባብዌ ፈረጠጠ። እንደ ቤት እንስሳ ከጓሮው የማያልፍ የቁም እስረኛ ሆኖ ጃጀ።
እነ ስዩም መስፈን ላመኑበት ርዕዮተ አለም በጽናት እንደቆሙ፣ ላመኑበት መርህ ከአባሎቻቸው፣ ደጋፊያቸውና ህዝባቸው ሳይነጠሉ እስከመጨረሻ ድረስ አብረው እንደቆሙ፣ የጽናት ተምሳሌት ሆነው፣ በጀግንነት አለፉ።
ሲያልፉም እንደፈሪ ሲሸሹ በጀርባ ተመተው ሳይሆን፣ ሞትን ፊት ለፊት ተጋፍጠው፣ ጥይት በግንባርና በደረታቸው ገብቶ፣ በድፍረትና በጽናት ነበር ጽዋቸውን የተጎነጩት።
ልዩነቱ ግልጽ ነው!!
ለአገልግሎታችሁ፣ ለሰጣችሁን የሞራል ስንቅ እጅግ እናመስግናለን! በሰላም እረፉ!!
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!