የኩላሊት ሽያጭ ህግና ስነ-ምግባር

ከዓመታት በፊት በአገራችን ሳምንታዊ የግል ጋዜጣ ላይ እንዲህ የሚል ማስታወቂያ ወጥቶ አይቻለሁ ‹‹እባካችሁ እርዱኝ አንዱ ኩላሊታችሁን ለግሱኝ›› የለግሱኝ ጥሪው ህይወት ማዳን እስከሆነ ድረስ ማስታወቂያው በተለየ መልኩ አትኩሮታችንን ላይስብ ይችላል፡፡ ግን ማስታወቂያው በስተመጨረሻው ላይ ማጠቃለያ መልዕክትም አለው፡፡ ‹‹ኩላሊቱን ለግሶ ህይወቴን ላዳነልኝ ግለሰብ ወሮታውን እከፍላለሁ፡፡›› የክፍያው መጠን ባይገለጽም በማስታወቂያው ላይ የቀረበው ጥያቄ ‹ነፃ› ወይም ‹ልግስና› ስላለመሆኑ ድምዳሜ ላይ መድረስ አይከብድም፡፡ ልግስናም ተባለ ሌላ ስያሜ ተሰጠው ለሚሰጠው ነገር በልዋጩ የሚከፈል ዋጋ እስካለ ድረስ የውሉ ዓይነት ከስጦታ ውል ወደ ሽያጭ ውል ይሸጋገራል፡፡

አሁን ላይ ቢሆን ኖሮ ይህን መሰሉ ማስታወቂያ በህግ የተከለከለ በመሆኑ የጋዜጣው ባለቤትም ደፍሮ አያወጣውም፡፡ በማስታወቂያ አዋጅ ቁጥር 759/2009 በአንቀጽ 6(1)(ሀ) እንደተመለከተው የማንኛውም ማስታወቂያ ይዘት ህግና ስነ-ምግባርን የማይጻረር መሆን አለበት፡፡ አዋጁ በአንቀጽ 7 ላይ ህግና ስነ-ምግባርን የሚጻረሩ በማለት ከፈረጃቸው የማስታወቂያ ይዘቶች አንዱ የሕብረተሰቡን አካላዊና አእምሯዊ ጤንነት ወይም ደህንነት ለጉዳት የሚያጋልጥ ድርጊት እንዲፈጸም የሚያነሳሳ ማስታወቂያ ነው፡፡ ስለሆነም ማስታወቂያው ከዚህ ውስጥ የሚመደብ እንደመሆኑ ክልከላ ተደርጎበታል፡፡ ክልከላውን መተላለፍ የወንጀል ድርጊት ሲሆን ከብር 20ሺ በማያንስና ከብር 150ሺ በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ ያስቀጣል፡፡ [የማስታወቂያ አዋጅ ቁጥር 759/2009 አንቀጽ 34(1)(ሐ)]

ትኩረቴ በማስታወቂያ አዋጁ ላይ ሳይሆን ከሰውነት አካል ሽያጭ በተለይም ከኩላሊት ሽያጭ ጋር በተያያዘ የህግና የስነ-ምግባር ጉዳዮችን መዳሰስ ይሆናል፡፡ ኩላሊታችንን ብንሸጠውስ? ምን ችግር አለው?

ኩላሊትን ጨምሮ የሌሎች የሰውነት አካላት ሽያጭ ከህግና ከሥነ-ምግባር አንፃር ያስከትሉት ውዝግብና ንትርክ በአሁኑ ወቅት ጡዘት ላይ የደረሰ ቢሆንም ድርጊቱ ከተጀመረና ከተጧጧፈ ግን ከ20 ዓመት በላይ ሆኖታል፡፡ በተለይ የኩላሊት ሽያጭ ሻጩ ከመሞቱ በፊት የሚደረግ ግብይት በመሆኑና ወሰን ሳይገድበው በየአህጉሩ በፍጥነት እየተስፋፋ በመሆኑ የየአገሪቱ የህክምና ባለሙያዎች፤ የፓርላማ አባላትና ሌሎች በጉዳዩ ያገባናል የሚሉ ደጋፊና ተቃዋሚ ወገኖች ግራ ቀኝ ይዘው ክርክራቸውን እየጧጧፉት ነው፡፡

የኩላሊት ገበያውም ከቀን ወደ ቀን እየደራ ኩላሊትም እየተቸበቸበ ይገኛል፡፡ በህንድ፣ በደቡብ አሜሪካ፣ በሩሲያ፣ በአውሮፓና በአረብ አገራት ኩላሊት ከሰውነት የአካል ክፍልነት ወደ ሸቀጥነት እየተቀየረ የመምጣቱ ሁኔታ ድርጊቱ ስር የሚሰድና ወደፊትም መግቻ ቁልፍ ለማግኘት አዳጋች የሚያደርገው ይመስላል፡፡ በተለይ አንዲት የህንድ መንደር ከሞላ ጎደል ሁሉም ነዋሪዎቿ አንድ ኩላሊታቸውን ሸጠው በአንዱ ብቻ የሚኖሩበት በመሆኑ ‹የኩላሊት ቀጠና› (kidney district) የሚል ስያሜ ልታገኝ ችላለች፡፡

የህጉን አቋም ስንመለከት በብዙ አገሮች የሰውነት ክፍሎችን መሸጥ ሆነ መግዛት በግልጽ የተከለከለ ነው፡፡ በአገራችን አሁን ባለው የወንጀል ህግ መሰረት ገንዘብ አሊያም ጥቅም ለማግኘት ብሎ የሰውነት አካልን መስጠት ሆነ በተጎጂው ፈቃድ መውሰድ ሁለቱም በወንጀል ያስቀጣሉ፡፡ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 573(1) እንደተመለከተው ገንዘብ አሊያም ጥቅም ለማግኘት ብሎ የሰውነት አካልን መስጠት እንዲሁም ከሞት በኋላ የሰውነት ክፍልን ለሌላ ሰው ወይም ድርጅት ለማስተላለፍ መስማማት በቀላል እስራት ወይም በመቀጮ ያስቀጣል፡፡

ቅጣቱ በሰጪ ላይ ቀላል ሲሆን በተቀባዩ ላይ ግን ህጉ የሚያስቀምጠው ቅጣት ከበደ ያለ ነው፡፡ በዚሁ መሰረት ገንዘብ አሊያም ጥቅም ለማግኘት በተበዳዩ ፍቃድ የሰውነት አካልን መውሰድ ተጎጂው እያለ ከሆነ ከአምስት ዓመት እስከ አስር ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት የሚያስቀጣ ሲሆን ከተበዳዩ ሞት በኋላ ከሆነ ደግሞ ከአምስት አመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ያስቀጣል፡፡ [የወንጀል ህግ ቁጥር 573(2)]

በተመሳሳይ መልኩ በፍትሕብሔር ህግ ቁጥር 18 ላይ እንደተመለከተው ሙሉ አካልነትን /integrity of the body/ የሚያቃውስ ማንኛውም የሰውነት ክፍሎች ላይ የሚፈፀም ተግባር የተከለከለ ነው። በሌላ አነጋገር አንዲት ሴት ፀጉሯን ቆርጣ ብትሸጥ ወይም ደም ብትለግስ ፀጉሩም ጊዜውን ጠብቆ ስለሚያድግና ደሙም ከ48 ሰዓታት በኋላ ስለሚተካ ሙሉ አካልነትን የሚያቃውስ ተግባር ባለመሆኑ የተፈቀደ ነው፡፡ ከሁለት ኩላሊቶች መካከል አንደኛው ተቆርጦ ቢወጣ ግን ምንም እንኳን ከባድ የሚባል የጤና ቀውስ ባያስከትልም አንድ ሰው በተፈጥሮ ሊኖረው የሚገባውን አካላዊ መዋቅር የሚቃረን በመሆኑ የሽያጭ ድርጊቱም በአንቀጽ 18 መሰረት የተከለከለ ነው፡፡ በውል ህጋችን አንቀጽ 1678 (ለ) እና 1716(ሀ) መሰረት አንድ ውል ህጋዊ ውጤት እንዲኖረው የውለታው ጉዳይ ህጋዊና ሥነ-ምግባርን የማይቃረን መሆን እንዳለበት በመደንገጉ በኩላሊት ሻጭና ገዢ መካከል የሚደረገው ውል ዋጋ አልባ እንደሆነ ይቀራል፡፡

በፍትሐብሔር ህጉ በጥቅል ከተቀመጠው በተጨማሪ የአካላት ክፍሎችና ህብረ-ሕዋሳት ልገሳና ሽያጭ በተመለከተ ቁጥጥር የሚያደርግ ህግ እስካሁን በቀጥታ በህግ አውጪው የወጣ ባይሆንም የምግብ፤ የመድሃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 661/2001ን ለማስፈጸም የወጣው የምግብ፤ የመድሃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 299/2006 ይህን ጉዳይ አስመልክቶ ዝርዝር ድንጋጌዎችን ይዟል፡፡ በዚሁ መሰረት በደንቡ አንቀጽ 59 ንዑስ አንቀጽ 2 እንደተመለከተው አንድ ሰው በህይወት ዘመኑ ወይም ህይወቱ ካለፈ በኋላ የአካል ክፍሎቹንና ህብረ-ህዋሳቱን በልገሳ ለማስተላለፍ ሆነ በምንም መልኩ እንዳይወሰዱ ለመከልከል ያልተገደበ ነጻነት ተሰጥቶታል፡፡

ይህም ማለት የአካል ክፍሎችንና ህብረ-ህዋሳትን በሕይወት ዘመን ወይም ከሞት በኋላ ለሌላ ሰው ወይም ድርጅት በሽያጭ ማስተላለፍ ሆነ ለማስተላለፍ መስማማት ክልከላ የተደረገበት [ደንብ ቁጥር 299/2006 አንቀጽ 59 ንዑስ አንቀጽ 5] ቢሆንም ያለምንም ወሮታ ሆነ ክፍያ ከሆነ ግን “እሰጣለው” የሚለው የተስፋ ቃል በህግ ተቀባይነት ተሰጥቶታል፡፡ የአካል ክፍሎችንና ህብረ-ህዋሳትን ለመለገስ የሚሰጠው የተስፋ ቃል ተስፋ ሰጪው በህይወት ባለበት በማንኛውም ጊዜ ሊሽረው መብት አለው፡፡ የመሻሩ ውጤት ለጋሹ ከግዴታ ነጻ የሚያደርገው ሲሆን ተለጋሹ በተሰጠው የተስፋ ቃል ተነሳሰስቶ ላደረገው ወጪ ሁሉ (በተለይ የተስፋ ቃሉ በክፉ ልቦና የተሰጠ ከሆነ) ለጋሹ ካሳ የመክፈል ግዴታ ተጥሎበታል፡፡ [ደንብ ቁጥር 299/2006 አንቀጽ 59 ንዑስ አንቀጽ 3 እና 4]

አንድ ሰው ህጋዊ በሆነ የተስፋ ቃል የአካል ክፍሎችን ወይም ህብረ-ህዋሳትን ከሌላ ሰው ማግኘቱ በራሱ ሰውነት ላይ ወዲያኑ በህክምና ንቅለ-ተከላ (transplantation) ሊደረግለት ይችላል ማለት አይደለም፡፡ ደንብ ቁጥር 299/2006 አንቀጽ 59 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ እንተመለከተው የአካል ክፍሎችና ህብረ-ህዋሳት ንቅለ-ተከላ ማከናወን የሚቻለው የተቀባዩን ህይወት ለማቆየት ወይም የሰውነት አቋሙን ለማስተካከል ሌላ የተሻለ አማራጭ መንገድ የማይገኝ መሆኑ በሕክምና ቦርድ ሲረጋገጥ ነው፡፡

በሌሎች ብዙ አገራት የኩላሊት ሽያጭ በህግ የተከለከለ ተግባር ሲሆን በተወሰኑት ደግሞ በወንጀል ጭምር የሚያስቀጣ ድርጊት ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ግን በሁለት ጎራዎች መሃል ለሙግትና ክርክር መንስዔ የሚሆነው ጥያቄ እየተነሳ የጦፈ ክርክር እየተደረገበት ይገኛል፡፡ ኩላሊት በህጋዊ መንገድ መሸጥ አለበት ወይስ የለበትም? ከወደ እንግሊዝና ህንድ አካባቢ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጡት መልሶች በየራሳቸው ጠንካራ እና ሚዛን የሚደፉ ናቸው፡፡ የኩላሊት ሽያጭን የሚደግፉ ወገኖች ድርጊቱ የሁለትዮሽ ጠቀሜታ እንዳለው ይገልፃሉ፡፡ ‹‹በአንድ በኩል በኩላሊት እጦት ሊሞት የነበረው ግለሰብ ከሞት ይተርፋል፡፡ በሌላ በኩል በከፋ ድህነት ውስጥ ሲማቅቅ የነበረው ግለሰብ ጤናው ሳይቃወስ አንደኛው ኩላሊቱን በመሸጥ ከድህነት ቀንበር በቀላሉ ይቀቃል›› ይህን ይመስላል የሚያቀርቡት ሃሳብ፡፡ ከዚህ ሃሳባቸው ተነስተው የሚደርሱበት ድምዳሜም ድርጊቱ ሥነ-ምግባርን የማይፃረር እግዜርም የሚወደው ስራ እንደሆነ ነው፡፡ የአንድ ኩላሊት የገበያ ዋጋ እስከ እስከ አምስት ሺ ዶላርና ከዛም በላይ የሚደርስ ሲሆን በእርግጥም ይህ ገንዘብ የደሃን ህይወት በከፊል ሊቀይር ይችላል፡፡

ከዚህ ሃሳብ በተቃራኒ የተሰለፉት ወገኖች ከሰው ልጅ ሰብዓዊ ክብር አንፃር ለገንዘብ ብሎ የተከበረውን የሰው ልጅ የሰውነት አካል መሸጥ አስነዋሪነቱን በማስረገጥ ድርጊቱን አምርረው ይቃወማሉ፡፡ ደጋፊዎች ባይጠፉም በርካታ ሐኪሞችም ድርጊቱ በህክምና ሥነ-ምግባር ተቀባይነት እንደሌለው በመግለጽ ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል፡፡ ከተቃዋሚዎች ጎራ ክፉኛ ነቀፌታ የገጠመው ኩላሊት በገንዘብ ይሸጥ መባሉ ብቻ ነው፡፡ እስከ አሁን ድረስ በፈቃደኝነት የተመሰረተ ነፃ የኩላሊት ልገሳ ወይም ስጦታ ውግዘት አልገጠመውም፡፡ ሽያጩን ግን ‹‹የሰው ልጅን ክብር የሚያቆሽሽ›› በሚል ነው የሚገልጹት፡፡ የአገራችን ህግም ቢሆን የሰው ህይወትን ለማዳን ኩላሊትን ሆነ ሌላ የሰውነት አካልን በነጻ መስጠት ወይም መለገስ በወንጀልነት አይፈርጀውም፡፡

ሌላው ተደጋግሞ የሚሰማው ስሞታ ከኩላሊት ሽያጭ የሚገኘው ገንዘብ በአግባቡ ለባለኩላሊቶች አለመድረሱና ህይወታቸውንም አለመለወጡ ነው፡፡ የኩላሊት ሽያጭ ከተፈቀደ ‹‹የኩላሊት ዘረፋ ወንጀል›› በእጅጉ እንደሚባባስ ስጋታቸውን የገለፁም አልጠፉም፡፡ ይሁን እንጂ አፈፃፀሙና አተገባበሩ በመንግስት ቁጥጥር ስር በሚሆን የገበያ ስርዓት ህጋዊ መንገድ መዘርጋት ሊፈጠር ለሚችለው ስጋትና ችግር ፍቱን መፍትሄ እንደሆነ በመግለጽ የኩላሊት ሽያጭ ደጋፊዎች ችግሩን ያጣጥሉታል፡፡ ወንጀሉ በዚሁ መልኩ የሚወገድ አለመሆኑን በመጥቀስም ህጋዊነት ብቸኛው መፍትሄ እንደሆነ ለማሳመን ይጥራሉ፡፡ የኩላሊት ሽያጭ ደጋፊዎች በሽያጩ ሂደት ከባለኩላሊቱ ይልቅ በመሃል የሚንሳፈፉ ሶስተኛ ወገን ደላሎች ይበልጥ ተጠቃሚዎች እንዳይሆኑ የሚቀርበውን ስጋት በተመሳሳይ መልኩ ህጋዊ የመቆጣጠሪያ ስልት በመቀየስና አፈፃፀሙን በበላይነት የሚመሩ ድርጅቶችን በማቋቋም ግንኙነቱ በሻጭና በገዢ መካከል ብቻ እንዲሆን በማድረግ ውጤታማ በሆነ መንገድ ሊካሄድ እንደሚችል ለማሳመን ይጥራሉ፡፡

ሌላው በተጠቃሚዎች የሚሰነዘረው ሂስ ሽያጩ የኩላሊት ልገሳ ወይም ነፃና ሰብዓዊ እርዳታን መሰረት ያደረገ የኩላሊት ስጦታን ያዳክማል የሚል ሲሆን ለዚህም ቢሆን ምላሽ ተሰጥቶበታል፡፡ ክርክራቸውን በምሳሌ ሲያስረዱም ለደም ፈላጊዎች በነፃ የሚሰጠው ደም በገንዘብ የሚሸጥ ቢሆን ኖሮ የደም ለጋሾች ቁጥር የመመንመኑ ሁኔታ እውነትነት የለውም ይላሉ፡፡ ግን ልብ በሉ! ደም ሲለገስ በ48 ሰዓታት ውስጥ የሰውነታችን የደም መጠን ቀድሞ ወደነበረበት ሁኔታ ይመለሳል፡፡ ኩላሊት ግን አንድ ጊዜ ሄደ ማለት እስከ መጨረሻው ሄደ ማለት ነው፡፡ ከሚከፈለው መስዋእትነት አንፃር የኩላሊት ልገሳ አብዛኛውን ጊዜ የሚካሄደው በቂ ገንዘብ ኖሯቸው ለሰብዓዊ እርዳታ ብቻ ለመለገስ በሚወስኑ ግለሰቦች እንዲሁም በአንዳንድ ዘመዳሞችና ፍቅረኞች መካከል በመሆኑ እነዚህ ወገኖች ኩላሊት በገንዘብ የመሸጡ ነገር ሃሳባቸው ላያስቀይራቸው ይችላል፡፡ በተግባር እየታየ ካለው እውነታ አንፃር ሲታይ ይህ ምላሽ በፊት ለቀረበው ተቃውሞ በቂ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

ይሁንና ክርክሩ መቋጫ አልተገኘለትም፡፡ ዋናውና መሰረታዊ ተደርጎ የተወሰደው የመከራከሪያ ነጥብ አስታራቂ ሃሳብ አልተገኘለትም፡፡ ጭብጡን በጥያቄ መልክ እንዲህ ላስቀምጠው ‹‹አንድ ሰው በራሱ ሰውነት ላይ ፍፁም ስልጣን አለው? ወይም ሊኖረው ይገባል?›› ለአንዳንዶች መልሱ በጣም ቀላል ነው፡፡ ‹አዎና!› ይላሉ ባለማመንታት ‹ከፈለግኩኝ እግሬን እቆርጠዋለሁ ቢያሻኝ አይኔን አውጥቼ እጥለዋለሁ፡፡ ማን ሊያገባው ይችላል?›

ሲያዩት ቀላል የሚመስለው ጥያቄ አከራካሪነቱ ገሃድ ወጥቶ የሚታየው ከፍትሐብሔር ህግጋት በተለይ ከውል ህግ መርሆዎች አንፃር ሲታይ ነው፡፡ የቅድሙ ጥያቄም መልኩን ቀይሮ ‹‹የተዋዋዩ ወገኖች ነፃት እስከ ምን ድረስ መሄድ አለበት? ወይም ኩላሊት ለመሸጥ የተደረገው ውል በፍርድ ቤት ተቀባይነት አግኝቶ መተግበር አለበት ወይ?›› የሚል አዲስ ገጽታ ያላብሳል፡፡ የተዋዋይ ወገኖች ነፃት ገደብ ምክንያቱ ግን ዞሮ ዞሮ አነስተኛ የመደራደር አቅም ያላቸውን ወገኖች ጥቅም ለማስጠበቅና ከለላ ለማድረግ እንዲሁም በዋነኛነት የህብረተሰቡን መልካም እሴትና ሥነ-ምግባ ሳይበረዝና ሳይበላሽ እንዲጠበቅ ሲባል ነው፡፡ ይህም ነጥብ በራሱ ወደ መጀመሪያ ላይ ወደ ነካካነውና ኩላሊትን መሸጥ ከሥነ-ምግባር አንጻር ተቀባይነት አለው ወይስ የለውም? ወደሚለው ሰፊ ክርክር መልሶ ይወስደናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የንብረት ህግ ጽንሰ-ሓሳብ በራስ አካል ላይ ሰለሚኖር የባለቤትነት መብት (self-ownership) ላይ ተፈጻሚነት ይኖረዋልን? የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድደናል፡፡ እኔም እስቲ እዚሁ ላይ ትቻችሁ ልሂድ፡፡ ለመሆኑ ኩላሊት ቢሸጥ አስነዋሪነቱ ምንድነው? የኩላሊት ሽያጭ በስፋት እየተከሰተ ያለው የሚበሉትና የሚጠጡት በሌላቸውና ድህነት የተስፋፋባቸው አካባቢዎች ከመሆኑ አንፃር ወደኛው ዘንድም የመምጣቱ አጋጣሚ ሰፊ ነውና ለጥያቄው ያላችሁን ወርውሩበት፡፡

©ማክዳ

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *