ሰኞ ካርቦን ልቀት ለመቀነስ የ$68 ሚልዮን ዶላር ድጋፍ አገኘች – ቅዳሜ በመዲናይቱ አቅራቢያ የቆሻሻ ናዳ ፈርሶ 82 113 ሰው ሞተ

በኢንተርኔት ከሚለቀቁ ኢትዮጵያን የሚመለከቱ ዘገባዎች በallAfrica.com አማካኝነት የሚለቀቁ ዘገባዎች በቁጥር ሚዛን የሚደፉ ናቸው። በዚህ ድረገጽ የሚለቀቁ ዜናዎች ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ስለ ልማት፣ ግስጋሴ፣ ህዳሴ፣ ሽልማት፣ የተሳካ ስብሰባ፣ ተስፋ ሰጪ ዕቅድ፣ ወዘተ ብቻ የሚመለከቱ ናቸው። ዓለም ዓቀፍ ሚድያዎች እየተቀባበሉ በስፋት ሽፋን የሚሰጧቸው አሳዛኝ ክስተቶች፣ በዚህ ድረገጽ በቂ የሚድያ ሽፋን ሲያገኙ አይታዩም። ይኽ የሚሆነው ለምንድን ነው የሚል ጥያቄ ካጫረብኝ ወራቶች አለፉ። ሰሞኑን ትኩረት ሰጥቼ በደንብ ተከታተልኩት።

ይህ ድረገጽ ከተለያዩ የሚድያ ተቋማት የሚላኩለትን ዘገባዎች እንደ አንድ ፕላትፎርም ተቀብሎ ያስተናግዳል። ከሚላኩለት ጽሁፎች የሚጨምረውም ሆነ የሚቀንሰው ነገር የለውም። በማያሻማ ሁኔታ ግልጽ አድርጎ በየዘገባዎቹ ስር እንዳስቀምጠው፣ በማን የተጠናቀረ ዘገባ እንደሆነ፣ ኮፒ ራይቱ የማን እንደሆነ፣ አድራሻውን ጭምር በመጥቀስ በግርጌ ማስታወሻው ያስቀምጣል። የዚህ ድረገጽ ሚና ዘገባዎችን ከየዘርፉ ተቀብሎ ማሰራጨት ብቻ ነው።

ባለፉት ሁለት ሳምንታት በዚህ ድረገጽ ከቀረቡ ኢትዮጵያን የሚመለከቱ ዘገባዎች ከ75 በመቶ በላይ የመጡት ከአንድ የሚድያ ተቋም ብቻ ነው። ይኸው የሚድያ ተቋም የኢትዮጵያ መንግስት ልሳን የሆነውና በኢንግሊዝኛ የሚዘጋጀው Ethiopian Herald ነው (ሊንኩን ተጭነው ምስሉን ይመልከቱ)።  በየዘገባዎቹ ስር የEthiopian Herald ኮፒ ራይት መሆኑን የሚገልጽ ነገር ብታገኙም፣ ወደ ኦሪጅናሉ ዘገባ የሚያመራ ሊንክ (ማስፈንጠርያ) አታገኙም። የEthiopian Herald ዋና ድረገጽ ራሱ ማስፈንጠሪያው አይሰራም። (ላለፉት ሁለት ሳምንታት ካነበብኳቸው ዘገባዎች በየአንዳንዷ ሊንክ ተከትዬ ሞክሬው አንድም ጊዜ ሰርቶ አያውቅም። ይህን ጽሁፍ በማዘጋጅበት ሰዓትም ጽሁፌን አቋርጬ ሞክሬዋለሁ። ወፍ የለም።)

የመንግስት ልሳን የሆኑ ሚድያዎች ተሰሚነትን አጥተው ህዝብ ሌሎች አማራጮችን መከተል ከጀመረ ከራርሟል። ስለሆነም ዘገባዎቹን በራሱ ድረገጽ ከማቅረብ፣ በሶስተኛ ወገን የሚድያ አውታሮች (በነallAfrica.com) በኩል በማቅረብ ማጨናበሩ አዋጭ ሆኖ አግኝተውታል።  ለተወሰ ጊዜም ቢሆን ብዙዎቻችን ያታለለ ብልጠት ነበር። (ለምሳሌ በግሌ በትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋዜጨኞች እየተዘጋጀ የሚቀርብ የውጭ ገለልተኛ ሚድያ ይመስለኝ ነበር – እስከቅርብ ጊዜ ድረስ።)

ለመሆኑ ከEthiopian Herald ውጪ ሌሎች የአገራችን ሚድያዎች በዚህ ፕላትፎርም አማካኝነት ዘገባቸውን የሚያሰራጩ አሉ? በጣም ጥቂት ቢሆኑም አሉ። አልፎ አልፎ Addis Fortune እና Addis Standard ዘገባዎቻቸውን ሲያቀርቡ ይታያሉ። የተቀሩት ደግሞ እንደነ VOAና ሱዳን ትሪቡን የመሳሰሉ ንብረትነታቸው የሌሎች አገራት የሆኑ ሚድያዎች ናቸው።

የኢትዮጵያን መንግስት በመቃወምና ግድፈቶችን ነቅሰው በማውጣት የሚታወቁት አንዳንዴም የኢትዮጵያ ህዝብ እውነተኛ ልሳን ናቸው የሚባሉት እነ ESATOMNECADFORUM እና የመሳሰሉ የዜና አውታሮች ዘገባዎቻቸውን በዚህ ፕላትፎርም ማቅረብ ያልቻሉት ለምን ይሆን?

ወደድንም ጠላንም allAfrica.com ከፍተኛ የኢንተርኔት ትራፊክ ያለውና በሚልዮኖች በሚቆጠሩ አፍሪካውያንና ምዕራባውያን በየቀኑ የሚጎበኝ አውታር ነው። በዚህ አውታር የመንግስት ልሳን የሆነው Ethiopian Herald መልኩን ቀይሮ የተሳካ ፕሮፓጋንዳ ሲነዛ በቸልተኝነት ሊታለፍ የሚገባው ጉዳይ አይደለም። በአገር ውስጥ ተአማኒነቱን ያጣውን ያህል በውጭው ዓለምም እንዲያጣ የሁሉም ባለሞያና አክቲቭስት ርብርብ ያስፈልጋል።

አንድ የማይካድ ስኬታማ ፕሮፓጋንዳ ቢኖርና ለዚህ ስኬት የነallAfrica.com ድርሻ ጎልቶ የሚታይበት ቦታ ቢኖር ኢትዮጵያ የአየር ለውጥ ለመከላከል “አረንጓዴ አብዮት” በተሳካ ሁኔታ በማካሄድ ላይ ነች የሚለው ወሬ ነው። የቆሻሻ ክምር ተደርምሶባቸው ዜጎች ከመሞታቸው ከቀናት በፊት ኢትዮጵያ ካርቦን ኒውትራል አገር ለመሆን በምታደርገው ጥረት ከዓለም ባንክ የ$68 ሚልዮን ዶላር ድጋፍ ማግኘቷ የሚገልጽ ዘገባ ተሰርቶ ነበር። የቆሻሻ ክምር ተራራ ሰርቶ፣ ዜጎች ሰፈረውበት፣ ከቆሻሻው የለት ጉርሳቸውን የሚለቃቅሙበት ምድራዊ ሲኦል አፍንጫቸው ስር ይዘው፣ የለጋሾችን ልብ አሸንፈው እርዳታ በየጊዜው ማግኘታቸው፣ የተቀረነው ዜጎች መስራት የሚጠበቅብንን ያህል እንዳልሰራን የሚያሳይ ነው። ራሳችንን ልንወቅስና ልንጠይቅ ይገባል!

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *