“ከኦሮሞ የማይወለድ ቡዳ ነው ይባላል” – ዶ/ር ዮሀንስ ዘለቀ

ዶ/ር ዮሀንስ ዘለቀ ከኢሳት ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ጋር ያደረጉት ቆይታ አወዛጋቢነቱ ቀጥሏል። ዶ/ሩ ከተናገሯቸው ቀነጫጭበው እሳት ለመጫር ልዩ ፍላጎት ያላቸው ሀይሎች ስራቸውን እንዳከናወኑ ይሰማኛል። ያም ሆኖ ያልጠበቅናቸው ሰዎችም ተከፍተው በስሜት ሲጽፉ ታዝበናል። በማህበራዊ ሚድያ አወዛጋቢ ከሆኑት የዶ/ር ዮሀንስ አስተያየቶች፣ ለኢትዮጵያ ኋላቀርነት ሰለሞናዊውን ስርወ መንግስት በተወሰነ ደረጃ ተጠያቂ ማድረጋቸው እና ጎጃሜ ሆኖ ከኦሮሞ የማይወለድ የለም ማለታቸው ናቸው። በነዚህ ሁለቱ ነጥቦች ዙሪያ የግል እይታዬን ካነበብኩት እንደሚከተለው ለማካፈል ወደድኩ።

1. ሰለሞናዊው ስርወ መንግስትና የኢትዮጵያ ስልጣኔ መዳከም

የአክሱም ስልጣኔ የተዳከመውና ያከተመለት ምክንያት ተብሎ ከሚጠቀሰው አንዱ ኢትዮጵያ የክርስትና እምነትን በንጉስ ኢዛና ዘመነ መንግስት መቀበሏ ነው። የክርስትና እምነት ምድራዊ ህይወትን አለዝቦ ሰማያዊ ህይወት ላይ ትኩረት ማድረጉ፣ ለአክሱማውያን ብቻ ሳይሆን በዘመናቸው ገናና ለነበሩት ለነ ቫይኪንግስም ያዳከመ መሆኑ በታሪክ መዛግብት ሰፍሮ ይገኛል። ሰለሞናዊው ስርወ መንግስት፣ ዘውዱን በክርስትና የእምነት መሰረት ላይ ማኖሩ፣ እምነቱን እንዲስፋፋና ስር እንዲሰድ በማድረግ፣ ዛሬ ድረስ ባገራችን እንደምናየው፣ ምድራዊ ህይወትን ችላ ብሎ በሁሉም ዘርፍ ሰማያዊ ጣልቃ ገብነትን የሚጠባበቅ ህዝብ ይዘን እንድንቀር አድርጓል።

ለአውሮፓ ስልጣኔ በር ከፋቹ የማርቲን ሉተር ኪንግ የፕሮቴስታንት ሪፎርም (ተሀድሶ) መሆኑ ይነገራል። ከማርቲን ሉተር ኪንግ ሪፎርም 30 ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ በነ ደቂቀ እስጢፋኖስ ተከታዮች አማካኝነት ተመሳሳይ ተሀድሶ ተሞክሮ የነበረ ቢሆንም የይሁዳ አንበሳ ነኝ የሚል የሰለሞናዊ ስርወ-መንግስት ንጉስ (ከዘመኑ ካህናት ጋር በመተባበር) በአሰቃቂ ሁኔታ ድምጥማጣቸውን እንዲጠፉ መደረጉ በፕ/ር ጌታቸው ሃይሌ ወደ አማርኛ በተተረጎመው የደቂቀ እስጢፋኖስ ገድል አንብበናል።

ዛሬ ለስልጣኔ እንቅፋት የሆነ ባህል አለን ከተባለ፣ መነሻው በኢትዮጵያ ያሉት የሶስቱ ገናና ሃይማኖቶች መሰረታዊ ፍልስፍና ነው የሚል እምነት አለኝ። ሀብት ማካበት፣ ብዙ መሻት፣ ጥሮ ግሮ መብላት፣ ነግዶ ማትረፍ ወዘተ የማያበረታቱ፣ ይልቁንም ስንፍናን በተስፋ እየጠቀለሉ፣ ጭቆናን በባሰ አታምጣብን የመጽናኛ ምልጃ እያወራረዱ ጥልቅ እንቅልፍ ውስጥ የጣሉን እምነቶች ናቸው የነበሩን ብል የተሳሳትኩ አይመስለኝም። ክርስትና ደግሞ በነገስታቱም የተደገፈና የበላይ ስለነበር፣ ለኋላቀርነታችን ትልቁን ድርሻ ይይዛል ቢባል ማጋነን አይሆንም። ከዚህ አንጻር ሲታይ እምነቱን ከንጹህ መንፈሳዊ የህይወት መንገድ ወደ ፖለቲካዊ መጠቀሚያነት ቀይረው በምድር ላይ የነበራቸውን ስልጣን፣ ዝናና ሀብት ለማስጠበቅ የሰሩበት የሰለሞናዊ ስርወ መንግስት አራማጆችና ተባባሪ ካህኖቻቸው ትልቁን “ብሌም” ቢወስዱ ተገቢ ነው።

2. “ከኦሮሞ የማይወለድ ቡዳ ነው ይባላል”

ጎጃም ባብዛኛው ኦሮሞ ነው ሲባል ቀላል የማይባሉ ሰዎችን የሚያስቆጣ መሆኑን የተረዳሁት የዛሬ ሁለት ዓመት በማህበራዊ ሚድያ በደረሰብኝ ውግዘት ነበር። ከዶ/ር ዮሀንስ በፊት ባለፈው ዶ/ር ሀይሌ ላሪቦም በኢሳት ቀርበው ተመሳሳይ ነገር ተናግረዋል። ነገር ግን ያኔ ትኩረት አስቀያሾቹ የኦሮሞ የብሔር ፖለቲከኞች ስለነበሩ፣ የጎጃም ኦሮሞ መባልም ሆነ የወለጋ ኦሮሞ አይደለም መባል ብዙም ትኩረት ሳይሰጠው የታለፈ ነበር።

ዶ/ር ዮሃንስ አባ ባህረይን ጠቅሰው ጎጃም የነበረውን ሁኔታ ያስረዱ መሰለኝ። አባ ባህረይን ጠቅሰው ፕ/ር ጌታቸው ሀይሌ ተመሳሳይ “ክሌይም” ያቀርባሉ። ተሻለ ጥበቡ “The Making of Modern Ethiopia” በሚለው መጽሃፉ ተክለጻድቅ መኩሪያን ጠቅሶ ገጽ 38 ላይ እንዲህ ሲል ጽፏል፣

“… It is seldom noted that the struggle against the Zamana Masafent was not just one of creating a centralized power, but also that it was a struggle agains the Oromo dominance at Dabra Tabor, which was the epicienter of an Oromo arc of rule running through North/Western Wallo, Southern Gondar, Damot and Gojjam.”

አክሎም ተሻለ ጥበቡ እንዲህ ይላል፥

“Even less noted is how deep the Oromo expansion of the 16th and 17th centuries had resulted in the Oromization of the ruling house of Gojjam. Since Atse Susenyos’ coronation, where he billeted Oromo chawa known as Illmana Densa (still a name of a region in Gojjam), on the balagar, Gojjam was ruled by Christianized, Amharic/Speaking, assimilated Oromos. From Yosedek – the 18th century Gudru Oromo ruler of Gojjam – to Ras Hailu the Great, Negus Tekle Haimanot, and Ras Hailu Tekle Haimanot, the ruleres of Gojjam were Oromos who assmilitaed with the Amhara, converted to Christianit and spoke Amharic.”

በተጨማሪም ጸጋ ኢታን Integration and Peace in East Africa በተሰኘው መጽሀፏ ስር (Oromo assimilation in hailand Gojjam በሚል ንኡስ ርዕስ ስር ተመሳሳይ ነገር በዝርዝር ጽፋለች።

ፕ/ር መሓመድ ሑሴንም በበኩሉ፥ “በምስራቅና በደቡብ አባይ የነበሩ መሪዎች ኦሮሞዎችን በጉልበት ማስገበር ባይችሉም … By their own initiative the Oromo continued to settle both in Gojjam and Begameder, where they submitted to and served the state, embracing Orthodox Christianity, thus becoming part of the mainstream of Amhara society” ሲል ይገልጻል።

በባህሩ ዘውዴ A History of Modern Ethiopia ተመሳሳይ ነገር ያነበብኩ ይመስለኛል። ዶ/ር መረራ ከመታሰራቸው በፊት ሚድያ ላይ ተመሳሳይ ነገር ሲያወሩ ሰምቻለሁ። በአንድ ጥናታዊ ጽሁፋቸው የቅኝ መገዛት ፖለቲካን ለሚያቀነቅኑ የኦሮሞ ምሁራን በሰጡት መልስ፣ «Oromo were able to become kings and queens of imperial Ethiopia – the best examples being Iyyassu, Haile Selassie, King Michael of Wollo and King Takle-Haymanot of Gojjam» ሲሉ ጽፈዋል።

እነዚህ አብነቶች ተደማምረው የሚመሰክሩት እውነታ ቢኖር ጎጃሜ ሆኖ የኦሮሞ ደም የሌለው ማግኘት የሚከብድ መሆኑን ነው። ይህ ምስክርነት እኔ እዚህ ከጠቀስኳቸው ጥቂት አብነቶች በላይ በበርካታ ምሁራን ተደጋግሞ የሚነገር ነው። በዚህ የጎጃም ታሪክ ላይ የወሎና የሸዋ ህብረብሔራዊነት ሲታከልበት፣ “አማራ የበላይ ብሔር ነበረ” “ሌላውን ደፍጥጦ ኢትዮጵያን በምስሉ ሊፈጠራት ሞከረ” ለሚሉ የብሔር ፖለቲከኞች የማይሸሹትና ፊት ለፊት መጋፈጥ ያለባቸው ቁልፍ ጥያቄ ያጭራል፣ “የቱ ነው አማራ?”። ህዝቡም የተቀላቀለ ከሆነ… የኦሮሞ ምሁራን ሳይቀር እንደሚመሰክሩት … በአመራር ላይም የተለያየና የተሰባጠረ የብሔር ማንነት ያላቸው ከነበሩበ … የአንድ ብሔር የበላይነት ነበረ ማለት እንዴት ይቻላል?

ብሄር ተኮር ታሪክን ለፖለቲካ ትርፍ የማይጠቀሙ፣ በሞያቸው አንቱ የተባሉ (በተሰማሩበት መስክ ከፍተኛ reputation ያተረፉ) አንጋፋ የኢትዮጵያ ምሁራን ከየትም ይምጡ ከየት፣ የዘር ሀረጋቸው ምንም ይሁን ምን፣ በአንድነት የሚመሰክሩት እውነታ ቢኖር፣ ከደቡብ እስከ ሰሜን፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ የአገራችን ክፍል፣ የኢትዮጵያ ህዝብ የተቀላቀለ መሆኑና አንዱን ከሌላው መለየት ፈጽሞ የማይቻል መሆኑን ነው። ዶ/ር ዮሃንስ ከዚህ የተለየ የተናገረ አይመስለኝም።

ዋቢ ማጣቀሻዎች

ጌታቸው ሀይሌ 1996ዓም. ደቂቀ እስጢፋኖስ

Merera Gudina 2006. Contradictory Interpretation of Ethiopian History

Mohammed Hassen 2015. The Oromo and the Christian Kingdom of Ethiopia

Teshale Tibebu 1995. The Making of Modern Ethiopia: 1896-1974

Tsega Etefa 2012. Integration and Peace in East Africa: A History of the Oromo Nation

[fbcomments]

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *