እውቀት በሞጁል አይገደብም

መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ኢኮኖሚክስ ስንማር፣ አስተማሪዎቹ (አብዛኞቹ ባችለር ዲግሪ ብቻ የነበራቸው ነበሩ) ባዘጋጁት ሞጁል መሰረት ነበር የምንማረው። አስተማሪው ርዕስ ይመርጣል፣ ከተለያዩ ስራዎች ኮፒ ፔስት እያደረገ ጥራዙን ይሰራዋል። ያውም አብዛኛውን ግዜ ከአንድ ወይም ከሁለት መጽሃፍ ብቻ የተውጣጣ ኮፒ ፔስት ነው። በባችለር ምሩቅ ቀርቶ በፒኤችዲ ደረጃም ይሔ ዘዴ ድክመት አለበት። ተቃራኒ ሃሳቦችን የማስተናገድ አቅሙ አነስተኛ ነው። በዛ ላይ አንድ ተማሪ፣ በተመረጠለትና በተቀደደለት ቦይ የሚፈስ ሳይሆን፣ በራሱ ጥረትና መንገድ እውቀት እንዲገበይ ነው ማበረታታት የሚገባን። ሞጁሎቹን እየሸመደድን A ለማምጣት ያኔ ባይቸግረንም፣ በበኩሌ እዚህ አገር ስመጣ የተማርኩትና የሚጠበቅብኝ አራምባና ቆቦ ሆኖ ነው ያገኘሁት።

ለምሳሌ ልጥቀስ፣ እኛ የተማርንበት አብዛኛው ትዬሪ መሰረት የሚያደርገው በስታንዳርድ (ኒዮክላሲካል) ኢኮኖሚ እሳቤዎች ላይ ነው። ሌሎች እሳቤዎች እንዳሉ እንኳን አላውቅም ነበር። እነዚህ እሳቤዎች ብዙ ግዜ መሰረት እንደሌላቸውና ለመነሻ ብቻ እንደምንጠቀምባቸው ያወቅኩት እዚህ ስመጣ ነው። እሳቤዎቹን ባማሻሻል የተገነቡ Schools of thought ነፍ መሆናቸውን ያወቅኩት፣ በባችለር ደረጃ የሚሰጥ፣ ነገር ግን ማስተርስ ለመመረቅ ማንዳቶሪ የሆነ፣ ኮርስ ስወስድ ነው። Zero Transaction Cost የሚባል ነገር ትክክል አይደለም በሚል፣ Information Symmetry አለ (ሻጭና ሸማች፣ ሰራተኛና አሰሪ፣ አበዳሪና ተበዳሪ ሁሌም እኩል መረጃ አላቸው) የሚባል እሳቤ ትክክል አይደለም የሚል፣ ሰዎች ሁሌም የራሳቸውን (የግል) ጥቅም የሚያስቀድም ውሳኔ ብቻ ነው የሚወስኑት የሚለው እሳቤ ትክክል አይደለም የሚል የተለያዩ ስኩልስ ኦፍ ቶውት መኖራቸውን አላውቅም። የእነዚህ ስኩል ኦፍ ተውት መስራቾች የኖቤል ተሸላሚ የሆኑት ደግሞ አንዳንዶቹ ከመወለዴ በፊት ጭምር ነው። አንዳንዶቹ ትምህርት ከመጀመሬ በፊት ነው። የቆዬና የበለጸገ አማራጭ ትዮሪ እያለ፣ ልናውቅ የምንችልበትን አጋጣሚ ሳይፈጥሩልንና ሞጁሎቹ ውስጥ ሳያካትቱ ነው የተማርነው። ከሞጁሎቹ ውጭ እውቀት ያለ ሳይመስለን እየሸመደድን አልፈን መጣን። እዚህ ስመጣ እንቁልልጭ አልን። ኢኮኖሚክስን ሀ ብዬ ነው እንዳዲስ የተማርኩት ብል ማጋነን አይሆንም።

በዩኒቨርሲቲ ደረጃ መምህራን ሞጁል ማዘጋጀታቸው ይህን ያህል ድክመት ካለበት፣ በአገር ደረጃ እንዴት ሶስት ግለሰቦች ብቻ ባዘጋጁት ሞጁል ትውልድ እንዲታጠር ይጠበቃል? ምን አይነት እብደት ነው??! እያወራሁ ያለሁት የታሪክ ሞጁል ስለመዘጋጀቱ በተመለከተ ነው። ትውልዱ በባያዝድ ሚድያዎችና በብሔር በታጠሩ የፖለቲካ ድርጅቶች አማካኝነት የሚጋተው ተረት አንሶ በዚህ መንገድም የእውቀት አጥር ለማበጀት መሞከር ብልግና ነው። ቢያንስ አካዳሚውን ለቀቅ አድርጉት። ነጻነቱን ስጡት። የትምህርት ተቋማት፣ ከፖለቲካ አጀንዳና ርዕዮተ ዓለም የጸዱ፣ የእውቀት መናገሻ ብቻ መሆን አለባቸው። ዜጎች ክፍት በሆነና ሙሉ ነጻነት ባለው እውቀትን የመገበያያ ተቋም፣ እውቀታቸውን አዳብረው እንዲወጡ፣ ፖለቲከኞች እየገባችሁ ከመፈትፈትና ከማቡካት ብትጠበቁ ለትውልዱም ይበጃል። እንዴት እውቀት በሞጁል ይገደባል?? ያውም ገና ያልዳበረና አነጋጋሪ የሆነ የታሪክ እውቀት? (ዶክተር የሚባል ማዕርግ አድራጊ ፈጣሪነትን የሚያላብስ ዘውድ ሆነ እንዴ?!)

እውነተኛ አስተማሪዎች መንገዱን ብቻ ያሳያሉ። የተለያዩ እይታዎችን፣ ተቃራኒዎችን ጭምር፣ እኩል ያስተናግዳሉ። እነዚህን እይታዎች የሚያስተናድጉ Mandatory Reading List አዘጋጅተው ይሰጣሉ። ተማሪዎች አንብበውና አመዛዝነው የራሳቸውን ግንዛቤ ያዳብራሉ። ሳይንስ በሚጠይቀው መንገድ ሃሳባቸውን እያቀረቡ ይሞግቱ ዘንድ፣ ሃሳቦችን ውድቅ ያደርጉ ወይም ያጠናክሩ ዘንድ ነጻነቱን ስጧቸው። በሞጁል የተገደበ እውቀት ከመስጠት ይልቅ፣ አውዱንና ግዜውን በአጥጋቢ ሁኔታ ሸፍነዋል ተብሎ የሚታመንባቸውን ስራዎች በዘርፉ የዳበረ እውቀት ባላቸው ምሁራን (የውጭ ጭምር) ዝርዝር ተዘጋጅቶ ቢሰጣቸው የተሻለ አማራጭ ነው። እነዛን እያጠኑ የራሳቸውን መደምደሚያ እንዲያስቀምጡ ተማሪዎቹ እድሉ ይሰጣቸው።

ጊዜው critical thinking የሚበረታታበት፣ conformist approach የሚወገዝበት ነው። አስተማሪው የሚያምንበትን ብቻ እየሸመደድን ጽፈን A እና B ስናገኝ ያወቅን ይመስለን ነበር፣ ለካስ የአስተማሪውን እይታ conform እያደረግን ብቻ ነበር። ከጊዜው ጋር የማይሄድ ዘዴ ነው። ዜጎች ቴክኖሎጂ የፈጠረላቸውን እድል እንዳይጠቀሙ የሚያግድ ኋላ ቀር ዘዴ ነው።

እውቀት በሞጁል አይገደብም።

1 reply

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *