ፋሲል የኔአለምና ተክሌ ይሻው በዩትዩብ
… ያደረጉትን ሙሉ ቃለ ምልልስ ዛሬ ሰማሁ። ቀደም ሲል ስለ ተክሌ ይሻው የሰጠሁት አስተያየት በጽሁፍ መልክ ለፕ/ር ላጲሶ ተዘጋጅቶ የነበረ መልስ በራሱ በተክሌና በረዳት ካሜራ ማኑ እገዛ እዛው ቢሮው ውስጥ እያነበበ ተቀርጾ በሁለት ክፍል ዩቱብ ላይ የለጠፈውን አይቼና አድምጬ ነበር። ስለፋሲል የሰጠሁት አስተያየት ደግሞ የተክሌን ምላሽ ዩቱብ ላይ አይቼ ፋሲል እዚህ ፌስቡክ ላይ የጻፈውን ካነበብኩ ብኋላ ነበር። ፋሲል በጽሁፉ እንዳስቀመጠው አቶ ተክሌ ይሻው በእርግጥም ያንን በጽሁፍ መልስ ያዘጋጀውን ምላሽ በቀጥታ በኢሳት የማቅረብ እድል ሊሰጠው አይገባም ነበር። መከልከሉ በጣም ተገቢ ነው። ከዛ ይልቅ ሁለቱም ያካሄዱት መራራ ክርክር ውጤታማና አስተማሪ እንደሆነ ይሰማኛል። (ተክሌ በጽሁፍ አዘጋጅቶ እያነበበ የሰጠውን ምላሽ ያላዳመጠ ሰው ይህ አባባሌ ሊገባው ስለማይችል አስተያየት ከመስጠቱ በፊት በቅድሚያ እንዲያዳምጠው ይመከራል።)
በሁለቱ መካከል ወደ ተደረገው ቃለመጠይቁ ስንመጣ ደግሞ የሚከተለውን ሚዛናዊ እይታዬን አስቀምጣለሁ።
በቅድሚያ ቃለመጠየቁ ከቃለመጠይቅ ይልቅ ወደ ክርክር ያዘነበለ እንደነበር ይሰማኛል። የHard Talk ዓይነት ባህሪ የነበረው በመሆኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢሳትን እንደሚድያ ከልቤ ያደነቀኩበት አጋጣሚ ነበር። ባለፈው እንዳልኩት ሲሳይ አጌናን መከታተል የሚመቸኝ አቀራረቡ የዚህ ዓይነት ባህሪ ስላለው ነው። የራሱን እምነትና አቋም ቆልፎ ይዞ፡ ከተለያዩ ቦታዎች የሚሰነዘሩ ሃሳቦችን አሰባስቦ ቃለመጠይቅ ለሚደረግለት ሰው አንድባንድ በማውሳት ሲያፋጥጣቸው ሳይ ይመቸኛል። ቃለመጠይቅ ማለት መሆን ያለበት እንደዛ ነው ሰዎች ከራሳቸው ጋር የሚጋጭ ነገር ሲያወሩ እያስቆምክ አጥርቶት እንዲሄድ ማድረግ። የሌሎችን/ተቃራኒ ሃሳቦችን/ እያቀሩብ መልስ እንዲሰጡባቸው ማድረግ ወዘተ። ብዙ ጊዜ ኢሳት ላይ የምናየው ግን (ከዚህ በፊት ፕ/ር መስፍንም እንደተቹት)አንድ ሰው ለቃለመጠይቅ ከቀረበ ግራና ቀኝ ሳይወጠር በባዶ ሜዳ ብቻውን የመሰለውን እየደሰኮረ ትክክልም ይሁን ስህተት አስተሳሰቡን/ግንዛቤው ዘርግፎብን ሲወርድ ነው። እነ ጃዋር በኢሳት ሚድያ በፓልቶክ ወዘተ ዝና በዝና የሆኑት ይህን ዓይነት አጋጣሚ ተጠቅመው ነው። ወጥሮ የሚይዛቸው በሌለበት የመሰላቸውን እያወሩ ከመድረኩ ሲወርዱ በተከታዮቻቸው ዘንድ እንደ ብቸኛ አዋቂ የተቆጠሩበት ብሎም እነሱም ወደ ትምክህት ደረጃ የደረሱበት በዚህ የተሳሳተ የሚድያ አካሄድ ይመስለኛል።
በዚህ ረገድ ፋሲል የኔአለም ጥሩ ጅምር ነው የጀመረው ሊበረታታ ይገባል። ባይሆን ለፋሲል የምተቸው ነገር ቢኖር በተክሌ ይሻው ላይ የነበረውን ያክል ጥንካሬ በፕ/ር ላጲሶ ላይ አለማሳየቱ ነው። እሳቸው ላይ በጣም ለዘብተኛ ነበር። እውነቱን ለመናገር እሳቸው በጣም ዘባርቀዋል። እርስበእርሱ የሚጋጭ ነገር በየደቂቃው ባናት ባናቱ ሲያቀርቡ ነበር። ከነዛ መካከል በወቅቱ እዚህ የፌስቡክ ገጼ ላይ ለቀልድ እንዳስቀመጥኩት፡ ተክሌ ይሻውም በዚህ ቃለ ምልልስ እያነሳ መልስ ለመስጠት እንደሞከረው ብዙ የዘባረቁት ነገር ነበር። ለምሳሌ ኦሮሞ የሰፈረበት ምድር የኦሮሞ ነው፡ አዲስአበባ የኦሮሞ ናት፡ ኦሮሞ እዚሁ የነበረ ነው (በጥሶ የገባ ጀግና እንጂ ወርሮ አይደለም)ወዘተ ዓይነት ዝብረቃዎች በፋሲል በቀላሉ ሊታለፉ የማይገባቸው እና ፕ/ሩ እንዲያጠሩት መወጠር የነበረባቸው ጉዳዮች ናቸው። እዚህ ላይ ተክሌ ይሻው ውነት አለው። መልስ የሚያስፈልጋቸው አንኳር ጉዳዮች ነበሩ።
የክርክሩ ዋና ጭብጥ መስሎ የተሰማኝ ደግሞ፡ “ላጲሶ የኢትዮጵያን ታሪክ ሰርዘን እንጽፈዋለን ማለታቸው የአማራን አንገት ለማስደፋት ወይም ለአማራ ካላቸው ጥላቻ የተነሳ ነው” የሚለው የተክሌ ክስ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ፋሲል በጣም ተገቢ የሆነና በሳል አቋም ይዞ ተክሌን ማፋጠጡ ተገቢ ነው እላለሁ። ለምን? ለሁሉም ግልጽ እንደሆነው የኢትዮጵያ ታሪክ ተብሎ የምናውቀው ሚዛኑ በቅድሚያ ወደ ነገስታቱ ቀጥሎም ወደ ቤ/ክ/ያን ቀጥሎም ወደ ሰሜኑ ክፍል እያለ በመጨረሻ ወደ ጋራና ሸንተረሩ የሚያመዝን ሆኖ ነው የምናገኘው። ህዝቡንና አኗኗሩን በሚመለከት፡ የኢኮኖሚ የፖለቲካና የማህበራዊ ተቋማትን የሚመለከት ታሪክ በጣም ውሱን ሲሆን ከሰሜኑ በታች ስላለው ያገሪቱ ክፍል ደግሞ ከአፈታሪክ ያልዘለለ ታሪክ እናገኛለን።
የታሪክ ባለሞያዎች የተጻፉትን ታሪኮች የማረጋገጥ ያልተጻፉትን የማጥናት የሞያ ግዴታ አለባቸው። ሁሉንም የሚያስማማ ታሪክ አለን ማለት አይቻልም፡ ዓይናውጣነት ካልሆነ በስተቀር፡ የለንም። ያ ነው ሃቁ። ስለዚህ የማናውቀው ተጠንቶ የሚታወቀው ተረጋግጦና ተጣርቶ የአገሪቱን አጠቃላይ ታሪክ መጻፍና ማጥናት ወደፊትም ለዘመናት የሚቆይ የባለሞያዎች ስራ ነው። ላጲሶ እንጽፋለን ማለታቸው ተክሌን ለምን እንዳስቆጣው እና አማራን ከመጥላት ጋር ለምን እንዳያያዘው ግራ የሚያጋባ ነው። ፋሲል ይህንን አንኳር ነጥብ ለመሞገት መሰለኝ አብዛኛውን ሰዓት ተክሌን በማፋጠጥ ያጠፋው።
ላጲሶ አዲስ የኢትዮጵያ ታሪክ እየጻፍኩ ነው ማለታቸው ስህተቱ ምኑ ላይ ነው?ያን ሁላ ሰዓት ያከራከረው የተክሌ ምክንያቱ ምንድን ነው?ከመጻፍ እንዲቆጠቡ ነው ወይስ ምን?ላጲሶ እኮ ከዚህ በፊት ስለአገሪቱ ጽፈዋል። ታሪክ ቴክኖሎጂ አይደል ነገር በየጊዜው አዳዲስ ፈጠራ አይጨመርበት። ድሮ የጻፉትን ሽረው አዲስ ነገር ሊጽፉ ይሁን ወይም መጠነኛ ማስተካከያ ሊያቀርቡ አናውቅም። እስኪጽፉት ድረስ መጠበቅ ግድ ነው። ያኔ ተገቢውን መልስ ባለሞያዎቹም ሆኑ ህዝቡ ይሰጣቸዋል። ከወዲሁ ቡራከረዮ ማለት ግን ታሪክን በሞኖፖል ለመቆጣጠር ከመቋመጥ ለይቼ አላየውም እኔ።
የታሪክ ባለሞያዎች ከየትም ይምጡ ከየት ሙያቸው በሚፈቅደው መንገድ ስለአገራቸው ስለህዝቡ ወዘተ አቅማቸው የፈቀደውን ያህል ይጻፉ። የተጻፈውን የሚሽር ሊሆንም እኮ ይችላል። ሙያው በሚፈቅድላቸው መንገድ እስካጠኑትና እውነት እስከጻፉ ድረስ ማንም ምንም ሊል አይችልም። ከዘባረቁ ደግሞ ፍርዳቸውን ያገኛሉ። የቸገረን ከሙያው ውጪ ያለው ሰው እኔ ያልኩት ብቻ ለምን አይሆንም የሚል መብዛቱ ነው። ታሪክ ከተለያየ አቅጣጫ ታይቶ መጻፉ ክፋት የለውም፡ ለውይይት ለክርክር ለጥናት ለምርምር ወዘተ በር ይከፍታል እንጂ። ቆንጆዎቹ ሲወለዱ ደግሞ እንክርዳዱን ገለባውን ምኑን ለይተው ህዝቡን በጠቅላላ የሚያግባባ የነጠረ ታሪክ ይጽፋል። እስከዛው ግን የኢትዮጵያን ታሪክ ትነኩ እና ዋ!የኢትዮጵያ ታሪክ መነካካት ለአማራ ያላችሁን ጥላቻ የሚገልጽ ነው፡ ወዘተ የሚሉ የቁራ ጩኸቶች ከስህተትም በላይ ከዚህ በፊት እንዳልኩት ኢትዮጵያዊነትን ከአማራነት ለይቶ/ነጥሎ ማየት ያለመቻል ቀውስ/ውዝንብር ነው።
መልካም ቅዳሜ!