ፌስቡክ ነጻ ነውን?
ፌስቡክ የፈለግነውን ያህል አካውንት በነጻ መክፈት እንችላለን። የፈለግነውን ነገር ያለ ገደብ መጻፍ፣ መለጠፍ፣ መኮመንት፣ ማካፈል ወዘተ እንችላለን። የኮፒ ራይት ኢሹ የማያስነሳና መሰረታዊ ስነምግባሮችን የማይጥስ እስከሆነ ድረስ።
ያም ሆኖ ፌስቡክ ነጻ ነውን? በእርግጥ አንዳንዶቻችን ሲም ገዝተን በየጊዜው ሲያልቅ መሙላት ሊጠበቅብን ይችላል። ትንሽ ቢሆንም ይህ ራሱን የቻለ ወጪ ነው። ይሁንና ኢንተርኔት በነጻ የመጠቀም እድሉ ላለንስ ፌስቡክ ነጻ ነውን?
መልሱን ለናንተ ልተወውና ኢኮኖሚክስ ያስተማረችኝን ላካፍላችሁ። እያንዳንዱ ነገር ዋጋው የሚተመነው ባለው ኦፖርቺኒቲ ኮስት ነው። አንድ ጫማ ለመስራት 40 ሰዓት የሚፈጅብኝ ከሆነና አንድ ሱሪ ለመስፋት 20 ሰዓት የሚፈጅብኝ ከሆነ ፣ ጫማ ለመስራት ከፈለግኩ በገበያ መሸጫ ዋጋው ቢያንስ ከሱሪው ዋጋ እጥፍ መሆን አለበት። ካልሆነ በ40 ሰዓቱ ሁለት ሱሪ አምርቶ ለገበያ ማቅረብ ያዋጣኛል።
ፌስቡክ በቀን ሁለት ሰዓት የማጠፋ ከሆነ፣ ያጠፋሁትን ሰዓት ያህል የሆነ ጥቅም (ትርፍ/እርካታ/ወዘተ) ማግኘት መቻል አለብኝ። በገንዘብ ለመተመን ከተፈለገ፣ ፌስቡክ በመጠቀም ባጠፋሁት ሰዓት ፋንታ በተሰማራሁበት ዘርፍ ተጨማሪ ስራ ሰርቼ ቢሆን ኖሮ ምን ያህል ገቢ አገኝ ነበር ብለን ማስላት እንችላለን። ተመኑ እንደየገቢያችንና እንደየሙያችን ይለያያል። በሰዓት ከፍተኛ ክፍያ የሚያገኙ ሰዎች፣ ለፌስቡክ የሚመድቡት ሰዓት ይቀንሳል። ዜሮ ሊሆንም ይችላል። በአንጻሩ ደግሞ ስራ የሌለው ሰው አብዛኛውን ሰዓት ለፌስቡክ ሊመድብ ይችላል። እርካታን ለማግኘት ሌላ የተሻለ አማራጭ እስከሌለው ድረስ።
ኢኮኖሚስቶች በአንድ ወቅት ያደረጉት ጥናት እንደሚያመላክተው ፌስቡክ ከ1ቢልዮን በላይ ተጠቃሚ ሲኖሩት በቀን ወደ 250 ሚልዮን ሰዓታት ይጠቀማሉ። አንድ ሰው በሰዓት የሚከፈለው ዝቅተኛ ደሞዝ ግምት ውስጥ አስገብተን ብናሰላው (በምዕራቡ ዓለም 6ዶላር ሲሆን በድሃ አገራት ደግሞ 1ዶላር ነው) የፌስቡክ አማካይ የቀን ገቢ ቢያንስ 875ሚልዮን ዶላር መሆን አለበት ማለት ነው። እና ፌስቡክ ነጻ ነውን?
በቀን አንድ ሰዓት ፌስቡክ ላይ ካጠፋችሁ ቢያንስ 20 ብር (1ዶላር) በቀን አጥታችኋል ማለት ነው። ለአንድ ሰዓት ስትጠቀሙ 20 ብር የሚያህል ጥቅም አገኛችሁበት? በምዕራቡ ዓለም የምትኖሩ ከሆነ ደግሞ ቢያንስ 6ዶላር አጥታችኋል። በአንድ ሰዓት የፌስቡክ ቆይታችሁ ያጣችሁትን ገንዘብ ያህል ጥቅም አግኝታችሁበታል? መልሱን ለራሳችሁ ልተወውና በአንዲት መልዕክት ጽሁፌን ልቋጭ።
ፌስቡክን ከተጠቀማችሁ አይቀር wisely ተጠቀሙበት። ነጻ አይደለም። የምታባክኑትን ሰዓት ያህል ጥቅም ማግኘት ወይም መልዕክት ማስተላለፍ ይኖርባችኋል። ካልሆነም put your time on another productive activity – በሽተኞችን ፣ እስረኞችን ጎብኙበት፣ ለህጻናት መጽሀፍ አንብቡበት፣ ቤተመጻህፍት ጎብኙበት፣ ወዘተ
ሰናይ መዓልቲ