ምዕራፍ አሥራ አንድ#
ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች#
አንቀጽ 93 ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ#
ሀ/ የውጭ ወረራ ሲያጋጥም ወይም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰትና በተለመደው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይቻል ሲሆን፣ ማናቸውም የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የሕዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት፣ የፌዴራሉ መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመደንገግ ሥልጣን አለው፡፡
ለ/ የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የሕዝብን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት የክልል መስተዳድሮች በክልላቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊያውጁ ይችላሉ፡፡ዝርዝሩ ክልሎች ይህን ሕገ መንግሥት መሰረት በማድረግ በሚያወጧቸው ሕገመንግሥቶች ይወሰናል፡፡
በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 /ሀ/ መሰረት የሚታወጅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣
ሀ/ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሥራ ላይ ባለ ጊዜ የታወጀ ከሆነ በታወጀ በአርባ ስምንት ሰዓታት ውስጥ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረብ አለበት አዋጁ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለት ሦስተኛው ድምጽ ተቀባይነት ካላገኘ ወዲያውኑ ይሻራል፡፡
ለ/ ከላይ በንዑስ አንቀጽ /ሀ/ ሥር የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሥራ ላይ ባልሆነበት ወቅት የሚታወጅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረብ ያለበት አዋጁ በታወጀ በአሥራ አምሥት ቀናት ውስጥ ነው፡፡
በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በምክር ቤቱ ተቀባይነት ካገኘ በኝላ ሊቆይ የሚችለው እስከ ስድስት ወራት ነው፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምጽ አንድን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በየአራት ወሩ በተደጋጋሚ እንዲታደስ ሊያደርግ ይችላል፡፡
ሀ/ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚታወጅበት ጊዜ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣቸው ደንቦች መሰረት የሀገርን ሰላምና ሕልውና፣ የሕዝብን ደህንነት፣ሕግና ሥርዓትን የማስከበር ሥልጣን ይኖረዋል፡፡
ለ/ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሥልጣን በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡትን መሰረታዊ የፖለቲካና የዴሞክራሲ መብቶችን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማወጅ ምክንያት የሆነውን ጉዳይ ለማስወገድ ተፈላጊ ሆኖ በተገኘውደረጃ፣ እስከ ማገድ ሊደርስ የሚችል ነው፡፡
ሐ/ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥራ የሚያወጣቸው ድንጋጌዎችና የሚወስዳቸው እርምጃዎች በማናቸውም ረገድ በዚህ ሕገመንግሥት አንቀጽ 1፣፣ 88፣ 25፣ እና 39 ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 የተቀመጡትን መብቶች የሚገድቡ ሊሆኑ አይችሉም፡፡
በሀገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚታወጅበት ወቅት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአባላቱና ከሕግ ባለሙያዎች መርጦ የሚመድባቸው ሰባት አባላት ያሉት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ ያቋቁማል፡፡ ቦርዱ አዋጁ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚጸድቅበት ጊዜ ይቋቋማል፣
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ የሚከተሉት ሥልጣንና ኃላፊነቶች አሉት፡፡
ሀ/ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት የታሰሩትን ግለሰቦች ስም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ይፋ ማድረግና የታሰሩበትን ምክንያት መግለጽ፣
ለ/ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የሚወሰዱት እርምጃዎች በማናቸውም ረገድ ኢሰብዓዊ አለመሆናቸውን መቆጣጠርና መከታተል፣
ሐ/ ማናቸውም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እርምጃ ኢሰብዓዊ መሆኑን ሲያምንበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም የሚኒስሮች ምክር ቤት እርምጃውን እንዲያስተካክል ሐሳብ መስጠት፣
መ/ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እርምጃዎች ኢሰብዓዊ ድርጊት የሚፈጽሙትን ሁሉ ለፍርድ እንዲቀርቡ ማድረግ፣
ሠ/ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲቀጥል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄ ሲቀርብ ያለውን አስተያየት ለምክር ቤቱ ማቅረብ፡፡
አንቀጽ 94 የፋይናንስ ወጪን በሚመለከት#
የፌዴራሉ መንግሥትና ክልሎች በሕግ የተሰጧቸውን ኃላፊነቶችና ተግባሮች ለማከናወን የሚያስፈልጋቸውን ወጪ በየበኩላቸው ይሸፍናሉ፤ ሆኖም ማንኛውም ክልል በውክልና ለሚፈጽመው ተግባር የሚያስፈልገው ወጪ ሌላ ስምምነት ከሌለ በቀር ውክልናውን በሰጠው ወገን ይሸፈናል፡፡
የፌዴራሉ መንግሥት ለክልሎች የተመጣጠነ እድገት እንቅፋት ካልሆነ በስተቀር ለአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ፣ ለመልሶ መቋቋምና ለልማት ማስፋፊያ ለክልሎች ብድርም ሆነ እርዳታ ሊሰጥ ይችላል፡፡ የፌዴራሉ መንግሥት ክልሎች ለሚያስፈልጋቸው ወጪ የሚያደርገውን ድጐማ በሚመለከት ኦዲትና ቁጥጥር የማድረግ ሥልጣን ይኖረዋል፡፡
አንቀጽ 95 የፋይናንስ ገቢን በሚመለከት#
የፌዴራሉ መንግሥትና ክልሎች የሚዋቀረውን የፌዴራል አደረጃጀት የተከተለ የገቢ ክፍፍል ያደርጋሉ፡፡
አንቀጽ 96 የፌዴራል መንግሥት የታክስና የግብር ሥልጣን#
የፌዴራል መንግሥት በወጪና ገቢ ዕቃዎች ላይ የጉምሩክ ቀረጥ፣ የታክስና ሌሎች ክፍያዎች ይጥላል፣ ይሰበስባል፡፡
በፌዴራል መንግሥትና በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተቀጣሪዎች ላይ የሥራ ግብር ይጥላል፣ ይሰበስባል፡፡
በፌዴራል መንግሥት ባለቤትነት ሥር በሆኑ የልማት ድርጅቶች ላይ የንግድ ትርፍ ግብር፣ የሥራ ግብር፣ የሽያጭና የኤክሳይስ ታክስ ይጥላል፣ ይሰበስባል፡፡
በብሔራዊ የሎተሪ እና ሌሎች የዕድል ሙከራ ገቢዎች ላይ ታክስ ይጥላል፣ይሰበስባል፡፡
በአየር፣ በባቡርና በባሕር ትራንስፖርት ገቢዎች ላይ ታክስ ይጥላል፣ ይሰበስባል፡፡
በፌዴራል መንግሥት ባለቤትነት ሥር በሚገኙ ቤቶችና ሌሎች ንብረቶች ገቢ ላይ ግብር ይጥላል፣ ይሰበስባል፤ ኪራይ ይወስናል፡፡
የፌዴራል መንግሥት አካላት ከሚሰጧቸው ፈቃዶችና አገልግሎቶች የሚመነጩ ክፍያዎችን ይወስናል፣ ይሰበስባል፡፡
የሞኖፖል ታክስ ይጥላል፣ ይሰብሰባል፡፡
የፌዴራል የቴምብር ሽያጭ ቀረጥ ይጥላል፣ ይሰበስባል፡፡
አንቀጽ 97 የክልል መስተደድሮች የታክስና የግብር ሥልጣን#
ክልሎች፣ በክልል መስተዳድርና በድርጅት ተቀጣሪዎች ላይ የሥራ ግብር ይጥላሉ፣ ይሰበስባሉ፡፡
የመሬት መጠቀሚያ ክፍያ ይወስናሉ፣ ይሰበስባሉ፡፡
በግል የሚያደርሱና በኅብረት ሥራ ማኅበራት በተደራጁ ገበሬዎች ላይ የእርሻ ሥራ ገቢ ግብር ይጥላሉ፣ ይሰበስባሉ፡፡
በክልሉ በሚገኙ ግለሰብ ነጋዴዎች ላይ የንግድ ትርፍ ግብርና የሽያጭ ታክስ ይጥላሉ፣ ይሰበስባሉ፡፡
በክልሉ ውስጥ በውኃ ላይ ከሚደረግ ትራንስፖርት በሚገኝ ገቢ ላይ ግብር ይጥላሉ፣ ይሰበስባሉ፡፡
በክልል መስተዳድር በግል ባለቤትነት ሥር ካሉ ቤቶችና ሌሎች ንብረቶች በሚገኝ ገቢ ላይ ግብር ይጥላሉ፣ ይሰበስባሉ፣ በባለቤትነታቸው ሥር ባሉ ቤቶችና ሌሎች ንብረቶች ላይ ኪራይ ያስከፍላሉ፡፡
በክልል መስተዳድር ባለቤትነት ሥር በሚገኙ የልማት ድርጅቶች ላይ የንግድ ትርፍ፣ የሥራ ግብር፣ የሽያጭና ኤክሳይስ ታክስ ይጥላሉ፣ ይሰበስባሉ፡፡
ብአንቀጽ 98 ንዑስ አንቀጽ 3 የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በማዕድን ሥራዎች ላይ የማዕድን ገቢ ግብር፣ የሮያሊቲና የመሬት ኪራይ ክፍያዎች ይጥላሉ፣ይሰበስባሉ፡፡
በክልል መስተዳድር አካላት ከሚሰጡ ፈቃዶችና አገልግሎቶች የሚመነጩ ክፍያዎች ይወስናሉ፣ ይሰበስባሉ፡፡
ከደን የሚገኝ የሮያሊቲ ክፍያ ይወስናሉ፣ ይሰበስባሉ፡፡
አንቀጽ 98 የጋራ የታክስና የግብር ሥልጣን#
የፌዴራል መንግሥትና ክልሎች በጋር በሚያቋቁሟቸው የልማት ድርጅቶች ላይ የንግድ ትርፍ ግብር፣ የሥራ ግብር፣ የሽያጭና የኤክሳይስ ታክስ በጋራ ይጥላሉ፣ይሰበስባሉ፡፡
በድርጅቶች የንግድ ትርፍ ላይ እና በባለ አክሲዮኖች የትርፍ ድርሻ ላይ ግብርና የሽያጭ ታክስ በጋራ ይጥላሉ፣ ይሰበስባሉ፡፡
በከፍተኛ የማዕድን ሥራዎችና በማናቸውም የፔትሮሊየምና የጋዝ ሥራዎች ላይ የገቢ ግብርና የሮያሊቲ ክፍያዎች በጋራ ይጥላሉ፣ ይሰበስባሉ፡፡
አንቀጽ 99 ተለይተው ስላልተሰጡ የታክስ እና የግብር ሥልጣኖች#
በዚህ ሕገ መንግሥት ተለይተው ያልተሰጡ ታክስና ግብር የመጣል ሥልጣኖችን በሚመለከት የፌዴሬሽኑ ምክር ቤትና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጋራ ስብሰባ በሁለት ሦስተኛ ድምጽ ይወስናሉ፡፡
አንቀጽ 100 የታከስና የግብር አጣጣል መርሆዎች#
ክልሎችና የፌዴራሉ መንግሥት ታክስና ግብር በሚጥሉበት ጊዜ የሚጠየቀው ታክስና ግብር ከምንጩ ጋር የተያያዘና በአግባቡ ተጠንቶ የተወሰነ መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡
በመካከላቸው የሚኖረውን መልካም ግንኙነት የማይጐዳና ከሚቀርበው አገልግሎት ጋር ተመጣጣኝ መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡
ለትርፍ የቆመ ድርጅት ካልሆነ በስተቀር ክልሎች በፌዴራሉ መንግሥት ንብረት ላይ፣ የፌዴራሉ መንግሥትም በክልሎች ንብረት ላይ ግብር ወይም ቀረጥ የማስከፈል ሥልጣን አይኖራቸውም፡፡
አንቀጽ 101 ዋናው ኦዲተር#
ዋናው ኦዲተር በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርቢነት በሕዝብ ተወካዮቸ ምክር ቤት ይሾማል፡፡
ዋናው ኦዲተር የፌዴራሉን የሚኒስቴርና ሌሎች መሥሪያ ቤቶች ሂሳቦች በመቆጣጠር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተመደበው ዓመታዊ በጀት፣ በበጀት ዓመቱ ለተሰሩት ሥራዎች በሚገባ መዋሉን መርምሮ ለምክር ቤቱ ሪፖርት ያቀርባል፡፡
ዋናው ኦዲተር የመሥሪያ ቤቱን በጀት በቀጥታ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ ያስጸድቃል፡፡
የዋናው ኦዲተር ዝርዝር ተግባር በሕግ ይወሰናል፡፡
አንቀጽ 102 የምርጫ ቦርድ#
በፌዴራልና በክልል የምርጫ ክልሎች ነጻና ትክክለኛ ምርጫ በገለለተኝነት እንዲያካሂድ ከማንኛውም ተጽእኖ ነጻ የሆነ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ይቋቋማል፡፡
የቦርዱ አባላት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሾማሉ፡፡ ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል፡፡
አንቀጽ 103 የሕዝብ ቆጠራ ኮሚሽን#
የሀገሪቱን የሕዝብ ቁጥር በየጊዜው የሚያጠናና ቆጠራ የሚያካሂድ የሕዝብ ቆጠራ ኮሚሽን ይኖራል፡፡
የኮሚሽኑ አባላት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሾማሉ፡፡
ኮሚሽኑ ዋና ጸሐፊ፣ አስፈላጊ ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ይኖሩታል፡፡
የኮሚሽኑ ዓመታዊ በጀት በቀጥታ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ይጸድቃል፡፡
የሕዝብ ቆጠራ በየአሥር ዓመቱ ይካሔዳል፡፡ በውጤቱም መሰረት የምርጫ ክልሎችን አከላለል የምርጫ ቦርድ በሚያቀርበው ረቂቅ መሠረት የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት ይወስናል፡፡
የኮሚሽኑ ተጠሪነት ለሕዝብ ተወካዮቸ ምክር ቤት ነው፡፡ ስለ ሥራው አፈጻጸፍ በየጊዜው ለምክር ቤቱ ሪፖርት ያቀርባል፡፡
አንቀጽ 104 የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሐሳብን ስለማመንጨት#
አንድ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሐሳብ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምጽ የደገፈው፣ የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምጽ የደገፈው ወይም ከፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች ውስጥ አንድ ሦስተኛው የክልል ምክር ቤቶች በድምጽ ብልጫየደገፉት ከሆነ ለውይይትና ለውሳኔ ለመላው ሕዝብና የሕገ መንግሥቱ መሻሻል ለሚመለከታቸው ክፍሎች ይቀርባል፡፡
አንቀጽ 105 ሕገ መንግሥቱን ስለማሻሻል#
1 በዚህ ሕገ መንግሥት ምዕራፍ ሦስት የተዘረዘሩት መብቶችና ነጻነቶች በሙሉ፣ይህ አንቀጽ፣ እንዲሁም አንቀጽ 104 ሊሻሻሉ የሚችሉት በሚከተለው አኳቃን ብቻ ይሆናል፡፡ - ሀ/ ሁሉም የክልል ምክር ቤቶች የቀረበውን ማሻሻያ በድምጽ ብልጫ ሲያጸድቁት፣ - ለ/ የፌዴራሉ መንግሥት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምጽ የቀረበውን ማሻሻያ ሲያጸድቀው፣ እና - ሐ/ የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምጽ ማሻሻያውን ሲያጸድቀው ነው፡፡ 2. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 ከተዘረዘሩት ውጭ ያሉት የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች ሊሻሻሉ የሚችሉት በሚከተለው አኳኊን ብቻ ይሆናል፤ - ሀ/ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት በጋራ ስብሰባ በሁለት ሦስተኛ ድምጽ የቀረበውን ማሻሻያ ሲያጸድቁት፣ እና - ለ/ ከፌዴሬሽኑ አባል ክልሎቸ ምክር ቤቶች ውስጥ የሁለት ሦስተኛ ክልሎች ምክር ቤቶች በድምጽ ብልጫ የቀረበውን ማሻሻያ ሲያጸድቁት ነው፡፡
አንቀጽ 106 የመጨረሻ ሕጋዊ እውቅና ስላለው ቅጂ#
የዚህ ሕገመንግሥት የአማርኛ ቅጂ የመጨረሻው ሕጋዊ እውቅና ያለው ሰነድ ነው፡፡