ምዕራፍ ስምንት#

የሕግ አስፈጻሚ አካል#

አንቀጽ 72 ስለ አስፈጻሚነት ሥልጣን#

  1. የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ የአስፈጻሚነት ሥልጣን የተሰጠው ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ነው፡፡

  2. ጠቅላይ ሚኒስትሩና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪዎች ናቸው፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላት በመንግሥት ተግባራቸው በጋራ ለሚሰጡት ውሳኔ የጋራ ኃላፊነት አለባቸው፡፡

  3. በዚህ ሕገ መንግሥት መሰረት በሌላ አኳኊን ካልተወሰነ በስተቀር የጠቅላይሚኒስትሩ የሥራ ዘመን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ዘመን ነው፡፡

አንቀጽ 73 የጠቅላይ ሚኒስትሩ አሰያየም#

  1. ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መካከል ይመረጣል፡፡

  2. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብላጫ መቀመጫ ያገኘው የፖለቲካ ድርጅት ወይም ያገኙት የፖለቲካ ድርጅቶች የመንግሥት ሥልጣን ይረከባል/ይረከባሉ፡፡

አንቀጽ 74 የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣንና ተግባር#

  1. ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሀገሪቱ ርዕሰ መስተዳድር፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ነው፡፡

  2. ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባሎችን ከሁለቱ ምክር ቤቶች አባላት ወይም ለሥራው ብቃት ካላቸው ሌሎች ግለሰቦች መካከል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በእጩነት አቅርቦ ሹመታቸውን ያጸድቃል፡፡

  3. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያወጣቸው ሕጐች፣ ፖሊሲዎች፣ መመሪያዎችና ውሳኔዎች ተግባራዊ መሆናቸውን ይከታተላል፣ ያረጋግጣል፡፡

  4. የሚኒስትሮች ምክር ቤትን ይመራል፣ ያስተባብራል፣ ይወክላል፡፡

  5. የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣቸውን ፖሊሲዎች፣ ደንቦች መመሪያዎችና ውሳኔዎች ተፈጻሚነት ይከተተላል፡፡

  6. የሀገሪቱን የውጭ ፖሊሲ በበላይነት ያስፈጽማል፡፡

  7. ኮሚሽነሮችን፣ የማዕከላዊ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኘሬዚዳንትና ምክትል ኘሬዚዳንትን እና ዋና ኦዲተርን መርጦ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሹመታቸውን ያጸድቃል፡፡

  8. የመስተዳድሩን ሥራ አፈጻጸምና ብኝት ይቆጣጠራል፣ አስፈላጊ የሆኑ የእርምት እርምጃዎችን ይወስዳል፡፡

  9. በዚሀ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 እና 7 ከተዘረዘሩት ውጭ የሆኑ ከፍተኛ የመንግሥት የሲቪል ሹመቶችን ይሰጣል፡፡

  10. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚያወጣው ሕግ ወይም በሚሰጠው ውሳኔ መሠረት ኒሻኖችንና ሽልማቶችን ለኘሬዚዳንቱ አቅርቦ ያሰጣል፡፡

  11. ስለ ሀገሪቱ ሁኔታ፣ በመንግሥት ስለተከናወኑ ተግባራትና ስለወደፊት እቅዶች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየወቅቱ ሪፖረት ያቀርባል፡፡

  12. በዚህ ሕገ መንግሥትና በሌሎች ሕጐች የተሰጡትን ሌሎች ተግባሮች ያከናውናል፡፡

  13. ሕገ መንግሥቱን ያከብራል፤ የስከበራል፡፡

አንቀጽ 75 ስለ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር#

  1. ምክትል ጠቅላይሚኒስትሩ፣

    • ሀ/ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተለይተው የሚሰጡትን ተግባሮች ያከናውናል፤

    • ለ/ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማይኖርበት ጊዜ ተክቶት ይሰራል፡፡

  2. ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሆናል፡፡

አንቀጽ 76 የሚኒስትሮች ምክር ቤት#

  1. የሚኒስትሮች ምክር ቤት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስተር፣ ሚኒስትሮችና በሕግ በሚወሰን መሰረት ሌሎች አባሎች የሚገኙበት ምክር ቤት ነው፡፡

  2. የሚኒስትሮች ምክር ቤት ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒሰትሩ ነው፡፡

  3. የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለሚወስነው ውሳኔ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪ ነው፡፡

አንቀጽ 77 የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባር#

  1. የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወጡ ሕጐችና የተሰጡ ውሳኔዎች በሥራ መተርጐማቸውን ያረጋግጣል፣ መመሪያዎችን ይሰጣል፡፡

  2. የሚኒስትሮችንና በቀጥታ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ተጠሪ የሆኑ ሌሎች የመንግሥት አካላትን አደረጃጀት ይወስናል፣ ሥራቸውን ያስተባብራል፣ ይመራል፡፡

  3. የፌዴራሉን መንግሥት ዓመታዊ በጀት ያዘጋጃል፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀርባል፣ ሲጸድቅም ተግባራዊነቱን ያረጋግጣል፡፡

  4. የገንዘብና የፋይናንስ ፖሊሲን ተግባራዊነት ያረጋግጣል፣ ብሔራዊ ባንክን ያስተዳድራል፣ ገንዘብ ያትማል፣ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ይበደራል፣ የውጭ ምንዛሪና የገንዘብ ልውውጥን ይቆጣጠራል፡፡

  5. የፈጠራና የኪነ ጥበብ መብቶችን ያስጠብቃል፡፡

  6. የኢኮኖሚያዊ፣ የማኅበራዊና የልማት ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎችን ይነድፋል፣ ያስፈጽማል፡፡

  7. አንድ ወጥ የመለኪያ ደረጃዎችና የጊዜ ቀመር ያወጣል፡፡

  8. የሀገሪቱን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ያወጣል፣ የስፈጽማል፡፡

  9. ሕግና ሥርዓት መከበሩን ያረጋግጣል፡፡

  10. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያውጃል፣ በዚህ ሕገ መንግሥት በተደነገገው የጊዜ ወሰን ውስጥ፣ የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ ያስጸድኝል፡፡

  11. የጦርነት ጉዳዮችን ጨምሮ በማናቸውም ጉዳዮች ላይ የሕግ ረቂቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀርባል፡፡

  12. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሰጡትን ሌሎች ተግባሮች ያከናውናል፡፡

  13. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚሰጠው ሥልጣን መሠረት ደንቦችን ያወጣል፡፡