ምዕራፍ ሰባት#
ስለ ሪፐብሊኩ ኘሬዚዳንት#
አንቀጽ 69 ስለ ኘሬዚዳንቱ#
ኘሬዚዳንቱ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ርዕሰ ብሔር ነው፡፡
አንቀጽ 70 የኘሬዚዳንቱ አሰያየም#
ለኘሬዚዳንትነት እጩ የማቅረብ ሥልጣን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡
የቀረበው እጩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና በፌዴሬሽኑ ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ በሁለት ሦስተኛ ድምጽ ከተደገፈ ኘሬዚዳንት ይሆናል፡፡
የምክር ቤት አባል ኘሬዚዳንት ሆኖ ከተመረጠ የተወከለበትን ምክር ቤት ወንበር ይለቃል፡፡
የኘሬዚዳንቱ የሥራ ዘመን ስድስት ዓመት ይሆናል፡፡ አንድ ሰው ከሁለት ጊዜ በላይ ለኘሬዚዳንትነት ሊመረጥ አይችል፡፡
የሪፐብሊኩ ኘሬዚዳንት ምርጫ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 መሰረት ከጸደቀ በኊላ ሥራውን ከመጀመሩ በፊት የጋራ ስብሰባው በሚወስነው ጊዜ ስብሰባው ፊት ለሕገ መንግሥቱና ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ያለውን ታማኝነት በሚቀጥሉት ቃላት ይገልጻል፡፡ «እኔ ……. በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኘሬዚዳንት በመሆን ሥራዬን ስጀምር የተጣለብኝን ከፍተኛ ኃላፊነት በታማኝነት ለመፈጸም ቃል እገባለሁ፡፡»
አንቀጽ 71 የኘሬዚዳንቱ ሥልጣንና ተግባር#
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽኑን ምክር ቤት ዓመታዊ የጋራ ስብሰበባ ይከፍታል፡፡
በዚህ ሕገ መንግሥት መሰረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያጸደቃቸው ሕጐችና ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በነጋሪት ጋዜጣ ያውጃል፡፡
ሀገሪቷን በውጭ ሀገሮች የሚወክሉትን አምባሳደሮችና ሌሎች መልክተኞች በጠ ቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት ይሾማል፡፡
የውጭ ሀገር አምሳደሮችንና የልዩ መልዕክተኞችን የሹመት ደብዳቤ ይቀበላል፡፡
በሕግ መሰረት ኒሻኖችና ሽልማቶችን ይሰጣል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕግ በተወሰነው መሰረት ከፍተኛ የውትድርና ማዕረጐችን ይሰጣል፡፡
በሕግ መሰረት ይቅርታ ያደርጋል፡፡