ምዕራፍ ስድስት#
ስለፌዴራሉ መንግሥት ምክር ቤቶች#
አንቀጽ 53 የፌዴራል መንግሥት ምክር ቤቶች#
የፌዴራሉ መንግሥት ሁለት ምክር ቤቶች ይኖሩታል፤ እነዚህም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ናቸው፡፡
ክፍል አንድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት#
አንቀጽ 54 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት#
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፤ ሁሉ አቀፍ፣ ነጻ ፣ ቀጥተኛ፣ ትክክለኛ በሆነና ድምጽ በሚስጥር በሚሰጥበት ሥርዓት በየአምስት ዓመቱ በሕዝብ ይመረጣሉ፡፡
የምክር ቤቱ አባላት በአንድ የምርጫ ክልል ውስጥ ከሌሎች ተወዳዳሪዎች መካከል አብላጫ ድምጽ ያገኘ ተወዳዳሪ አሸናፊ በሚሆንበት የምርጫ ሥርዓት ይመረጣሉ፡፡ የተለየ ውክልና ያሰፈልጋቸዋል ተብሎ የታመነባቸው አናሳ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በምርጫ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ይሆናሉ፡፡ ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት ቁጥር የሕዝብ ብዛትንና በልዩ ትኩረት ውክልና የሚሰጣቸው አናሳ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ቁጥር መሰረት በማድረግ 550 የማይበልጥ ሆኖ ከዚህ ውስጥ አናሳ ብሔረሰቦች 20 የማያንስ መቀመጫ ይኖራቸዋል፡፡ ዝርዝሩ በሕግ ይደነግጋል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት የመላው ሕዝብ ተወካዮች ናቸው፡፡ተገዢነታቸውም፣
ሀ/ ለሕገ መንግሥቱ፤
ለ/ ለሕዝቡ፤ እና
ሐ/ ለሕሊናቸው ብቻ ይሆናሉ፡፡
ማንኛውም የምክር ቤቱ አባል በምክር ቤቱ ውስጥ በሚሰጠው ድምጽ ወይም አስተያየት ምክንያት አይከሰስም፡፡ አስተዳደራዊ እርምጃ አይወሰድበትም፡፡
ማንኛውም የምክር ቤቱ አባል ከባድ ወንጀል ሲፈጽም እጅ ከፍንጅ ካለተያዘ በስተቀር ያለ ምክር ቤቱ ፈቃድ አይያዝም፤ በወንጀልም አይከሰስም፡፡
ማንኛውም የምክር ቤቱ አባል የመረጠው ሕዝብ አመኔታ ባጣበት ጊዜ በሕግ መሰረት ከምክር ቤት አባልነቱ ይወገዳል፡፡
አንቀጽ 55 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባር#
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዚህ ሕገ መንግሥት መሰረት ለፌዴራሉ መንግሥት በተሰጠው ሥልጣን ክልል ሕጐችን ያወጣል፡፡
በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 የተመለከተው አጠቃላይ ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚከተሉት ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ሕግ ያወጣል፤
ሀ/ የመሬትና የተፈጥሮ ሀብት፤ እንዲሁም ድንበር ተሻጋሪ ወይም ከአንድ ክልል በላይ የሚያስተሳስሩ ወንዞችና ሐይቆች አጠቃቀምን በተመለከተ፤
ለ/ በክልሎች መካከል የሚኖረውን የንግድ ልውውጥ፤ እንዲሁም የውጭ ንግድ ግንኙነትን በተመለከተ፤
ሐ/ የአየር፣ የባቡርና የባሕር መጓጓዣ፤ የፖስታና የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎቶችን እንዲሁም ሁለት ወይም ከሁለት በላይ ክልሎችን የሚያገናኙ አውራ መንገዶችን በተመለከተ፤
መ/ በዚህ ሕገ መንግሥት የተደነገጉትን የፖለቲካ መብቶች አፈጻጸምን እንዲሁም ምርጫን በተመለከተ፤
ሠ/ የዜግነት መብትን፤ የኢምግሬሽን፤ የስፖርትን፤ ወደ ሀገር የመግቢያና የመውጫ ጉዳዮችን እንዲሁም የስደተኞችና የፖለቲካ ጥገኝነት ጉዳዮችን በተመለከተ፤
ረ/ አንድ ወጥ የመጠን መለኪያ ደረጃና የጊዜ ቀመርን በተመለከተ፤
ሰ/ የፈጠራና የሥነ ጥበብ መብቶችን በተመለከተ፤
ሸ/ የጦር መሣሪያ መያዝን በተመለከተ፡፡
የሠራተኛ ጉዳይ ሕግ ያወጣል፡፡
የንግድ ሕግ /ኮድ/ ያወጣል፡፡
የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ያወጣል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሁኖ ክልሎች የፌዴራሉ መንግሥት የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ በግልጽ ባልተሸፈኑ ጉዳዮች ላይ ሕግ የማውጣት ሥልጣን ይኖራቸዋል፡፡
አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብን ለመፍጠር ሲባል በፌዴራል መንግሥት ሕግ እንዲወጣላቸው የሚያስገድዱ ለመሆናቸው በፌዴሬሽኑ ምክር ቤት የታመነባቸው የፍትሐብሔር ሕጐችን ያወጣል፡፡
የፌዴራል መንግሥት፤ የሀገርና የሕዝብ መከላከያ፤ የደህንነትና የፖሊስ ኃይል አደረጃጀት ይወስናል፡፡ በሥራ አፈጻጸም ረገድ የሚታዩ መሠረታዊ የዜጐችን ሰብዓዊ መብቶችና የሀገርን ደህንነት የሚነኩ ጉዳዮች ሲከሰቱ ያጣራል፤ አስፈላጊ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ያደርጋል፡፡
በአንቀጽ 93 በተመለከተው መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያውጃል፤ የሕግ አስፈጻሚው የሚያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተመልክቶ ይወስናል፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያቀርብለት የሕግ ረቂቅ መሰረት የጦርነት አዋጅ ያውጃል፡፡
የሀገሪቱን አጠቃላይ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ፣ የልማት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን፤ የፋይናንስና የገንዘብ ፖሊሲን ያጸድቃል፤ ገንዘብን፤ የብሔራዊ ባንክ አስተዳደር፤ የውጭ ምንዛሪንና ልውውጥን በተመለከተ ዝርዝር ሕግ ያወጣል፡፡
ለፌዴራል መንግሥት በተከለለው የገቢ ምንጭ ክልል ግብርና ታክስ ይጥላል፡፡የፌዴራል መንግሥት በጀት ያጸድቃል፡፡
የሕግ አስፈጻሚው አካል የሚዋዋላቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ያጸድቃል፡፡
የፌዴራል መንግሥት ፍርድ ቤት ዳኞችን፤ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላትን፤የኮሚሽነሮችን፤ የዋናው ኦዲተርን እንዲሁም የሌሎች ሹመታቸው በምክር ቤቱ መጽደቅ ያለበትን ባለሥለጣኖች ሹመት ያጸድቃል፡፡
የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ያቋቁማል፤ ሥልጣንና ተግባሩን በሕግ ይወስናል፡፡
የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋምን ያቋቁማል፤ ተቋሙን የሚመሩ አባላትን ይመርጣል፤ይሰይማል፡፡ ሥልጣንና ተግባሩን በሕግ ይወስናል፡፡
በማንኛውም ክልል ሰብዓዊ መብቶች ሲጣሱና ክልሉ ድርጊቱን ማቆም ሳይችል ሲቀር፤ በራሱ አነሳሽነትና ያለክልሉ ፈቃድ ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድ ለፌዴሬሽኑ ምክር ቤትና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ ጥያቄ ያቀርባል፤ በተደረሰበት ውሳኔ መሰረት ለክልሉ ምክር ቤት መመሪያ ይሰጣል፡፡
ምክር ቤቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩን እና ሌሎች የፌዴራሉ መንግሥት ባለሥለጣናትን ለጥያቄ የመጥራትና የሕግ አስፈጻሚውን አካል አሠራር የመመርመር ሥልጣን አለው፡፡
ለሕግ አስፈጻሚው አካል በተሰጠ ማንኛውም ሥልጣን ላይ የምክር ቤቱ አባላት በአንድ ሦስተኛ ድምፅ ሲጠይቁ ምክር ቤቱ ይወያያል፡፡ ምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ የመመካከርና አስፈላጊ መስሎ የታየውን እርምጃ የመውሰድ ሥልጣን አለው፡፡
ምክር ቤቱን የሚመሩ አፈ ጉባኤና ምክትል አፈ ጉባኤ ይመርጣል፤ ለምክር ቤቱ ሥራ የሚያስፈልጉትን ቋሚና ጊዜያዊ ኮሚቴዎች ያዋቅራል፡፡
አንቀጽ 56 የፖለቲካ ሥልጣን#
በምክር ቤቱ አብላጫ መቀመጫ ያገኘ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ጣምራ ድርጅቶች የፌዴራሉን መንግሥት የሕግ አስፈጻሚ አካል ያደራጃል/ያደራጃሉ፤ ይመራል/ይመራሉ፡፡
አንቀጽ 57 ስለሕግ አጸዳደቅ#
ምክር ቤቱ መክሮ የተስማማበት ሕግ ለሀገሪቱ ኘሬዚዳንት ለፊርማ ይቀርባል፤ ኘሬዚዳንቱ በአሥራ አምስት ቀናት ውስጥ ይፈርማል፡፡ ኘሬዚዳንቱ በአሥራ አምስት ቀናት ውስጥ ካልፈረመ ሕጉ በሥራ ላይ ይውላል፡፡
አንቀጽ 58 የምክር ቤቱ ስብሰባና የሥራ ዘመን#
ከምክር ቤቱ አባላት ከግማሽ በላይ ከተገኙ ምልዓተ ጉባኤ ይኖራል፡፡
የምክር ቤቱ የሥራ ጊዜ ከመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ እስከ ሰኔ ሰላሳ ነው፤ በመካከሉም ምክር ቤቱ በሚወስነው ጊዜ የአንድ ወር ዕረፍት ይኖረዋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመረጠው ለአምስት ዓመታት ነው፤ የሥራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሂዶ ይጠናቀቃል፡፡
ምክር ቤቱ ዕረፍት ላይ በሚሆንበት ጊዜ የምክር ቤቱ አፈጉባኤ ስብሰባ ሊጠራ ይችላል፡፡ ከምክር ቤቱ አባላት ከግማሽ በላይ ስብሰባ እንዲጠራ ከጠየቁ አፈ-ጉባኤው ስብሰባ የመጥራት ግዴታ አለበት፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባዎች በግልጽ ይካሄዳሉ፤ ሆኖም በምክር ቤቱ አባላት ወይም በፌዴራል የሕግ አስፈጻሚ አካል በዝግ ስብሰባ እንዲደረግ ከተየቀና ከምክር ቤቱ አባላት ከግማሽ በላይ ከደገፉት ዝግ ስብሰባ ሊደረግ ይችላል፡፡
አንቀጽ 59 የምክር ቤቱ ውሳኔዎችና የሥነ ሥርዓት ደንቦች#
በዚህ ሕገ መንግሥት በግልጽ በተለይ ካልተደነገገ በስተቀር ማናቸውም ውሳኔዎች የሚተላለፉት በምክር ቤቱ አባላት የአብላጫ ድምጽ ነው፡፡
ምክር ቤቱ ስለ አሠራሩና ስለ ሕግ አወጣጡ ሂደት ደንቦችን ያወጣል፡፡
አንቀጽ 60 ስለምክር ቤቱ መበተን#
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥልጣን ዘመኑ ከማለቁ በፊት አዲስ ምርጫ ለማካሄድ በምክር ቤቱ ፈቃድ ምክር ቤቱ እንዲበተን ለማድረግ ይችላል፡፡
በጣምራ የመንግሥት ሥልጣን የያዙ የፖለቲካ ድርጅቶች ጣምራነታቸው ፈርሶ በምክር ቤቱ የነበራቸውን አብላጫነት ያጡ እንደሆነ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ተበትኖ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ሌላ ጣምራ መንግሥት በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለመመስረት እንዲቻል ኘሬዚዳንቱ የፖለቲካ ድርጅቶችን ይጋብዛል፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶቹ አዲስ መንግሥት ለመፍር ወይም የነበረውን ጣምራነት ለመቀጠል ካልቻሉ ምክር ቤቱ ተበትኖ አዲስ ምርጫ ይደረጋል፡፡
በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 ወይም 2 መሰረት ምክር ቤቱ የተበተነ እንደሆነ ከስድስት ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ አዲስ ምርጫ መደረግ አለበት፡፡
ምርጫው በተጠናቀቀ በሰላሳ ቀናት ውስጥ አዲሱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሥራውን ይጀምራል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተበተነ በኊላ ሀገሪቱን የሚወራው ሥልጣን ይዞ የነበረው የፖለቲካ ድርጅት ወይም የፖለቲካ ድርጅቶች ጣምራ የዕለት ተዕለት የመንግሥት ሥራ ከማከናወንና ምርጫ ከማካሔድ በስተቀር አዲስ አዋጆችን፣ ደንቦችንና ድንጋጌዎችን ማውጣት ወይም ነባር ሕጐችን ማሻርና ማሻሻል አይችልም፡፡
ምዕራፍ ስድስት ክፍል ሁለት : የፌዴሬሽን ምክር ቤት#
አንቀጽ 61 የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት#
የፌዴሬሽን ምክር ቤት በፌዴራሉ መንግሥት አባል ክልሎች የሚገኙ ብሔሮች፣ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች የሚልኩዋቸው አባላት የሚወከሉበት ምክር ቤት ነው፡፡
እያንዳንዱ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ ቢያንስ አንድ ተወካይ ይኖረዋል፤በተጨማሪም የብሔር ወይም ብሔረሰቡ አንድ ሚሊዮን ሕዝብ አንድ ተጨማሪ ወኪል ይኖረዋል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት በክልል ምክር ቤቶች ይመረጣሉ፤ የክልል ምክር ቤቶች በራሳቸው ወይም በቀጥታ በሕዝብ እንዲመረጡ በማድረግ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል እንዲወከሉ ያደርጋሉ፡፡
አንቀጽ 62 የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባር#
ምክር ቤቱ ሕገ መንግሥቱን የመተርጐም ሥልጣን ይኖረዋል፡፡
የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤን ያደራጃል፡፡
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠን መብትን በተመለከተ በሚነሱ ጥያቄዎች ላይ በሕገ መንግሥቱ መሰረት ይወሰናል፡፡
በሕገ መንግሥቱ የተደነገገው የሕዝቦች እኩልነትና በሕዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነት ሥር እንዲሰድና እንዲዳብር ያደርጋል፡፡
ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር በጣምራ የተሰጡትን ሥልጣኖች ያከናውናል፡፡
በክልሎች መካከል ለሚነሱ አለመግባባቶች መፍትሄ ይፈልጋል፡፡
የክልሎችና የፌዴራሉ መንግሥት የጋራ ተብለው የተመደቡ ገቢዎች በሁለቱ መካከል የሚከፋፈሉበትን፤ እንዲሁም የፌዴራሉ መንግሥት ለክልሎች ድጐማ የሚሰጥበትን ቀመር ይወስናል፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕግ ሊወጣላቸው የሚገቡ የፍትሐብሔር ጉዳዮችን ይለያል፡፡
ማንኛውም ክልል ይህን ሕገ መንግሥት በመጣስ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንደሆነ የፌዴራሉ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ያዛል፡፡
የምክር ቤቱን የተለያዩ ቋሚና ጊዜያዊ ኮሚቴዎች ያቋቁማል፡፡
ምክር ቤቱ የራሱን አፈጉባኤና ምክትል አፈጉባኤ ይመርጣል፤ የራሱን የሥራ አፈጻጸምና የውስጥ አስተዳደር ደንብ ያወጣል፡፡
አንቀጽ 63 የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት መብት#
ማንኛውም የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት አባል በማናቸውም የምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ በሚሰጠው አስተያየት ወይም ድምጽ ምክንያት አይከሰስም፤ አስተዳደራዊ እርምጃም አይወሰድበትም፡፡
ማንኛውም የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት አባል ከባድ ወንጀል ሲፈጽም እጅ ከፍንጅ ካልተያዘ በስተቀር ያለ ምክር ቤቱ ፈቃድ አይያይዝም፤ በወንጀልም አይከሰስም፡፡
አንቀጽ 64 ውሳኔዎችና የሥነ ሥርዓት ደንቦች#
የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት ምልዓተ ጉባኤ የሚኖረው ከአባላቱ ሁለት ሦስተኛው የተገኙ እንደሆነ ነው፡፡ ማናቸውም ውሳኔ የሚያልፈው ስብሰባ ላይ ከተገኙት የምክር ቤቱ አባላት ከግማሽ በላይ ድምጽ ሲደገፍ ብቻ ነው፡፡
አባላት ድምጽ መስጠት የሚችሉት በአካል ሲገኙ ብቻ ነው፡፡
አንቀጽ 65 ስለ በጀት#
የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት በጀቱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማቅረብ ያስወስናል፡፡
አንቀጽ 66 የምክር ቤቱ አፈጉባኤ ሥልጣን#
የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የምክር ቤቱን ስብሰባዎች ይመራል፡፡
ምክር ቤቱን በመወከል ጠቅላላ የአስተዳደር ሥራዎችን ይመራል፡፡
ምክር ቤቱ በአባሎቹ ላይ የወሰነውን የዲስኘሊን እርምጃ ያስፈጽማል፡፡
አንቀጽ 67 ስብሰባና የሥራ ዘመን#
የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት ቢያንስ በዓመት ሁለት ጊዜ ይሰበሰባል፡፡
የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት የሥራ ዘመን አምስት ዓመት ይሆናል፡፡
አንቀጽ 68 በሁለቱም ምክር ቤቶች አባል መሆን የማይቻል ስለመሆኑ#
ማንኛውም ሰው በአንድ ጊዜ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት አባል ሊሆን አይችልም፡፡