ምዕራፍ አምስት#
የሥልጣን አወቃቀር እና ክፍፍል#
አንቀጽ 50 ስለ ሥልጣን አካላት አወቃቀር#
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በፌዴራል መንግሥትና በክልሎች የተዋቀረ ነው፡፡
የፌዴራሉ መንግሥትና ክልሎች የሕግ አውጪነት፣ የሕግ አስፈጻሚነትና የዳኝነት ሥልጣን አላቸው፡፡
የፌዴራሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥልጣን አካል የፌዴራሉ መንግሥት የሕዝብተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ ተጠሪነቱም ለሀገሪቱ ሕዝብ ነው፡፡ የክልል ከፍተኛ የሥልጣን አካል የክልሉ ምክር ቤት ነው፤ ተጠሪነቱም ለወከለው ክልል ሕዝብ ነው፡፡
ክልሎች፤ በክልልነትና ክልሎች አስፈላጊ ሆነው በሚያገኙአቸው የአስተዳደር እርከኖች ይዋቀራሉ፡፡ ሕዝቡ በዝቅተኛ የአስተዳደር እርከኖች በቀጥታ ይሳተፍ ዘንድ ለዝቅተኛ እርከኖች በቂ ሥልጣን ይሰጣል፡፡
የክልል ምክር ቤት በክልሉ ሥልጣን ስር በሆኑ ጉዳዮች የክልሉ የሕግ አውጪ አካል ነው፡፡ ይህንን ሕገ መንግሥት መሰረት በማድረግ የክልሉን ሕገ መንግሥት ያዘጋጃል፣ ያጸድኝል፣ ያሻሽላል፡፡
የክልል መስተዳድር የክልሉ ከፍተኛ የሕግ አስፈጻሚ አካል ነው፡፡
የክልል የዳኝነት ሥልጣን የፍርድ ቤቶች ብቻ ነው፡፡
የፌዴራሉ መንግሥትና የክልሎች ሥልጣን በዚህ ሕገ መንግሥት ተወስኗል፡፡ ለፌዴራሉ መንግሥት የተሰጠው ሥልጣን በክልሎች መከበር አለበት፡፡ ለክልሎች የተሰጠው ሥልጣን በፌዴራሉ መንግሥት መከበር አለበት፡፡
የፌዴራል መንግሥት በዚህ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 51 ከተሰጡት ሥልጣን እና ተግባሮች እንደአስፈላጊነቱ ለክልሎች በውክልና ሊሰጥ ይችላል፡፡
አንቀጽ 51 የፌዴራል መንግሥት ሥልጣንና ተግባር#
ሕገ መንግሥቱን ይጠብቃል፤ ይከላከላል፡፡
የሀገሪቱን አጠቃላይ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የልማት ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ዕቅድ ያወጣል፤ ያስፈጽማል፡፡
የጤና፣ የትምህርት፣ የባሕልና ታሪካዊ ቅርስ፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሀገር አቀፍ መመዘኛዎችና መሰረታዊ የፖሊሲ መለኪያዎችን ያወጣል፤ ያስፈጽማል፡፡
የሀገሪቱን የፋይናንስ፣ የገንዘብ፣ የውጭ ኢንቨሰትመንት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ያወጣል፤ ያስፈጽማል፡፡
የመሬት፣ የተፈጥሮ ሀብትና የታሪክ ቅርሶች አጠቃቀምና ጥበቃን በተመለከተ ሕግ ያወጣል፡፡
የሀገርና የሕዝብ የመከላከያና የደህንነት እንዲሁም የፌዴራል መንግሥት የፖሊስ ኃይል ያደራጃል፤ ይመራል፡፡
ብሔራዊ ባንክን የስተዳድራል፤ ገንዘብ ያትማል፤ ይበደራል፤ የውጭ ምንዛሪና ገንዘብ ልውውጥን ይቆጣጠራል፡፡ ክልሎች ከውስጥ ምንጮች ስለሚበደሩበት ሁኔታ ሕግና መመሪያ ያወጣል፡፡
የውጭ ግንኙነት ፖሊሲን ይወስናል፤ ፖሊሲውንም ያስፈጽማል፤ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ይዋዋላል፤ ያጸድቃል፡፡
የአየር፣ የባቡር፣ የባሕር መጓጓዣ፤ የፖስታና የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎቶች እንደዚሁም ሁለት ወይም ከሁለት በላይ ክልሎችን የሚያገናኙ አውራ መንገዶችን ያስፋፋል፤ ያስተዳድራል፤ ይቆጣጠራል፡፡
ለፌዴራሉ መንግሥት በተሰጡት የገቢ ምንጮች ክልል ግብርና ቀረጥ ይጥላል፤ያስተዳድራል፤ የፌዴራል መንግሥት በጀት ያረቃል፤ ያጸድቃል፤ ያስተዳድራል፡፡
ሁለት ወይም ከሁለት በላይ የሆኑ ክልሎችን የሚያስተሳስሩ ወይም ድንበር ተሻጋሪ የሆኑ ወንዞችና ሀይቆችን አጠቃቀም ይወስናል፤ ያስተዳድራል፡፡
በክልሎች መካከል የሚደረግን የንግድ ግንኙነትና የውጭ ንግድን ይመራል፤ይቆጣጠራል፡፡
በፌዴራል መንግሥት ገንዘብ የተቋቋሙ አንድ ወይም ከአንድ ክልል በላይ የሚሸፍኑ የአገልግሎት ተቋሞችን ያስተዳድራል፤ ያስፋፋል፡፡
ከክልል አቅም በላይ የሆነ የጸጥታ መደፍረስ ሲያጋጥም በክልሉ መስተዳድር ጥያቄ መሰረት የሀገሪቱን የመከላከያ ኃይል ያሰማራል፡፡
በዚህ ሕገ መንግሥት የተረጋገጡትን የፖለቲካ መብቶች ለማስፈጸም አስፈላጊ የሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶችን እንዲሁም ምርጫን በሚመለከት ሕጐች ያወጣል፡፡
በሀገሪቱ በአጠኝላይም ሆነ በተወሰኑ የሀገሪቱ ክፍሎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያውጃል፤ አዋጁን ያነሳል፡፡
የዜግነት ጥያቄ ይወስናል፡፡
የኢምግሬሽንና የስፖርት፤ ወደ ሀገር የመግቢያና፤ የመውጫ ጉዳዮችን፤ ስለስደተኞችና ስለ ፖለቲካ ጥገኝነት ይወስናል፤ ይመራል፡፡
የፈጠራና የድርሰት መብቶችን ይፈቅዳል፤ ይጠብቃል፡፡
አንድ ወጥ የመለኪያ ደረጃዎችና የጊዜ ቀመር ያወጣል፡፡
የጦር መሳሪያ ስለመያዝ የጦር መሣሪያ ሕግ ያወጣል፡፡
አንቀጽ 52 የክልል ሥልጣንና ተግባር#
በሕገ መንግሥቱ ለፌዴራሉ መንግሥት በተለይ ወይም ለፌዴራሉ መንግሥትና ለክልሎች በጋራ በግልጽ ያልተሰጠ ሥልጣን የክልል ሥልጣን ይሆናል፡፡
በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የክልሎች ሥልጣንና ተግባር የሚከተሉትን ያጠቃልላል፤
ሀ. ራስን በራስ ማስተዳደርን ዓላማ ያደረገ ክልላዊ መስተዳደር ያዋቅራል፤ የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ይገነባል፤ ይህን ሕገ መንግሥት ይጠብቃል፤ ይከላከላል፤
ለ. የክልል ሕገ መንግሥትና ሌሎች ሕጐችን ያወጣል፤ ያስፈጽማል፤
ሐ. የክልሉን የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የልማት ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና እቅድ ያወጣል፤ ያስፈጽማል፤
መ. የፌዴራሉ መንግሥት በሚያወጣው ሕግ መሰረት መሬትና የተፈጥሮ ሀብትን ያስተዳድራል፤
ሠ. ለክልሉ በተወሰነው የገቢ ምንጭ ክልል ግብርና ታክስ ይጥላል፤ ይሰበስባል፤ የክልሉን በጀት ያወጣል፤ ያስፈጽማል፤
ረ. የክልሉን መስተዳድር ሠራተኞች አስተዳደር የሥራ ሁኔታዎች በተመለከተ ሕግ ያወጣል፤ ያስፈጽማል፤ ሆኖም ለአንድ የሥራ መደብ የሚያስፈልጉ የትምህርት የሥልጠናና የልምድ መመዘኛዎች ከአጠቃላይ የሀገሪቱ መመዘኛዎች ጋር የተቀራረቡ መሆናቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት ይኖርበታል፡፡
ሰ. የክልሉን የፖሊስ ኃይል ያደራጃል፤ ይመራል፤ የክልሉን ሰላምና ጸጥታ ያስብቃል፡፡