ምዕራፍ ሦስት#
መሰረታዊ መብቶችና ነጻነቶች#
አንቀጽ 13: ተፈጻሚነትና አተረጓጐም#
በማንኛውም ደረጃ የሚገኙ የፌዴራል መንግሥትና የክልል ሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈጻሚ እና የዳኝነት አካሎች በዚህ ምዕራፍ የተካተቱን ድንጋጌዎች የማክበርና የማስከበር ኃላፊነትና ግዴታ አለባቸው፡፡
በዚህ ምዕራፍ የተዘረዘሩት መሠረታዊ የመብቶችና የነጻነቶች ድንጋጌዎች ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሕግጋት፣ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ስምምነቶችና ዓለም አቀፍ ሰነዶች መርሆዎች ጋር በተጣጣመ መንገድ ይተረጐማል፡፡
ክፍል አንድ - ሰብዓዊ መብቶች#
አንቀጽ 14#
የሕይወት፣ የአካል ደህንነትና የነጻነት መብት ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሰስ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነትና የነጻነት መብት አለው፡፡
አንቀጽ 15 የሕይወት መብት#
ማንኛውም ሰው በሕይወት የመኖር መብት አለው፡፡ ማንኛውም ሰው በሕግ በተደነገገ ከባድ የወንጀል ቅጣት ካልሆነ በስተቀር ሕይወቱን አያጣም፡፡
አንቀጽ 16 የአካል ደህንነት መብት#
ማንኛውም ሰው በአካሉ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት የመጠበቅ መብት አለው፡፡
አንቀጽ 17 የነጻነት መብት#
በሕግ ከተደነገገው ሥርዓት ውጭ ማንኛውም ሰው ወንድም ሆነ ሴት ነጻነቱን/ቷን አያጣም/አታጣም፡፡
ማንኛውም ሰው በሕግ ከተደነገገው ሥርዓት ውጭ ሊያዝ፣ ክስ ሳይቀርብበት ወይም ሳይፈረድበት ሊታሰር አይችልም፡፡
አንቀጽ 18 ኢሰብዓዊ አያያዝ ስለመከልከሉ#
ማንኛውም ሰው ጭካኔ ከተሞላበት፣ ኢሰብዓዊ ከሆነ ወይም ክብሩን ከሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት የመጠበቅ መብት አለው፡፡
ማንኛውም ሰው በባርነት ወይም በግዴታ አገልጋይነት ሊያዝ አይችልም፡፡ለማንኛውም ዓላማ በሰው የመነገድ ተግባር የተከለከለ ነው፡፡
ማንኛውም ሰው በኃይል ተገዶ ወይም ግዴታ ለማሟላት ማንኛውንም ሥራ እንዲሠራ ማድረግ የተከለከለ ነው፡፡
በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 3 «በኃይል ተገዶ ወይም ግዴታን ለማሟላት»የሚለው ሐረግ የሚከተሉትን ሁኔታዎች አያካትትም፤
ሀ. ማንኛውም እስረኛ በእስራት ላይ ባለበት ጊዜ በሕግ መሠረት አንዲሠራ የተወሰነውን ወይም በገደብ ከእስር በተለቀቀበት ጊዜ፣ የሚሠራውን ማንኛውም ሥራ፣
ለ. ማንኛውም ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ሕሊናው የማይፈቅድለት ሰው በምትክ የሚሰጠውን አገልግሎት፣
ሐ. የማኅበረሰቡን ሕይወት ወይም ደህንነት የሚያሰጋ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ወይም አደጋ በሚያጋጥምበት ጊዜ የሚሰጥ ማንኛውም አገልግሎት፣
መ. በሚመለከተው ሕዝብ ፈቃድ በአካባቢው የሚፈጸመውን ማንኛውንም ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ የልማት ሥራ፡፡
አንቀጽ 19 የተያዙ ሰዎች መብት#
ወንጀል ፈጽመዋል በመባል የተያዙ ሰዎች የቀረበባቸው ክስና ምክንያቶቹ በዝርዝር ወዲያውኑ በሚገባቸው ቋንቋ እንዲነገራቸው መብት አላቸው፡፡
የተያዙ ሰዎች ላለመናገር መብት አላቸው፤ የሚሰጡት ማንኛውም ቃል ፍርድ ቤት በማስረጃነት ሊቀርብባቸው እንደሚችል መረዳት በሚችሉት ቋንቋ እንደተያዙ ወዲያውኑ ማስገንዘቢያ እንዲሰጣቸው መብት አላቸው፡፡
የተያዙ ሰዎች በአርባ ስምንት ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት የመቅረብ መብት አላቸው፡፡ ይህም ጊዜ ሰዎቹ ከተያዙበት ቦታ ወደ ፍርድ ቤት ለመምጣት አግባብ ባለው ግምት የሚጠይቀውን ጊዜ አይጨምርም፡፡ ወዲያውኑ ፍርድ ቤት እንደቀረቡ በተጠረጠሩበት ወንጀል ለመታሰር የሚያበቃ ምክንያት ያለ መሆኑ ተለይቶ አንዲገለጽላቸው መብት አላቸው፡፡
የያዛቸው የፖሊስ መኮንን ወይም የሕግ አስከባሪ በጊዜው ገደብ ፍርድ ቤት በማቅረብ የተያዙበትን ምክንያት ካላስረዳ፣ ፍርድ ቤቱ የአካል ነጻነታቸውን እንዲያስከብርላቸው የመጠየቅ ሊጣስ የማይችል መብት አላቸው፡፡ ሆኖም ፍትሕ እንዳይጓደል ሁኔታው የሚጠይቅ ከሆነ ፍርድ ቤቱ የተያዘው ሰው በጥበቃ ሥር እንዲቆይ ለማዘዝ ወይም ምርመራ ለማካሄድ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሲጠየቅ አስፈላጊ በሆነ መጠን ብቻ ሊፈቅድ ይችላል፡፡ የሚያስፈልገውን ተጨማሪ ጊዜ ፍርድ ቤቱ ሲወስን ኃላፊ የሆኑት የሕግ አስከባሪ ባለሥልጣኖች ምርመራውን አጣርተው የተያዘው ሰው በተቻለ ፍጥነት ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ያለውን መብት የሚያስከብር መሆን አለበት፡፡
የተያዙ ሰዎች በራሳቸው ላይ በማስረጃነት ሊቀርብ የሚችል የእምነት ቃል እንዲሰጡ ወይም ማናቸውንም ማስረጃ እንዲያምኑ አይገደዱም፡፡ በማስገደድ የተገኘ ማስረጃ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡
የተያዙ ሰዎች በዋስ የመፈታት መብት አላቸው፡፡ ሆኖም በሕግ በተደነገጉ ልዩ ሁኔታዎች ፍርድ ቤት ዋስትና ላለመቀበል ወይም በገደብ መፍታትን ጨምሮ በቂ የሆነ ዋስትና ማረጋገጫ እንዲቀርብ ለማዘዝ ይችላል፡፡
አንቀጽ 20 የተከሰሱ ሰዎች መብት#
የተከሰሱ ሰዎች ክስ ከቀረበባቸው በኃላ ተገቢ በሆነ አጭር ጊዜ ውስጥ በመደበኛ ፍርድ ቤት ለሕዝብ ግልጽ በሆነ ችሎት የመሰማት መብት አላቸው፡፡ ሆኖም ተከራካሪዎቹን የግል ሕይወት፣ የሕዝብን የሞራል ሁኔታና የሀገሪቱን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል ብቻ ክርክሩ በዝግ ችሎት ሊሰማ ይችላል፡፡
ክሱ በቂ በሆነ ዝርዝር እንዲነገራቸው እና ክሱን በጽሁፍ የማግኘት መብት አላቸው፡፡
በፍርድ ሂደት ባሉበት ጊዜ በተከሰሱበት ወንጀል እንደ ጥፋተኛ ያለመቆጠር፣በምስክርነት እንዲቀርቡም ያለመገደድ መብት አላቸው፡፡
የቀረበባቸውን ማናቸውንም ማስረጃ የመመልከት፣ የቀረቡባቸውን ምስክሮች የመጠየቅ፣ ለመከላከል የሚያስችላቸውን ማስረጃ የማቅረብ ወይም የማስቀረብ እንዲሁም ስክሮቻቸው ቀርበው እንዲሰሙላቸው የመጠየቅ መብት አላቸው፡፡
በመረጡት የሕግ ጠበቃ የመወከል ወይም ጠበቃ ለማቆም አቅም በማጣታቸው ፍትሕ ሊጓደል የሚችልበት ሁኔታ ሲያጋጥም ከመንግሥት ጠበቃ የማግኘት መብት አላቸው፡፡
ክርክሩ በሚታይበት ፍርድ ቤት በተሰጠባቸው ትእዛዝ ወይም ፍርድ ላይ ሥልጣን ላለው ፍርድ ቤት ይግባኝ የማቅረብ መብት አላቸው፡፡
የፍርዱ ሂደት በማይገባቸው ቋንቋ በሚካሄድበት ሁኔታ በመንግሥት ወጪ ክርክሩ እንዲተረጐምላቸው የመጠየቅ መብት አላቸው፡፡
አንቀጽ 21 በጥበቃ ሥር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች መብት#
በጥበቃ ሥር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች ሰብዓዊ ክብራቸውን በሚጠብቁ ሁኔታዎች የመያዝ መብት አላቸው፡፡
ከትዳር ጓደኞቻቸው፣ ከቅርብ ዘመዶቻቸው፣ ከጓደኞቻቸው፣ ከሃይማኖት አማካሪዎቻቸው፣ ከሐኪሞቻቸው እና ከሕግ አማካሪዎቸው ጋር ለመገናኘትና እንዲጐበቿቸውም ዕድል የማግኘት መብት አላቸው፡፡
አንቀጽ 22 የወንጀል ሕግ ወደኊላ ተመልሶ የማይሰራ ስለመሆኑ#
ማንኛውም ሰው የወንጀል ክስ ሲቀርብበት የተከሰሰበት ድርጊት በተፈጸመበት ጊዜ ድርጊቱን መፈጸሙ ወይም አለመፈጸሙ ወንጀል መሆኑ በሕግ የተደነገገ ካልሆነ በስተቀር ሊቀጣ አይችልም፡፡ እንዲሁም ወንጀሉን በፈጸመበት ጊዜ ለወንጀሉ ተፈጻሚ ከነበረው የቅጣት ጣሪያ በላይ የከበደ ቅጣት በማንኛውም ሰው ላይ አይወሰንም፡፡
የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 ቢኖርም፣ ድርጊቱ ከተፈጸመ በኊላ የወጣ ሕግ ለተከሳሹ ወይም ለተቀጣው ሰው ጠቃሚ ሆኖ ከተገኘ ከድርጊቱ በኊላ የወጣው ሕግ ተፈጻሚነት ይኖረዋል፡፡
አንቀጽ 23 በአንድ ወንጀል ድጋሚ ቅጣት ስለመከልከሉ#
ማንኛውም ሰው በወንጀል ሕግና ሥነ ሥርዓት መሠረት ተከሶ የመጨረሻ በሆነ ውሳኔ ጥፋተኛነቱ በተረጋገጠበት ወይም በነጻ በተለቀቀበት ወንጀል እንደገና አይከሰስም ወይም አይቀጣም፡፡
አንቀጽ 24 የክብርና የመልካም ስም መብት#
ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ ክብሩና መልካም ስሙ የመከበር መብት አለው፡፡
ማንኛውም ሰው የራሱን ስብዕና ከሌሎች ዜጐች መብቶች ጋር በተጣጣመ ሁኔታ በነጻ የማሳደግ መብት አለው፡፡
ማንኛውም ሰው በማንኛውም ስፍራ በሰብዓዊነቱ እውቅና የማግኘት መብት አለው፡፡
አንቀጽ 25 የእኩልነት መብት#
ሁሉም ሰዎች በሕግ ፊት እኩል ናቸው፤ በመካከላቸውም ማንኛውም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግ በሕግ እኩል ጥበቃ ይደረግላቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ በዘር፣በብሔር፣ብሔረሰብ፣በቀለም፣ በጾታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ አመጣጥ፣ በሀብት፣በትውልድ ወይም በሌላ አቋም ምክንያት ልዩነት ሳይደረግ ሰዎች ሁሉ እኩልና ጨባጭ የሕግ ዋስትና የማግኘት መብት አላቸው፡፡
አንቀጽ 26 የግል ሕይወት የመከበርና የመጠበቅ መብት#
ማንኛውም ሰው የግል ሕይወቱ፣ ግላዊነቱ፣ የመከበር መብት አለው፡፡ ይህ መብት መኖሪያ ቤቱ፣ ሰውነቱና ንብረቱ ከመመርመር እንዲሁም በግልይዞታው ያለ ንብረት ከመያዝ የመጠበቅ መብትን ያካትታል፡፡
ማንኛውም ሰው በግል የሚጽፋቸውንና የሚጻጻፋቸው፣ በፖስታ የሚልካቸው ደብዳቤዎች፣ እንዲሁም በቴሌፎን፣ በቴሌኮሙኒኬሽንና በኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች የሚያደርጋቸው ግንኙነቶች አይደፈሩም፡፡
የመንግሥት ባለሥለጣኖች እነዚህን መብቶች የማክበርና የማስከበር ግዴታ አለባቸው፡፡ አስገዳጅ ሁኔታዎቸ ሲፈጠሩና ብሔራዊ ደህንነትን፣ ሕዝብን ሰላም፣ወንጀልን በመከላከል፣ ጤናንና የሕዝብን የሞራል ሁኔታ በመጠበቅ ወይም የሌሎችን መብትና ነጻነት በማስከበር ዓላማዎች ላይ በተመሰረቱ ዝርዝር ሕጐች መሰረት ካልሆነ በስተቀር የእነዚህ መብቶች አጠቃቀም ሊገደብ አይችለም፡፡
አንቀጽ 27 የሃይማኖት፣ የእምነትና የአመለካከት ነጻነት#
ማንኛውም ሰው የማሰብ፣ የሕሊና እና የሃይማኖት ነጻነት አለው፡፡ ይህ መብት ማንኛውም ሰው የመረጠውን ሃይማኖት ወይም እምነት የመያዝ ወይም የመቀበል፣ ሃይማኖቱንና እምነቱን ለብቻ ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን በይፋ ወይም በግል የማምለክ፣ የመከተል፣ የመተግበር፣ የማስተማር ወይም የመግለጽ መብትን ያካትታል፡፡
በአንቀጽ 90 ንዑስ አንቀጽ 2 የተጠቀሰው አንደተጠበቀ ሆኖ የሃይማኖት ተከታዮች ሃይማኖታቸውን ለማስፋፋትና ለማደራጀት የሚያስችሏቸው የሃይማኖት ትምህርትና የአስተዳደር ተቋማት ማቋቋም ይችላሉ፡፡
ማንኛውንም ሰው የሚፈልገውን እምነት ለመያዝ ያለውን ነጻነት በኃይል ወይም በሌላ ሁኔታ በማስገደድ መገደብ ወይም መከልከል አይቻልም፡፡
ወላጆችና ሕጋዊ ሞግዚቶች በእምነታቸው መሰረት የሃይማኖታቸውንና የመልካም ሥነ ምግባር ትምህርት በመስጠት ልጆቻቸውን የማሳደግ መብት አላቸው፡፡
ሃይማኖትና እምነትን የመግለጽ መብት ሊገደብ የሚችለው የሕዝብን ደህንነት፣ሰላምን፣ ጤናን፣ ትምህርትን፣ የሕዝብን የሞራል ሁኔታ፣ የሌሎች ዜችን መሰረታዊ መብቶች፣ ነጻነቶች እና መንግስት ከሃይማኖት ነጻ መሆኑን ለማረጋረገጥ በሚወጡ ሕጐች ይሆናል፡፡
አንቀጽ 28 በስብእና ስለሚፈደሙ ወንጀሎች#
ኢትዮጵያ ባጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እና በሌሎች የኢትዮጵያ ሕጐች በሰው ልጅ ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ተብለው የተወሰኑትን ወንጀሎች፤የሰው ዘር የማጥፋት፣ ያለፍርድ የሞት ቅጣት እርምጃ የመውሰድ፣ በአስገዳጅ ሰውን የመሰወር፣ ወይም ኢሰብዓዊ የድብደባ ድርጊቶችን በፈጸሙ ሰዎች ላይ ክስ ማቅረብ በይርጋ አይታገድም፡፡ በሕግ አውጪው ክፍልም ሆነ በማንኛውም የመንግሥት አካል ውሳኔዎች በምሕረት ወይም በይቅርታ አይታለፉም፡፡
ከዚህ በላይ የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 የተቀሱትን ወንጀሎች ፈጽመው የሞት ቅጣት ለተፈረደባቸው ሰዎች ርዕሰ ብሔሩ ቅጣቱን ወደ ዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ሊያሻሽለው ይችላል፡፡
ክፍል ሁለት - ዴሞክራሲያዊ መብቶች#
አንቀጽ 29 የአመለካከት እና ሐሳብን በነጻ የመያዝና የመግለጽ መብት#
ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት ለመያዝ ይችላል፡፡
ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሐሳቡን የመግለጽ ነጻነት አለው፡፡ ይህ ነጻነት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሑፍ ወይም በሕትመት፣ በሥነ ጥበብ መልክ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ፣ ማንኛውንም ዓይነት መረጃና ሐሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨት ነጻነቶችን የካትታል፡፡
የኘሬስና የሌሎች መገናኛ ብዙኃን፣ እንዲሁም የሥነ ጥበብ ፈጠራ ነጻነት ተረጋግጧል፡፡ የኘሬስ ነጻነት በተለይ የሚከተሉትን መብቶች ያጠኝልላል፣
ሀ. የቅድሚያ ምርመራ በማንኛውም መልኩ የተከለከለ መሆኑን፣
ለ. የሕዝብን ጥቅም የሚመለከት መረጃ የማግኘት ዕድልን፡፡
ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች፣ ሐሳቦችና አመለካከቶች በነጻ መንሸራሸራቸውን ለማረጋገጥ ሲባል ኘሬስ በተቋምነቱ የአሠራር ነጻነትና የተለያዩ አስተያየቶች የማስተናገድ ችሎታ እንዲኖረው የሕግ ጥበቃ ይደረግለታል፡፡
በመንግሥት ገንዘብ የሚካሄድ ወይም በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለ መገናኛ ብዙኃን የተለያዩ አስተያየቶችን ለማስተናገድ በሚያስችለው ሁኔታ እንዲመራ ይደረጋል፡፡
እነዚህ መብቶች ገደብ ሊጣልባቸው የሚችለው የሀሳብና መረጃ የማግኘት ነጻነት በአስተሳሰባዊ ይዘቱና ሊያስከትል በሚችለው አስተሳሰባዊ ውጤት ሊገታ አይገባውም በሚል መርህ ላይ ተመስርተው በሚወጡ ሕጐች ብቻ ይሆናል፡፡ የወጣቶችን ደህንነት፣ የሰውን ክብርና መልካም ስም ለመጠበቅ ሲባል ሕጋዊ ገደቦች በነዚህ መብቶች ላይ ሊደነገጉ ይችላሉ፡፡ የጦር ቅስቃሴዎች እንዲሁም ሰብዓዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ መግለጫዎች በህግ የሚከለከሉ ይሆናል፡፡
ማንኛውም ዜጋ ከላይ በተጠቀሱት መብቶች አጠቃቀም ረገድ የሚጣሉ ሕጋዊ ገደቦችን ጥሶ ከተገኘ በሕግ ተጠያቂ ሊሆን የችላል፡፡
አንቀጽ 30 የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት#
ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን መሣሪያ ሳይዝ በሰላም የመሰብሰብ፣ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነትና፣ አቤቱታ የማቅረብ መብት አለው፡፡ ከቤት ውጭ የሚደረጉ ስብሰባዎችና ሰላማዊ ሰልፎች በሚንቀሳቀሱባቸው ቦታዎች በሕዝብ እንቅስቃሴ ላይ ችግር እንዳይፈጥሩ ለማድረግ ወይም በመካሔድ ላይ ያለ ስብሰባ ወይም ሰላማዊ ሰልፍ ሰላምን፣ ዴሞክራሲያዊ መብቶችንና የሕዝብን የሞራል ሁኔታ እንዳይጥሱ ለማስጠበቅ አግባብ ያላቸው ሥርዓቶች ሊደነገጉ ይችላሉ፡፡
ይህ መብት የወጣቶችን ደህንነት፣ የሰውን ክብርና መልካም ስምን ለመጠበቅ፣የጦርነት ቅስቀሳዎች እንዲሁም ሰብዓዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ መግለጫዎችን ለመከላከል ሲባል በሚወጡ ሕጐች መሰረት ተጠያቂ ከመሆን አያድንም፡፡
አንቀጽ 31 የመደራጀት መብት#
ማንኛውም ሰው ለማንኛውም ዓላማ በማኅበር የመደራጀት መብት አለው፡፡ ሆኖም አግባብያለውን ሕግ በመጣስ ወይም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በሕገ ወጥ መንገድ ለማፍረስ የተመሰረቱ ወይም የተጠቀሱትን ተግባራት የሚያራምዱ ድርጅቶች የተከለከሉ ይሆናሉ፡፡
አንቀጽ 32 የመዘዋወር ነጻነት#
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም በሕጋዊ መንገድ ሀገሪቱ ውስጥ የሚገኝ የውጭ ዜጋ በመረጠው የሀገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመስረት፣እንዲሁም በፈለገው ጊዜ ከሀገር የመውጣት ነጻነት አለው፡፡
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወደ ሀገሩ የመመለስ መብት አለው፡፡
አንቀጽ 33 የዜግነት መብቶች#
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ/ኢትዮጵያዊት ከፈቃዱ/ከፈቃዷ ውጭ ኢትዮጵያዊ ዜግነቱን/ዜግነትዋን ሊገፈፍ ወይም ልትገፈፍ አይችልም/አትችልም፡፡ኢትዮጵያዊ / ኢትዮጵያዊት ዜጋ ከሌላ ሀገር ዜጋ ጋር የሚፈጽመው/የምጽትፈጽመው ጋብቻ ኢትዮጵያዊ ዜግነቱን / ዜግነትዋን አያስቀርም፡፡
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የኢትዮጵያ ዜግነት በሕግ የሚያስገኘውን መብት ጥበቃና ጥቅም የማግኘት መብት አለው፡፡
ማንኛውም ዜጋ ኢትዮጵያዊ ዜግነቱን የመለወጥ መብት አለው፡፡
ኢትዮጵያ ከአጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር በማይቃረን መንገድ በሚወጣ ሕግ እና በሚደነገግ ሥርዓት መሰረት የኢትዮጵያ ዜግነት ለውጭ ሀገር ሰዎች ሊሰጥ ይችላል፡፡
አንቀጽ 34 የጋብቻ፣ የግልና የቤተሰብ መብቶች#
በሕግ ከተወሰነው የጋብቻ ዕድሜ የደረሱ ወንዶችና ሴቶች በዘር፣ በበሔር፣በብሔረሰብ ወይም በሃይማኖት ልዩነት ሳይደረግባቸው የማግባትና ቤተሰብ የመመስረት መብት አላቸው፡፡ በጋብቻ አፈጻጸም፣ በጋብቻው ዘመንና በፍቺ ጊዜ እኩል መብት አላቸው፡፡ በፍቺም ጊዜ የልጆችን መብትና ጥቅም እንዲከበር የሚያደርጉ ድንጋጌዎች ይደነገጋሉ፡፡
ጋብቻ በተጋቢዎች ነጻና ሙሉ ፈኝድ ላይ ብቻ ይመሰረታል፡፡
ቤተሰብ የኅብረተሰብ የተፈጥሮ መሰረታዊ መነሻ ነው፡፡ ከኅብረተሰብና ከመንግሥት ጥበቃ የማግኘት መብት አለው፡፡
በሕግ በተለይ በሚዘረዘረው መሰረት በሃይማኖት፣ በባሕል የሕግ ሥርዓቶች ላይ ተመስርትው ለሚፈጸሙ ጋብቻዎች እውቅና የሚሰጥ ሕግ ሊወጣ ይችላል፡፡
ይህ ሕገ መንግሥት የግል እና የቤተሰብ ሕግን በተመለከተ በተከራካሪዎች ፈቃድ በሃይማኖቶች ወይም በባሕሎች ሕጐች መሰረት መዳኘትን አይከለክልም፡፡ ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል፡፡
አንቀጽ 35 የሴቶች መብት#
ሴቶች ይህ ሕገ መንግሥት በአረጋገጣቸው መብቶችና ጥበቃዎች በመጠቀም ረገድ ከወንዶች ጋር እኩል መብት አላቸው፡፡
ሴቶች በዚህ ሕገ መንግሥት በተደነገገው መሰረት በጋብቻ ከወንዶች ጋር እኩል መብት አላቸው፡፡
ሴቶች በበታችነትና በልዩነት በመታየታቸው የደረሰባቸውን የታሪክ ቅርስ ከግምት ውስጥ በማስገባት ይህ ቅርስ እንዲታረምላቸው በተጨማሪ የድጋፍ እርምጃዎች ተጠቃሚ የመሆን መብት አላቸው፡፡ በዚህ በኩል የሚወሰዱት እርምጃዎች ዓላማ በፖለቲካዊ፣ በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ መስኮች እንዲሁም በመንግሥት እና በግል ተቋሞች ውስጥ ሴቶች ከወንዶች ጋር በእኩልነት ተወዳዳሪና ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ እንዲቻል ልዩ ትኩረት ለመስጠት ነው፡፡
ሴቶች ከጐጂ ባሕል ተጽዕኖ የመላቀቅ መብታቸውን መንግሥት ማስከበር አለበት፡፡ ሴቶችን የሚጨቁኑ ወይም በአካላቸው ወይም በአዕምሮአቸው ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ሕጐች፣ ወጐችና ልማዶች የተከለከሉ ናቸው፡፡
ሀ. ሴቶች የወሊድ ፈቃድ ከሙሉ የደመወዝ ክፍያ ጋር የማግኘት መብት አላቸው፡፡ የወሊድ ፈቃድ ርዝመት ሴቷ የምትሠራውን ሥራ ሁኔታ፣የሴቷን ጤንነት፣ የሕጻኑንና የቤተሰቡን ደህንነት ከግምት ውስጥ በማስገባት በሕግ ይወሰናል፡፡
ለ. የወሊድ ፈቃድ በሕግ በሚወሰነው መሰረት ከሙሉ የደመወዝ ክፍያ ጋር የሚሰጥ የእርግዝና ፈቃድን ሊጨምር ይችላል፡፡
ሴቶች በብሔራዊ የልማት ፖሊሲዎች ዕቅድና በኘሮጀክቶች ዝግጅትና አፈጻጸም፣በተለይ የሴቶችን ጥቅም በሚነኩ ኘሮጀክቶች ሐሳባቸውን በተሟላ ሁኔታ እንዲሰጠ የመጠየቅ መብት አላቸው፡፡
ሴቶች ንብረት የማፍራት፣ የማስተዳደር፣ የመቆጣጠር፣ የመጠቀምና የማስተላለፍ መብት አላቸው፡፡ በተለይም መሬትን በመጠቀም፣ በማስተላለፍ፣ በማስተዳደርና በመቆጣጠር ረገድ ከወንዶች ጋር እኩል መብት አላቸው፡፡ እንዲሁም ውርስን በሚመለከት በእኩልነት የመታየት መብት አላቸው፡፡
ሴቶች የቅጥር፣ የሥራ እድገት፣ የእኩል ክፍያና ጡረታን የማስተላለፍ እኩል መብት አላቸው፡፡
ሴቶች በእርግዝናና በወሊድ ምክንያት የሚደርስባቸውን ጉዳት ለመከላከልና ጤንነታቸውን ለማስጠበቅ የሚያስችል የቤተሰብ ምጣኔ ትምህርት፣ መረጃ እና አቅም የማግኘት መብት አላቸው፡፡
አንቀጽ 36 የሕጻናት መብት#
ማንኛውም ሕጻን የሚከተሉት መብቶች አሉት፤
ሀ. በሕይወት የመኖር፣
ለ. ስምና ዜግነት የማግኘት፣
ሐ. ወላጆቹን ወይም በሕግ የማሳደግ መብት ያላቸውን ሰዎች የማወቅና የእነሱንም እንክብካቤ የማግኘት፣
መ. ጉልበቱን ከሚበዘብዙ ልማዶች የመጠበቅ፣ በትምህርት½ በጤናውና በደህንነቱ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ሥራዎች እንዲሠራ ያለመገደድ ወይም ከመሥራት የመጠበቅ፣
ሠ. በትምህርት ቤቶች ወይም በሕጻናት ማሳደጊያ ተቋሞች ውስጥ በአካሉ ከሚፈጸም ወይም ከጭካኔና ኢሰብዓዊ ከሆነ ቅጣት ነጻ የመሆን፡፡
ሕጻናትን የሚመለከቱ እርምጃዎች በሚወሰዱበት ጊዜ በመንግሥታዊ ወይም በግል የበጐ አድራጐት ተቋሞች፣ በፍርድ ቤቶች፣ በአስተዳደር ባለሥልጣኖች ወይም በሕግ አውጪ አካላት የሕጻናት ደህንነት በቀደምትነት መታሰብ አለበት፡፡
ወጣት አጥፊዎች፣ በማረሚያ ወይም በመቋቋሚያ ተቋሞች የሚገኙ፣ በመንግሥት እርዳታ የሚያድጉ ወጣቶች፣ በመንግሥት ወይም በግል እጓለ ማውታን ተቋሞች ውስጥ የሚገኙ መጣቶች ከአወቂዎች ተለይተው መያዝ አለባቸው፡፡
ከጋብቻ ውጭ የተወለዱ ሕጻናት በጋብቻ ከተወለዱ ሕጻናት ጋር እኩል መብት አላቸው፡፡
መንግሥት ለእጓለ ማውታን ልዩ ጥበቃ ያደርግላቸዋል፡፡ በጉዲፈቻ የሚያድጉበትን ሥርዓት የሚያመቻቹና የሚያስፋፉ እንዲሁም ደህንነታቸውን ትምህርታቸውን የሚያራምዱ ተቋሞች እንዲመሰረቱ ያበረታታል፡፡
አንቀጽ 37 ፍትሕ የማግኘት መብት#
ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም ለሌላ በሕግ የዳኝነት ሥልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብና ውሳኔ ወይም ፍርድ የማግኘት መብት አለው፡፡
በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 የተመለከተውን ውሳኔ ወይም ፍርድ፤
ሀ. ማንኛውም ማኅበር የአባላቱን የጋራ ወይም የግል ጥቅም በመወከል፣
ለ. ማንኛውም ቡድን ወይም ተመሳሳይ ጥቅም ያላቸውን ሰዎች የሚወክል ግለሰብ ወይም የቡድን አባል የመጠየቅና የማግኘት መብት አለው፡፡
አንቀጽ 38 የመምረጥና የመመረጥ መብት#
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በቀለም፣ በዘር፣ በብሔር፣ በብሔረሰብ፣ በጾታ፣በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ ወይም በሌላ አመለከካከት ወይም በሌላ አቋም ላይ የተመሰረተ ልዩነት ሳይደረግበት የሚከተሉት መብቶች አሉት፤
ሀ. በቀጥታ እና በነጻነት በመረጣቸው ተወካዮች አማካኝነት በሕዝብ ጉዳይ አስተዳደር የመሳተፍ፣
ለ. ዕድማው 18 ዓመት ሲሞላ በሕግ መሰረት የመምረጥ ፣
ሐ. በማናቸውም የመንግሥት ደረጃ በየጊዜው በሚካሄድ ምርጫ የመምረጥና የመመረጥ፡፡ ምርጫው ሁሉ አቀፍ፣ በሁሉም እኩልነት ላይ የተመሰረተና በሚስጥር ድምጽ አሰጣጥ መራጩ ፈቃዱን በነጻነት የሚገልጽበት ዋስትና የሚሰጥ መሆን አለበት፡፡
በፖለቲካ ድርጅቶች፣ በሠራተኞች፣ በንግድ፣ በአሠሪዎችና በሙያ ማኅበራት ለተሳትፎ ድርጅቱ የሚጠይቀውን ጠቅላላና ልዩ የአባልነት መስፈርት የሚያሟላ ማንኛውም ሰው በፍላጐቱ አባል የመሆን መብቱ የተከበረ መሆን አለበት፡፡
በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 በተመለከቱት ድርጅቶች ውስጥ ለኃላፊነት ቦታዎች የሚካሄዱ ምርጫዎች ነጻና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ይፈጸማሉ፡፡
የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 እና 3 ድንጋጌዎች የሕዝብን ጥቅም ሰፋ ባለ ሁኔታ የሚነኩ እስከሆነ ድረስ በሕዝባዊ ድርጅቶች ላይ ተፈጻሚ ይሆናሉ፡፡
አንቀጽ 39 የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች መብት#
ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከመገንጠል ያለው መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለ ገደብ የተጠበቀ ነው፡፡
ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ በቋንቋው የመናገር፣ የመጻፍ፣ቋንቋውን የማሳደግ እና ባሕሉን የመግለጽ፣ የማዳበርና የማስፋፋት እንዲሁም ታሪኩን የመንከባከብ መብት አለው፡፡
ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ ራሱን የማስተዳደር ሙሉ መብት አለው፡፡ ይህ መብት ብሔሩ፣ ብሔረሰቡ፣ ሕዝቡ በሰፈረበት መልክዓ ምድር ራሱን የሚያስተዳድርበት መንግሥታዊ ተቋማት የማቋቋም እንዲሁም በክልልና በፌዴራል አስተዳደሮች ውስጥ ሚዛናዊ ውክልና የማግኘት መብትን ያጠቃልላል፡፡
የብሔር፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መብት ከሥራ ላይ የሚውለው፤
ሀ. የመገንጠል ጥያቄ በብሔር፣ በብሔረሰቡ ወይም በሕዝቡ የሕግ አውጪ ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ የድምጽ ድጋፍ ተቀባይነት ማግኘቱ ሲረጋገጥ፤
ለ. የፌዴራሉ መንግሥት የብሔር፣ የብሔረሰቡ ወይም የሕዝቡ ምክር ቤት ውሳኔ በደረሰው በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለጠያቂው ብሔር፣ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ሕዝበ ውሳኔ ሲያደራጅ፤
ሐ. የመገንጠሉ ጥያቄ በሕዝበ ውሳኔው በአብላጫ ድምጽ ሲደገፍ፤
መ. የፌዴራሉ መንግሥት መገንጠሉን ለመረጠው ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ምክር ቤት ሥልጣኑን ሲያስረክብ፤
ሠ. በሕግ በሚወሰነው መሠረት የንብረት ክፍፍል ሲደረግ ነው፡፡
በዚህ ሕገ መንግሥት ውስጥ «ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ» ማለት ከዚህ ቀጥሎ የተገለጸውን ባህርይ የሚያሳይ ማኅበረሰብ ነው፡፡ ሰፋ ያለ የጋራ ጠባይ የሚያንጸባርቅ ባሕል ወይም ተመሳሳይ ልምዶች ያላቸው፣ ሊግባቡት የሚችሉበት የጋራ ቋንቋ ያላቸው፣ የጋራ ወይም የተዛመደ ሕልውና አለን ብለው የሚያምኑ፣የሥነ ልቦና አንድነት ያላቸውና በአብዛኛው በተያያዘ መልክዓ ምድር የሚኖሩ ናቸው፡፡
አንቀጽ 40 የንብረት መብት#
ማንኛውም የኢትዮጵያ ዜጋ የግል ንብረት ባለቤት መሆኑ/መሆኗ ይከበርለታል/ ይከበርላታል፡፡ ይህ መብት የሕዝብን ጥቅም ለመጠበቅ በሌላ ሁኔታ በሕግ እስካልተወሰነ ድረስ ንብረት የመያዝና በንብረት የመጠቀም ወይም የሌሎችን ዜጐች መብቶች እስካልተቃረነ ድረስ ንብረትን የመሸጥ የማውረስ ወይም በሌላ መንገድ የማስተላለፍ መብቶችን ያካትታል፡፡
ለዚህ አንቀጽ ዓላማ «የግል ንብረት» ማለት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ወይም ሕጋዊ ሰውነት በሕግ የተሰጣቸው ኢትዮጵያዊ ማኅበራት ወይም አግባብ በአላቸው ሁኔታዎች በሕግ በተለየ በጋራ የንብረት ባለቤት እንዲሆኑ የተፈቀደላቸው ማኅበረሰቦች በጉልበታቸው፣ በመፍጠር ችሎታቸው ወይም በካፒታላቸው ያፈሩት ተጨባጭ የሆነና የተጨባጭነት ጠባይ ሳይኖረው ዋጋ ያለው ውጤት ነው፡፡
የገጠርም ሆነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግሥትና የሕዝብ ብቻ ነው፡፡ መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ንብረት ነው፡፡
የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች መሬት በነጻ የማግኘትና ከመሬታቸው ያለመነቀል መብታቸው የተከበረ ነው፡፡ አፈጻጸሙን በተመለከተ ዝርዝር ሕግ ይወጣል፡፡
የኢትዮጵያ ዘላኖች ለግጦሽም ሆነ ለእርሻ የሚጠቀሙበት መሬት በነጻ የማግኘት፣የመጠቀምና ከመሬታቸው ያለመፈናቀል መብት አላቸው፡፡ ዝርዝር አፈጻጸሙ በሕግ ይወሰናል፡፡
የመሬት ባለቤትነት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ መንግሥት ለግል ባለሀብቶች በሕግ በሚወሰን ክፍያ በመሬት የመጠቀም መብታቸውን ያስከብርላቸዋል፡፡ ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል፡፡
ማንም ኢትዮጵያዊ በጉልበቱ፣ ወይም በገንዘቡ በመሬት ላይ ለሚገነባው ቋሚ ንብረት ወይም ለሚያደርገው ቋሚ መሻሻል ሙሉ መብት አለው፡፡ ይህ መብት የመሸጥ፣ የመለወጥ፣ የማውረስ፣ የመሬት ተጠቃሚነቱ ሲቋረጥ ንብረቱን የማንሳት፣ ባለቤትነቱን የማዛወር ወይም የካሳ ክፍያ የመጠየቅ መብትን ያካትታል፡፡ ዝርዝር አፈጻጸሙ በሕግ ይወሰናል፡፡
የግል ንብረት ባለቤትነት መብት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ መንግሥት ለሕዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ተመጣጣኝ ካሳ በቅድሚያ በመክፈል የግል ንብረትን ለመውሰድ ይችላል፡፡
አንቀጽ 41 የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የባሕል መብቶች#
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሀገሪቱ ውስጥ በማንኛውም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የመሰማራትና ለመተዳደሪያው የመረጠውን ሥራ የመሥራት መብት አለው፡፡
ሁሉም ኢትዮጵያዊ መተዳደሪያውን፣ ሥራውንና ሙያውን የመምረጥ መብት አለው፡፡
የኢትዮጵያ ዜጐች ሁሉ በመንግሥት ገንዘብ በሚካሄዱ ማኅበራዊ አገልግሎቶች በእኩልነት የመጠቀም መብት አላቸው፡፡
መንግሥት የጤና፣ የትምህርትና ሌሎች የማኅበራዊ አገልግሎቶችን ለሕዝብ ለማቅረብ በየጊዜው እየጨመረ የሚሄድ ሀብት ይመድባል፡፡
መንግሥት የአካል እና የአዕምሮ ጉዳተኞችን፣ አረጋዊያንንና ያለወላጅ ወይም ያለአሳዳጊ የቀሩ ሕጻናትን ለማቋቋምና ለመርዳት የሀገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም በፈቀደው ደረጃ እንክብካቤ ያደርጋል፡፡
መንግሥት ለሥራ አጦችና ለችግረኞች ሥራ ለመፍጠር የሚያስችል ፖሊሲ ይከተላል፤ እንዲሁም በሚያካሂደው የሥራ ዘርፍ ውስጥ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሥራ ኘሮግራሞችን ያወጣል፣ ኘሮጀክቶችን ያካሂዳል፡፡
መንግሥት ዜጐች ጠቃሚ ሥራ የማግኘት ዕድላቸው እየሰፋ እንዲሄድ ለማድረግ አስፈላጊ እርምጃዎችን ይወስዳል፡፡
ገበሬዎችና ዘላን ኢትዮጵውያን በየጊዜው እየተሻሻለ የሚሄድ ኑሮ ለመኖር የሚያስችላቸውና ለምርት ካደረጉት አስተዋጽኦ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ተገቢ ዋጋ ለምርት ውጤቶቻቸው የማግኘት መብት አላቸው፡፡ መንግሥት የኢኮኖሚ፣የማኅበራዊና የልማት ፖሊሲዎችን በሚተልምበት ጊዜ በዚህ ዓላማ መመራት አለበት፡፡
መንግሥት የባሕልና የታሪክ ቅርሶችን የመንከባከብና ለሥነ ጥበብና ለስፖርትመስፋፋት አስተዋጽኦ የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡
አንቀጽ 42 የሠራተኞች መብት#
- ሀ. የፋብሪካና የአገልግሎት ሠራተኞች፣ ገበሬዎች፣ የእርሻ ሠራተኞች፣ ሌሎች የገጠር ሰራተኞች፣ከተወሰነ ኃላፊነት ደረጃ በታች ያሉና የሥራ ጠባያቸው የሚፈቅድላቸ የመንግሥት ሠራተኞች የሥራና የኢኮኖሚ ሁኔታዎችን ለማሻሻል በማኅበር የመደራጀት መብት አላቸው፡፡ ይህ መብት የሠራተኛ ማኅበራትና ሌሎች ማኅበራትን የማደራጀት፣ ከአሠሪዎችና ጥቅማቸውን ከሚነኩ ሌሎች ድርጅቶች ጋር የመደራደር መብትን ያካትታል፡፡
- ለ. በንዑስ አንቀጽ /ሀ/ የተመለከቱት የሠራተኛ ክፍሎች ሥራ ማቆምን ጨምሮ ቅሬታቸውን የማሰማት መብት አላቸው፡፡
- ሐ. በንዑስ አንቀጽ /ሀ/ እና /ለ/ መሠረት እውቅና ባገኙት መብቶች ለመቀም የሚችሉት የመንግሥት ሠራተኞች በሕግ ይወሰናሉ፡፡
- መ. ሴቶች ሠራተኞች ለተመሳሳይ ሥራ ተመሳሳይ ክፍያ የማግኘት መብታቸው የተጠበቀ ነው፡፡
ሠራተኞች በአግባቡ የተወሰነ የሥራ ሰዓት ዕረፍት፣ የመዝናኛ ጊዜ፣ በየጊዜው ከክፍያ ጋር የሚሰጡ የዕረፍት ቀኖች፣ ደመወዝ የሚከፈልባቸው የሕዝብ በዓላት እንዲሁም ጤናማና አደጋ የማያደረስ የሥራ አካባቢ የማግኘት መብት አላቸው፡፡
እነዚህን መብቶች ተግባራዊ ለማድረግ የሚወጡ ሕጐች በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት እውቅና ያገኙትን መብቶች ሳይቀንሱ የተጠቀሱት ዓይነት የሠራተኛ ማኅበራት ስለሚቋቋሙበትና የጋራ ድርድር ስለሚካሄድበት ሥርዓት ይደነግጋሉ፡፡
አንቀጽ 43 የልማት መብት#
የኢትዮጵያ ሕዝቦች በአጠቃላይም ሆነ በኢትዮጵያ ያሉ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች በተናጠል የኑሮ ሁኔታቸውን የማሻሻልና የማያቋርጥ እድገት የማግኘት መብታቸው የተጠበቀ ነው፡፡
ዜጐች በብሔራዊ ልማት የመሳተፍ በተለይም አባል የሆኑበትን ማኅበረሰብ የሚመለከቱ ፖሊሲዎችና ኘሮጀክቶች ላይ ሐሳባቸውን እንዲሰጡ የመጠየቅ መብት አላቸው፡፡
መንግሥት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚገባቸው ስምምነቶችም ሆኑ የሚያደርጋቸው ግንኙነቶች የኢትዮጵያን የማያቋርጥ እድገት መብት የሚያስከብሩ መሆን አለባቸው፡፡
የልማት እንቅስቀሴ ዋና ዓላማ የዜጐችን እድገትና መሰረታዊ ፍላጐቶች ማሟላት ይሆናል፡፡
አንቀጽ 44 የአካባቢ ደህንነት መብት#
ሁሉም ሰዎች ንoህና ጤናማ በሆነ አካባቢ የመኖር መብት አላቸው፡፡
መንግሥት በሚያካሂዳቸው ኘሮግራሞች ምክንያት የተፈናቀሉ ወይም ኑሮአቸው የተነካባቸው ሰዎች ሁሉ በመንግሥት በቂ እርዳታ ወደ ሌላ አካባቢ መዘዋወርን ጨምሮ ተመጣጣኝ የሆነ የገንዘብ ወይም ሌላ አማራጭ ማካካሻ የማግኘት መብት አላቸው፡፡