ምዕራፍ ሁለት#
የሕገ መንግሥቱ መሰረታዊ መርሆዎች#
አንቀጽ 8: የሕዝብ ሉዓላዊነት#
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣንባለቤቶች ናቸው፡፡
ይህ ሕገ መንግሥት የሉዓላዊነታቸው መግለጫ ነው፡፡
ሉዓላዊነታቸውም የሚገለጸው በዚህ ሕገ መንግሥት መሰረት በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸውና በቀጥታ በሚያደርጉት ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ አማካይነት ይሆናል፡፡
አንቀጽ 9: የሕገ መንግሥት የበላይነት#
ሕገ መንግሥቱ የሀገሪቱ የበላይ ሕግ ነው፡፡ ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሰራር፣እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረውም፡፡
ማንኛውም ዜጋ፣ የመንግሥት አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሌሎች ማኅበራት እንዲሁም ባለሥልጣኖቻቸው፣ ሕገ መንግሥቱን የማስከበርና ለሕገ መንግሥቱ ተገዢ የመሆን ኃላፊነት አለባቸው፡፡
በዚህ ሕገ መንግሥት ከተደነገገው ውጭ በማናቸውም አኳኊን የመንግሥት ሥልጣን መያዝ የተከለከለ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ያጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሀገሪቱ ሕግ አካል ናቸው፡፡
አንቀጽ 10: የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች#
ሰብዓዊ መብቶችና ነጻነቶች ከሰው ልጅ ተፈጥሮ የሚመነጩ፣ የማይጣሱና የማይገፈፉ ናቸው፡፡
የዜጐች እና የሕዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይከበራሉ፡፡
አንቀጽ 11: የመንግሥትና የሃይማኖት መለያየት#
መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው፡፡
መንግሥታዊ ሃይማኖት አይኖርም፡፡
መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፡፡ ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፡፡
አንቀጽ 12: የመንግሥት አሠራርና ተጠያቂነት#
የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን አለበት፡፡
ማንኛውም ኃላፊና የሕዝብ ተመራጭ ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ ይሆናል፡፡ሕዝብ በመረጠው ተወካይ ላይ እምነት ባጣ ጊዜ ከቦታው ለማንሳት ይችላል፡፡ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል፡፡