ምዕራፍ አንድ#

ጠቅላላ ድንጋጌዎች#

አንቀጽ 1: የኢትዮጵያ መንግሥት ስያሜ#

ይህ ሕገ መንግሥት ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ የመንግሥት አወቃቀር ይደነግጋል፡፡በዚህ መሰረት የኢትዮጵያ መንግሥት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በሚል ስም ይጠራል፡፡

አንቀጽ 2: የኢትዮጵያ የግዛት ወሰን#

የኢትዮጵያ የግዛት ወሰን የፌዴራሉን አባሎች ወሰን የሚያጠቃልል ሆኖ በዓለም አቀፍ ስምምነቶች መሰረት የተወሰነው ነው፡፡

አንቀጽ 3: የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ#

  1. የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሐል ቢጫ፣ ከታች ቀይ ሆኖበመሐሉ ብሔራዊ ዓርማ ይኖረዋል፡፡ ሦስቱም ቀለማት እኩል ሆነው በአግድም ይቀመጣሉ፡፡

  2. ከሰንደቅ ዓላማው ላይ የሚቀመጠው ብሔራዊ ዓርማ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች እና ሃይማኖቶች በእኩልነትና በአንድነት ለመኖር ያላቸውን ተስፋ የሚያንጸባርቅ ይሆናል፡፡

  3. የፌዴራሉ አባሎች የየራሳቸው ሰንደቅ ዓላማና ዓርማ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ዝርዝሩን በየራሳቸው ምክር ቤት ይወስናሉ፡፡

አንቀጽ 4: የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር#

የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር የሕገ መንግሥቱን ዓላማዎችና የኢትዮጵያ ሕዝቦች በዴሞክራሲ ሥርዓት አብረው ለመኖር ያላቸውን እምነት፣ እንዲሁም የወደፊት የጋራ ዕድላቸውን የሚያንጸባርቅ ሆኖ በሕግ ይወሰናል፡፡

አንቀጽ 5: ስለ ቋንቋ#

  1. ማናቸውም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በእኩልነት የመንግሥት እውቅና ይኖራቸዋል፡፡

  2. አማርኛ የፌዴራሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ ይሆናል፡፡

  3. የፌዴሬሽኑ አባሎች የየራሳቸውን የሥራ ቋንቋ በሕግ ይወስናሉ፡፡

አንቀጽ 6: ስለ ዜግነት#

  1. ወላጆቹ/ወላጆኟ ወይም ከወላጆቹ/ከወላጆኟ አንደኛቸው ኢትዮጵያዊ/ኢትዮጵያዊት የሆነ/የሆነች የኢትዮጵያ ዜጋ ነው/ናት፡፡

  2. የውጭ ሀገር ዜጐች የኢትዮጵያ ዜግነት ሊያገኙ ይችላሉ፡፡

  3. ዜግነትን በሚመለከት ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል፡፡

አንቀጽ 7: የፆታ አገላለጽ#

በዚህ ሕገ መንግሥት ውስጥ በወንድ ፆታ የተደነገገው የሴትንም ፆታ ያካትታል፡፡