መ ግ ቢ ያ#

እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች፥

በሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እድገታችን እንዲፋጠን፣ የራሳችንን ዕድል በራሳችን የመወሰን መብታችንን ተጠቅመን፣ በነጻ ፍላጐታችን፣ በሕግ የበላይነት እና በራሳችን ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ በጋራ ለመገንባት ቆርጠን በመነሳት፤

ይህን ዓላማ ከግብ ለማድረስ፣ የግለሰብና የብሔር/ብሔረሰብ መሰረታዊ መብቶች መከበራቸው፣ የጾታ እኩልነት መረጋገጡ፣ ባሕሎችና ሃይማኖቶች ካለአንዳች ልዩነት እንዲራመዱ የማድረጉ አስፈላጊነት ጽኑ እምነታችን በመሆኑ፤

ኢትዮጵያ ሀገራችን የየራሳችን አኩሪ ባሕል ያለን፣ የየራሳችን መልክዓ ምድር አሰፋፈር የነበረንና ያለን፣ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በተለያዩ መስኮችና የግንኙነት ደረጃዎችተሳስረንአብረን የኖርንባትና የምንኖርባት ሀገር በመሆንዋ፤ ያፈራነው የጋራ ጥቅምና አመለካከት አለን ብለን ስለምናምን፤

መጪው የጋራ ዕድላችን መመስረት ያለበት ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማችንን በማሳደግ ላይ መሆኑን በመቀበል፤

ጥቅማችንን፣ መብታችንና ነጻነታችንን በጋራ እና በተደጋጋፊነት ለማሳደግ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባቱን አስፈላጊነት በማመን፤

በትግላችንና በከፈልነው መስዋዕትነት የተገኘውን ዴሞክራሲና ሰላም ዘላቂነቱንለማረጋገጥ፤

ይህ ሕገ መንግሥት ከዚህ በላይ ለገለጽናቸው ዓላማዎችና እምነቶች ማሰሪያ እንዲሆነንእንዲወክሉን መርጠን በላክናቸው ተወካዮቻቸን አማካይነት በሕገ መንግሥት ጉባኤ ዛሬ ኅዳር 29 ቀን 1987 አጽድቀነዋል፡፡