ኢኮኖሚክ ሪፎርም ወይስ የትግራይ ጦርነት እያስከፈለ ያለው ዋጋ?
ሰላም ናችሁሳ?!
የትግራይ ጦርነት እያስከፈለ ያለው ዋጋ አይጣል ነው። ጦርነቱ ህወሓትን ሳይሆን ኢኮኖሚውን በአየር ላይ እንደተበተነ ዱቄት አደረገው። አዲስ ብድርና እርዳታ ለጦር መሳሪያ መግዣ እየዋሉ፣ በ3 አስርት አመታት በዳዴ የተገነባውን ኢኮኖሚ አወደሙ። ሪዘርቭ ነጠፈ። መላወሻ ጠፋ። የልመና ቋት ተይዞ ከስንቱ ደጅ ቢጠናም፣ የአገሪቱን ንብረት ለመቸብቸብ ምን ቢንደፋደፉም፣ መጀመሪያ ሰላም አውርድ ተባለ። ሰላም ከሌለ ማን ሪስኪ አሴቶችህን ይገዛል? ማን ያበድራል? የገኘኸውን መልሰህ የጦር መሳሪያ ልትገዛበት? ከሁሉም በላይ በሰጡህ ማግስት ክልችው ልትል እንደማትችል ምን ማረጋገጫ አለ? ሳይወድ በግዱ በፕሪቶሪያ ተገኘ። ፕሪቶሪያ ከሻዕቢያና ከፋኖ ጋር አናከሰው። ምን ማናከስ ብቻ፣ ደም አፋሰሰው፣ ለሌላ የማያባራ ጦርነት ዳረገው እንጂ። ከሁሉም ጋር ተናቆረ። ከትግራይ፣ ከአማራ፣ ከኦሮሞ አንጃ፣ ከቁርጥ ቀን ጌታው ከሻዕቢያ። ከሁሉም ተነጥሎ፣ በከተማዋ ታጥሮ ሲቀር፣ አዲስ ወዳጅ ፍለጋ ናወዘ። የምዕራባውያንን ወዳጅነት መልሶ ለማግኘት ለሶማሊላንድ እውቅና ሰጥቼ በበርበራ ቤዝ መስርቼ ቢባህር ሃይሌን ዳግም አቋቁሜ ከነሀውቲዎች ጋር እቧቀስላችኋለሁ አለ። ይህን ባለ ሳምንት ሶማሊያም በአቅሟ ቁም ስቅሉን አሳየችው። ኤርትራን ግብጽን ቱርክንና ሌሎችን ከጎና እያሰለፈች እስቲ ሞክራት አለችው። የብልጽግና እምቡር እምቡር የአንድ ሳምንት ወሬ ሆኖ አለፈ። በርበራ ከነአካቴው ተረሳ። እንኳን ቀይ ባህርና አሰብ ሊገኙ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድም ዳግም ዝር እንዳይል በጎረበት አገር ታገደ። ቢጨንቅ ብሪክስ ጋር መሞዳመድ ተጀመረ። አገር በቀል የኢኮኖሚ ለውጥ በብሪክስ አጋርነት እውን እናደርጋለን ተብሎ ተለፈፈ። በጦርነት ኢኮኖሚህን ለማውደም (ይህ ነውና አገር በቀሉ ሪፎርምህ!) የብሪክስ አባል መሆን ምን ያስፈልገዋል? ከነቻይና እና ራሽያ ጋር አብሮ በመስራት የኢኮኖሚ ሉኣላዊነቴን አስከብራለሁ፣ በማንም ዲክቴት እየተደረግኩ አልኖረም፣ ጳራራም ጲሪሪም እያለ በአደባባይ ባደነቆረን በጥቂት ሳምንታት፣ ድሃ አገር ሉአላዊነት የለውም በሚለው ጭባ ፈሊጡ ተነድቶ፣ ለአይኤምኤፍ ትዕዛዝ እጁን ሰጠ። ሽንፈቱንና ክሽፈቱን በሰበር ዜና አበሰረን። በመግለጫ ጋጋታ ራሱን ሸነገሎ ሊያሳምነን ሞከረ። ኦሮማይ እጅ ወደ ላይ ተሰቀሏል። ትላንት በንጹሃን ህይወት እየፈረዱ ያጨበጭቡ የነበሩ እጆች ዛሬ የራሳቸውን ጉሮሮ እያነቁ እንደነበር እየተረዱ ያሉ ይመስለኛል። ወይስ ገና ናችሁ? አልገባችሁም?
አብይ አሕመድ ስልጣን ከመጣ ወዲህ እንኳን አዲስ ምርትና ስራ ሊፈጥር ቀርቶ፣ የነበረውንም መጠበቅ አልቻለም። በጦርነት አወደሞታል። በባሌም በቦሌም ተብላ የምትገኝ ምንዛሪ ለጦር መሳሪያ መሸመቻና እየዋለ፣ የአገሪቱ ካዝና አሟጥጦታል። ወደ አገሪቱ የምትገባውን እያንዳንዷን ዶላር ፍለጋ፣ የአብይ መንግስት እንደማፊያ በአገሪቱ የጥቁር ገበያ ተሰማርቶ ከኦፊሻል ምንዛሪው በእጥፍ እየጨመረ በብላክ ማርኬት የውጭ ፈረንካ ይገዛል። መግዣ ብሩ ከየት ያመጣዋል? በገፍ አፍሶ ጦርነት ውስጥ ለሚማግዳቸው ሚልዮኖች ስንቅ መግዣ ብሩ ከየት ያመጣዋል? በሞተች ኢኮኖሚ ቅንጡ ፓርኮችንና ቤተመንግስቶችን የሚገነባበት ብር ከየት ይመጣል? አያመርት። የረባ ገቢ የለው፣ ብሩን ከየት ያመጣዋል? ልክ ገምታችኋል፣ በብጣሽ ወረቀት ትዕዛዝ ብሩን እንደጉድ እያተመ ነዋ። ምርት በሌበትና ኢኮኖሚው በወደመበት አገር፣ ገበያውን ያጥለቀለቁ እልፍ አእላፍ የብር “ወረቀቶች” ጥቂት ምርቶችን ሲያሳድዱ ሲውሉ የዋጋ ግሽበት ይፈጥራሉ። በዚህ መልኩ የዋጋ ግሽበት ጣራ ነካ። ስራ አጥነትና የተደራጀ ሌብነትና አፈና ተንስራፋ። ወጥቶ መግባት የማይቻልበት ሁኔታ ተፈጠረ። የመንግስት ባንኮች የተደራጀ ዝርፊያ የሚቀናበርባቸው ዋነኛ የሴራ ማእከላት ሆኑ። ማን ምን ያክል ብር አለው፣ ማንን ብታፍን የረባ ራንሰም ታገኛለህ የሚሉ መረጃዎችን ከመቸብቸብ ጀምሮ የራንሰም ክፍያዎችን በባንኩ በኩል እንዲፈጸሙ እስከማድረግ ድረስ የተደራጀው ሌብነት ስር ሰደደ። (ትግራይ ላይ ከተደረገው አይን ያወጣ የመንግስት ሌብነት፣ ባንክ እስከመዝጋትና የሁሉንም ቁጠባ ባንክ እስከማገድ ከተፈጸመው ድርጊት አንጻር ይህ የራንሰም ሌብነት ኢምንት ቢሆንም፣ የሚበላውን ያጣ የመንግስት ሰራተኛ ሌብነትና ማጅራት መቼነትን ከጌታው ባይማር ነው የሚገርመው።) ገና ሌሎች ብዙ ነገሮችም ይከተላሉ።
ከመንግስት ለውጥ ውጭ፣ ኢትዮጵያን ምንም አይነት ሪፎርም ካለችበት ምስቅልቅል አያወጣትም። የመንግስት ለውጥ ሲኖር፣ በህዝቦች መካከል የተፈጠረውን ቅራኔ ለማለዘብ፣ ድርድርና ውይይት ሲደረግ፣ እርቀ ሰላም ሲወርድ፣ ይህን ግምት ውስጥ ያስገባ አዲስ ስርዓት ሲመሰረት፣ የህግ የበላይነት በሰፈነበት አገር ሰው ኑሮውን ለማሸነፍ ደፋ ቀና ማለት ሲጀምር፣ ምናልባት ያኔ ምርት እያደገ፣ አዲስ ስራ እየተፈጠረ፣ ስራ አጥነትና ወንጀል እየቀነሰ፣ ወደ ተሻለ ህይወት ሊያመራ ይቻላል። ምናልባት ያኔ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እያገገመና አይደገ ሊሔድ ይችላል። አሁን ባለበት ሁኔታ ግን፣ ይህ የአሁኑ ሪፎርም ተብዮው ቅዠት ህዝቡ የውስጥ ተባዮችን ከመቀለብ አልፎ የውጭ መዥገሮችን ሊያደልብ ካልሆነ በስተቀር የሚተርፈው ሰባራ ሳንቲም አይኖርም። የአብይ አሕመድ ስርዓት እስካለ ድረስ ሰላም ሰፍኖ ሰዉ ወደ ስራና ልማት ይመለሳል ማለት ዘበት ነው። ከግጭቶቹ ባሻገር፣ በስርዓቱ ዙሪያ የተሰገሰጉ ማፊያዎችና ማጅራት መቺዎች ሌላ ራስ ምታት ናቸው (ለስልጣኑ ሲል በየሳምንቱ ስለሚፐውዛቸው፣ ብሂላቸውን እንደሚያስተምራቸው ሳይሻሩ በፊት መብላት ግድ ነው። እርሱ ለስልጣኑ እስከሞተ ድረስ እነሱም ለሆዳቸው ይሞታሉ!)። ከዛም ባሻገር ህግና ደንብ ማስከበር የሚያስችል ቁመና ላይ መድረስ ፈጽሞ የማይችል፣ ከሸገር ውጭ መላወስ የማይችል ሽባ ስርዓት ነው። በዚህ ሁኔታ አዲስ ስራ ፈጠራና ምርት የማሳደግ ሁኔታዎች ፈጽሞ ሊኖሩ አይችሉም። በመሆኑም ግሽበቱ እየባሰ ይሔዳል። እየባሰ ለመሔዱ አንዱና ዋነኛው ምልክት ደግሞ የታቀደው ዲቫልዌሽንና በዋጋ ግሽበቱ ምክንያት የገንዘባቸው የመግዛት አቅም ለወረደባቸው ወገኖች ድጎማ እናደርጋለን (የደሞዝ ጭማሪ እናደርጋለን) የሚለው መግለጫቸው ነው። ጭማሪ ባያደርጉ ራሱ፣ እናደርጋለን የሚለውን መግለጫ ብቻውን ከዛሬዋ እለት ጀምሮ የዋጋ ግሽበቱን የሚያባብስ ይሆናል፣ ምክንያቱም ነጋዴም የድርሻውን ለመውሰድ እንደማንኛውም ምክንያታዊ ሰው እርምጃ ይወስዳል እና! በትልቁ ደግሞ የትኛውን የረባ ላኪ (የአገር ውስጥ ምርትን ለውጭ ገበያ የሚያቀርብ) ድርጅት ሊጠቅም እንደሚችል ባናውቅም፣ (ኢንስታንት) ቡና ሳይቀር ከውጭ ለሚያስገባ የዞረበት ማህበረሰብ ዲቫልዬሽኑ አናቱን በስቶ ለሚወጣ ራስ ምታት ሊዳርገው እንደሚችል ሳይታለም የተፈታ ነው። ይህ ሁሉ ለሁለት አመታት ቁም ስቅል ለታየበት የአይኤምኢፍ የገንዘብ ብድር ለማግኘት ሲባል ነው። ብድሩ በከፊል መልሶ የአሜሪካን ትሬዠሪ ቢል ለመግዛት ይውላል (ሲያቆላምጡት ሪዘርቭ የሚሉት ነው)። የተቀረው ደግሞ በነሱ ትዕዛዝ ምን ላይ እንደሚውል አብረን የምናየው ይሆናል።
የአበሻ ዘር እድሜ ልኩን አገሩን የሚጠላ ባንዳ መሪ ሲለው የነበረን መለስ ዜናዊን ይቅር በለን የሚልበት ሌላ አጋጣሚ እንሆ ትላንት ተፈጠረ። የመለስ ስም ከተነሳ አይቀር፣ እውቁ ኢኮኖሚስት ጆሴፍ ስቲግልዝ የሰጠውን ምስክርነት በማጋራት ጽሁፌን ልቋጭ፥ ሌሊቱን ሙሉ ከአይኤምኢፍ ልኡካን ጋር ጆ ባለበት ሲከራከር አድሮ ጧት የነገረው ነው። በእርዳታ መልክ የምታገኘውን ገንዘብ ጭምር ሪዘርቭህን ለማደለብ ከተጠቀምክበት እናበድርሃለን ይሉታል። ትምህርት ቤቶች ለመገንባት ከስዊድን መንግስት ያገኘውን ብር ትምህርት እንዲሰራበት አይኤምኤፍ አይፈቅድም። የአሜሪካን ትሬዠሪ ቢል እንዲገዛበት ይፈልጋሉ። ትምህርት ቤቱን ካልገነባ ከስዊድን ብቻ ሳይሆን ከሌሎች መሰል አገራትም እርዳታ የማግኘት እድሉ እንደሚቀንስ ያውቀዋል። ሰጥተነው ለሌላ ነገር አውሎታል (እንዳትሰጡት የሚል አንደምታ ያለው) ወሬ ሊያሰራጩበት እንደሚችሉ ያውቃል። በዚህ የነደደው መለስ፣ 17 ዓመት የታገልኩት እኮ ለምኜ ያገኘሁትን ብር ምን ላይ ማዋል እንዳለብኝ አንድ አርም ቼየር ቢሮክራት ዲክቴት እንዲያደርገኝ አይደለም በማለት ወግዱ ይላቸዋል። አይኤምኤፍን የሚተቸው ጆ በዚህና በሌሎች ምክንያት መለስን ያደንቀው ነበር። (ያው ፖለቲካውን እንጂ የኢኮኖሚክስ እውቀቱን ድሮም ቢሆን ከሚያደንቁለት ሰው ነበርኩ ወንድማችሁ!)
ሌላ አንድ ምሳሌ ልጨምራችሁ። ይኼኛው ደግሞ መለስን በጣም ይቃወመው ከነበረ ሌላ ታዋቂ ኢኮኖሚስት የተገኘ ነው፣ ከዊልያም ኢስተርሊ። አይኤምኤፍ ለአንዲት ድሃ ገረቤት አገር የፖሊሲ ፕሪስክሪፕሽን የመስጠት ማንዴት ይጣልበታል፣ ስትራክቹራል አድጃስትመንት ፕሮግራም በሚባልበት ዘመን። ታድያ ፕሪስክሪፕሽኖቹ ታትመው የሚለቀቁበት አንድ ፎርም አለ። ኮፒ ፔስት አድርገው የአንዱን አገር ፕሪስክሪፕሽን ለሌላው ፕሪንት አድርገው ሲልኩት የአገሪቱን ስም አንኳን መቀየር ረስተዉት ነበር ይላል። አስቂኝና አሳዛኝ ነገር ነበር። (እግረ መንገድ በኛም ላይ አይኤምኤፍ ሳይሆን ሌላ መሰል ድርጅት ተመሳሳይ ነገር ሰርቶ ነበር። በኢትዮና ኤርትራ ድንበር መካከል ባለጌ ወንበሩ ላይ ቁጭ ብሎ በማስመሪያ ሻጥ በማድረግ፣ ለማያባራ ግጭትና ጦርነት አሻራውን ጥሎ ያለፈ አዲስ “ህጋዊ” ካርታ ሰርቶ አስረክቦናል። ዛሬ ማንም ሰው በ15 ደቂቃ የዩትዩብ ቪድዮ የካርታ ስራ ተምሮ፣ የተሰራውን ቆሻሻ ስራ መገንዘብ ይችላል።)
ምንም እንኳን ሩጫና ምርቃናው ትለቀቃለች ተብሎ ተስፋ የተጣለባት ብሯን የሚመለከት ቢሆንም፣ በተንዛዛ የብሔራው ባንክ መግለጫ፣ የአይኤምኤፍ ትንበያዎች እንደ ራዕይ ዮሃንስ ብስሜት ተጠቅሰዋል። እነዚህ ፖሊሲዎች ተግባራዊ ሲሆኑ ኢኮኖሚው በ8 በመቶ ያድጋል፣ ገበያው ይረጋጋል፣ ሪዘርቩ ያድጋል ወዘተ። ሲጀመር የሚተነብዩት ነገር ወደ ትክክለኛነት የሚጠጋ ቢሆን፣ ከምንም በላይ የራሳቸው መንግስት አገራት ነበር ባለሞያዎቹን የሚፈልጓቸው። እነሱ እያሉ እንዴት የ2008 ፋይናንሺያል ክራይስስ ሊፈጠር ይፈቅዳል? እነሱ እያሉ እንዴት ኮቪድ ተፈጥሮ የራሳቸው ሚልዮኖች እንዲሞቱ ይፈቀዳል? እንዴት የዩክሬን ጦርነት፣ የመካከለኛው ምስራቅ ትርምስ፣ ወዘተ ተፈጥረው፣ በአለም ላይ የነበራቸውን ከፍታ ሊያሳጣቸው ሲንደፋደፉ ማየትን ይፈቅዳሉ? እነሱም እንደኛ ሰዎች ናቸው። የተማሩትን ተምረን፣ የወሰዱትን ኮርስ ወስደን፣ ያነበቡትን መጻህፍት አንብበን፣ የሚችሉትን የፕሪድክሽን ሞዴል ችለንም፣ በነአይኤምኤፍ እንድንሰራ ሊፈቅዱልን ቀርቶ፣ ቅንጣት የምናውቅ የማይመስላቸው፣ በነሱ ትዕዛዝ ስር እንድንኖር ብቻ የሚፈቅዱልን ሰዎች ናቸው። እጅና እግር የሌለውን መንግስት አድርጎ መሰየም ይችሉበታል። በቀውስ ላይ ቀውስ እየቀፈቀፉ አስበርግገው፣ አዳክመው፣ እጅ ወደላይ ማለት የዘውትር ስልታቸው ነው። ዘ ሾክ ዶክትሪንን አንብባችኋል መቼስ? ዘ ኮንፌሽን ኦፍ አን ኢኮኖሚክ ሂት ማን የተባለውን መጽሃፍስ? ኪኪንግ አወይ ዘ ላዳር የተሰኘውንስ? እስኪ ሞክሯቸውና ቁርጣችሁን እወቁ! (ቁም! አንተኛው ራስህን በስራ ወይም አነቃቂ መጽሃፍቶችን በማንበብ ከምታነቃቃ ይልቅ ብርህን እየቀፈቀፍክ የዳዊት ድሪምስን የቅዠት ድጋም ባመነብነብ በአቋራጭ መክበር ለምትፈልግ ይህ አየመለከትም!)
እናማ እሏችሁለው ከዛሬ ጀምሮ ኢምፍ ጀዝባውን እንደኳስ ጢባጢቤ ይጫወትባታል። እርሱም የህዝቡ አናት ላይ መሽናቱን ይቀጥላል። እኔ ከኢኮኖሚ ሪፎርም ይልቅ ለፖለቲካዊ ለውጥ ምቹ ሁኔታ የፈጠረ ክስተት ሆኖ ነው የታየኝ። ከእውር ጥላቻና ፍራቻ የተላቀቀ ትውልድ አገሩን ይረከባል። እርግጥ ነው አንድ አጥንት (እንደ ወልቃይት አይነት) ጣል ሲያደርጉለት እዛችው ላይ ተተክሎ በመቅረት መሃሉን ጭምር ለማጣት ለሚያላዝን ይህ አይታየውም።
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!