ተደራጅ

ቀስተዳመና በአዲስ አበባ ሰማይ ላይ! አዲስ ቀን? (Credit: Paul Schemm | Washington Post)

የአዲስ አበባ ህዝብ ተደራጅ

ሰለሞን ነጋሽ | መስከረም 2011

When you complain, nobody wants to help you” Stephen Hawking

የአዲስ አበባ ህዝብ እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ህዝብ ባልተወከለበት፣ ባልተወያየበት፣ ይሁንታውን ባልሰጠበትና ኢህአዴግ ፅፎ ባፀደቀው ህገመንግስት ያለምንም ጥያቄ ሲገዛ ቆይቷል።

ያም ሆኖ “ህገመንግስቱ” የአዲስ አበባ ህዝብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብት አለው ቢልም (አንቀፅ 49/2) ህዝቡ ለአንዲትም ቀን በመረጠው መሪ ራሱን አስተዳድሮ አያውቅም።

ለዚህ ዋናው ምክንያት ደግሞ እንደሌሎች የኢትዮጵያ “ህዝቦች” ራሱን የቻለ አንድ ህዝብ ተደርጎ አለመታየቱና ማንም ዘውጌ የሚቀራመተው ባለቤት አልባ ንብረት ተደርጎ መወሰዱ ነው።

የአዲስ አበባ ህዝብ በተፈጥሮ የሚገባውን መብትና ጥቅም እንዲያስከብር አደራጅቶ የሚያታግለው የፖለቲካ ድርጅትም አላገኘም። እስከዛሬ ድረስ ሲገዛ የኖረው ገጠር መሰረታቸውን ባደረጉና በብሔር በተደራጁ የሌላ ክልል ፓርቲዎች (የኢህአዴግ ድርጅቶች) ብቻ ነው። እንዴት የህወሓት፣ የኦህዴድና የብአዴን አባላት የአዲስ አበባ ምክር ቤት ተወካይና የከተማዋ አስተዳዳሪ ከንቲባ ይሆናሉ? It’s absurd እኮ!!

እነዚህ ድርጅቶች የተመሰረቱት የክልላቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ነው። ስለሆነም ሁሉም የሚያሳስባቸው ድርጅታቸውንና ክልላቸውን የአዲስ አበባ ልዩ ተጠቃሚ እንዴት ማድረግ እንደሚቻል እንጂ ከተማዋ ውስጥ የሚኖረው ህዝብ በተፈጥሮ የሚገባውና “ህገመንግስቱ” የሰጠው መብትና ጥቅም መከበሩ አለመከበሩ አይደለም።

ስለሆነም ነው የፌደራል መንግስትን በበላይነት የሚመራ አሸናፊ ቡድን ዘውትር አዲስ አበባን እንደግል ንብረቱ በማየት በተለያየ መንገድ ሲቀራመታት የኖረው።

ቀደም ሲል ህወሓት፣ የከተማዋን ምክር ቤት በመቆጣጠር፣ ከምክር ቤቱ የፈለገውን እየመረጠ በመሾም የግል ጥቅሙን የሚያስጠብቅበት የዘረፋ ስራ ሲያከናውን ኖሯል። አሁን ደግሞ ባለተራው፣ ህገመንግስቱንም የከተማዋ መተዳደሪያ ቻርተሩንም በሚጻረር መልኩ ባሰኘው ግዜ የህግ ማሻሻያ በማድረግ፣ የምክር ቤቱ አባል ያልሆነ ሰው በህገወጥ መንገድ ሾሞ የማይገባውን ጥቅም ለማስጠበቅ እየተረባረበ ይገኛል። ይኽ ሁሉ ሲሆን ህዝቡ መብቱን መጠየቅና ማስከበር እንደሚችል ህዝብ ሳይሆን እንደ ህንጻውና መንገዱ ወይም በአጠቃላይ እንደ ንብረት መቆጠሩን ያሳያል። አዲስ አበቤው ራሱን ባለማደራጀቱ ለጥቃት ተጋልጧል።

የአዲስ አበባ ህዝብ የሚገባውን መብትና ጥቅም እንዲያስከብር፤ በከተማዋ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዋና ተዋናይና መሪ ሆኖ የራሱን እጣ ፈንታ በራሱ እንዲወስን ከምን ግዜም በላይ ዛሬ መደራጀት ይኖርበታል።

ተደራጅቶም የሚከተሉትን 3 መሰረታዊ የመብት ጥያቄዎችን ማስከበር ይኖርበታል፥

1. “ህገመንግስቱን” ተወያይቶበት፣ የማሻሻያ ሀሳቦቹን አቅርቦና ተስማምቶ ማጽደቅ መቻል፤

2. አዲስ አበቤው ራሱን የቻለ ማንነት ያለው ህዝብ እንደመሆኑ መጠን፣ የህዝብ ብዛቱ በክልል ደረጃ ከተዋቀሩ አንዳንድ ክልሎች የሚበልጥ እንደመሆኑ መጠን፣ አዲስ አበባ ራሱን የቻለ ክልል ሆኖ ህዝቡ ራሱን በራሱ ማስተዳደር እንዲችል ማድረግ፤

3. የክልሉ መንግስት (የከተማዋ አስተዳደር) የሚኖረው አውቶኖሚና ማንዴት እንዲህውም ከፌደራል መንግስትና ከሌሎች ክልላዊ መንግስታት ጋር የሚኖረው ግኑኝነት በማያሻማ ሁኔታ በህግ ማስደንገግና የህገመንግስቱ አካል ማድረግ ይኖርበታል።

******

አዲስ አበቤውን ለማደራጀት፣ አዲስ አበባና የህዝቡ ጥቅም ላይ ብቻ ትኩረት ያደረገ የፖለቲካ ፓርቲ እንደሚያስፈልግ በመረዳት፣ ችቦውን ለኩሰነዋል።

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *